>

ከድንቅ ከፍታ ወደ ጥልቅ ዝምታ (ቢቢኤን ሬድዮ)

 

ለዘመናት በዉስጥ የታፈዉ ብሶት ታምቆ ቆይቷል።ይህ ብሶት እሳተ ጎመራ ሆኖ ይፈነዳል የሚል ስጋት ሐይሎ ነበር። ይህንን እሳተ ጎመራ ለማስተንፈስ በሚመስል መልኩ በህወሃት የሚመራዉ አምባገነናዊ መንግስት በእምነት ተቋም ዉስጥ ረጅም እጁን ዘረጋ። መጅሊስ የሚባለዉን የእምነት ተቋም ወረሰና ነዉጥ ከማያጣት ሊባኖስ ያመጣዉን የእምነት አንጃ አስገድዶ ለመጫነ ሞከረ። ኢስላም ከ1400 አመታት በፊት የገባባትን አገርን ህወሃት ለማወክ ሞከረ። እዉቅ የሐይማኖት ሊቃዉንት ሳይቀር ስልጠና መሰልጠን አለባቸዉ የሚል መመሪያ ወጣና ተገበረ።

ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ይህንን የመንግስት ጣልቃገብነት ለመቋቋምና መፍትሔን ለመሻት ወኪሎችን መረጡ። ህዝባዊ ዉክልና ያገኙት ወኪሎች የመንግስት አካላት ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔን ያመጡ ዘንድ ጣሩ። ጉዳዩ ‘ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ’ ሆነና ሐያ አመት የኢትዮጵይን ህዝብ እግር-ተወርች የጠፈረዉ የህወሃት መንግስት የህዝብ ወኪሎችን አሰረ። ንጹሗን ዜጎች በአሳሳና በገርባ ደማቸዉ ፈሰሰ። በርካቶች ታሰሩ። በርካቶች ተሰደዱ።የእምነት አባቶች ተረጋግተው ወገንና አገርን ማገልገል በሚገባቸዉ የእድሜ እርከን ላይ ሳሉ ያሉበትን ቀዬ፣ቤተሰብንና ተማሪዎቻቸዉን ትተው መሰደዱ ግዴታቸው ሆነ።

ህወሃት በኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ላይ የጭቆና ቀንበር ቢያጠልቅም ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ይህንን የጭቆና ቀንበር አጥልቆ በጨቋኞች ጫማ ስር ሆኖ መኖርን አልመረጡም። በአገርም፣ በስደትም ያለው በመቀናጀት ድምጻችን ይሰማ በሚሉት የወል የትግል መስተጻምር ተቆራኝቶ ”እምቢኝ አሻፈረኝ!” ማለቱን መረጠ። ሁሉም እንደ አቅሙ፣ ሁሉም እንደችሎታዉ ይህንን ሰላማዊ የትግል ዘለበት አጠለቀ። ይህ የትግል ጎዳና ሙስሊሞች ብቻ የሚጓዙበት ሳይሆን የእምነትና የዘር ልዩነት ያልበገራቸው አገር ወዳድ ክርስቲያን ኢትዮጵያዉያን ተቀላቀሉት። ይህም ታሪካዊ ከፍታ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል።

*ሰላማዊ ሐይል*

የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የዘመናት ብሶት ሲፈነዳ እሳተ ጎመራ ይሆናል ብለዉ ትንቢት ይናገሩ የነበሩት ልሒቃን እስኪያፍሩ ድረስ የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ትግል የሰላም ብስራት ሆነ። ከልብ-ወደ-ልብ በሚዘረጋ የአላማ መስተጻምር የተሳሰረው ትግል አለም አቀፋዊ እውቅናን አገኘ። ከአገር ዉጪ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና መንግስታት ትግሉ ፍጹም ሰላማዊ የሆነና ሌላዉ የሙስሊም አለም በአርኣያነት የሚከተለው ተምሳሊት መሆኑን መሰከሩ። ሶስት አመት አገር አንቀጥቅጥ ትግል ተደረገ። ሰላም ሐይል እንዳላት በገሃድ ተስተዋለች። የኢትዮጵያ ከተሞች፣የገጠሩ ክፍል፣ጋራዉ ሸንተረሩ “ድምጻችን ይሰማ” የሚል መስተጋብር የሚስተዋልበት ሆነ።

ትግሉ ሰላማዊ ቢሆንም ህወሃት ሰላማዊ አልሆነም። ማሰር፣ መግደሉን ቀጠለ። ይህንን ድምጻችን ይሰማ የሚለዉን የወል ጉዞ የቃኙና ተመሳሳይ ተግባራትን የሚያከናዉኑ ሌሎች አገራዊ ትግሎች ተበሰሩ። አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ ድምጽን የማሰማት ጉዞን ጀመሩ። ይህ ጉዞ ሁሉንም ኢትዮጵያዉያን በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ዉስጥ ያሰባሰበ ቢሆንም፤ አፋኝ በሆነው የህወሃት ስርዓት ታላቅ ጉዳት ደረሰበት።

ትግሉ ዳግም በሌላ አቅጣጫ ተወለደ። መላዉ ኦሮምያ ሙስሊም፣ክርስቲያን፣ዋቄ ፈታ ሳይባባል በህወሃት መንገፍገፉን አደባባይ ወጥቶ አሳወቀ። አፋኝ ገዳይ የሆነው የህወሃት ስርዓት መፈናፈኛ አጣ። ጎንደር “የኦሮሞ ደም ደሜ ነዉ!” ብሎ ተነሳ። ጎንደር ህወሃት የሚባል የአገር ፍቅር ስሜት የሌለው ከፋፋይ ቡድን አገሪቷን እያጠፋ መሆኑን አደባባይ ወጥቶ አሳወቀ። የጎጃም ህዝብም የጎንደርን ህዝብ በይፋ ወጥቶ ተቀላቀለው። ለዚህ ሰላማዊ ህዝብ ህወሃት የሰጠዉ ምላሽ አጋዚ በሚባለዉ ሰዉ በላ ጦር ግድያንና ሁከት መፍጠር ሆነ። ትግሉ በዜጎች ልቦና ላይ ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነት አድጎ አገራዊ ለዉጥን ለማምጣት ጥርጊያ ጎዳናዎች እየተመቻቹ ባሉበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን።

*ትግሉንና አቅጣጫዉን መፈተሽ*

ለዚህ ተግባራዊና ልባዊ የሆነ ህዝባዊ እምቢተኝነት መሰረት የሆነው የሙስሊሞች የድምጻችን ይሰማ ንቅናቄ በአገር ዉስጥና በዉጪ ያለዉ ደጋፊው የሚሔድበትን አቅጥጫ ሊፈትሽ ግድ ይለዋል።ንቅናቄዉ የጀመረውን ብሔራዊ ጭቆናን የመቀልበስ ትግል ዳግም አድሶና ተቀናጅቶ አገራዊ ፋይዳን ለመፈየድ ሚና መጫወት በሚገባው ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን። የአገሪቷ ግማሽ አካል የሆነዉ ህዝብን መብትን ለማስከብር ብሎም ነጻነትን ለማቀዳጀት የሚኖረው የትግል ጎዳና አንድና አንድ ነዉ ብሎ መወሰን አይቻልም።ሰለዚህ አዋጭ የሆኑ ሁለገብ የትግል መስመሮች መኖራቸው አሌ-የማይባሉ በመሆናቸው በትግል መስመር መጣብብ ኬላ ለተጋረጠበትን ወገን ቅያስ ማበጀቱ የህዝብን ሐላፊነት የመወጣቱ አካል ነዉ።

*የታሪክ ከፍታ*

ይህ የሙስሊሞች ሰላማዊ ትግል ሙስሊሞች ብቻ የተሳተፉበት ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን “የኔ” ብለዉ አመኔታን የሰጡት የታሪክ ከፍታ ነው። ህወሃት በአፍሪካ ቀንድ የሚፈነዳ እሳተ ጎመራ በሙስሊሞች በኩል ይመጣል ብሎ ክርስቲያን አማኒያንን ለማታለል ሲሞክር ከጳጳሳት እስከ ምእምናን ያሉ ክርስቲያን ወገኖች ‘እኛም አዉቀናል ጉድጓድ ምሰናል!’ በማለት ያገር ፍቅር ስሜታቸዉን በመግለጽ የፍቅር ተሐድሶን ያሰረጹበት ትግል ነው።

ይህ ትግል የሙስሊሙን አለም ፖለቲካዊ፣ስነልቦናዊ፣ሐይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን የቃኙ ተመራማሪዎች ለሌላዉ አለም ተምሳሊት ይሆናል ብለዉ ተስፋ የጣሉበት ነው። ተመራማሪዎቹም መዳረሻዉን በመቀኛት በታሪክ ድርሳናት ላይ በመዘክርነት ሊያሰፍሩት በአንክሮ የሚመለከቱት ሒደት ነዉ።ይህ ትግል ሐይማኖታዊ መብትን ከማስከበር ዘልጎ አገራዊ ቤዛዎች ለሁሉም ኢትዮጵያዉያን የሚታፈሱበት የወል ብስራት ነዉ። ይህ ትግል ጅማሮዉ ከድል ደጃፍ ለመድረስ ቃልኪዳን የተገባበት ነዉ።የድሉ ሚዛን ታስረው በተፈቱና መስዋእትነት በከፈሉ ድንቅ እህትና ወንድሞች ወቅታዊ ሁናቴ ከፍና ዝቅ የሚል ሊሆን አይገባም የሚል እምነት አለ።ይህ ትግል ለመገንባት በታቀዱ ግንባታዎች፣ለመሰራት በታሰቡ ልማታዊ ንድፈ-ሐሳቦች መካከል የሚቀየጥ ሳይሆን ሰዉ በሰዉነቱ የሚያስፈልገዉ ነጻ የመሆን እሴት የሚበሰርበት ሊሆን ይገባል። ይህ ትግል የስርዓቱን መዋቅር ቦርቡሮ በመግባት ብዙ ልቦችን ማርኮ ሊያሰልፍ የሚገባዉ ቢሆን እንጂ በስርዓቱ መዋቅር ዉስጥ ባሉ የመንታ መንገድ ባለሟሎች የሚቦረቦር መሆን የለበትም። ይህ ትግል “የእስኪያልፍ ያለፋልና የባሰዉን አታምጣ” ብሒሎች መናኸሪያ ሳይሆን የታነጸበትና የአሸናፊነት መንፈስ አቅም በቻለዉ መጠን የሚተገበርበት ነዉ።

*ታላቁ የዝምታ ሐይል*

ታላቁ ሐይል የሚስተዋለው ዝምታ ነዉ። ከሶስት ጥልቅ የትግል አመታት በሗላ ለዉጥን ማምጣት የሚችለዉ ትዉልድ ዝምታን በሁኔታዎች አስገዳጅነት ሲመርጥ ተስተዉሏል።ህወሃት በህገመንግስታዊ ምህዋር ስር የተጠየቁን ሶስት ጥያቄዎች የመመልስ አቅምን አጥቷል። ጭቆናዉ ብሔራዊ ሆኖ ሳለ የጭቆናዉ መለኪያ ሶስት ጥያቄ ነው ብሎ ማሰቡ ከግዜ መወንጨፍ ጋር አብሮ የማይራመድ የትላንት ሐቅ መሆኑን መገንዘቡ ተገቢ መሆኑን ለመረዳት አስተዋይ ብቻ መሆን ነዉ ሚያሻው።

መንግስት ያለሆነውን የማፍያ ቡድን መንግስታችን የሚል ቁልምጫን ተችሮ የጥያቄ መላሽ መሆኑን ማመላከት ተገቢ አይደለም የሚል የሚሊዮኖች ድምጽ ከዝምታዉ ባሻገር ያስተጋብል። ባንጻሩ ከተጨቆኑ ህዝቦች የሚጠበቀው የሚሊዮኖችን ዝምታ ሰብሮ ባሉት አገራዊ የትግል መዋቅሮች ገብቶ መስራት ነዉ የሚል ስምምነት ደርቷል።ቢያንስ እንኳ በትግል ጉዞ ወቅት የተፈጥሩ አለመግባባቶችን ለማስቀረት ሁሉንም ወገን ሊያማክል የሚችል የወል አላማ መቅረጽ ተገቢ ነዉ።ታሪካዊ ከፍታዉ በትግል ሒደት ዉስጥ እስከመጨረሻው መታገል የመረጡ የሚገለሉበትና በትግሉ ሒደት ዉስጥ ዳተኛ የነበሩት በባትሪ ተፍልገው ያልሆኑበትን የሚሆኑበት አይደለም።

ከኦሮምያዉ ቄሮ እስከ አማራዉ የጎበዝ አለቃ ባሉት የለዉጥ ሒደቶች ዉስጥ ተቀይጦ ለዉጥን ለማምጣት የሚጥረው ድምጻችን ይሰማ ባዩ ትዉልድ ድጋፍን ይሻል። ሌላዉ ዝም ያለዉ ትዉልድ የለዉጡን ረድኤት ለማፈስ ዝምታዉን ሰብሮና ተባብሮ መዉጣቱ ተገቢ ነዉ የሚል አቋም አለ።ዳሩ ግን ዝምታን አሰባሪ ጎልቶ የሚታይና የሚመራ አካል እጦት የሚፈጠሩት የጎንዮች መሰናክሎች ኪሳራን ደራቢ እየሆኑ ነው።

ለዉጥ እዉን እንዲሆን የትግል ሒደትን መፈተሽ፣መመርመርና መወያያት አስፈላጊ ነው። የትግሉ ከፍታ ከዝምታም ባሻገር ስልታዊ ለዉጥን አድርጎ የትዉልድን አደራና ቃልኪዳን ከስኬት ማድረሱ ተገቢ ነዉ የሚል ህዝባዊ ቁጭት አለ። ጉዳዩ በጎራ የሚያከፋፍል፣በመቧደን የሚያፈራርጅ፣በመንጋ ( mob) ተደራጅቶ የሚያሰዳድብ ሳይሆን፤ አሁን ያለዉንና መጪዉ ትዉልድ ከጭቆና ቀንበር አላቆ የነጻነትን እስትንፋስን በማህበረሰብ ላይ የማስረጽ ተልእኮ ነውና ልብ ያለዉ ልብ ይበል ለማለት እንወዳለን።

Filed in: Amharic