>

“የቴዎድሮስ ራዕይ” ትያትር - በኔ እይታ (ክንፉ አሰፋ)

 

በታሪከኛዋ አምስተርዳም ከተማ በሚገኝ አንድ የሲኒማ ማዕከል ውስጥ የሃበሻ ዘር ታጭቋል። ቲያትር ቤቱ ጢም ያለው ቲያትሩ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት ነው። ወትሮውን በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ በግዙፍ አዳራሽ ውስጥ ሞልቶ የሚታየው በጸሎት ቤቶች ብቻ ይመስለኛል። ምሽት ላይ የሚደረጉ የአበሻ ኮንሰርቶችም ቢሆኑ አረፋፍደው ነው የሚሟሟቁት። በዚህኛው እንግዳ ክስተት አግራሞቴን ገና ሳልጨረስ፣ ሌላ ነገር አየሁ። ትያትሩን ጨርሼ ስወጣ በሩ ላይ ሕዝብ ለሁለተኛው ዙር ተሰልፏል።… ከሰዓት እረፍት በኋላ “የቴዎድሮስ ራዕይ”ን በአምስተርዳም ደገሙት!

የኢትዮጵያ ቲያትር በሆላንድ ሃገር ሲታይ በታሪክ ይህ የመጀመርያው ነው። ቲያትሩ “የቴዎድሮስ ራዕይ” መሆኑ ደግሞ ከስኬቱ ጋር ተዳምሮ በሁሉም ዘንድ ልዩ ስሜት የፈጠረ ይመስላል። በጌትነት እንየው ፀሃፊነት፤ በጣይቱ ማእከል አዘጋጅነትየቀረበው ይህ ቲያትር፤ በአለምጸሃይ ወዳጆ መሳጭ ትረካ ይጀምራል። ከዚያም በእነ ገብርዬ ጣፋጭ ወግ ዘና እያደረገ ያቆየንና፤ መልሶ ደግሞ ቁጭት ውስጥ ይከትተናል። ገብርዬን ሆኖ የተጫወተው ራሱ ጌትነት እንየው ነው።

“ትልቅ ነበርን፤ ትልቅ እንሆናለን!” ይለናል የቋራው አንበሳ። አንድ በነበርንበት ወቅት ምን ያህል ሃያል መሆናችንን ላላስተዋለው፤ ለዚህ ትውልድ ይህ መልዕክት የንዴት ስሜትን ብቻ ፈጥሮ አላለፈም።  መልእክቱ በእያንዳንዱ ተመልካች ልብ ውስጥ የቁጭትን አዝመራም ዘርቷል።

በሰዎች ተገፋፍቶም ይሁን፤ አልያም ሰው ለማግኘት ሲል ወደ አዳራሹ የታደመ ተመልካች ሊኖር ይችላል። እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ግን ተመልካቹ ሁሉ፤ ሃዘኑን በልቅሶ፣ ደስታውን በጭብጨባ እየገለጸ፤ ከአዳራሹን ያናጋው ነበር። ቁጭትን ያልሰነቀ አልነበረም። ማንነትን እየተፈታተነ የሚገነፍል የወኔ አቶን በደስታ እና በሃዘን ሲቃ የተደበላለቀ ሲወጣ በግልጽ ይታያል።

በትያትሩ ሂደት ውስጥ እየተፈራረቀ የሚከሰተው የደስታ እና የሃዘን ስሜት፤ የተመልካቹን ቀልብ ወጥሮ ይዞት ነበር። ይህ በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ የሚጉላላው የቁጭት ሃሳብ ስሜትን እየኮረኮረ ይጓዝና ወደ መሃል ዘለቅ ሲል አንድ ጥያቄ መጫሩ አይቀርም። “ይህ ትያትር የቴዎድሮስ ራዕይ” ነው ወይንስ የቴዎድሮስ “ፈተና”? የሚል ጥያቄ።

ዘመኑ የርስ-በርስ መባላት ነበር። ዘመኑ ሃገራችን በውጭ ወራሪዎች ጥርስ ውስጥ የገባችበት ወቅት ነበር። ሕዝቡም ዳር እስከዳር በአጼው ላይ የተነሳበት፣ በአጠቃላይ”ክፉ” የሚባል ወቅት ነበር። ይህ ሁሉ ቁልል ችግር ያለው አጋዥ ሚስቱ ተዋበችን በተነጠቀው፤ በአጼው ጫንቃ ላይ ነው። የቋራው አንበሳ ዘመኑን ለመዋጀት የሚወጣው አቀበት እና የሚወርደው ቁልቁለት ቲያትሩ በቀላል የትወና ጥበብ ያሳየናል።

“የቴዎድሮስ ራዕይ” በረቀቀ ጥበብ ያታጀበ ትያትር መሆኑን የምንገነዘበው በእንደዚህ አይነቱ ከተመልካቾች ስሜት ነው። የስሜቱ መጠን እና አይነት የሚለካው፤ በእያንዳንዱ ተመልካች የታሪኩን አረዳድ ደረጃ መሆኑ እንዳለ ሆኖ። አንዳንዶች ከት ብለው ይስቃሉ፣ ሌሎች ያለቅሳሉ ፣ ገሚሶቹ ደግሞ በቁጭት ጥርስ ያፉዋጫሉ።

ያም ሆኖ የራዕዩ ምስጢር የሚገባኝ ትንሽ ዘግየት ብሎ ነው።  በንግስናው ዘመን “እወድሻለው!” የሚላት ሃገሩን በእልፈተ ህይወቱ ቅጽበትም ይደግመዋል። አጼ ቴዎድሮስ በእንግሊዝ ጦር ጉልበቱ በተፈታ ወቅት እጁን ለግዞት አልሰጠም ብሎ በራሱ ላይ ሲጨክን፤ ቃሉን በተግባሩ ሲያጸናው እናያለን። ትልቅ ሆና ማየት የሚሻት ኢትዮጵያን “እወድሻለሁ!” እያለ ሽጉጡን ጠጥቶ በክብር አለፈ። የእሱ ራእይ ለዘመናዊዋ ኢትዮጵያ የመሰረት ድንጋይ መጣሉ ብቻ አይደለም፣ ይህ ንጉስ ለነጻነት ሲል ራስን ሰውቶ በክብር የመኖር ተምሳሌት መሆኑም ነው።

አለምጸሃይ ወዳጆ በየመሃሉ ብቅ እያለች ታሪኩን ትተርካለች። እንደጅረት የሚፈሰው እንባዋ ከሚነድደው ከሃገር ፍቅርስሜት የተነሳ ነውና እስዋን የተመለከተ ሁሉ ልቡ እየተነካ ሳያስበው ያነባል። ይህች ውድ የጥበብ ሰው ይህንን ታሪካዊ ትያትር ይዛ አትላንቲክን ስትሻገር፤ በውስጥዋ የሚግለውን የሃገር ፍቅር እና አንድነትን ሰንቃ የመጣች መሆኑን ስሜትዋ ብቻ ሳይሆን ተግባርዋም ይነግረናል። በቴዎድሮስ ራዕይ የቲያትር ጉዞ፣ አብረዋት የሚዞሩት የጥበብ ሃዋርያትም ግዜያቸውን፣ እውቀታቸውን፤ እንቅልፋቸውን እና ገንዘባቸውን መስዋዕት ማድረጋቸው ያለ ምክንያት አይደለም።

ትላንታችን ብለን እንደዋዛ ያሳለፍነው ያ ክፉ የክፍፍል ዘመን፣ እነሆ ዛሬያችን ላይ መደቀኑ እንቅልፍ ይነሳል።

Filed in: Amharic