>

የሮሄንጂያዎች ሰቆቃ እና የአን ሳን ሱቺ ነገር - እልቂት በዘመነ ስልጣኔ (ኤፍሬም እንዳለ)

“ከውሀው አጠገብ ነበርኩ፡፡ በአስራዎቹ ዕድሜ ያሉትና ለአቅመ አዳም የደረሱትን በጠብመንጃ እየተኮሱ ገደሏቸው፡፡ ህጻናትና አራሶች ግን ውሀ ውስጥ ተወረወሩ፡፡ አንዷ የእሱ የስድስት ዓመት ልጄ ሀሲና ነች፡፡” የምስኪን አባት ሰቆቃ፡፡

ይህ የሆነው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አይደለም፡፡ ይህ የሆነው በሩዋንዳ የቱትሲዎች ጭፍጨፋ ጊዜ አይደለም፡፡ ይህ የሆነው በናዚ ጀርመን የአይሁዶች ጭፍጨፋ ጊዜ አይደለም፡፡ ይህ የሆነውና እየሆና ያለው አሁን ነው፣ ሰሞኑን…የቀድሞዋ በርማ የአሁኗ ማይንማር ውስጥ፡፡

በዚሁ ሰለጠነ በተባለ ዘመን ህጻናት እና አራሶች ከእነነፍሳቸው ባህር ውስጥ ተወረወሩ፡፡ ወጣቶችና ለአቅመ አዳም የደረሱት ያለምንም መከላከያ፣ ያለምንም መሸሸጊያ በጥይት ተቆሉ፡፡ ወንጀላቸው አንድ ብቻ ነበር — በቡድሂስቶች አገር አናሳ ሙስሊሞች መሆናቸው፡፡
የሮሂንጊያ ሙስሊሞች ላይ ሰሞኑን የተፈጸመው ጭካኔ ለማመን እንኳን የሚከብድ ነው፡፡

ምናልባትም የማይንማር ገዳዮች እንደ ቀድሞው ዘመን የፈለጉትን አድርገው ሁሉም ነገር ተሸፋፍኖ የሚቀር መስሏቸው ይሆናል፡፡ እንደዛ አልሆነም፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ነው:: እንኳን ያደረጉት ያቀዱት እንኳን ተደብቆ የማይኖርበት ዘመን ነው፡፡

የአራስ ልጅ ሬሳ ላይ በሁለት እግሩ የቆሙ ሰው ሲታይ ከዚህ በላይ ምን ጭካኔ ሊኖር ይችላል! ለቁጥር የበዙ ሬሳዎች ተረፍርፈው ሲታዩ፣ ከዚህ በላይ ምን ጭካኔ ሊኖር ይችላል!

የማይንማር ጭፍጨፋ ሁለት ነገሮችን ይበልጥ ግልጽ አድርጎ አውጥቷል፡፡ የሰው ልጅን የአውሬነት ባህሪይ አሳይቷል፣ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀንን የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ጭምብል አስውልቆ አስጥሏል፡፡ ዓለምን የተቆጣጠሩት ሚዲያዎች ምን አሉ?

በሽብርተኞች ጥቃት በአውሮፓና በምዕራቡ ዓለም የጥቂት ንጹሀን ህይወት ሲጠፋ በቀጥታ ስርጭታቸው ዓለምን ትንፋሽ የሚያሳጥሩት መገናኛ ብዙሀን ምነው አሁን አንደበታቸውን ቆለፋቸው? ምነው የሮሂንጊያ ሙስሊሞች ሰቆቃ አልሞቃቸው፣ አልበርዳቸው አለ! ለነገሩ በማይናማር በጨካኞች የምትጠፋ ነፍስ፣ በፓሪስ ጎዳናዎች በአሸባሪዎች ከምትጠፋ ነፍስ ታንሳለች ማለት ነው? ይህን መሰል ጭፍጨፋ የእነሱ በሆኑና በቆዳ ቀለምም ሆነ በእምነት በቀረቧቸው ህዝቦች ላይ ቢፈጸም ይሄኔ ዓለምን በጥፍሯ አያቆሟትም ነበር !

መልሶቹ ይሄን ያህል ናላ አያዞሩም፡፡ ተጠቂዎቹ አውሮፓውያን አይደሉም፣ አሜሪካውያን አይደሉም፣ የመገናኛ በዙሀኑ ባለንብረቶች ወገኖች አይደሉም… ከኒው ዮርክ ሰማይ ጠቀሶች፣ ከፓሪስ አደባባዮች፣ ከብረስልስ ጎዳናዎች ርቅው የሚኖሩ ኑሮ ማለት የማያልቅ ሰቆቃ የሆነባቸው የሮሂንጊያ ምስኪን ሙስሊሞች እንጂ፡፡ በነገራችን ላይ በአሁኑ ጊዜ ሮሂንግያዎች ማይንማር ውስጥ እንደ አናሳ ብሄር እውቅና አልተሰጣቸውም፡፡

ያለፉትም ሆኑ የአሁኑ መንግሥታት “የቤንጋል ስደተኞች” በሚል ነው የሚያውቋቸው፡፡ በአያት ቅድመ አያቶቻቸው መሬት የሚኖሩት ሮሂንግያዎችን በ1982 ነበር የበርማ ወታደራዊ መንግሥት ዜግነታቸውን የነጠቃቸው፡፡

የቀድሞዋ በርማ ወታደሮች ፊቱኑም በጭካኔያቸው የታወቁ ናቸው፡፡ ከሁሉም ግራ አጋቢ የሆነው ግን የሰላምና የተመስጦ ኃይማኖት የሚባለው የቡድሂዝም መነኩሴዎች የግድያውና የጭፍጨፋው መሪ ተዋንያን መሆናቸው ነው፡፡ በወታደሮችና በፖሊሶች ድጋፍ የሮሂንጊያዎችን ቤቶችን አጋዩ፣ አቆሰሉ፣ ገደሉ፣ ወንዝ ውስጥ ወረወሩ፡፡ በእርግጥም የሚያም ነው፡፡

“ወታደሮች በሰሜን አቅጣጫ ጥቃት መክፈታቸውን ስሰማ ወንዝ ውስጥ ዘልዬ ገባሁ፣፡ ሁለት ወንድ ልጆቼ አብረውኝ ነበሩ፣ 10 እና 12 ዓመታቸው ነበር፡፡” አንድ ተራፊ የተናገረው ንግግር፡፡
የቤተሰቡ ሌሎች ስምንት አባላት ግን ተገድለዋል፡፡ ሌሎች ሁለት ወንድ ልጆቹ የደረሱበት አልታወቀም፡፡ የሦስት ዓመትና የአንድ ዓመት የልጅ ልጆቹን ደግሞ ወንዝ ውስጥ ወረወሯቸው፡፡ የእሱ የ55 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድሙ … ከአስር በላይ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ አልቀውበታል፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ግን ከሁሉም በላይ የሚያስገርም፣ “አይ ፖለቲካ!” የሚያሰኝና “በፊትም ቢሆን ስታስመስል ነው እንጂ ስልጣን ነበር የምትፈልገው፣” የሚያሰኙ ነገሮች ተከስተዋል – አን ሳን ሱቺ ላይ፡፡
የቀድሞዋ የሰብአዊ መብት ፊታውራሪ፣ የአሁኗ የ70 ዓመቷ የማይናማር መሪ ይህ ሁሉ ሲሆን ጭጭ ነው ያሉት፡፡ ትንሽም የተነፈሷት ብትኖር “የአሸባሪዎች ሥራ ነው!” ያሏት ነች… እንደ ሌሎች አምባገነን መሪዎች፡፡ ፈላጭ፣ ቆራጭ አገዛዝን፣ የምስኪን በርማውያን በደልን ሲፋለሙ ዕድሜያቸውን ፈጅተዋል የተባሉት ሴትዮ እውነቱን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ የአምባገነኖችን ካርድ መዘዙ፡፡
ሴትዮዋ ለአሥራ አምስት ዓመት ገደማ ቤታቸው ተከርችሞባቸው በቁም እስር በነበሩ ጊዜ ሁሉ ዓለም ሲጮህላቸው ነበር፡፡

“ለሰብአዊ መብት በታገለች ምን አደረገች!”
“ለፍትህና ለእኩልነት በታገለች ምን አጠፋች!”
“ስለ ህዝቦች እኩልነት በዘመረች ምን በደለች!”
እየተባለ ተጮኸላቸው፡፡ “ይቺን ሴትዮ ካልፈታችሁ…” እየተባለ ወታደራዊ ገዥዎቹ ላይ ማእቀበ ሁሉ ተጥሏል፡፡ የኖቤል የሰላም ሽልማትም ተሰጣቸው፡፡ ገጽታቸው የዓለም የቴሌቪዥን ስክሪኖች ላይ ነገሰ፡፡

እንግዲህ እኚሁ ሴት ናቸው አሁን በማይናማር ቤተመንግሥት ውስጥ ከተደላደሉ በኋላ እንዲህ የከፋ የዘር ማጽዳት ጭፍጨፋ ሲካሄድ ነገሩን ከማስተካከል ይልቅ ጭራሽ የአብዬን ወደ እምዬ እያደረጉት ያሉት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ሳይቀር የተጠና ዘር ማጽዳት አይነት ነገር ብሎታል፡፡

በነገራች ላይ የሴትዮዋ ዝምታ አይገርምም የሚሉም አሉ፡፡ በሰኔ 2012 በተሰማው የኖቤል ንግግራቸው ድንበሮችን ስለሚሻገሩ ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ተስፋቸውን ግልጸው ነበር፡፡ ይህንኑ እየተናገሩባት በነበረችው በዛቹ ሰዓት ግን ማይናማር ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ሮሂንግያዎች ጭፍጨፋና ሞትን እየሸሹ ነበር፡፡

በ2012 በቡድሂስቶችና በሮሂንግያ ሙሰሊሞች መካከል በተከሰተ ግጭት 140‚000 ሮሂንግያዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከዛ ጊዜ በኋላም በሺህ የሚቆጠሩት ባሀር በልቷቸዋል፣ ወይም በህገወጥ ሰው አዟዟሪዎች ሰቅጣጭ ካምፖች ውስጥ አልቀዋል፡፡

ሌላም የሚጠቅሱባቸው ነገር አለ፡፡ በዛው ዓመት ግንቦት ውስጥ ከቢቢሲዋ ሚሻል ሁሴይን ጋር ለቃለ መጠይቅ ይቀመጣሉ፡፡ በዚህ ወቅት የተናገሩትን አንድ ዓረፍት ነገር በመጥቀስ ነው ምን ይገርማል የሚሏቸው፡፡ “ቃለ መጠይቅ የምታደርግልኝ ሙስሊም እንደሆነች ማንም አልነገረኝም፣” ነበር ያሉት፡፡ ከዚህ በላይ የሴትዮዋን አስተሳሰብ ሊገልጽ የሚችል ምን አለ ነው የሚሏቸው፡፡

የሳተላይት ምስሎች ሙሉ መንደሮች ሲጋዩ አሳይተዋል፡፡ የአሁኑ ዘመቻ ሮሂንግያዎችን ከማይንማር ለማስወገድ የመጨረሻው ዘመቻ ይመስላል እየተባለ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች እንኳን ሰብአዊ እርዳታ ማድረግ አልቻሉም፡፡

ግን ፖለቲካ አስቀያሚ ነው፣ በየእለቱ እንደምናየው በጣም አስቀያሚ፡፡ በፖለቲካ እናት ጥሩ ዋጋ እስካወጣች ድረስ ዓይን ሳያሹ የምትሸጥበት አስቀያሚ ጨዋታ ነው፡፡ የዛሬው የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ የዛሬው የህዘቦች አኩልነት አፈ ቀላጤ የነገ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን የሚሆንበት አስቀያሚ ጨዋታ — ፖለቲካ፡፡ እናም አን ሳን ሱቺ ፖለቲከኛ ናቸው !!

ራሳቸው በ2013 በሰጡት አንድ
ቃለ መጠይቅ፣ “ፖለቲካ የጀመርኩት እንደ ሰብአዊ መብት ተከላካይ ሳይሆን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ መሪነት ነው፡፡ ያ ማለት ፖለቲከኛ ማለት ካልሆነ ምን እንደሆነ አላውቅም…” ብለዋል፡፡

ዓለም ጮሆ፣ ጮሆ ከቁም እስር አስፈትቶ የስልጣን ማማ ላይ እንዳላደረሳቸው እሳቸው ግን ህጻናትን ከነ ነፍሳቸው ባህር ውስጥ መወረወር ደረጃ የደረሰ የድንጋይ ዘመን ጭካኔ በዓይናቸው ስር እየተካሄደ ለሮሂንጊያ ሙስሊሞች ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ፡፡

ይልቁንም ዲስኩሩ የስልጣን ጥማቱ ጭምብል የሆነ የእውነተኛ ፖለቲከኛ ካርዳቸውን ነው መዘዙት፡፡ “አክራሪ አሸባሪዎችን እየተዋጋን ነው፣” አሉ፡፡

በቡድሂዝም አፈ ታሪክ በስተኋላ ቡድሃ የሚባለው ወጣቱ ሲድሃርታ ከዓለም ተገልሎ በትልቅ ቤተመንግሥት ይኖር ነበር፡፡ ስለውጪው ዓለም የማወቅ ጉጉት ያድርበትናም ከቤተመንግሥቱ ይወጣል፡፡ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜም አንድ በእድሜ የገፉ አዛውንት፣ አንድ በሽተኛና አንድ ሬሳ ያያል፡፡ በጣምም ይረበሻል፡፡ በአራተኛ ጊዜ ሲወጣም አንድ የሚለምን መነኩሴ ያገኛል፡፡

የመነኩሴው እርጋታና የመንፈስ እርካታ ልቡን ስለነካው ዓላማዊውን ህይወት በቃኝ ይላል፡፡ በ80 ዓመቱ በምግብ መመረዝ ሞተ የተባለው ቡድሀ ተከታዮቹ በሮሂንጂያ ሙስሊሞች ላይ እየፈፀሙ ያሉትን ግፍ ቢያውቅ ኖሮ ልቡ ምን ያህል በተሰበረ ነበር ያስብላል፡፡

ምክንያቱም የወታደሮቹ ጭካኔ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ ከ300 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ቡድሂዝም የሚታወቀው ከሌሎች በጎ እሴቶች በተጨማሪ የሰላምና የጽሞና እምነት በመሆኑ ነውና…

Filed in: Amharic