>

ማኪቬሊያዊ ፖለቲካ እና መዘዙ (ዶ/ር ታዬ ንጉሤ)

በቅርቡ ከአንድ የቅርብ ጓደኛዬ ጋር ስለ ፖለቲካ ስንጨዋወት ቀጥሎ የተመለከተውን ወግ አወጋኝ፡፡ በአንድ ወቅት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሆነ አካባቢ ነው፤ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ከሕዝቡ ጋር ስብሰባ ሲያካሂዱ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ አዛውንት አስተያየት ለመስጠት ብድግ ይሉና ፊታቸውን ወደ ተሰብሳቢው በመዞር በጣታቸው ወደ ዐይናቸው እያመለከቱ በኦሮምኛ “kuni maali?” (“ይህ ምንድን ነው?”) ብለው ይጠይቃሉ፡፡

ተሰብሳቢውም “Hay! ija dhaa” (ዐይን ነዋ) ብለው ይመልሳሉ፡፡ አዛውንቱም መልሰው “abeden, ija mitii; hudu dhaa” (በፍጹም ዐይን አይደለም “ቂጥ” እንጂ) ብለው ሲሉ የስብሰባው አዳራሽ በሳቅ ተናጋ፡፡ ቀጥለውም ይኸውላችሁ የኢሕአዴግ ፖለቲካም እንዲህ ዐይን ያወጣ ክህደት ነው ብለው የምሳሌያቸውን ጭብጥ አስረዱ፡፡
እንዲሁም በቅርቡ አንድ ሰው ሲያወጋኝ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡ የተከሰተውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ፣ በመንግሥት ተቋሞች ውስጥ ለሚገኙ የአመራር አካላት በተሰጠው “የጥልቅ ተሐድሶ” ሥልጠና ላይ የነበረው አንዱ አጀንዳ በዚህ የኢሕአዴግ የአገዛዝ ሥርዐት ውስጥ “ዕውን የሕወሓት የበላይነት አለን?” የሚል ነበር፡፡ እኔም መልሼ ታዲያ የሥልጠናው ተሳታፊዎች በአጀንዳው ላይ የነበራቸው ምላሽ እንዴት ነበር? ብዬ ጠየቅሁት፡፡ እሱም የስብሰባውን ግልጽነት እያደነቀ አንዳንድ ተሳታፊዎች በመከላከያና የደኅንነት ቁልፍ የሆኑ መንግሥታዊ ተቋማት አመራር ያሉትን ሰዎች በመጥቀስ በርግጥም የሕወሓት የበላይነት እንዳለ አስተያየት ሰነዘሩ አለ፡፡ ነገር ግን አለ፣ መድረኩን ከሚመሩት የሕወሓት አባላት በተለይም አንዱ በዕድሜ ወጣት የሆነ እጅግ ተናጋሪ ካድሬ (በእሱ አባባል “ትንሹ መለስ”) የተለያዩ የመከላከያ ሐሳቦችን እየጠቀሰ የሕወሓት የበላይነት እንደሌለ አስረዳ፡፡ እኛም ተቀበልነው አለኝ፡፡ ይህን ሲለኝ ወዲያው በጭንቅላቴ ውስጥ የመጣብኝ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የአዛውንቱ ምሳሌያዊ አነጋገር ነበር፡፡
አንዳንድ ሰዎች “ፖለቲካ የመዋሸት ስልት ነው” ብለው ሲናገሩ እሰማለሁ፡፡ እንዲያውም ማኪቬሊ የተባለው ጣሊያናዊ ፈላስፋ “ዘ ፕሪንስ” በሚለው ዝነኛ መጽሐፉ ውስጥ እንደሚያትተው፣ አንድ ውጤታማ ገዢ “የቀበሮና የአንበሳ” ባሕሪያትን አጣምሮ ሊይዝ ይገባል ይላል፡፡ የቀበሮው ባሕሪ የሚወክለው ማጭበርበርና ማስመሰልን ሲሆን፤ የአንበሳው ባሕሪ የሚወክለው ደግሞ የኃይለኝነትንና በጉልበት የማንበርከክ ሥልትን ነው፡፡ ማኪቬሊ ለገዢዎች የሥልጣን ጊዜን እንዴት ማስረዘም እንደሚችሉ ሲመክር፡ እየቀጠፉ፣ እያጭበረበሩና በኃይል እየደቆሱ መግዛት እንደሚገባቸው አበክሮ ያስገነዝባል፡፡ ባጭሩ ማኪቬሊያዊ ፖለቲካ አስመሳይነት፣ ማጭበርበርና ኃይልን ያማከለ የፖለቲካ ስልት ነው፡፡
ባለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ የቆየው የኢሕአዴግ ሥርዓት በጥሞና ሲመረመር ማኪቬሊያዊ የአገዛዝ ማኑዋልን ታማኝነት እየተረጎመ የሚገኝ ይመስላል፡፡ እንደሚመስለኝ ይህም የሆነበት የራሱ ታሪክ አለው፡፡ ሲጀምር የኢሕአዴግ አስኳል የሆነው ሕወሓት ኢትዮጵያ የሚል የፖለቲካ አጀንዳ አልነበረውም፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው በፖለቲካ አጀንዳነት የመጣው በትግሉ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ኢትዮጵያን የሚያህል አገር የማስተዳደር ኃላፊነት ሳያስበው በእጁ ላይ በመውደቁ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የሚለውም ድርጅት የወቅቱን የፖለቲካ ጥያቄ ለመመለስ በጥድፊያ የተዋቀረ የቶሎ ቶሎ የይድረስ ቤት ነው፡፡
የኢሕአዴግ ማኪቬሊያዊ ፖለቲካ ሥረ መሠረቱም ኢትዮጵያን በተለያዩ “ዘውጎች” ከፋፍሎ በመግዛት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለዚህም የመከራከሪያ ነጥቡ ኢትዮጵያ ስትመሠረት “ሉዓላዊ” በሆኑ ዘውጎች በኃይል ወደአንድነት እንዲመጡ ተገደው ነው የሚል ነው፡፡ ሰሞኑን ታትሞ በገበያ ላይ የዋለው የደራሲ ሀብታሙ አለባቸው “ታላቁ ተቃርኖ” የሚል መጽሐፍ ይህን የመከራከሪያ ነጥብ ትንሽ ወሰብሰብ አድርጎ የአካዳሚ ገጽታ አልብሶት ብቅ ብሏል፡፡ በርግጥ መጽሐፉን ላየው ራሱ በተቃርኖ ሐሳቦች የተሞላና የተመሠረተበትም ኀልዮት የተፋለሰ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ይወጣል፡፡ ለምሳሌ መጽሐፉ በመጀመሪያ ገጾቹ የሥራውን አግባብነት ሲያስረዳ፣ ይህን ሥራ ለየት የሚያደርገው አወቃቀሩ ቀደም ሲል በሶሲዮሎጂ የትምህርት መስክ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረውን የ“ስትራክቸራል ፈንክሽናሊዝም” አተያይ ላይ እንደተመሠረተ ይገልጻል፡፡ እዚህ ላይ የመጽሐፉን ዐቢይ ተቃርኖ ልብ ልንል ይገባል፡፡ መሠረቱን በዚህ የምዕራባውያን ሥነ ዕውቀት በሆነው “ስትራክቸራል ፈክሽናሊዝም” ላይ ጥሎ ሲያበቃ፣ በመጽሐፉ የውስጥ ገጾች ላይ ግን የምዕራባውያንን ሥነ ዕውቀት በአጠቃላይ በሌሎች ሕዝቦች ላይ የፈጸመውን የእእምሮ በደል ሲኮንን ይታያል፡፡
በነገራችን ላይ ይህ “የስትራክቸራል ፈንክሽናሊዝም” ዕይታ በአሁኑ ወቅት በሶሲዮሎጂ የትምህርት መስክ ተቀባይነት አጥቶ ወደ ቅርጫት ከተወረወረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ ወደ ዝርዝር ሐሳቦች ሲገባ የተለያዩ ሶሲዮሎጂካል ጽንሰ ሐሳቦችን እያነሳ ለመከራከር ይሞክራል፡፡ ሆኖም ግን ክርክሩ በመንገደኛ ሶሲዮሎጂካል ዕውቀት (common-sense sociological knowledge) ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የመጽሐፉን ጭብጥ የበልጥ አጨቅይቶት ይታያል፡፡ በሌላ በኩል የመጽሐፉ ዐቢይ ግድፈት የኢትዮጵያን ታሪክ በተቃርኖ ክስተቶች መሞላቱ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ተለይቶ የወረደ ልዩ እርግማን አድርጎ መመልከቱ ነው፡፡ ለመሆኑ የየትኛው አገር ታሪክ ነው ከተቃርኖ ክስተቶች ነጻ የሆነው? ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ ብታስስ አንድም አገር ከዚህ የተቃርኖ ክስተቶች የጸዳ ሆኖ አይገኝም፡፡ ይህ ተቃርኖ ከሌለው አገሩ ታሪክ የለውም ማለት ነው!!
ወደፊት ሀያሲዎች በዚህ መጽሐፍ ላይ ያለውን ዝርዝር ፍልሰት በስፋት እንደሚዳስሱት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን ወደ ዋናው ነጥብ እንመለስ – ኢሕአዴግ ማኪቬሊያዊ ፖለቲካን በኢትዮጵያ ውስጥ ሲተገብር በዋነኛነት የተጠቀመበት ስልት “የፍርሃትና የጥርጣሬ ባሕል” (Culture of Fear and Suspicion) በኅብረተሰቡ ውስጥ በስፋት እንዲሰፍን በማድረግ ነው፤ ግምገማን ልብ ይሏል፡፡ በርግጥ በዚህች አጭር ጽሑፍ ውስጥ የሥርዓቱን ማኪያቬሌያዊ ድርጊቶች በዝርዝር ማቅረብ አስቸጋሪ በመሆኑ አንኳር በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ይሞከራል፡፡
“ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል” የሚል አንድ የቆየ አባባል አለ፡፡ የዚህን አባባል ትክክለኛነት የምንረዳው የዚህ ሥርዓት ዋና ቀኖና በሆነው “የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት” የሚለውን ዲስኩር በጽሞና ስናይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ በጻፍኳቸው መጣጥፎች የዚህን አባባል ተቃርኖ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ ያውም እነኚህ ሦስት ቃላት፣ ማለትም “ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ” የሚባሉት በትክክለኛ ትርጓሜቸው ሲታዩ ሦስት የተለያዩ የሕዝብ ስብስቦችን እንደሚያመለክትና በምንም ዓይነት እኩል ያልሆኑ ጽንሰ ሐሳቦች ሆኖ እያለ፤ ይህን እኩልነት ብሎ በተደጋጋሚ ሲለፈፍ፣ አሁን አሁን ለሕዝቡም ቢሆን እውነት እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ በተግባር ደግሞ ያለው እውነታ እጅግ ወሰብሰብ ያለና ይህን የእኩልነት ዲስኩር በምንም ዓይነት አመላካች እንዳልሆነ የለት ተዕለት ሕይወታችን ይመሰክራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የእኩልነት ዜማ እንኳን በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ሕዝቦች ቀርቶ ራሱ ኢሕአዴግ ብሎ ባዋቀራቸው አራት የጎሣ ፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ እንኳን እንደማይሠራ ሁሉም የሚያውቀው ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በእውነቱ ከሆነ ኢሕአዴግ የሚለውን የለበጣ ስያሜ ሲፋቅ የምናገኘው ሕወሓትን ነው፡፡ በተግባርም እንደሚታየው የተቀሩት ድርጅቶች ሌሎችን ክልሎች የሚያስተዳድሩ “የሕወሓት እንደራሴዎች” እንጂ የራሳቸው ህልውና ያላቸው ነጻ ድርጅቶች በፍጹም አይደሉም፡፡ ድርጅቱ ከአንድ ወጥ የፖለቲካ ፓርቲነት ይልቅ የተለያዩ የጎሣ ድርጅቶች ስብስብ ሆኖ ለረጅም ጊዜ መቆየቱ የሚያስረዳን አንድነትና እኩልነትን የማይሻ የትምክህት እና የጠባብነት ወይም የጎሠኝነት ስሜት ተጠቂ መሆኑን ነው፡፡ የሚገርመው ግን ይህን የትምክህትና የጥበት ባሕሪ በሌሎች ላይ ተለጥፎ ሲታይ ነው፡፡
ይህ ሥርዓት እንደ ዋነኛ ድል ከሚቆጥራቸው ክንውኖች አንዱ የዴሞክራሲን ሥርዓት ለሕዝቡ ማጎናጸፉን ነው፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ እጅግ ሰፋ ያለና የተወሳሰበ የፖለቲካ እሳቦት ነው፡፡ ይህም ሆኖ የጽንሰ ሐሳቡ ዋነኛ መለኪያዎች ሆነው ከሚወስዱት መካከል አንድን መንግሥት የሚያዋቅሩት ሦስቱ አካላት፤ ማለትም የሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው መለያየትና እርስ በርሳቸው መጠባበቅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን በፍጹም አንዱን የመንግሥት አካል ከአንዱ መለየት የማይቻልና ሁሉም የአንድ ሳንቲም የተለያዩ ገጽታዎች ነው የሚመስሉት፡፡ ይህ ጉዳይ አሁን አሁን በመርሕ ደረጃ እንኳን መቀመጡ ተረስቶ ገለልተኛ የመንግሥት ተቋማት ናቸው ተብሎ ከተደነገጉት እንደ ፖሊስና የፍርድ ቤት ተቋማት ደጃፎችና ግንቦች ላይ የገዥው ፓርቲ መፍክሮች ተንጠልጥለው ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ የዴሞክራሲ ዋና መሠረቱ ተናደ ማለት ነው፡፡
ሌላው ከዚህ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚያያዘው፣ በተወሰኑ ዓመታት ልዩነት የሚካሔደው ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ቢሆን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየን፣ ቀደም ሲል ለይስሙላም ቢሆን የነበረው የብዙሃን ፓርቲ ሥርዓት ቀስ በቀስ ደብዛው ጠፍቶ በአንድ ጠቅላይና “አውራ” ፓርቲ መዳፍ ሥር ወድቆ መገኘቱን ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በየአምስት ዓመቱ የሚካሔደው ምርጫ ገዢው ፓርቲ መቶ በመቶ “እያሸነፈበት” በአሁኑ ሰዓት ትርጉም አልባ እየሆነ መጥቷል፡፡ እዚህም ላይ ዴሞክራሲ ባዶ ፕሮፖጋንዳ ሆኖ ቀረ ማለት ነው፡፡
ሦስተኛው የዴሞክራሲ ገጽታ ሰዎች ሐሳባቸውን በነጻ የሚገልጹበት የሚደያ ሥርጭት ነው፡፡ ይህንን በሚመለከት ራሱ ገበያው የሚነግረን ብዙ ነገር አለ፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ እጅግ በተቀራረበ ርቀት ላይ እንደ አሸን ፈልቶ የሚያገኙት ሥጋ ቤት፣ ጫት ቤት፣ መጠጥ ቤትና ፖሊስ ጣቢያዎች ሲሆን (በነገራችን ላይ የፖሊስ ጣቢያዎች ብዛት ከሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ቁጥር ጋር በፍጹም የሚወዳደር አይደለም፤ ያውም እንደ አዲስ አበባ ባለ ንጽሕናዋ የተጓደለ ከተማ) መጽሔትና ጋዜጣ ለመግዛት ግን ስንት ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ከተማ ውስጥ የሚያገኙት ከሦስትና ከአራት አማካይ ቦታዎች የዘለለ አይሆንም፡፡ ለዚያውም የሚያገኙት የቁንጅና፣ የስፖርትና የሜድካል ጋዜጣና መጽሔቶችን ነው፡፡ ይህ አፍራሽ አዝማሚያ ምን ያህል በሕዝቡ የንባብ ባሕል ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ መገመትም አያዳግትም፡፡
ከዚህ የዴሞክራሲ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሥርዓቱ ሌላው “ዐቢይ ድል” ነው የሚለው ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድልን የሚያጎናጽፈውን የፌደራል አወቃቀርን ነው፡፡ በርግጥ ይህ ሥርዓት በዋና ተቃዋሚዎች ከሚወገዝበት አንዱ ምክንያት አገሪቱን በጎሣ በተሸነሸኑ ክልሎች በመከፋፈልና ለእነሱም “ሰፊ የሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል” መብት በመስጠቱ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ይህም ቢሆን በተግባራዊነቱ ላይ ጥልቅ ጥያቄ ያጭራል፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ክልሎች በተለያየ ጊዜ የሚወጡት ዐዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ከአንድ ምንጭ የፈለቁ ሐሳቦች በመሆናቸው ነው፡፡ እውን እውነተኛ የሆነ የራስ በራስ አገዛዝ ባለበት አገር እንዴት ሁሉም ክልሎች በአንድ ዓይነት ቅኝት ሊቃኙ ይችላሉ? እንደ እውነቱ ከሆነ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአንድ ጠቅላይ አገዛዝ ሥር መውደቋ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ በጎሣ ላይ የተመሠረት የአስተዳደር ክፍፍል ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ የማኅበረሰብ ግጭቶችን እንደ አሸን አፍልቷል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምንሰማው የድንበር የይገባኛል ግጭት የሚከሰተው በሉዓላዊ አገሮች መካከል ነበር፡፡ አሁን ግን “ዕድሜ ለጎሣ ፌደራሊዝም” በኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው የድንበር የይገባኛል ግጭት በአንድ አገር ውስጥ ባሉ የአስተዳደር ክልሎችና ጎጦች ሆኗል፡፡
በኢኮኖሚው ረገድ በመንግሥት ሚዲያ ከምንሰማው የእጥፍ አኃዝ ዕድገት በተጻራሪ በውኑ የገበያ ዓለም የሚታየው እውነታ መሠረታዊ ሸቀጦች በራሽን ለዜጎች የሚከፋፈሉበት፣ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለረኀብ የሚጋለጡበት፣ የዋጋ ንረት በመቶ ፐርሰንቶች የሚወጣበት፣ ከምርታማነት ይልቅ ድለላ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስና በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉና እየተስፋፉ የመጣበት የተንጋደደ (misguided) ኢኮኖሚ ነው፡፡
በማኅበራዊው ዘርፍ ደግሞ የባሕል ዝቅጠት፣ ዋልጌነት፣ ሥራ እጥነት፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ ወንጀለኛነት እና የሱስ ተጠቂነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ነው፡፡
እንደኔ አተያይ እነኚህና ሌሎች በቦታ ጥበት ምክንያት ያልተጠቀሱ ሺሕ የሚሆኑ የማኪቬሊያዊ የፖለቲካ ድርጊቶች አሁን ይህን ሥርዓት ለገባበት አጣብቂኝ ዋና ምክንያት ይመስሉኛል፡፡ “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ አሁን የገባበትን ቀውስም ለመፍታት እየወሰደ ያለው የኀይል እርምጃና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አገሪቱን በከባድ የፖለቲካ ድባብ ሥር እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡ የሕዝቡን ቅሬታና ተቃውሞ ወደ ጎን በመተው በራሱ ድርጅታዊ አሠራር መፍትሔው በራስ ላይ የሚካሄድ “ጥልቅ ተሐድሶ” ነው በሚል የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ለማድበስበስ ይሞክራል፡፡
ሲጀመር “የጥልቅ ተሐድሶ” ዲስኩር መሠረታዊውን የፖለቲካ ጥያቄ በማድበስበስ ወደ ተራ አስተዳደራዊ ጉዳይ አውርዶ ያገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም የተደረገ ማኪቬሊያዊ የፖለቲካ ሤራ ነው፡፡ በመጨረሻ ውጤቱንም እንዳየነው ጥቂት “የሕወሓት እንደራሴዎች” ሥልጣን ከመሸጋሸግ ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳላመጣ በሙሉ ልብ መመስከር ይቻላል፡፡ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደሚባለው ብሂል ቀደም ሲል የነበረው የፖለቲካ ችግር ባግባቡ ባለመፈታቱ በቅርቡ አመጹ እዚህም እዚያም መልሶ ብቅ ጥፍት ሲል ይስተዋላል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ለአገሪቱም ለዘለቄታው ጠቃሚ የሚሆነው እርምጃ አሁን አገሪቱ የገባችበትን ችግር መንስኤ በጽሞና እና በተረጋጋ መንፈስ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ በመመርመር አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ይህን ለማድረግ እውን ቅንነቱና ብልህነቱ ካለ ጊዜው የረፈደ አይመስለኝም፡፡

Filed in: Amharic