>

ዘመዶቼ፣ እንዴት ሰነበታችሁ?... (ህይወት እምሻው)

ዘመዶቼ፣ እንዴት ሰነበታችሁ? እንዴትስ ከረማችሁ?

እኔማ…ከረጅም የዝምታ ጊዜ በኋላ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳትን አስታክኬ ከድሮ የቅኔ መፅሃፍ ላይ ባገኘኋት ስንኝ፣

‹‹ቆስሎ የነበረ በዝምታ ወስፌ፣
አሁን ተናገረ ተፈወሰ አፌ›› ብዬ እየፎከርኩ ልመለስ ነበር ሃሳቤ፡፡

አዲሱን ዓመት አስመልክቼ፣ ‹‹እሰይ! እነሆ አምላክ በደግነቱ አዲስ ታሪክ እንፅፍበት ዘንድ ሌላ 365 ባዶ ገፆች ሰጠን›› ልላችሁ ነበር ፍላጎቴ፡፡

ምን ያደርጋል! አዲስ ዓመት አዲስ እድል እንጂ አዲስ ልብ አይሰጠምና፣ ያው እንደምታዩት ፣ 2010ን አጀማመራችን አንገት የሚያስደፋ፣ ራስ የሚያስይዝ እንጂ ዳንኪራ የሚያስረግጥ ፣ የሚያስፈነጥዝ አልሆነም፡፡

ገና ካሁኑ በባዶ ገፆቻችን ላይ እየፃፍነው ያለነው ነገር ክፉኛ ያሰጋል፡፡
በፍርሃት ያርዳል፡፡

በየቦታው የእሳቱን መቆስቆስ፣ የፍሙን መራገብ ባዩ ጊዜ፣

‹‹እንዲህ ጤሶ ጤሶ የነደደ እንደሆን
የአመዱ መፍሰሻ ስፍራው ወዴት ይሆን?›› በሚል ጭንቀት ሰቅፎ ይይዛል፡፡

የሆነው ሆነና….ዘመዶቼ፣ እንዴት ሰነበታችሁ? እንዴትስ ከረማችሁ?

Filed in: Amharic