>
5:13 pm - Friday April 19, 0052

በሶማሌ እና በኦሮሞ የተከሰተው ግጭት ዋና ተዋናይ ወያኔ ነው (ጋዜጠኛ አበበ ገላው)

የጥላቻ ፖለቲካ ውጤቱ የከፋ መሆኑን ለማገናዘብ ትንሽ የታሪክ ገጾችን ማገላበጥ በቂ ነው። ሂትለር በአለማችን ላይ ተወዳዳሪ የሌለውን እልቂት የጫረው ጥላቻን በመስበክ ነበር። እኛ ታላቅ ዘር ነን፣ አይሁዳይውያን እና ሌሎች “ተውሳኮች” (vermins) ናቸው የሚለው ስብከት ተራውን ጀርመናዊ ዜጋ ብቻ ሳይሆን ምሁራን የነበሩ አዋቂዎችን ጭምር አስክሮና አነሁልሎ የግፍና እልቂት ተዋንያን እንዲሆኑ አድርጓቸው ነበር። የዘር ፖለቲካ ያለጥላቻና መከፋፈል አይሰራም።
ወያኔም ከምስረታው ጀምሮ ጥላቻን እየሰበከ አገሪቷን ለከንቱ አላማ በጦርነት እሳት ለበብልቦ የድሃ ገበሬ ልጅ በከንቱ አለቀ። ደርግ ወድቆ የተመኙት የስልጣን ወንበር ላይ ሲቆናጠጡ ባሰባቸው። ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍለው ለእያንዳንዱ ብሄረሰብ ነጻ አውጭ ግንባር በማቋቋም በተለይ በአማራ ህዝብ ላይ አስከፊ የዘር ጥላቻ፣ የስነልቦና ጦርነት በመክፈት ማንንም በድሎ የማያቅ ምስኪን የአማራ ገበሬ ከየአካባቢው እንዲፈናቀል፣ እንዲገደልና በፍርሃት ተሸማቆ እንዲኖር አደረጉት። በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች በህወሃት ቆስቋሽነት ሲፈናቀሉና ሲገደሉ መለስ ዜናዊ በእብሪትና በጥላቻ ተውጥሮ የግፉ ሰለባዎች ዛፍ ስለመነጠሩ ነው የተፈናቀሉት ሲል በአደባባይ ተሳለቀባቸው። ድግነቱ የሚስኪኖችን እንባ የሚያብስ አምላክ ፍርዱን አላዛባም!
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎችም በሰላም የኖሩ ህዝቦች እንዲናቆሩ፣ ወድ ግጭትና መፋጠጥ እንዲያመሩ መንገዱን ሁሉ ጠረጉ። ይህ ሁሉ ሸር የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሳያቸው እንዲሳካ የታለመ አሳፋሪና ሰብአዊነት የጎደለው እኩይ ተግባር ሲሆን ሌላውን እያናቆሩ እነርሱ አገሪቷን በዘረፋ እርቃኗን አስቀሯት። ለእነርሱ እድገት ማለት ሌላውን ወደኪሳራ እየገፉ፣ መሬት እየዘረፉ፣ ምስኪን እያፈናቀሉ አድሏዊ ግንባታና የአሻጥር ቢዝነስ መስራት ነው። የወያኔ ስኬት ባጭሩ ይሄው ነው።
የሩዋንዳ እልቂት የተከሰተው በአንድ ጀንበር አልነበረም። ለረጅም ዘመናት ሁቱዎችና ቱትሲዎች እንዲጠላሉ በዘር እንዲፈራረጁ እና እንዲናናቁ በገዢዎች ሲቀመም የቆየ የዘር ፖሊቲካ ውጤት ነው። ዘርና ሃይማኖት ከፖለቲካ ጋር ፈጽሞ ሊቀላቀሉ እንደማይገባ አብዛኛው አለም ተቀብሎ የፖለቲካ ጨዋታ ከሃሳብና ከ አይዲዎሎጂ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፣ በህግ ያግዳሉ። በሌላው አገር በህግ የሚያስቀጣ የዘር የጥላቻ ቅስቀሳ በእኛው አገር ህገ መንግስታዊ ጥበቃ የሚደረግለት መብት ነው። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው።
ህወሃት ያለዘር ፖለቲካ ህልውናውን ያጣል። የአናሳ አገዛዝ (minority regime) መሰረት ይናጋል፣ በዘር ላይ የተመሰረተ ዝርፊያና አፈና ያከትመለታል።
ዛሬ ህወሃት የለኮሰው እሳት መልሶ እራሱን ቢለበልበው እንደለመደው ለዘመናት ተስማምቶ የኖረን ህዝብ መርዝ እየረጨ ያጋጫል። በሶማሌ እና በኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጆች የተከሰተው ግጭት ዋና ተወናይ እንደ ተለመደው ወያኔ ነው። ይህ ሃቅ እየታወቀ አንዳንዶች የፖሊቲካ ትርፍ የሚያስገኝ መስሏቸው እያጋጋሉት ነው። ውጤቱ ግን የበለጠ አደገኛ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ህዝቦች ለዘመናት የገነቡትን ትስስር መበጣጠስ ቀላል ነው። የአንድ አገር ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን ማፈራረስ እንደመገንባቱ ከባድ አይደለም።
የዘር ፖሊቲካ ጨዋታ የህወሃትን እድሜ ከማራዘም ባሻጋር የሚያመጣው ፋይዳ እንደማይኖር ለማንም ግልጽ ነው። ጭቆኖች በጋራ በዚህ አስከፊ የዘረኞች ስርአት ላይ አምርረው በአንድነት ሊነሱ ይገባቸል።
በየሶሻል ሚድያው የጥላቻ ፖሊቲካን የሚያራግቡ ህዝብን በጅምላ የሚፈርጁ እና የሚያጥላሉ በሙሉ በቃ ሊባሉ ይገባቸዋል። የሶሻል ሚድያ አክቲቪስቶች አሉታዊ ሚና ከመጫወት ይልቅ የጠራ አላማ ይዘው ህዝብን የማቀራረብ በጋራ ጠላታችን ላይ የማተኮር ስራ ሊሰሩ ይገባቸዋል። ከትናንት ስህተት ከመማር የተሻለ ብልህነት የለም። ሁሉንም ለማድረግ አልመሸም!
Filed in: Amharic