>

‹‹ጠላቴን አብዛልኝ›› አለ ያገራችን ሰው! (ልጅ አምደ ጽዮን)

“They” LOST the Battles!

 I Hope “they” will also LOSE the War!


በወርሃ ሚያዚያ አልበሙን ሲለቅ ‹‹ … እርሱ እኮ የቀድሞው የነገሥታቱ ስርዓት እንዲመለስ የሚጮህ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ … የአንድ ብሔር የበላይነት አቀንቃኝ …›› ብለው ሰደቡት፤ አፌዙበት … አልበሙ ግን የሽያጭ ክብረ ወሰን ሰበረ! … ድል አድራጊነቱን ጀመረ!

¤¤¤
እነስም አይጠሩ ጩኸታቸውን ቀጠሉ … ግን እንዲያም ሆኖ አንድ እሁድ ዕለት ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ በብዛት ከተነበቡ ዜናዎች መካከል ቀዳሚው የእርሱ ጉዳይ ሆነ፤ ዘፈኑ ቢልቦርድ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ አንደኛነቱን ተቆናጠጠ፤ ታላላቅ የዓለም መገናኛ ብዙኃን በሩን አንኳኩተው ለቃለ-መጠይቅ ደጅ ጠኑት! … ሌላ ድል!
¤¤¤
‹‹…ወቅቱ እኮ ኢ-ፍትሃዊ ነው … ምን ሰርቶ ነው ይህ ሁሉ መገናኛ ብዙኃን የሚቀባበለው?…›› አሉና የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ወሬያቸውን ማውራት ቀጠሉ … ሰውየው የዋዛ አይደለምና እነርሱ የጥላቻ መርዛቸውን ሲረጩ፣ እርሱ በፍቅር ሽልማቶችንና ክብሮችን ደራረበ … ሌላ ድል! (ስንተኛ ድል ነው? መቁጠር ሰለቸኝ! ቁጠሩ)
¤¤¤
አልበሙን እንዳያስመርቅ ከለከሉት፡፡ ወዳጆቹ ‹‹አይዞህ … ከጎንህ ነን!›› አሉት፡፡ ድርጊቱን ትልልቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለዓለም ኅብረተሰብ ሲያቀርቡት የሰውየው ገናናነት ይበልጥ ጨመረ፡፡ [‹‹ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ምን አገባቸው?››] እንዳትለኝ … ቢልቦርድ ላይ አንደኛ ሆኖ የተቀመጠው ዘፈን እኮ የሰውየው የፍቅርና የአንድነት ስብከት እንጂ የጠላቶቹ ፕሮፓጋንዳ አይደለም … ሌላ ድል! (ቁጠሩ፣ ቁጠሩ)
¤¤¤
ይህ በሆነ በጥቂት ቀናት ልዩነት ደግሞ፣ ዛሬም ድረስ ምስጢሩ ቢተነተን ከተወዳጅነቱ ዝቅ የማይለውንና ምስጢርነቱ የማያልቀውን ዘመን ተሻጋሪውን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብርን›› በዘጠኝ ደቂቃዎች ሲያቀርበው ሌላ ገናናነትን ክብርን ጨመረ! … እዚህ ጋ ከድልም አለፈና ሌላ ጣጣ ይዞ መጣ … የሌሎች ዘፋኞችን አለመቻል ዐሳይቶን የነበረው ሰው አሁን ደግሞ የፊልም ሰሪዎቻችንንም አለመቻል ዐሳየን!
¤¤¤
(ወዳጄ ወደ ጦርነት ከመግባትህ በፊት የተጋጣሚህን አቅም በሚገባ እወቅ፤ ከዚያ ወይ ትገጥማለህ ወይ በሰላም ትገብራለህ! … አቅም ቢኖርህም እንኳ ጦርነትን ለመምራትም እኮ የጦር አመራር ስልት ያስፈልግሃል … ለነገሩ የዚህኛው ጦርነት ተጋጣሚዎች መሰረታዊ ልዩነታቸው የስልት ሳይሆን የአቅም ነው፤ አቅም ያለው እያሸነፈ ነው!)
¤¤¤
በዚህ ከቀጠሉ ውጊያዎቹን መሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከሰውየው ጋር የገጠሙትን ሙሉ ጦርነትም ይሸነፋሉ! ያኔ የመንግሥት ዝቅታ የግለሰብ ከፍታ እንላለን … ለነገሩ አሁንም ቢሆን የቴዲን ከፍታ በተግባር አይተናል!
They LOST the Battles! I Hope they will also LOST the War! 
‹‹ጠላቴን አብዛልኝ›› አለ ያገራችን ሰው!
¤¤¤

 

Filed in: Amharic