>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7324

ይድረስ ለኢንጂነር ይልቃል ጌትነት

(Mohammed A. Endris እንደጻፈው)

‘በበፍቃዱ የኢትዮጵያዊነት አረዳድ ላይ የእኔ አስተያዬት’ በሚል ኢንጂነር ይልቃል አንድ ፅሁፍ ከትበዋል፡፡ በፍቃዱ ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ ያለ«ኢትዮጵያዊነት» ልትኖር አትችልምን? ሲል ባቀረበው ሰፋ ያለ ፅሁፍ ላነሳቸው ሀሳቦችም መልካም የሚሉትን በማወደስ በመሰረታዊነት ግን የፅሁፉን ጭብጥ ተችተው ፅፈዋል፡፡ እኔም ኢንጂነሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ካላቸው ስፍራ እና ይህን ለመሰለው የሀሳብ መለዋወጥ ዝግጁ መሆናቸውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ባነሱት ሀሳብ ዙሪያ ጥቂት ጉዳዮችን ለማንሸራሸር ፈልግሁ፡፡ በቅድሚያ በዚህ አጀንዳ የግል ሀሳባቸውን ማካፈላቸውን እና የውይይት በር መክፈታቸውን እንደ አንድ የፖለቲካ መሪ ተገቢ ሚናቸውን እንደተወጡ በማመን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በ 10 ዋና ዋና ነጥቦች በተዋቀረው ፅሁፋቸው ውስጥ ከተሞክሮ እና ነባራዊውን ሁኔታ ከተረዱበት በመነሳት የሰጧቸው በርካታ ጠቃሚ ሀሳቦች አሉ፡፡ የመልዕክታቸው ገንቢ ጎን አንባቢ ተገንዝቦ እንዲተገብረው በመተው ተጨማሪ የሀሳብ ልውውጥ ይጠይቃሉ ባልኳቸው ጉዳዮች ላይ ለማተኮር እፈልጋለሁ፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዋና ዓላማ ከኢትዮያዊነትጋ በተያዘ የመቀርቡ ጥያቄዎች ላይ ባለድርሻዎች የሚያደርጉትን ውይይት እንዲቀጥል ማድረግ እና የጋራ መፍትሄ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የግል ሀሳብን ማቅረብ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ ውይይት በህብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን እንዲዳስስ እና መርህንም መሰረት ያደረገ መፍትሄ እንዲመጣ በኢንጂነር ይልቃል ጽሁፍ ውስጥ አሉ የምላቸውን የይዘት ስህተቶች እና የውስጥ ተቃርኖዎች መጠቆም እንደስልት ተጠቅሜአለሁ፡፡

ከፅሁፉ ቀዳሚ ትኩረቴን የሳበው በትምህርተ ጥቅስ ያስቀመጡትና ስለኢትዮጵያዊነት የተነሳው የመወያያ አጀንዳ ” ‘አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ስነልቦናን የሚወክል ሀሳብ’ ነው” የምትለዋ ሀረግ ናት፡፡ ትኩረቴን የሳበችውም ‘የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች’ ለማለት በነባሩ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እራሳቸውን የሚገልፁ ብዙሀኑ ይሁኑ አልያም የተወሰኑት ብቻ በሚለው ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ ድምዳሜ እስካሁን አንብቤ ስለማላውቅ ነው፡፡ የአንዳንዶች ስነልቦና ብቻ ለመሆኑ ማረጋገጫ ሊቀርብለት ካልቻለ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ አገር የተቀበለ ሁሉ ላይታደስ ተገንብቷል በሚባለው ኢትዮጵያዊነትም ተስማምቷል ከሚል የተሳሳተ ድምዳሜ የተወሰደ ይሆን የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአድዋ ዘመቻ ጣልያንን ለመውጋት በአንድነት ተሰልፈዋል ማለት የውስጥ የፖለቲካ ሀይሎች የሚፈጥሩት ብሄርተኝነት የወለደው መገለል ላይ ብዙሀኑ ቅሬታ የላቸውም ለዚያም ቅሬታ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲመጣ አይታገሉም ማለት አይደለም፡፡ ከሀገር ፍቅር እና ጀግንነት (Patriotism) ስሜት የሚመነጭ ኢተዮጵያዊነትን የአንድ ማህበረሰብ የበላይነት የገነነበትን ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ኢትዮጵያዊነትን ከመቀበል ጋር አስተካክሎ ቀሪዎቹን ‘አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች’ በሚል አልተወከልኩም የሚሉትን አሳንሶ ለማቅረብ መሞከር ጉዳዩን ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝና የሚመጥን መፍትሄ እንዳይመጣ እንቅፋት ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ምናልባትም ብዙሀኑ ኢትዮጵያን እንጂ ‘ኢትዮጵያዊነትን’ ያልተቀበለ መሆኑ ነባራዊውን የፖለቲካ አሰላለፍ በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንንም ወደጎን ብንለው የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ብለው ኢንጂነሩ ያነሱት ሀሳብ ለነዚያ የህብረተሰብ ክፍሎች ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ አለ የሚል ፖለቲካዊ ትርጉም ያዘለ ነው፡፡

አንድ በብሄራዊ ደረጃ የሚወዳደርን የፖለቲካ ፓርቲ እንደመራ ፖለቲከኛ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሱት ጥያቄ ካለ ያንን ጥያቄ እውቅና በመስጠት ፖለቲካዊ መፍትሄ ማምጣት ኃላፊነታቸው ስለመሆኑ ለኢንጂነር ይልቃል አይነገርም፡፡ በታሪክ አረዳድም ይሁን በኢትዮጵያዊነት አረዳድ የተለያዩ አማራጭ አተያዮች መኖራቸውን በፅሁፋቸው ማስፈራቸው ደግሞ የብሄር እና የሀይማኖት ነፃነት በኢትዮጵያ የነበራቸው ይዞታ የወለዷቸው የተለያዩ አተያዮች ማስታረቂያ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊኖር እንደሚገባው ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን የገጠሩ ህዝብ እራሱን በብሄሩ እንደማይገልፅ እና በብሄር መሻኮቱ የከተማው ባህሪ እንደሆነ ለማሳየት የሄዱበት መንገድ ጥያቄውን ተሰርቶ ባለቀ ኢትዮጵያዊነት ስም ሸፋፍኖ ለማለፍ የተደረገ ወደመፍትሄም የማያቃርብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በወጉ ያልተያዙ ጥያቄዎች በድህረ የኢትዮጵያ አብዮት ያመጡትን የፖለቲካ ቀውስ ዳግም የማይጋብዝበትም ምክንያት የለም፡፡ የ60ዎቹ አብዮተኞች ማንነት ላይ የተመሰረቱ ጥያቄዎችን በሙሉ ከመደብ ትግል ጋር ብቻ ለመተንተን ያሳዩት አቋም የብሄር ጥያቄ ገፍቶ ሲመጣ አሰባሳቢ ህብረብሄራዊ ኢትዮጵያዊነትን ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ እንዳይገራ እንቅፋት ሆኖታል፡፡ እውቅና የተሰጠው ጥያቄ የጋራ መፍትሄ ስለሚፈለግለት በኢትዮጵያዊ ማዕቀፍ ውስጥ እልባት የማግኘት እድል ስለሚኖረው አሉታዊ ተፅእኖውን መቀነስ ይቻላል፡፡ ከ43 አመት በኋላ በመሬት ላይ ያለን እውነታ ዳግም አስተባብለን ጥብቅና የምንቆምለት አንድ ወጥ ኢትዮጵያዊነት ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው የፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ እንዳይሆንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

በፅሁፋቸው ውስጥ “ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም እንዲመች አድርጎ እንደገና መበየን በፖለቲካው ዓለም ውኃ የሚያነሳ ክርክር አይደለም፡፡ ተግባራዊ ለማድረግም ያስቸግራል” የሚለው አገላለፅ ከየትኛው የፖለቲካ አስተሳሰብ የተቀዳ እንደሆነ ፈፅሞ ግልፅ አይደለም፡፡ ለብሄርተኝነት ጥያቄ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማምጣት መጣሩ ውሃ የማያነሳ ክርክር መባሉ ለጨዋታ ያህል የቀላቀሉት ሀሳብ ካልሆነ የፖለቲካ እና በፖለቲካ ፓርቲነት ተደራጅቶ የመታገልን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት አገላለፅ ነው፡፡ ለብሄርተኝነት ጥያቄ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመፈለግ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመርጡት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ሁነኛ መሳሪያ ነው፡፡ በሶሸሊዝም ርዕዮተ ዓለም ላይ የቆሙ ፓርቲዎች ከሶሸሊዝም መርህ የሚቀዳ የናሽናሊዝም አረዳድ አላቸው፡፡ እንደሰማያዊ ፓርቲ በሊበራሊዝም የሚመራ ፓርቲም ከሊበራሊዝም ርዕዮተዓለም የሚመዘዝ የብሄርተኝነት ጥያቄዎች መፍቻ መፍትሄዎች አሏቸው፡፡ በተጨማሪም ፖለቲካ Consensus and reconciliation ላይ የተመሰረተ ሳይንስ መሆኑ በሁሉም ርዕዮተአለም ውስጥ ገባ ወጣ እየተባለ መፍትሄ የመፈለግ እድል ይሰጣል፡፡ የናሽናሊዝም ጥያቄ የታሪክ፣ የማንነት፣ የባህል፣ የሀይማኖት፣ የህዝቦች አሰፋፈር እና መስተጋብር…ጥያቄ ሆኖ ሳለ ለነዚህ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊገኝ አይችልም ማለት ብሄርተኝነት ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ወደመሀል የሚያመጣ ፖለቲካዊ መፍትሄ ስለማይኖራቸው ሁሉም በያዘው መስመር ወደጠርዝ በመሄድ ውጥረት የማይለቀው አገራዊ የፖለቲካ ዲስኮርስ ይስፋፋ ብሎ ከመጋበዝ እንዴት ሊለይ እንደሚችል ማብራሪያ ያሰፈልገዋል፡፡

ሌላው ነጥብ ኢንጂነር ይልቃል በፅሁፋቸው ላይ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን አንድ ትርጉም እንዳላቸው እያቀያየረ ተጠቅሟል ሲሉ በፍቃዱን ይከሱታል፡፡ ሻገር ብለውም ሁሉንም የሚያግባባ አንድ ወጥ የኢትዮጵያዊነት ትርክት መያዝ አይቻልም ሲሉ የተለያዩ አይነት የኢትዮጵያዊነት ትርክቶች መኖራቸውን፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የተነጣጠሉ መሆናቸው፤ በታሪክ አረዳድም የተለያየ አይነት የኢትዮጵያዊነት አረዳድም ሊኖር ይችላል ሲሉ ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ የሚያመጣ ሀሳብ ያሰፍራሉ፡፡ በፅሁፋቸው ቀሪ ክፍሎች ግን በተቃራኒው እራሳቸውን ሲሞግቱ ይታያል፡፡ ለዚህ ትልቁ ማሳያ ደግሞ በፍቃዱ በፅሁፉ ‘ከቅርብ ግዚያት ወዲህ ኢትዮጵያዊነት በየቦታው ስሙ መጉላቱ የኢትዮጵያዊነትን ማበብ ወይንስ የብሄር ፖለቲካው የፈጠረውን ጫና መከላከያ ስልት’ ብሎ ላቀረበው ጥያቄ ኢንጂነሩ የሰጡት መልስ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እያበበ መሆኑን በማመን ኢህአዴግ በ26 አመት አገዛዝ ዘመኑ ኢትዮጵያዊነትን ሊንደው አልቻለም ሲሉ የተለያዩ ያሏቸውን የኢትዮጵያዊነት አረዳዶች አንድ ከመናድ የዳነ የጋራ ቅርስ ይዘት ይሰጡታል፡፡ ኢህአዴግ ሊንደው ፈልጎ ያልተሳካለት ኢትዮጵያዊነት አለ ማለታቸው ግን ዛሬም ከፊሉ ልዩ ጥበቃ የሚያደርግለት ከፊሉ ከትከሻው ሊያወርደው የሚፈልገው ኢትዮጵያዊነት አለ እንደማለት መሆኑን ለምን እንደዘነጉት አላውቅም፡፡ ‘ባልተናደው ኢትዮጵያዊነት’ አልተወከልንም የሚሉ ክፍሎች በተጨባጭ መኖራቸው እርሳቸውን አሉ ካሏቸው የተለያዩት የኢትዮጵያዊነት አተያይ ውስጥ አንዱን ብቻ ወግነው የቆሙ እንዳደረጋቸውስ አምነውበት ይሆን ወይ ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ በአንድ በኩል የተለያየ ኢትዮጵያዊነት አረዳድ አለ ብሎ በዚያው ፅሁፍ ስላልተሸረሸረው ኢትዮጵያዊነት መከራከርም የሀሳብ መፋለሱን መደበቅ የሚያስቸግር ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ከዚያም አልፎ የተለያየ የኢትዮጵያዊነት አረዳድን የሚቀበል ሰው የተለየ አስተሳሰብ ያቀረበን ሰው ከከፍተኛ ትችት እስከ ኑፋቄ እና ክህደት በሚያደርስ ፍረጃ ውስጥ መግባቱ ጤናማና በሳል ውይይትን የሚያደናቅፍ አቀራረብ ነው፡፡ የተለየ ሀሳብ በማራመዱም ለመማር እና ለመታረም ፍቃደኛ አይደለም በማለት አንድ ሰው ተማረ እና ታረመ ለመባል የግድ ወደአንድ አስተሳሰብ ብቻ መምጣቱን ማሳየት ነው የሚጠበቅበት ማለቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው እንደ በፍቃዱ ያሉ ለነባሩ አስተሳሰብ የቀረቡት ላይ ሲሆን ሌሎችን ወደባሰ ፅንፍም የሚጋብዝ ነው፡፡

በፍቃዱ በፅሁፉ ውስጥ የኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር መፈክር ዋና ማጠንጠኛው ኢትዮጵያ እነደ አገር ያላትን ቀጣይነት የተመለከተ ነው የሚል ሀሳብ አንስቷል፡፡ በመሰረቱም ከብሄርተኝነትጋ ተያይዞ ያሉ አስቸጋሪ ጉዳዮች መፍትሄ የሚያጡት የአንድ አገርን እንደ አገር መቀጠል ሀሳብ ላይ መግባባት ካልተቻለ እንጂ በዚያ አገር ዙሪያ የተለያየ አይነት አገራዊነትን ለማካተት በሚደረገው ጥረት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን በኢትዮጵያ አገራዊ ህልውና እና በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በእኩል በመመዘን አንድ አይነት የአገራዊነትን ምልከታ መንቀፍ አገርን ከመንቀፍ የመመደብ አካሄድ ነው፡፡ ይህም አካሄድ አካታች፣ አሰባሳቢ እና መካከለኛ የሚባል መፍትሄ እንዳይመጣ እንቅፋት ይሆናል፡፡ ለዚህ እንደመፍትሄ የተጠቆመው ደግሞ በዜግነት መብት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡

ኢንጂነር ይልቃል ግን ይህንን የፅሁፉን አስኳል ሳይዳስሱት አልፈውታል፡፡ እሳቸው የሚከተሉት የፖለቲካ ርዕዮተዓለምም ይህን አቋም ደግፈው እንዲቆሙ የሚያስገድዳቸው ስለነበር ዋናው አቋም ላይ ከማተኮር ተገንጣይ ማሳያዎች ላይ ሀሳብ ለመስጠት መርጠዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያ በምትባለው ምድር ለሚኖሩ ሁሉ በዜግነት ላይ የተመሰረተ መገለጫ እናድርገው የሚለውን የበፍቃዱን ሀሳብና ለሀሳቡ ማስረጃነት ያመጣቸውን መከራከሪያዎች አማራጭ መፍትሄ በሚጠቁም መልኩ ቢተቹት ኖሮ ፅሁፋቸውም የተሸለ ትርጉም ይኖረው ነበር፡፡ እሳቸው በሚያምኑበት በሊበራል ዴሞክራሲ መስመር Liberal Nationalism የሚባለው ብሄርተኝነት ዋነኛ መገለጫ ከሚባሉት አንዱ ህገመንገስትን ማእከል ያደረገ በህግ የበላይነት ላይ የሚመሰረት የዜጎች አስተዳደር ነው፡፡ ሁለተኛው ሊበራል ናሽናሊዝም እያንዳንዱ ብሄር ከሌለው ብሄር እኩል መሆንን፣ ነፃ እና የራሱን እድል በራስ መወሰንን አምኖ የሚቀበል የናሽናሊዝም አይነት ነው፡፡ በሶስተኛነት ደግሞ ሊበራል ናሽናሊዝም ትኩረቱን አገር ብቻ ሳያደርግ ዋና መርሁ የሆነው ግለሰብ ላይ የሚያተኩር፤ ግለሰቦችም ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት…ሳይገድባቸው እኩል መሆናቸውን የሚያምን ነው፡፡ ‘የግለሰብ ጉዳይ የአገር ጉዳይ ነው-የአገር ጉዳይም የግለሰብ ጉዳይ ነው’ በሚል መርህ የሚታወቀው የሊበራል ዲሞክራሲ መስመር በኢትዮጵያ ምድር ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሱትን ኢትዮጵያዊነት አይወክለኝም ጥያቄን በዚያው መስመር የመፍታት አቅሙ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደውም ይህ ጥያቄ መልስ የሚያገኝበትን መንገድ ማሰብ ከሁሉም ፓርቲዎች በበለጠ ሁኔታ ኃላፊነት ያለባቸው በዚህ ርዕዮዓለም የሚያምኑት ናቸው፡፡ ግለሰብን ማእከል ያደረገው ናሽናሊዝም ደግሞ ወደመስመር የሚገባው በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ያለምንም ልዩነት በሚኖራቸው የዜግነት መብት ላይ የተመሰረተ ዋስትና ሲኖር ነው ብሎ ያምናል-ሊበራል ናሽናሊዝም፡፡ በሁሉም መልኩ ብናየው በፍቃዱ ያነሳው ዜግነት መብት ላይ የተመሰረተ የብሄርተኝነት አረዳድ ኢንጂነሩ ደግፈውት ሊከራከሩ ሲገባ በተቃራኒው ዜግነት መብት ላይ ብቻ የተመሰረተ አካሄድ መፍትሄ አለመሆኑን ለማሳየት የሄዱበት ርቀት ሊበራል ናሽናሊዝም የኢትዮጵያን የብሄርተኝነት ጥያቄ መፍታት አይችልም፤ እንደፓርቲ ፕሮግራምም ሊበራሊዝም ለኢትዮጵያ የሚመጥን አይደለም የሚል መልዕክት እንዳያስተላልፍ ኢንጂነሩ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንዲህ መርህ እና አተገባበር ከሚጣረሱባቸው ምክንያቶች ዋናው አተገባበሩ ከራስ አመለካከት እና ጥቅም ተቃራኒ የሆነ ውጤት እንደሚያመጣ ሲታመን ነው ፡፡ በዚህ ግዜ መርህ ይጣሳል፡፡ በአንድ ወቅት ዋነኛ የግለሰብ መብት የሚያሳስባቸው ምሁር ስለኢትዮጵያ ታሪክ በሚደረግ ክርክር ላይ ለረዥም ግዜ ከሚያምኑበት አቋም ተቃራኒ ላይ ቆመው ሲከራከሩ ታዝቢያለሁ፡፡ ለወትሮው አገር ማለት ሰው ነው ብለው የሚያምኑት እኒሁ ምሁር አገር ማለት ሰው ከሆነ የኢትዮጵያ አገራዊ ታሪክ የሰዎቿ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህል እና ማንነት የህዝቦቿ ባህል እና ማንነት ነው፡፡ አሁን ኦፊሴላዊ የሚባለው ታሪክ እና ማንነት የኢትዮጵያ ህዝቦችን ታሪክ እና ማንነት የማይወክል ከሆነ አገር ማለት ሰው ነውና የህዝቦቿን ታሪክ እና ማንነት ሊወክል በሚችል መልኩ አዲስ ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል የሚል ጥያቄ ሲነሳ ‘አገር ማለት መሬቱ ነው’ ወደሚል 180 ዲግሪ የተቀለበሱበትን ክስተት አስታውሳለሁ፡፡ በዚህኛው ስሌታቸው አገር ማለት መሬት ከሆነ የአገሪቱ ታሪክ መሬቱን አስገብሮ የገዛው አካል ታሪክ ነው ወደሚለው ይወስዳቸዋልና፡፡ ይህን መሰሉ ለሚያምኑበት መርህ በየትኛውም አጋጣሚ ለመቆም ቁርጠኝነት ማጣት በተለይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከባድ የተዓማኒነት ችግርን የሚፈጥር ጉዳይ ነውና ጥንቃቄ ይሻል፡፡

በስተመጨረሻም የኢንጂነር ይልቃል ፅሁፍ ያለውን መሰረታዊ የመርህ ስህተት እና የሀሳብ ተቃርኖዎቹን ማከም ቢቻል ትልቅ የመወያያ ርዕስ ይሆናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብሄርተኝነት አንኳር የፖለቲካ ጥያቄ በሆነባቸው አገራት አጀንዳውን በሚገባው መድረክ እና በሚመለከታቸው አካላት መወያያ እንዲሆን ማቅረብ መርህን መሰረት ያደረገ መፍትሄ ለማምጣት ይረዳል፡፡ በአገራችን ይህን መሰሉን ስስ አጀንዳ ሚዛን በሳተ መልኩ ወገንተኝነት ላይ ብቻ ለሚያጠነጥኑ ክርክሮች ማቅረብ የሚያቀራርብ መፍትሄ እንዳይመጣ አድርጓል፡፡ ከዚህ አንፃር በፍቃዱ ያቀረበው መወያያ እና ኢንጂነር ይልቃል ያከሉት ፅሁፍ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በስተመጨረሻም መሰል የብዙሀን ጥያቄዎችን በአላየሁም መንፈስ ማለፍ የሚኖረው ዘላቂ ጉዳት ታሳቢ ተደርጎ አጀንዳውን ወደ መሀል በማምጣት ሀሳቦችን በማፍታታት መፍትሄዎችን በጋራ መተለም የሁላችንም ኃላፊነት እንደሆነ በመጠቆም ላብቃ።

Filed in: Amharic