>
5:13 pm - Wednesday April 18, 5764

''የአስማማው እንባ'' (በኣዲስ ጉዳይ)

ለወትሮው ፈገግታ የማይለየው ብስል ቀይ ፊቱ ዛሬ ጠቁሯል። ድሮም ለማበጠር ብዙም የማይጨነቅለት ጸጉሩ አሁንም እንደቀድሞው ነው። አንድ ቦታ ላይ ተተክለው መቆየት የማይሆንላቸው ዓይኖቹ ከመሬት ላይ መነቀል አቅቷቸዋል። ምናልባት በጋዜጠኝነት ዘመኑ ስለሰዎች መታሰርና ፍርድ ቤት መቅረብ ዘግቦ ይሆናል እንጂ ራሱ ታሳሪ ሆኖ ዳኞች ፊት ሲቆም ግን የመጀመሪያው ነው። በፖሊስ በታሰረበት የመጀመሪያዎቹ ቀናት የነበረው ጥንካሬና ተስፋ አሁን የጨለመ መስሏል። ድካም የማያውቀው አስማማው ደክሟል። ፊቱ ላይ ተስፋ መቁረጥና ጥያቄ ይነበባል።
ከተያዙበት ቀን ጀምሮ ለሦስተኛ ጊዜ በቀጠሮ የቀረቡትን የዞን ዘጠኝ ጦማርያንን ጉዳይ ለማየት የተሰየመው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ተረኛ ዳኛ ፖሊስ ያቀረበውን “ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልኝ” የሚል ማመልከቻ በንባብ ካሰሙ በኋላ የአስማማው ግራ መጋባት የበለጠ የጨመረ መሰለ። ፖሊስ ለሚያካሂደው ምርመራ የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀው አስማማውን ጨምሮ የተያዙትን 9 ተጠርጣሪዎች ከሽብር ተግባር ጋር በተያያዘ ለመክሰስ የሚያስችለውን ማስረጃ ለማሰባሰብ መሆኑን በማመልከቻው ሲገልጽ የአስማማው ፊት ቅጭም አለ። በዚያች ቅጽበት የተለዋወጠ ፊቱን ያየ ሰው አስማማው በዛሬው ችሎት ላይ ይህ ይገጥመኛል ብሎ እንዳላሰበ መመስከር ይችላል። በርግጥም የሆነው እንደዚያ ነበር። ዐይኖቹ የእንባ ኳስ አዘሉ። ከስሜቱ ጋር ግብግብ ገጠመ።
ዳኛው ፊት ለፊታቸው ወደቆሙት ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስና እንዲሁም መምህርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ወደሆነው ዘላለም ክብረት ፊታቸውን አዙረው “ለመጨረሻ ጊዜ ምርመራ የተደረገላችሁ መቼ ነበር?” ብለው ጥያቄ ሲያቀርቡ ግን አስማማው በዝምታው መግፋት አልቻለም። ለወትሮው ስሜታዊ ሆኖ ሲናገር ሊቆጣጠረው የማይችለው ጮክ ያለ ድምጹ ዛሬ በዚህ ሁኔታ እያለ እንኳን ጉሮሮውን አልፎ ለመውጣት ጉልበት አላገኘም። ሰለል ባለና በተሰበረ ድምጸት፣ ተደነቃቅፈው እዚያው ጉሮሮው ውስጥ በቀሩ ቃላት ዳኛውን እያየ አቤቱታውንም፣ ጥያቄውንም ማቅረብ ጀመረ። ጀምሮ መጨረስ ግን አልሆነለትም…ተሸነፈ።
“…ከተያዝኩበት ዕለት ጀምሮ ‘ስለዞን ዘጠኝ የምታውቀው ነገር አለና ተናገር’ እየተባልኩ እየተጠየቅኩ ያለሁት…”
በንግግሩ መሃል ጉሮሮው ውስጥ እየተመሰጉ የሚገቡት የምሬት ቃላት ድምጹን ዋጡት። ውሎና አዳራቸው ከወረቀትና ከኮምፒዩተር ጋር የሆነው ድፍርስ ዐይኖቹ በዚያው ቅጽበት በርበሬ መሰሉ። እንባ አርግዘዋል። እነዚያ የእንባ ዘለላዎች ከዐይኑ እንዳይወርዱ እየታገለና ሳግ እየተናነቀው ቀጠለ።
“…ከፍተኛ የሆነ የስነልቡና ተጽዕኖ እየደረሰብኝ ነው…” አስማማው ከዚህ በላይ መቋቋም አልቻለም።
ወደላይ አንጋጠጠ፣ ግድቡን ጥሶ ሊወጣ እንደሚታገል ጎርፍ ያስጨነቁትን የእንባውን ዘለላዎች ወደውስጥ ሊውጣቸው ሞከረ። አልሆነለትም። ዐይኖቹ ሲጨፈኑ እንባው ዝርግፍ ብሎ ወረደ። የሚያምንበትን ሃሳብ ተናግሮ ማንንም ለማሳመን የማይሰንፈው ርቱዕ አንደበቱ ዛሬ ተሸነፈ። ለሰው ቃላት የሚያበድረው ጋዜጠኛ ስሜቱን ቃላት አንሰውት በእንባ ተናገረ። …ከጥቂት ሰከንዶች ጸጥታ በኋላ ሲቃ በሚተናነቀው ድምጹ የመጨረሻውን ቃል ተነፈሰ። የወትሮ ትህትናው ግን አሁንም አልራቀውም።
“…ይቅርታ ክቡር ፍርድ ቤት…”
በችሎቱ ፊት ስለፈሰሱት የራሱ እንባዎች ራሱ ይቅርታ ጠየቀ።
“…የሰራሁት ወንጀል ካለ ይነገረኝ ብልም የሚነግረኝ የለም”
አስማማው ከዐይኖቹ እንባውን እየጨመቀ በሲቃ አንደበቱ የተናገራቸውን ቃላቶች ጨርሶ ዝም አለ። ችሎቱ ለሰከንዶች በፍጹም ጸጥታ ተውጦ ዝም ቢልም ከአስማማው እንባ ጀርባ፣ ጉሮሮው ውስጥ ተቀርቅረው ከቀሩት ቃላት ኋላ የእውነትና ፍትሕ ናፍቆት፣ የንጽህና አዋጅ፣ የማንነትን ምስክርነት በዝምታው ውስጥ ጮክ ብለው ተሰምተዋል። በዚህ የጥቂት ሰከንዶች ጸጥታ መሃል ከታዳሚያኑና ከአስማማው እህት የለቅሶ ሳግ ውጪ የሚሰማ ነገር አልነበረም።
አስማማው ወትሮም የፈራው ይህንኑ ነበር። እጅግ የምትወደው ታላቅ እህቱም ሆነ የሚሰራበት አዲስጉዳይ መጽሔት የሥራ ባልደረቦቹ እንዲህ ባለ ተስፋ መቁረጥና ምሬት ሲያለቅስ አይተውት አያውቁም። የርሱ ፊት ከቀልድ፣ ከሳቅና ጨዋታ ውጪ እንባ አድራሻው አልነበረም። አስማማው ታሞ እንኳን ፊቱ ጨፍግጎ አያውቅም። ዛሬ እንባ ያቆሩ ዐይኖቹን ወዳጆቹ አይተው ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ እህቱ ማልቀሱን አይታ እንዳትረበሽ፣ ከራሱ ይልቅ ለሌሎች ስሜት ተጨንቆ ከራሱ ጋር ታግሎ ነበር። አልተሳካለትም እንጂ። ለዚህም ነበር በመጀመሪያው ቀጠሮ እለት ፖሊስ ለፍርድ ቤት እንደተናገረው ይህ ጋዜጠኛ ለቤተሰቡ ስልክ ለመደወል እድል የተሰጠው።
አስማማው ያሰሩትን ፖሊሶች ‘ስልክ አስደውሉና ቤተሰቤን አገናኙኝ’ ሲል የወተወታቸው ለእህቱ አንዲት መልዕክት ለማስተላለፍ ብቻ ብሎ ነው። “በቅዳሜው የግንቦት 9 የቀጠሮ ቀን እኔ ስለማልቀርብ እንዳትመጪ!” ይህንን ለእህቱ የተናገረው አይታው እንዳትረበሽ ነበር። አልተሳካለትም።
እህቱ ገና ከማለዳ ጀምሮ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ተገኝታ ደጅ ደጁን እያየች ቆማለች። ከስሯ ተለይቶ የማያውቀውን ታናሽ ወንድሟን ናፍቃዋለች። ድንገት ወደሥራ ለመሄድ ከቤቱ ሲወጣ ሲጠብቁት በነበሩት ፖሊሶች ተይዞ የተወሰደውንና ያልተመለሰውን አስማማውን ዳግም ወደቤቷ ማስገባት ተመኝታለች። ከራሷ አስበልጣ እንደምታውቀው የምትመሰክርለት ወንድሟ ከጋዜጠኝነት ሌላ ሕይወት እንደሌለው፣ ከመጻፍና ማንበብ ውጪ የአንዲትም ነገር ሱስ ተገዢ እንዳልሆነ፣ ከወቅታዊ ጉዳዮችና በማንበብ ከሚያገኛቸው ቁምነገሮች ውጪ ሌላ ትርኪ ምርኪ ለማውራትና ለመሥራት ፍላጎቱ እንዳልሆነ አሳምራ ታውቃለች።
ስለሰው ክፉ ለመናገር አንደበቱ የማይታዘዝለት አስማማው ዛሬ ከጋዜጠኛ የሙያ ባልደረቦቹና ከጦማሪ ጓደኞቹ ጋር መሳሪያ በታጠቁ ፖሊሶች ታጅቦ ሲገባ ስታይ ስሜቷን መቆጣጠር አልተቻላትም። በተለይ እነዚያ ከስክሪፕቶ ውጪ ሌላ ነገር የማያውቁት እጆቹ በካቴና ታስረው እንደወንጀለኛ በፊት ለፊቷ በፖሊስ እየተነዳ ሲሄድ ያየች ጊዜ አዕምሮዋን ሳተች። ሰላምታ ላቀረቡለት የሥራ ባልደረቦቹ የታሰሩት እጆቹን ጨቁኖ በአንገቱ ብቻ አጸፋውን መልሶላቸው ሲሄድ ስታየው አመማት። ወትሮ ፈገግታውን ከምታውቀው፣ ዛሬ ግን ጭንቀቱን ፊቱ ላይ ካነበበችው ወንድሟ ጋር ዐይን ለዐይን በተያዩበት ቅጽበት የማታውቀው ስሜት ነዘራት። ድንገት ሞት እንደተረዳ ሰው መሬት ላይ ድፍት አለችና እየጮኸች ማልቀስ ጀመረች።
“አስማማውን አታውቁትም… አንድ ቀን እንኳን እንደልጅ ሳይጫወት… ከልጅነቱ ጀምሮ እንደትልቅ ሰው እንደኖረ …አንድ ቀን እንኳን እንደእኩዮቹ ወጣትነቱን ሳያውቀው… ወይኔ ወንድሜን!”
የርሷ የልመና ቃላት የአስማማውን ንጹህነት መስክረው ከእስር ባያስለቅቁትም ስለርሱ ማለት የምትችለው ነገር ግን ይህንን ብቻ ነበር። ምርር ባለ ለቅሶዋ ውስጥ የወንድሟን ፍጹም ንጹህነት ተናግራ አስማማው ካቴና እና እስር የሚገባው ጋዜጠኛ አለመሆኑን ነበር የገለጸችው። አስማማው ከፍርድ ቤት ወጥቶ ይዞት ወደመጣው የፖሊስ መኪና ውስጥ ሲገባም እየተንሰቀሰቀች በእንባ በራሱ ዐይኖቿ ሸኝታዋለች። እሱም እህቱን ለማጽናናትና ወዳጆቹንና የሥራ ባልደረቦቹን ‘ደህና ነኝ’ ለማለት ፈገግታውን ለማሳየት እየሞከረ በካቴና የታሰረ እጁን ወደላይ ከፍ በማድረግ ሰላምታ ሰጥቷቸዋል። ዳግም ከ28 ቀን በኋላ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ወደማዕከላዊ ምርመራ መምሪያ ተመልሷል። ሰኔ 7 ቀን ምን ይዞ እንደሚመጣ የሚያውቅ ማንም የለም።
አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ከህዳር 1999 ጀምሮ ሕትመት ላይ በቆየችው ሮዝ እና ከሰኔ 2003 ጀምሮ በየሳምንቱ መታተም በጀመረው አዲስጉዳይ መጽሔት ላይ የጋዜጠኝነት ሥራውን ሰርቷል። የመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል ከሚኖርበት አካባቢ ሩቅ በነበረበት ጊዜም ሆነ አሁን ሥራውን ይዞ ማለዳ ላይ ቀድሞ ቢሮ የሚገኘው አስማማው ነበር።
እጁ ከመጽሐፍና ከሚነበቡ ነገሮች ጋር የማይለያየው አስማማው በብዙ ርዕሰጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ውይይቶች የሚያቀርባቸው ሃሳቦች በስሜት የሚነዱ አይደሉም። በሚያምንበትና ልክ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ማስረጃ ጠቅሶ፣ የጥናት ጽሑፎችን ዋቢ አድርጎ፣ በጉዳዩ ላይ የተነገሩ እውነታዎችን ዘርዝሮ ይከራከራል እንጂ በዘፈቀደ ሃሳቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሲል ብቻ የሚሟገት ሰው አይደለም። በብዙሃኑ ‘ልክ አይደሉም’ የተባሉ ጉዳዮች በርሱ ዐይን ግን ምናልባት ልክ ሆነው የሚገኙበት አንግል ሊኖር ይችላል ብሎ የሚመረምር “ለአንዱ ትክክል የሆነ ለሌላ ስህተት፣ ለአንዱ ስህተት የሆነ ለሌላው ልክ ነው” የሚል ጠንካራ ዕምነት ያለው ጋዜጠኛ ነው። ብዙ ጊዜ ታዲያ ይህ አቋሙ እንዳለው ልክ ሆኖ የሚገኝበት አጋጣሚ ይበዛል።
አስማማው እምቅ ችሎታው የሚገለጠው፣ በማንበብና ዓመታት በቆየ የጋዜጠኝነት ልምዱ ያካበተው እውቀት የሚመነዘረው በአዲስጉዳይ ኤዲቶሪል ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የሃሳብ ፍጭት ውስጥ የራሱን አተያይ መግለጽ ሲጀምር ነው። “አዲስጉዳይ ሁሌም ለድምጽ አልባዎች ድምጽ መሆን አለበት” የሚል ጠንካራ አቋም አለው። በአዲስጉዳይ መጽሔት ላይ ለሚሰሩ ዘገባዎች ሚዛናዊነት የሚታገልና ከገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጀምሮ የትኛውም አመለካከት ያላቸው አካላት በመጽሔቱ ላይ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ ሳይሰለች የሚሰራ ጋዜጠኛ ነበር። በተለይም በሙያው ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደሚያውቁት ኢትዮጵያ ውስጥ ከጋዜጠኝነት ሥራ አስቸጋሪ ነው የሚባለውን ምሁራንን፣ባለሥልጣናትንና የሥራ ኃላፊዎችን ለቃለመጠይቅ ፈቃደኛ የማድረግና አግባብቶ ሃሳባቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ የማስቻል ተግባር ለአስማማው የየዕለት ሥራው ነበር። የቃለመጠይቅ ተደራጊዎች ማንገራገርና እምቢታ እልሁን ቢያስጨርሰውም የቤት ሥራውን ሳይፈጽም ግን አይተኛም።
በአንድ ወቅት ለቃለመጠይቅ ከጠዋቱ በ4 ሰዓት የቀጠሩት አንድ ምሁር በስብሰባና በተለያዩ ምክንያቶች እስከምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ አቆይተውት ሊለቃቸው ባለመቻሉ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ይዘውት ሄደው ቃለምልልሱን እንደሰጡት ባልደረቦቹ ያስታውሳሉ። ለዚህ ነው ብዙዎች ቃለመጠይቅ ያደረገላቸው ታዋቂ ምሁራንና የፖለቲካ ሰዎች ለአስማማው ትሕትና፣ ሚዛናዊነትና ሞጋችነት አድናቆታቸውን የሚቸሩት። ከመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ብዙዎቹን በመጽሔቱ ቃለመጠይቅ አምድ ለማስተናገድ ያላሰለሰ ሙከራ አድርጎ ሳይሳካለት ቢቀርም እስከታሰረበት ቀን ድረስ ግን ተስፋ አልቆረጠም ነበር።ምናልባት ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ አድርጎላቸው፣ ደብዳቤ በጸሐፊዎቻቸው በኩል አስገብቶላቸው በአካልም አግኝቷቸው በተለያዩ ምክንያቶች መልስ ለመስጠት ቀጠሮ ሲያራዝሙበት የቆዩት እንደ አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ አቶ መኩሪያ ኃይሌ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የአስማማውን መረጃ የማግኘት ጥረት በግላቸው አድንቀውለት ሊሆንም ይችላል። አስማማው የሚሰራበት መጽሔት የሚያምንበትንና የአንድ ወገን አተያይን ብቻ ላለማስተናገድ የተቻለውን ያህል ርቀት መሄድን አጥብቆ የሚደግፍና በተግባር ለመተርጎም የሚታትር ጋዜጠኛ ነበር።
ከእጁ ላይ መጽሐፍ፣ ወረቀት፣ ወይም የሆነ የሚነበብ ነገር የማይለየው አስማማው በተለይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተሰሩ የጥናት ጽሑፎችንና በታሪክና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚታተሙ መጽሐፍትን እየገዛ የማንበብ ልማድ ነበረው። አዲስጉዳይ መጽሔት የፖለቲካ ሰዎች የሚያሳትሟቸውን መጽሐፍት ይዘትና አንደምታዎች በተመለከተ ዘገባ በሰራበት ወቅት አስማማው በአንድ ሳምንት 5 መጽሐፍት ላይ የዳሰሳ ጽሑፍ ማዘጋጀቱ ከማይረሱት ብቃቶቹ አንዱ ነው።
አስማማው ብዙ ጋዜጠኞች ሊያናግሯት ዕድል ያላገኙትን የ ‘Tower in The Sky’ ደራሲ ሕይወት ተፈራን አባል ወደሆነበት የወጣቶች ቡክ ክለብ ጋብዟት እሷም ጥሪውን አክብራ ተገኝታለት የሕይወት ልምዷን ለአሁኑ ትውልድ እንድታካፍል ያስቻለ ንባብ ወዳድ ጋዜጠኛም ነው።
አስማማው ከጋዜጠኝነት መርሆች ውስጥ ያለማዳላት (Fairness) ለሚለው መርህ አብዝቶ ተጨናቂ ነው። “ፕሬስ የሁሉንም አካል ሃሳብ ያለአድልዎና በእኩል መንገድ ማስተናገድ ይገባዋል፣ ማበላለጥና ወገንተኝነት ለጋዜጠኝነት የሚሆኑ ቃላት አይደሉም” ይል ነበር። በአዲስጉዳይ መጽሔት ላይ የማንኛውም ወገን አቤቱታም ሆነ ምላሽ ትክክልም ይሁን ስህተት በእኩል ሁኔታ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ አጥብቆ የሚከራከር ጋዜጠኛ ነበር።
አስተሳሰቡ ምክንያታዊ የመሆኑንና የሚውልባቸው ቦታዎች ከፍ ያሉ ሰዎችን የሚያገኝበት የመሆኑን ያህል ለአለባበሱ ብዙም የማይጨነቅ፣ ተብለጭልጮ መታየት ብዙም ምቾት የማይሰጠው ሰው ነው። ባልደረቦቹም ሆነ ጓደኞቹ የሚያውቁት አስማማው ቀለል ያለች ቢጫ ቲሸርትና ጂንስ ሱሪ የሚያዘወትር፣ እግሩ ላይ የሚሰማውን ህመም ለመቀነስ የጫማ ክሩን አጥብቆ የማያስር፣ እጁ ላይ የሚነበብ ነገር የማያጣ፣ ሲሄድ ረጋ ብሎ ግን እንደነገሩ የሚራመደውን አስማማውን ነው። ልታይ ልታይ የማይልና ከዩኒቨርሲቲ ከወጣ ዓመታት ቢቆጠሩም ራሱን ‘ገና ተማሪ ነኝ’ ብሎ ለማወቅ ያዘጋጀ ጋዜጠኛ በመሆኑም ከበላዩም ይሁን ከበታቹ ያሉ ባልደረቦቹ ያዘዙትን ሁሉ በፍጹም ትህትና ለመፈጸም “እሺ” ከማለት ቦዝኖ አያውቅም። ‘እሺ’ በአስማማው አፍ ውስጥ ሺኅ ጊዜ የምትደጋገም ቃል መሆኗ ብቻውን የሥራ ባልደረቦቹ እንዲያከብሩት ያደረገው ነገር ነው።
አስማማው ኃይለኛ የጨጓራ ህመሙ ደርቦ ያስከተለበት የወገብ ህመም ሁሌም ጤናውን የሚያቃውሰው ሰው ቢሆንም እንዲህም ሆኖ ሥራ ሲደራረብበት እንኳን ቅሬታውን የሚያቀርበው ሰርቶ ከጨረሰ በኋላ ነው። ከሥራው በሚያገኘው ገንዘብ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረውና የሰራበትን ክፍያ ለመውሰድ እንኳን ይሉኝታ የሚጫነው አስማማው ዛሬ ከውጭ አሸባሪ ኃይሎች ጋር በመገናኘትና ገንዘብ በመቀበል ተጠርጥሯል። ብጥብጥና ሁከትን በግልጽ የሚያጥላላው አስማማው ዛሬ ብጥብጥና ሁከት ለመፍጠር በማሴር ተጠርጥሯል። ሽብርን የሚያወግዘው ጋዜጠኛ ዛሬ ሽብር ፈጽሟል ተብሏል። ምናልባትም እንባው ግድቡን ጥሶ የወጣው የቀረበበትን ክስ ከራሱ ማንነትና ሙያዊ ክብር ጋር ሲያስተያየው ተጣርሶበት ይሆናል።
አስማማው ራሱን በሚያውቀውና ቤተሰቦቹ፣ ባልደረቦቹና ወዳጆቹ በሚያውቁት ልክ ገና ብዙ ለማወቅና ለመማር የሚታተር አንድ ተራ የዚህች ሃገር ጋዜጠኛ እንጂ አሸባሪ ነው ብሎ ለመደምደም ምላስ መያዝ ብቻ ሳይሆን ድንጋጤም ይፈጥራል።
ነገ የሚተማመንባት እውነትና ፍትሕ ነጻ ካወጡት አስማማው በራሱና ከሳሾቹ በሰጡት ማንነቱ መካከል ያለውን ልዩነት ራሱ ጽፎ ያስነብበን ይሆናል። ይህ ይሆን ዘንድም አጥብቀን እንመኛለን።

Filed in: Amharic