>

ኣውጡት! (ዘበኣምላክ -ኖርዝ ፖል)

የልጅ ኣምሰሱ ኣይጠላም እንዲሉ፣ ነፍሱዋን በገነት ያኑረውና፤ የእኔዋም እናት ንፍጣም ልጇን ከነንፍጡ ማሳደጉዋን ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ላድርገው።
”እማ’ በሰፈሩ ልጆች ”ንፍጦ” የሚል ተቀጽላ  የተሰጠውን ልጇን የማያባራ የንፍጥ ዝናብ ስትጠርግ ኖራለች።የኋላ ኋላ ግን (ማደጌ ነው መሰለኝ)እራሴን ለመርዳት ወደ ውስጥ መማግ መጀመሬን ያልወደደችው እናቴ፣ ”ኣውጣው የማሪያም ልጅ  ይተካልሃል” ነበር የምትለኝ። ኣዎ ሁሉንም ማድረግ የማይገደው ኣምላክ፣ያወጣሁትን ሲተካልኝ በማየቴ መማጉን ተውኩና፣ መክላቱን ለመድኩት።
ዕውነት ነው የማይበጅህን ነገር ማስወገድ ለስጋም ለነፍስም መድህን ስለመሆኑ ዕድሜ ያባጀን ሁሉ በሚገባ እናውቀዋለን።በእርግጥ የራበው ሆድ በምራቅ ጠብታ ሊታገስ መቻሉ ምራቅን መዋጥ ለጊዜው ባይከፋም ዘለቄታዊ መፍትሔ ግን ሊሆን ኣይችልም። ይህንን የምለው የተፈጥሮን ሰብኣዊ ኣካል ስነ-ተፈጥሮኣዊ ሁነት ላስተምር ማሰቤ ኣይደለም። ለዚህም ዕውቀቱን ኣልታደልኩም። ግን ከጊዜያዊ ይልቅ ዘለቄታዊ መፍትሔ ተመራጭ መሆኑን ለማወቅ ግድ ስነ-ሁለንተናዊ ምሁር መሆን ኣያስፈልግም። ለዚህ መኖራችን ብቻ በቂ ነው።
ትላንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ የሚሉዋት ጥንታዊና ታሪካዊ ሃገር፣ ባባዕድ ሃይላት ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቆመጥ ስትመታ፣ መኖሩዋ ሳያንስ፣ ህዝቡዋም በዘመኑ  ወንበር እየገፉ በሚንግሱባት ነገስታት ውጥንቅጣዊ ኣገዛዝ ስር ሲታመስ፣ ሲረገጥ፣ሲሰደድና ሲገደል ኣለ። በኣጼው ዘመን የወየበውን የኣገዛዝ ዘይቤ ኣሽቀንጥሮ ለመጣል እምቢ ብሎ የስርዓቱን መሰረት ክፉኛ ባወዛወዘው የህዝብ ኣመጽ ተከልሎ  የስልጣን እርከን ላይ ፊጥ ያለው ወታደራዊ መንግስት ለሃገርም ለራሱም ሳይበጅ ኣንድ ትውልድ ጭዳ ኣድርጎ ኣለፈ። በዚህም ወቅት ነበር የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው ህብረትና  ጀግንነት መሸርሸር የጀመረው።
እየተገደልን እንዳናለቅስ ስንታዘዝ፣ እምባችንን ወደ ውስጥ መማግ ተገደን ነበር። እየተገደልን ማልቀሱ ለምን  እንዳስፈራን ኣላውቅም። ”ኣውጣው የማሪያም ልጅ ቸር ነው ይተካልሃል” ብለው የማያወጡት እምባ!…እንዲያም ሆነ እንዲህ  ደርግ ከ 17 ዓመታት በኋላ በስርዓቱ መበስበስ ሳቢያ ጊዜውና በለስ በቀናው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ተተካ። በእርግጥ ይህ ወየምቱ ስርዓት ከደርግ ጋር ወታደራዊ ፍልሚያ ሲያደርግ ቢቆይም፣ የደርግ ውድቀት ግን ዛሬ በዘር ስሜት ያደፉ ጥቂት ግለሰቦች እንዲሚያስቡት ሳይሆን ደርግ በነበረው ወታደርዊ ጉልበቱ መቆም ኣለመቻሉ ሲሆን ይህም በማያሻማ መንገድ የህዝብ ጥላቻ የፈጠረው ልምሻ ነው። ስርዓቱ፣ ስርዓተ- ነፍሱን ግንቦት ላይ የዘከረው ወያኔ ዲሞክራሲን የሚያቀነቅን ድንቅ ኣቀንቃኝ መሆኑን ምዕራባዊያን ሳይቀሩ በሆታ ተቀበሉት። ኣድናቂዎችም በረከቱለት። ከመባውም ኣላጎደሉበትም። እኛም በጎፍላ ዲሞክራሲያዊ ቅኝት  ሃይማኖታዊ ባህላዊና  ሃገራዊ ግዴታችንን ኣራከስነው። ቤተሰባዊ ግዴታችንንም ”ዲሞክራሲያዊ ስሜቴ” በምትል ‘ክር’ በጎደላት ጎፍናኝ ቅኝት ቦታ ኣሳጣናት።ሃገርና ህዝብ ግን ሞት የጀመርንበት ዋዜማ ላይ ነበርን።
ሙት ወቃሽ ኣያድርገኝና በመንፈሳዊ ነቀርሳ ክፉኛ የተጎዱት የወቅቱ መሪ መለስ ዜናዊ በህዝብና በሃገር ላይ ያላቸውን ጥላቻ ሲገልጹ ጊዜ ኣልፈጀባቸውም። ኣማራውን ነፍጠኛ፣ ኦሮሞውን ጦረኛ፣ ወላይታውን ልግምተኛ፣ ጉራጌውን ቀማተኛ በማለት መዝለፍ ጀመሩ። እንደውም ታሪካችንን ተረት ተረት፣ ባንዲራችንን ጨርቅ ኣሉት። ይህን ሁሉ ሲሉን ግን ”ይመቻችሁ” ነበር መልሳችን ። ከፈለጋችሁ ”ተዋጉንም” ብለው ነበር… በድፍረት። እኛ ማን ሆነን እነማን ሆነው ከእነሱ ጋር መዋጋታችንን ባላውቅም ”እረ በምን ኣቅማችን ልብ ሲኖር ኣይደል እንዴ?” ብለን ኣጉተምትመን ሽንፈታች ንን ኣሳወቅን። ከዚህ በሁዋላ ምን  እንዲያደርጉን እንጠብቃለን?
”ጅብ የነከሰ ኣህያ ዱላ ኣያላቅቀውም።እናም ማጅራታችን ተነክሶ የተቀመረው የዘር ስሜት ተግባራዊ መሆን ጀመረ። ሰባ ሚሊዮን በላይ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ በሰባ ኣክፍሎ  መቀመጫውን ምንሊክ ቤተመንግስት ላይ  ያደላደለው ወያኔ፣ በእርግጥም የፖለቲካ ስሌቱ ውጤታማ ስላደረገው እነሆ 23 ዓመታትን እንዳሻው እያረጠብን ኣለ። የሚገርመው ነገር ወያኔ የፈጠረልንን የዘር ሒሳብ መልመጃ ኣድርገን የምንመራበት  የዋሆች መኖራችን ነው። በተለይም በሰለጠነው ዓለም የሚኖሩና የተቃዋሚ ድርጅት ኣመራር ከሆኑ ግለሰቦች ይህንን ስንሰማ ምን ይህል ለወያኔ የስነልቦና ጥቃት እንደተሸነፍን እራሳችንን መገምገም ተገቢ ይመስለኛል። ከጦርነት ሁሉ ትልቁ ጦርነት ደግሞ ይሄው ነው። ምሁር ነን የሚሉና ዲግሪ የሚቆጥሩልን፣ በተለይም በነጻው የባዕድ ምድር ላይ እየኖሩ በጠባብ የዘር ስሜት ማጥ ውስጥ ገብተው ሲወራጩ ማየት የተለመደ ነው። የሚቆጥሩልንን ዲግሪ ‘ድግር’ አንኳን ብንለው ምግባራቸው የበሬን ያህል ውሃ ኣያነሳም።
የዚህ ጽሑፍ ኣቅራቢ እንደሚያምነው ህዝብ ፍጹም ዕውነት ነው። ኣለመታደል ሆኖ እንዳሻው እያበሻቀጠ በሚገዛን ወያኔ እግር ስር ሆነን ድንቁርነታችን ብቻ ሳይሆን ሓሞት ኣልባነታችን በተደጋጋሚ ቢነገረንም ሰማነው እንጂ ኣልተቀበልነውም። የሰማነውን እንቀበል ዘንድ ህልቆ መሳፍርት በሌላቸው ተቃዋሚ ድርጅቶች በኩል በስማ በለው ጆሮኣችንን እስኪታመም ይጮህብናል። ወደድንም ጠላንም ግን በዘርና በሃይማኖት ላይ የተበተነው ገዳይ የፖለቲካ መርዝ ትውልድ ሊያሳጣን ነውና ቆም ብለን እናስብ። የሚነግሩንን ከመስማታቸው በፊት ግን እራሳቸውን ኣንድ  እንዲያደርጉ መመከር ያለባቸው ሃይሎች እንዳሉ ላወሳ እወዳለሁ። ወያኔ በቀደደልን ቦይ እየፈሰስን ዘረኝነትን ከማቀንቀን እንመለስ።
ዛሬ የወያኔ መሪዎች ህዝቡ በሃይማኖትና የዘር ልዩነት የማይታከም ጥላቻ ውስጥ መግባቱን በኣደባባይ በድል ስሜት ቢነግሩን ዕውነት ነው። ሲሻቸው በተናጥል፣ ካልሆነም በጅምላ እንደ ህጻን ልጅ እየኮረኮሙ የሚኮለኩሉትን ፺ ሚሊዮን ህዝብ ፈጥረዋል። በረሃብ እየቆነጠጡ፣በኣባይ ግድብና በህንጻ ግንባታ የሚያባብሉት ዘመኑ የፈጠራቸው የህዝብና የሃገር ተውሳኮች የማይገባቸውን ሃገርና ህዝብ የመምራት ሃላፊነት ተፈናጠውበታል። ግን እስከመቼ?!,,, የራበው ሆድ ጆሮ የለውም። የበላነው ሳይኖር የሰማነው ፕሮፓጋንዳ ልበ- ጡል ሊያደርገን ኣይገባም። የወያኔ ቱባ ባለስልጣናትም እራሳቸውን ኣግዝፈውና ቆልለው ህዝቡን እንደ ትንኝ ለመመልከታቸው በርካታ ዕውነቶች መግለጽ ይቻላል። ግን ንቀት ባወየበው ህሊና የተገራ ምላስ ስሜታቸውን ሊደብቁ ኣይችሉምና በይፋ እየነገሩን ነው። ይህ ጸሃይ የሞቀው ዕውነት ሁላችንም በሰውነታችን ሊያመን ሲገባ፣ ካንዳንድ  ግለሰቦች የምንሰማው የዘር ስሜት የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍርም እንደሆነ ይሰማኛል። ኣንድና የባዕድ ነጻ ሃገር ላይ ቆሞ የራስን ሃገር ማፍረስ ምን የሚሉት በሽታ ምልክት እንደሆነ ኣይገባኝም። ግን ክፉ…ክፉ ህመም ነው። ሁሌ ሃክ አንትፍ የማይሉት የዘር ሃክታ እየማጉ ማላዘን የጤነኛ ሰው ስሜት ኣይደለምና ”ኣውጡት!” እንበላቸው። የማሪያም ልጅ ቸር ነው። ከፈለጉት ይተካላቸዋል።
Filed in: Amharic