>
5:13 pm - Thursday April 18, 7929

ሀገሬ ጀልባ ናት!! (ደመቀ ከበደ)

ጣና ዳር : 2003

ማዕበል በሚያላጋው – ሀይቅ የምትላወስ
ነፋሱ እንደገፋት – የምትንከላወስ
ከሞት የሚታደግ – ‹‹ካፒቴን›› የሌላት
የውሐ ላይ ተጓዥ – ሀገሬ ጀልባ ናት፤

እዚች ጀልባ ላይ፤

ሀ)
ካፒቴኑን ገፍቶ – እጥልቁ ሀይቅ ላይ – እየወረወረ
ጎምቱ ነኝ ያለ ሰው – መሪውን ጨብጦ – መዘወር ጀመረ፤

ለ)
ዋና የማያቅ ሰው – ውሀ መንቦጫረቅ
በፍርሀት ርዶ – ቀሟል ሲነፋረቅ፤

ሐ)
በተሳፋሪ ላይ – ተስፋ የሚነዛ – ከንቱ ልወደድ ባይ
‹‹ያውና ደሴቱ!!›› – ይላል ጮክ ብሎ – ገና ምንም ሳያይ፤

መ)
ማዕበልና መውጅ – ጀልባዋን ሲያላጋ – ቁብ የማይሰጣቸው – የማይደነግጡ
‹ተናገረን ነበረ›› – ብሎ ለመተረት – እንዲያ እንደቋመጡ
እኒያው ‹‹አዋቂዎች›› – ተደላድለው መሀል – እንደተቀመጡ፤

ሠ)
በስልት አልባ ‹‹ሾፌር›› – ልባቸው የደማ – ዕድል የተቀሙ
‹‹በዝወራ ጥበብ›› – ሊያድኑ እሚለፉ – ‹‹ሰውን›› ያስቀደሙ
ከጠብደል ጠባቂ – እኒያው ሲታገሉ – እኒያው እየደሙ፤

ረ)
አንዴ በ‹‹ዘዋሪው›› – አንዴ በተጓዡ – አንደዜ በሌላው
ጀልባ ላይ ያለው ሁል – መውጅ ሲያላትመው – ጥልቅ ሀይቅ ሲበላው
ስቃዩን በሞላ – ለማየት የፈሩ
ራሳቸውን ቁልቁል – ያው ሲወረወሩ
/ወዲያው በሀይቅ አውሬ – በአዞ ተወረሩ፤/

ሰ)
በዚህ ማዕበል ውስጥ – ከዚች አንድ ጀልባ – ሲሳይ የናፈቁ
እኒያው ‹‹ሾተላዮች›› – ‹‹ስልቻ›› አዘጋጅተው – ቋምጠው ሲጠብቁ፤

ግና
እዚች ጀልባ ላይ – የወጣ ሰው ሁሉ
በ‹‹ስማኝ›› ‹‹አልሰማም››
በ‹‹ስጠው›› ‹‹አልሰጥም››
በ‹‹አድርግ›› ‹‹አታድርገው›› – እሚሆነው ሲያጣ – እንዲህ ሲደናበር
መልህቅ የሚጥል – አንድ ዋናተኛ ሰው – እየመጣ ነበር፡፡

Filed in: Amharic