>

የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል ፍላጎት!! (አፈንዲ ሙተቂ)

ምንም አትጠራጠሩ!! ይህንን ኃይል ያሰማሩት ወገኖች ምኞትና ግብ የታላቋን ሶማሊያ ህልም እውን ማድረግ ነው፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው የመሬት ወረራና ግድያ ከሁለት ክልሎች ግጭት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡

እስቲ አንድ ነገር ልንገራችሁ!! በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በኩል ያለው የኦሮሚያና የሶማሊ ክልል ወሰን የሚያበቃው በቢኬ ከተማ ላይ ነው፡፡ ይህ በካርታ ላይ ያለው ወሰን በ1997 በተካሄደው ሪፈረንደምም ተረጋግጧል፡፡ የሶማሊ ክልል ግን ያለ ምንም ከልካይ ድንበሩን ጥሶ የአፍደም እና የሙሉ ከተሞችን በራሱ ግዛት ውስጥ ካካተተ ቆይቷል፡፡ ከዚህም አልፎ የሚኤሶን ከተማ ለመንጠቅ በተደጋጋሚ ጊዜያት ወረራ ሲያካሄድ ሰንብቷል፡፡

ይበልጥ የሚደንቀው ግን ከድንበሩ በጣም በምትርቀውና ከአዋሽ ወንዝ ሀያ ኪሎሜትር ብቻ በምትርቀው የቦርዶዴ ከተማ ላይ የሚፈጽመው ጥቃት ነው፡፡ ከሚኤሶ እስከ ቦርዶዴ ያለው ርቀት ስልሳ ኪሎሜትር ያህል ይሆናል፡፡ በሁለቱ ከተሞች መካከል የአሰቦት፣ ኦዳ ጅጋ እና የኮራ ከተሞች አሉ (ከተሞቹ የሚገኙት የባቡር መስመሩን ተከትሎ ነው፤ በመኪና የሚጓዝ ሰው ላያያቸው ይችላል)፡፡ በዚህ መሬት ላይ በርካታ የገጠር መንደሮችም ይገኛሉ፡፡ የሶማሊ ልዩ ኃይል ይህንን ሁሉ መሬት አልፎ ነው ከቦርዶዴ ከተማ በስተምዕራብ ባለ መሬት ላይ “በሶማሊ ክልል፣ የሀርዲም ወረዳ” የሚል ታፔላ የተከተለው፡፡

ነገሩማ ከልዩ ኃይሉ አይደለም፡፡ ይህንን ሁሉ ጣጣ ያመጡት ኦሮሚያን አስተዳድራለሁ የሚለው ኦፒዲኦ እና ከርሱ ጀርባ የሚገኙት ስውር ወገኖች ናቸው፡፡ ጉዳዩን ለምዕራብ ሀረርጌ አርብቶ አደር ቢተውት በሶስት ቀን ውስጥ እልባት ሊፈታው ይችላል፡፡ ይሁንና አርብቶ አደሩና ገበሬው ራሱን እንዳይከላከል መሣሪያውን ነጥቀውታል፡፡ የወገኖቻቸው በግፍ መገደልና መፈቀናል አሳስቦአቸው አርሶ አደሩና ገበሬው ራሱን የሚከላከልበትን መሣሪያ የሚያስታጥቁ የወረዳና የዞን ባለስልጣናት በአንድ ጀምበር ይባረራሉ፡፡ በርካቶችም ይታሰራሉ፡፡

በመሠረቱ የኦሮሞና የሶማሊ ህዝቦች ወንድማማቾች ናቸው፡፡ ተዋልደዋል፡፡ ተዛምደዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የቋንቋ እና የባህል መመሳሰልም አላቸው፡፡ ፌዴሬሽኑ እነዚህን የመሳሰሉ የሚያስተሳስሩን ገመዶች እንዲጠናከሩ ማድረግ ነበረበት፡፡ ይሁንና በወረቀት ላይ ያለው ህግ በገዥዎች ፍላጎት የሚተረጎም በመሆኑ በተግባር ላይ በሚውልበት ጊዜ ውጤቱ ሌላ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ግጭት፣ ግድያ፣ ወረራ፣ ዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ወዘተ… ወዘተ….

እኛ ለ20 ዓመታት እንዲህ ከርመናል፡፡ ለወደፊቱም አላህ ይድረስልን እያልን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጄኔራል ሞሐመድ ዚያድ ባሬ 200000 ምርጥ ጦር አዝምቶ ለማሳካት ያልቻለውን የታላቋን ሶማሊያ ህልም ጅጅጋ የከተመው አብዲ ኢሌ “ልዩ ኃይል” ብሎ በሰየመው 30000 ግብስብስ ሠራዊት ብቻ እያሳካ በመሆኑ ለርሱና እርሱን ላዘመቱት ኃይሎች የ“እንኳን ደስ አላችሁ” መልእክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡

Filed in: Amharic