>

"ሁ ኢዝ ባድ?!" (አንዷለም ቡከቶ ገዳ)

Emye Minilik Henok Yeshitila 06042016ሰሞኑን ከሚከበረው የአጼ ሚኒሊክ ልደትና የጠ/ሚ መለስ ሙት አመት አንጻር ለሁለቱም ቀደምት መሪዎች ወዳጅም ሆነ ጠላት ሚዛናዊ ነው በሚል የቀረበች ነች፡፡ ሁለቱ መሪዎች በሰማይ ቤት ተገናኝተው አንዲት ዛፍ ስር ዱቅ ብለው ሲቀዱ “ነው፡፡

”እሺ ልጅ መለስ! እንዴት ነዉ ታዲያ! የሰማይ ቤት ኑሮን ለመድከዉ!?” አሉ ዐጼ ሚኒሊክ በያዙት ጭራ ዝንብ ከፊታቸዉ ላይ እያባረሩ
”አዎን ጃንሆይ መቼም የማይለመድ የለም” አለ መለስ በአክብሮት፡፡
”የኢትዮጲያ ንጉስ ነበርኩኝ ነዉ ያልከኝ?” አሉ አጼ ሚኒሊክ፡፡
”ንጉስ ሳይሆን ጠ/ሚኒስቴር ነበርኩኝ” አለ መሌ ፈጠን ብሎ
”አሃ! የበላይ አለሃ!?” አሉ አጼዉ
”የበላይ እንኳን የለኝም” አለ መለስ ፈርጠም ብሎ
”ታዲያ ንጉስ ነሃ!” አሉ ንጉሱ በእርግጠኝነት መንፈስ
”ያዉ በሉት!” አላቸዉ መለስ በቸልተኝነት ትከሻዉን ወደላይ እየሰበቀ ጉዳዩን ለማስረዳት ዉስብስብ ሲሆንበት፡፡
”እንዴት ነዉ ታዲያ የሀገሬ እድገት መቼም እኔ ከሞትኩኝ በኋላ ባለዉ መቶ አመት ስንትና ስንት ነገሮችን ሰርታችኋል ብዬ አስባለሁ?!” አሉ አጼ ሚኒሊክ ፡፡
በእርግጥ ህይወቱ አልፎ ወደእሳቸዉ የመኖሪያ ስፍራየሚመጣ ሃበሻ ባጋጠማቸዉ ቁጥር ስለ ኢትዮጲያ ወቅታዊ ሁኔታ ከመጠየቅ ቦዝነዉ አያዉቁም፡፡
”አዎ በጣም እንጂ ለምሳሌ ባቡር ጀምሬአለሁ፡፡” አለ መለስ በችኮላ
”ጀምሬአለሁ?! እኔ በዛን ዘመን የሰራሁትን ነገር ጀምሬአለሁ ትላለህ?!” አሉ ወሬዉን አቋርጠዉት
”አ…ዎ! ያዉ በድሮዉ እርሶ በሰሩት ባቡር ነበረ ስንጠቀም የነበረዉ…..” አለ መለስ አፈር እያለ፡፡
”እኔ በሰራሁት እስከአሁን!?” ቀወጡት ንጉሱ፡፡
”አዎ! ” አለ
”አበስገበርኩ! ….እ….ሺ….?!” አሉ በከፍተኛ መገረም፡፡
”እሱም በእኔ ዘመን ተበላሽቶ ስራ በዝቶብኝ አላስጠገንኩትም ነበር…እ.እ…” አለ መለስ፡፡ ሼም ወጥሮታል!
”ቤተመነግስትስ ሰራህ?” አሉ አሁንም ወሬዉን ሳይጨርስ አቋርጠዉ
”አረ አልሰራሁም! የእርሶ የድሮዉ ቤት ነበር የምኖረዉ” አለ አንገቱን እንደደፋ፡፡
”ዎ ማይ ጋድ!” አሉ አጼው፡፡ ይቺን እንግሊዝኛ ባለፈዉ ከማይክል የሰሟት ነች፡፡ማይክል እንደሞተ የተመደበዉ ከሚኒሊክ ጋር በአንድ ዶርም ሲሆን ከሼባው ጋር በጣም ተመቻችተዋል፡፡”ሙን ዎክ” አስለምዷቸዉ አሁን በሚገኙበት አጸደ ነፍስ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩት በ”ሙን ዎክ” ብቻ ሆኗል፡፡በምትኩ ማይክልን ሽለላ አስተምረዉት በዚያ ቀጭን ድምጹ ሲሸልል ሁሉም ይስቅበታል፡፡
”ቆይ በሌላ በሌላዉስ እንዴት ናችሁ?! ለምሳሌ ጦርነት ምናምን?” አሉ ተስፋ በመቁረጥ ድምጽ፡፡
”እኔ ሁለቴ ነዉ የተዋጋሁት፡፡ እንግዲህ አልሻባብንም ኤርትራን አሸንፌአለሁ” አለ መለስ በጦርነት ዙሪያ ቀደዳ ከተጀመረ ሚኒሊክን እንደማይችላቸዉ ያዉቃል፡፡
”ኤርትራ ደግሞ ማናት?! ይቺ መረብ ማዶ ያለችዉን አዉራጃ ነዉ የምትለኝ?” አሉ ባንገታቸዉ ወደ ሰሜን አቅጣጫ እየጠቆሙ ፡፡ለምዶባቸዉ ነዉ እንጂ ሰማይቤት ምእራብና ምስራቅ ብቻ ነዉ ያለዉ፡፡
”አዉራጃ!? የምን አዉራጃ!? አሁን እኮ ኤርትራ ሀገር ሆናለች፡፡ ያዉ እርሶስ ዝም ብለዉ ለጣሊያን አሳልፈዉ ሰጥተዋት የለ!” አለ መለስ በአሽሙር ድምጽ፡፡
”ታዲያ አሁንም በጣልያን ስር ነች የምትለኝ?” አሉት
”ጣልያንስ የለም፡፡ ግን አሁን በራሷ ነዉ የምትተዳደረዉ ፡፡”አሻፈረኝ!” አለች! ምን ማድረግ ይቻላል?!” አለ አሁንም ትከሻዉን በምንቸገረኝ አይነት እየሰበቀ፡፡
”እምቢ ካለችስ እምቢ ነዉ!፡፡ እዉነትህን ነዉ! ግን አንተ ያኔ ምን አልክ?” አሉ አጼዉ ፡፡ይህቺ ነጥብ ስትነሳ ደካማ ጎናቸዉ ስለሆነች እሳቸዉም አይመቻቸዉም፡፡
”እኔማ ምን እላለሁ! ደስ አለኝ እንጂ!” አለ መለስ
”እንዴት ደስ ይልሃል?” አሉት
”ስላሸነፍን ነዋ!” አላቸዉ
”ከእናት ሀገሯ እየተገነጠለች እንዴት ደስ ይልሃል?! ከተገነጠለችስ እንዴት ነዉ አሸነፍን የምትለኝ?!” በአግራሞት ጠየቁት፡፡
”እኔ የተዋጋሁት እኮ በተገንጣዮቹ በኩል ነዉ!” አለ መለስ
”ከኢትዮጲያ ጋር ተዋግተህ ሀገርህን አስገንጥለህ ነዉ የኢትዮጲያ ንጉስ የሆንከዉ?!” አሉት
”ብርቅ ነዉ እንዴ? እርሶስ ከጎጃሙ ንጉስ ተ/ሃይማኖት ተዋግተዉ ከወላይታዉ ጦና ተፋጅተዉ ከከፋዉ ጋኪ ሺሬኮ ተናንቀዉ ከሀረሩ ኢምር አብዱላሂ ተላልቀዉ ከኦሮሞዉ …..” በስሜት መናገር ጀመረ
”ታዲያ እኔ ብዋጋ ሀገሬን አንድ ለማድረግ የቆዳ ስፋቷን ለመጨመር እንጂ የገዛ መሬቷ ለማስገንጠል ነዉ እንዴ !?” በቁጣ አቋረጡት፡፡
”በእኛ ጊዜ ደግሞ የቆዳ ስፋት ለመጨመር የሚቻልበት ጉዳይ ስለሌለ እኔ አስራሰባት አመት ሙሉ የተወጋሁት ለህዝቡ የዲሞክራሲ መብት ለማሰገኘት ፡የብሄር እና የሃይማኖት እኩልነትን ለማስፈን ….” እየተናገረ እያለ አሁንም አቋረጡት፡፡
”17 አመት ሙሉ ጦርነት! ? ምን አይነት ደካሞች ናችሁ!? ታላቁ የአድዋ ጦርነት እንኳን አንድ ቀን አይደል እንዴ የፈጀዉ?! ለዛች ለእኔ ወንበር ነዉ ይሄ ሁሉ ልፋት?! ደህና ሜዳ መርጣችሁ ተቀጣጥራችሁ አንድቀን አትፈታተሹም ኖሯል?!” አሉ አጼ ሚኒሊክ
”አይ ጦርነት! እንደናንተ ጊዜ እኮ በቀጠሮ ታቦት ይዞ መዋጋት ቀረ! አሁን ከአምስት አመት በታች የሚያልቅ ጦርነት የለም” አላቸዉ፡፡
”እሺ የሆነስ ሆነ፣ ያሰብከዉ ተሳካልህ?! ከዚህ ሁሉ ድካምህ በኋላ ሀገርህ ሰዉ እንደፈለገ የሚናገርበት፡ የብሄር እና የሃይማኖት እኩልነት የተረጋገጠበት ሀገርስ ሆነችልህ?” አሉት በሀዘኔታ አይን እያዩት፡፡ 17 አመት ሙሉ ተዋጋሁኝ ካላቸዉ በኋላ የጦርነትን አስከፊነት አብጠርጥረዉ የሚያዉቁት ጦረኛ ንጉስ መለስን በልዩ አይን መመልከት ጀምረዋል፡፡
”አዎን” አለ መለስ ትንሽ በማመንታት ድምጽ፡፡
”እና አሁን ሰዉ የፈለገዉን ቢናገር የፈለገዉን ቢጽፍ አይታሰርም ነዉ የምትለኝ!?” አሉ በአግራሞት ድምጽ
”እሱማ ይታሰራል፡፡ እንደዉም አለም አሁን ኢትዮጲያን የሚያዉቃት በአድዋ ሳይሆን “አንደኛ የጋዜጠኛ አሳሪ እና አፋኝ ሀገር” በሚል ነው” አለ፡፡
በነገራችን ላይ በአዲሱ የመኖሪያ ስፍራቸው ሰዉ ለመዋሸት ቢፈልግ እንኳን መዋሸት አይችልም፡፡
”በእኔ ግዜ እንኳን አንድም ጋዜጠኛ አስሬ አላዉቅም፡፡ ያዘጋሁትም አንድም ጋዜጣ የለም!” አሉ ንጉሱ በኩራት
” አርስዎ ደግሞ ምን ጋዜጠኛ አሎት!? አንድ “አእምሮ” የሚባል እዛዉ ቤተመንግስት የሚታተም እርሰዎ በሾሙት ዘመድዎ የሚጻፍ እና ሀምሳ ፍሬ ታትሞ ለመኳንንቱ ብቻ የሚታደል ጋዜጣ አይደል እንዴ የነበሮት! ” ካላቸዉ በኋላ በሆዱ ”ወገኛ የሸዋ ሰዉ! ተመስገን ደሳለኝ እና እስክንድር ነጋ በሳቸዉ ጊዜ ቢኖሩ ይሄኔ አርባ ተገርፈዉ ይሰቀሉ ነበር!” አለ
”ግርፉማ አሁንስ መች ቀረላቸዉ እንደድሮዉ ጅራፉን መቁጠር ቀረ እንጂ!” አሉት ከቅርብ የአበሻ ሟቾች የሰሙትን አስታውሰው፡፡
በነገራችን ላይ ሰማይ ቤት በሆድ ማሰብ የሚባል ነገር የለም፡፡መለስም እረስቶት ነዉ እንጂ በሆዱ የሚያስበዉን እንደሚያዉቁ ያዉቃል፡፡
”ያም ሆነ ይህ በእርሶ ጊዜ ከነበረዉ በብዙ ነገር ተሻሽለናል፡፡ ለምሳሌ፡ ማንም ሰዉ መሪ የሚሆነዉ በችሎታዉ እንጂ እንደ እርስዎ ዘመን በስልጣን ላይ ሙጭጭ ብሎ ዘመድ አዝማዱን እና የልጅ ልጁን የሚሾምበት ጊዜ አብቅቷል!፡፡” አላቸዉ ፍርጥም ብሎ
”በጣም ደስ ይላል! መሪያችሁን በምርጫ ካርድ ማስወገድና መምረጥ ከጀመራችሁማ እሰየሁ ነዉ! እና አንተም እያለህ ምርጫ ተካሂዶ ነበር?” አሉ ሚኒሊክ በሀሳቡ መገረማቸዉን መደበቅ እያቃታቸዉ
”አዎ አራቴ ተካሂዷል” አለ መለስ በኩራት
”ከአራቱ ጊዜ ታዲያ አንተ ስንት ግዜ አሸነፍክ? ስንቴስ ተሸነፍክ? መቼም የሰዉ ሃሳብ ሁልጊዜ አንድ አይነት አይሆንም! የሀገሬን ሰዉ ባህሪ መች አጣሁት!” አሉ እየሳቁ
”አ…ይ ጃንሆይ…. ባጋጣሚ ሁሉንም ጊዜ እኔና ጓደኞቼ ነዉ ያሸነፍነዉ፡፡ ምንም ስልጣን የለቀቀ ሰዉ የለም!” አለ መለስ በሃፍረት አንገቱን እየደፋ
”ታዲያ ከኛ ጊዜ የሚለየዉ ምኑ ነዉ?! ወረቀት መጨረስ እንጂ! አይ እናንተ! የብሄር እኩልነትስ ያልከዉ ተሳካልህ?” አሉት ቅድም የገረማቸዉ እና “ወይኔ ሳልጀምረዉ!” የሚል መንፈሳዊ ቅናት ያሳደረባቸዉ የምርጫ ሃሳብ አሁን ተራ የልጆች የእቃ እቃ ጫወታ ሆነባቸዉ
”እሱስ ተሳክቷል! ስልጣን በመላዉ የኢትዮጲያ ልጆች ዘንድ በእኩል ተከፋፍሏል” አለ መለስ በምርጫ ዙሪያ ከደረሰበት ሸዋዊ ሽሙጥ በማገገም አይነት
”አሁን አንተ ሀገርህ ወየት ግድም ነዉ?” አሉት ሚኒሊክ በድንገት
”አድዋ ” አላቸዉ
”አድዋ ያቺ ታሪክ የሰራንባት!?” አሉ ቀና ብለዉ ፡፡አድዋ ሲባል ፊታቸዉ በራ፡ ወኔያቸዉ መጣ

”እና ትግሬ ነሃ!?” አሉ ፡፡ ”የዮሓንስ ዘር ተመልሶ ስልጣን ያዘ ወይኔ ሸዋ!” አሉ በሆዳቸዉ
”እና ሁሌም ሸዋ እድሜ ልክ ይግዛሎት” አላቸዉ በሆዳቸዉ ያሰቡትን አውቆ
”ሺት! ተበላሁ” አሉ (ይሄ ማይክል መቼም ያላስለመዳቸዉ ነገር የለም)
”እና አሁን የብሄር እኩልነት ስትል ከትግሬ ዉጭ ስልጣን ለሌሎቹ አከፋፍለሃል?” አሉት
”በሚገባ እንጂ ! አሁን ለምሳሌ ፕሬዝዳንቱ ኦሮሞ ነዉ” አላቸዉ
”ብሬዝዳንት ማለት በእኛ ጊዜ ተአማሪካ እንደሰማሁት ከሆነ ከንጉስ የማያንስ ነዉ! ታዲያ ካንተ በላይ ስልጣን ሰጠኸዉ ማለት ነዉ?! ይህማ ማለፊያ ነዉ!” አሉ በደግነቱ የቅድሙ አይነት መንፈሳዊ ቅናት ተመልሶ መጣባቸዉ
”አይ ስልጣን እንኳን ምንም የለዉም፡፡ እኔ የምወስነዉን መፈረም ብቻ ነዉ ስራዉ ፡፡ፊርማዉን እምቢ ቢልም ጉዳዩ ከመፈጸም አይቀርም ብዬ በአዋጅ አስቀድሜ አስቀምጫለሁ” አላቸዉ፡፡
ኤጭ! አሁንስ ዉሸት የማይቻልበት ቦታ መኖር መረረኝ!” አለ በሆዱ
”እኔም መሮኛል” አሉ መጀመሪያ በሆዱ ላወራዉ መልስ ለመስጠት፡፡ ለጥቀዉም ”ታዲያ ይሄማ “ጻፌትእዛዝ ነዋ !”ለምን “ብሬዝዳንት” ብላችሁ ስም ታበለሻለችሁ?! …እሺ ይሄስ ይሁን ….እንደዉ ሌላ ስልጣንስ ለማን ብሄር ሰጥተሃል?!” አሉት የቅድሙ የቅናት ስሜት ልክ ስለ ምርጫዉ ሲነግራቸው እንደተፈጠረባቸው ጊዜያዊ የቅናት ስሜት አለፈላቸዉ፡፡
”ለምሳሌ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ ሶማሌ ናቸዉ፡፡ በእርሶ ጊዜ መቼም ሶማሌ ለዚህ አይነቱ ስልጣን አይታሰብም!” አለ መለስ በኩራት
”እዉነትህን ነዉ! በኔ ጊዜ እንደዚህ አይነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የማቋቋም ቀልድም አይታሰብም! አሁን ፈረንጅ ለማስጎብኘት ሚኒስቴር ያስፈልጋል?! ወቸ ጉድ! ”ቢሊ ጂን …ሺ ኢዝ ኖት ማይ ላቭ!” አለ ማይክል፡፡ ቆይ እኔ በሚገባኝ ለምን አታስረዳኝም?!” አሉ ፡፡የማይክል የሆነ ነገር በሙሉ ትርጉሙ ባይገባቸዉም ይመስጣቸዋል፡፡
”ለምሳሌ የጦር ሚኒስቴርህ ብሄሩ ምንድነዉ?” አሉት በሳቸዉ ጊዜ ከነበሩ ዋና ዋና ሚኒስቴሮች አንዱን በመጥራት
”ስልጤ ነዉ፡፡ ሲራጅ ፈርጌሳ ይባላል” አላቸዉ
”ስልጤ ደግሞ ምንድነዉ?” አሉ፡፡እኔ ከሞትኩም በኋላ ኢትዮጲያ ተስፋፍታ ይሆን በሚል ጉጉት
”አይ እርስዎ አያዉቁትም በእኔ ጊዜ “ነጻ የወጣ” ብሄር ነዉ?” አላቸዉ
”ከማን ነዉ ነጻ የወጣዉ?”አሉ ንጉሱ በጉጉት
”ከጉራጌ ” አላቸዉ
”ጉራጌ ደግሞ ምንድነዉ?” አሉ የበለጠ በመገረም
”ብሄር ነዉ፡፡ በእርሶ ጊዜም ነበረ ግን እርሶ ካለ አማራ ማንንም አያዉቁም ያዉ…..” አላቸዉ
”ወቸጉድ !ሀገሩን ሁሉ ሸንሽነኸዉ የለ እንዴ! እና ይሄ ስልጤ ያልከዉ ሰውዬ የጦር ሚኒስቴሩ ጦሩን የሚያዘዉ እሱ ነዉ ማለት ነዉ?” አሉ
”አይ አይደለም፡፡ ጦሩን የሚያዘዉ ዋና መሪዉ ሌላ ነዉ “ሳሞራ” ይባላል” አላቸዉ፡፡ “ምነው ብሄሩን ባልጠየቁኝ!” አለ በሆዱ
”ለምን አልጠይቅህም! ብሄሩ ምንድነዉ?” አሉት፡፡የሆድ ሃሳብ ዋጋ የለዉም፡፡
”ትግሬ ነዉ” አላቸዉ ድምጹን ደከም አድርጎ
”እሺ ከዉጭ ሰዎች ጋር የሚገናኝ ውጪ ጀሀር የምትልከው ታማኝ የውጪ ጉዳይ ሰዉ ማነው? እኔ ራስ መኮንን የቅርብ ዘመዴን ነበር በየሀገሩ የምልከዉ፡፡ ግን ለመሆኑ አሁን እንደዚህ አይት ሚኒስቴርስ አላችሁ?” አሉ
”አዎ አለን፡፡ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይባላል” አለ መሌ በቸልተኝነት፡፡ ሼባው ወዴት እያመሩ እንደሆነ ገብቶታል፡፡
“እኔ እንደሚገባኝ ይሄ ትልቅ ስልጣን ነዉ፡፡እሱንስ ለየትኛዉ ብሄር ሰጠኸዉ?!” አሉት በሰርሳሪ አይቻቸው ትኩር ብለው እያዩት
”ለረዥም ጊዜ የነበረው ትግሬ ነዉ፡፡ ስዩም ይባላል፡፡ አሁን ግን ቀይሬዋለሁኝ” አለ በደከመ ድምጽ፡፡
”ራስና ደጃዝማቾችህስ?” አሉት ተስፋ በመቁረጥ
”በእኛ ጊዜ ራስ፡ ደጃዝማች፡ፈታዉራሪ የሚባል የለም ፡፡አሁን “ጄነራል እና ኮለኔል” ነዉ የምንላቸው፡፡” አላቸዉ
”ምነዉ እንደጥልያን!? የራሳችሁ ቋንቋ የት ሄዶባችሁ ነዉ ልጆች!! እሱን ተወዉ እሺ! አነዚህስ ጄነራሎችህስ የተለያዩ ብሄሮች ናቸዉ?” አሉት
”አረ አይደሉም! አብዛኞቹ እንዳውም ሁሉም ማለት ይቻላል ትግሬዎች ናቸዉ፡፡ለምሳሌ ባለፈዉ እኔ የሞትኩኝ ሰሞን እራሱ 34 ጄነራል ሲሾም 32 ቱ ትግሬዎች ነበሩ ” አለ፡፡ ቅድም “ለብሄር እኩልነት ነዉ የተዋጋሁት” ማለቱ እና በኚህ አሽሟጣጭ የሸዋ ሽማግሌ አፍ መግባቱ ጸጸተዉ
”እቴጌይቱስ? ” አሉት ፈገግ ብለዉ፡፡ እሳቸዉ ጣይቱ ጎንደሬዋን አግብተዉ የጎንደርና የሸዋን ህዝብ አስማምተዉ እንደኖሩ እያሰቡ፡፡
”እሷም ትግሬ ነች፡፡” አለ መለስ ፡፡ “በእናንተ ጊዜ ፎንቃ የለ ምን የለ! ከሀገር ሀገር ሳትተዋወቁ እየተጋባቹ !እኔና እኔም እንዳንተ የማላውቃትን ሼባ ወይም ህጻን ለፖለቲካ ብዬ ላግባልህ!?” አለ በሆዱ
“እሱስ ልክ ነህ! እኔም እኮ ዋና ፎንቃዬ ወ/ሮ ባፈና ነበረች” አሉ ሚኒሊክ፡፡በሃሳባቸዉ የወ/ሮ ባፈና ግብዳ መቀመጫ ዉል አለባቸዉ፡፡
መሌ ሀሳባቸዉን ባኖባቸዉ ፈገግ አለ፡፡
”ምን ታገጣለህ! ታዲያ የቱ ጋር ነዉ የብሄር እኩልነትን ያረጋገጥከዉ?!” አሉ በቁጣ፡፡ በዛዉም የተነቃባቸዉን ሃሳብ ለማስቀየስ
”አሁን እኮ ግን ብሄር ብሄረሰቦች በራሳቸዉ ቋንቋ ይዳኛሉ ፡ይሰራሉ…. ወዘተ…” አለ መለስ በድንገተኛ ቁጣቸዉ በመደንገጥ
”በእኔስ ጊዜ ቢሆን የጅማዉ አባጅፋር ህዝቡን በአማርኛ ነበር እንዴ የሚዳኘዉ? ካዎ ጦና የወላይታን ህዝብ ሲያስተዳድር የነበረው በወላይትኛ አልነበረም እንዴ? የማይመስል ነገር አታዉራብኝ! በስልጣንስ ክፍፍል ቢሆን እነ ራስ ጎበና ወሮመዎቹ አልነበሩ እንዴ ስንት ሺ ጦር የመሩት!? ደጃች ባልቻ ሳፎ(አባነብሶ) ፡ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ(አባመላ) የጦሩ አለቃ ወሮሞዎች አልነበሩም? ራስ መንገሻስ? ራስ አሉላስ? መቼ የዮሓንስ ናቸዉ ብዬ ጣልኳቸዉ?!” በቁጣ ተንቀጠቀጡ

”አረ ያራዳ ልጅ አይቆጡ! የኢትዮጲያ ህዝብ እንደዉ ምንም ሰሩ ምንም መርሳቱ አይቀር! እኛ ተጎዳን እንጂ” አላቸዉ
”እዉነትህን ነዉ ነገሩ ”ዩ ሮክ ማይ ወርልድ” ግባለት” አሉት እጃቸዉን ጨብጠዉ ወደ መለስ እየዘረጉ
ገባላቸዉ!
ስለሳቸዉ የእጅ ቆረጣ የኩሽ ህዝብ የሚያወራዉን በፍቅር እያዋዛ ነገራቸዉ፡፡ እሳቸውም እሱ ከመሞቱ በፊት በ97 ምርጫ በወታደር የተገደሉ ልጆች የነገሯቸዉን አዋዝተዉ ነገሩት፡፡ የማይክል ዘፈን ትዝ አላቸዉ
“አም ባድ….. አም ባድ…… ሁዝ ባድ?!” አሉት፡፡
መልሱን ለእናንተ ትቼዋለሁ፡፡

Filed in: Amharic