>

"ኧረ የጉልበቴን ሎሚ እንኳን እንዳታፈሱት?"(አግባው በቂሊንጦ እስር ቤት)

በጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ና ጌታቸው ሽፈራው

agbaw-from-kilintoአግባውን በአካል ያወኩት፣ ቂሊንጦ ሳለሁ የፍርድ ቤት ቀጠሮ በነበረን ዕለት ሲሆን እኔና ዳንኤል ሺበሺ ካቴና እጃችን ላይ እስኪገባ ድረስ በተረኛ ፖሊሶች ፍተሻ እየጨረስን ነበር። አግባውም ልደታ ፍርድ ቤት ቀጠሮ ስለነበረበት እኛ ወዳለንበት ስፍራ ዘግየት ብሎ መጣ። ከዳንኤል ጋር በፊት ይተዋወቁ ስለነበረ ተቃቅፈው ሰላም ተባባሉ። ከእኔ ጋርም ሰላም ተባባልን። እነእቶ በቀለ ገርባም በዕለቱ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ስለነበራቸው ተያይተን ሰላምታ ተሰጣጥተናል።

….አግባው እኛ ወደነበርንበት ዞን2 የተዘዋወረው በቅርቡ ሲሆን የዛሬ 18 ቀን ገደማ፣ ከምሳ ሰዓት መልስ እኛ ባለንበት ክፍል (8ኛ ቤት) በራፍ አቅራቢያ ቆመን ተነጋግረን ነበር። ከዚያ ቀደምም በመጠኑ ሀሳቦችን ተለዋውጠን እናውቃለን። በተለይ ስለደረሰበት እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ ድብደባ!

አግባው ላይ ትህትና፣ እርጋታ፣ ማስተዋልና የሰውን ስሜት ቀድሞ የመገንዘብ ባህሪ አይቼበታለሁ።

አግባው እንዲህ አለኝ፡- “ኤልያስ አንተ ጋዜጠኛ ነኝ። ሰሞኑንም በዋስ ተፈቺ መሆንህን እኔም አንተም እናውቃለን። ግን የደረሰብኝን ነገር አሁን ባሳይህ ደስ ይለኛል …”

እሺ ብዬ አግባውን ማየት ጀመርኩ። የለበሰውን ቱታ ሱሪ ወደላይ እስከሚችለው ድረስ ሰብስቦ ሰውነቱን አሳየኝ። እኔ ግን ምን ብዬ እንደምገልጽላችሁና ምን ቃል መርጬ እንደምጠቀም ከበደኝ። በድብደባ ክፉኛ የተጎዳው የእግሩ ክፍሎች አባብጠው፣ በልዘው፣ ወፋፍረም ሰንበር መሳይ አግድመቶች አውጥተው፣ አንዳንድ ቦታዎች ጎድጉደውና ተጉረብርበው የሰው ልጅ እግሮች አይመስሉም ነበር። በተለይ ጉልበቶቹ ላይ ያለው ጠበሳ ዝግንን ስላለኝ “ጉልበትህ ግን አሁን እንዴት ነው?” ስል ቃላት ለመጀመሪያ። ጊዜ ከአንደበቴ አወጣሁ። “ኧረ የጉልበቴን ሎሚ እንኳን እንዳታፈሱት?” ብዬ ብጠይቃቸውም በወቅቱ ሰሚ እንዳልነበረው አግባው በጨዋ አንደበት መለሰልኝ።

ብቻ በቆምኩበት ሰውነቴ ሽምቅቅ አለ። ልባዊ ሀዘን እንደወረረኝም “እጅግ ይዘገንናል፤ አይዞህ!” አልኩት። “ምን ይሄ ብቻ መቀመጫዬ ላይ የደረሰብኝን የድብደባ ጠበሳዎች ወደባዶ ስፍራ (ብዙ ሰው ወደሌለበት) ሄደን ላሳይህ። ከድብደባው በኋላ አራት አምስት ቀናት ሌሎች እስረኞች በግራ እና በቀኝ እጄን ይዘው ነው ሽንት ቤት እጠቀም የነበረው። ብዙ ደም የፈሰሰኝ ሲሆን በወቅቱ ራሴን ችዬ መንቀሳቀስ እንኳን አልችልም ነበር። …” አለኝ።

“አግባው፡- እሱን ማየቴ ይቅር፤ አሁን ያሳየኽኝ እንኳን መንፈሴን እጅግ ረብሾታል …እውነት ብርቱ ሰው ነህ። ዘግናኝ መከራን ተቋቁመሃል!” አልኩት – ትከሻውን ይዤ። “ፈጣሪ ከተበደሉት ጋር ነው” አልኩኝ በልቤም። ወንድማችን አግባው ይህን ሁሉ መከራ ፈጣሪ ከጎኑ ባይኖር ኖሮ እንዴት ያልፈዋል? ይቋቋመዋልስ?!

በወቅቱ አግባው በሰውነቱ ላይ ያሳየኝ የግፍ ህመም፣ ምልክትና ሰንበር ውስጤን ክፉኛ ስለረበሹት “አግባው ተመልሼ እመጣለሁ …” ብየው እጁን በመጨበጥ ወደክፍሌ አመራሁ። እርግጠኛ ነኝ፤ አግባው ያዘነና የተረበሸ ስሜቴን ተረድቶታል።

አግባው ሆይ፣ ፈጣሪ አሁንም ብርታቱን፣ ጥንካሬውንና ከለላውን ይስጥህ!

አግባው በቂሊንጦ እስር ቤት አዛዦች የተጠላባቸው “ምክንያቶች” የሚያሳዝኑ ናቸው።

አንድ ነባር እስረኛ በትይዩ ከሚተኛው ሰው ጋር ተስማምቶ አዲስ እስረኛ ሲመጣ ሁለቱ አልጋ መሃል ያለ ክፍተት ላይ ማስተኛት ይችላል። መሬት ላይ ነው። ለአዱሱ ሰው መንገድ ላይ ከሚተኛ ይሻለዋል። አግባውም ቻሌ ነጋ የሚባል የወልቃይት ልጅ አልጋ መሃል እንዲተኛ ያደርጋል። ሌላ ሰው ለሚያውቀው ሰው አልጋው መሃል ቦታ ሲሰጥ ምንም የማይሉት የተክላይ ልጆች “የሽብር ተከሳሽን አልጋ መሃል እያስተኛ ነው ” ብለው ከሰሱት።
ጉርባ ወርቁ እና ሻንቆ ብርሃኑ በ20ዎቹ መጀመርያ የሚገኙ በሽብር የተከሰሱ ወጣቶች ናቸው። ፊደል አልቆጠሩም። አግባው መመሪያ መፅሃፍትን አስመጥቶ ፊደል ያስቆጥራቸዋል፣ ሂሳብ ያለማምዳቸዋል። ከተፈረደባቸው ትምህርታቸውን ተምረው ይወጣሉ ብሎ ብዙ ይለፋል። ይደክማል። እነዚህን ወጣቶች ፊደል እንደሚያስቆጥር እየታወቀ ፖለቲካ እያስተማራቸው ነው ብለው ከሰውታል። በዚህ ምክንያት ጨለማ ቤት ገብቷል።
እስር ቤት ውስጥ ቤተሰብ ከእነ መኖራቸው የማያውቃቸው በርካታ እስረኞች ሞልተዋል። የሚቀይሩት ልብስ የሌላቸው በርካቶች ናቸው። ለእነዚህ በተለይ በሽብር ለተከሰሱ እስረኛ አግባው ከጎናቸው ነው። ልብስ እና በሶ ያስመጣላቸዋል። ያለውን ገንዘብ ያካፍላቸዋል። አብሯቸው ይውላል። የእስር ቤቱ አዛዦች አግባው ከእነዚህ እስረኞች ጋር “ወክ” ሲያደርግ ሁሉ ይበሽቃሉ። በአንድ ወቅት ብቻህን ወክ አድርግ እስከማለት ደርሰዋል።

የቂሊንጦ እስረኛ ቅዳሜና እሁድ ቆሎ “እየቃመ” ይጫወታል። አንዱ አልጋ ላይ በርከት ያሉ እስረኞች ቆሎ እየቃሙ ሲጫወቱ ፖሊስ ቢያይ ዝም ብሎ ነው የሚያልፈው። ያዘ ተብሎ ቆንጥሮም የሚያልፍ አለ። አግባው አልጋ ላይ ቆሎ ከተቃመ ግን ወዲያውኑ ሪፖርት ይደረግና እነ ካህሱ፣ ወደሃኪም፣ እነ ገብረማርያም፣ እነ አሰግለ፣ እነ ዘሩ፣ እነ ጉዕሽ ………ይግተለተላሉ። አግባው ይጠራል። ይከሰሳል። ወደ ጨለማ ቤት!
እነዚህ በጥላቻ የታወሩ የእስር ቤቱ አዛዦች በትዕዛዝ አግባውን አስደብድበውታል። ሸዋሮቢት ጉልበቱን መትተው መቅኒውን ያፈሰሱት በእነ ዘሩ ቀጥታ ትዕዛዝ እንደሆነ ታውቋል። አሁንም ለአግባው የሚፈልጉለት ሰበብ ብቻ ነው!

Filed in: Amharic