>

ስማ... ስማ!... መልካም ልደት (ታምሩ ተመስገን)

Emye Minilik Henok Yeshitila 06042016…. በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ በተለይ ከተፈሪ መኮንን በመለጠቅ የነገሱት መንግስታት አሁን ያለንበትን ጨምሮ ስለ ቀደሙት ማውሳት የሚቀናቸው መጥፎ መጥፎውን በተለይም ትውልድን ደም የሚቃባውን እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ እኔ ግን ለጥቄ ስጥፍ አክባሪህን አክብርን ሰንደቅ አድርጌ ይሆናል፡፡ እንግዲህ የፊታችን 12 የዳግማዊ ምኒልክ ልደትም መሆኑ አይደል!! ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ከአባታቸው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ እና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም 1836 ዓ.ም ነሃሴ 12 በአንኮበር ተወለዱ፡፡ እምየ በመወለዳቸው ትውልድ ምን ተጠቀመ ለሚለውን ጥያቄ መልሴን ከግልምጫ ጋር ለጥቄ እጥፋለሁ፡፡
.
…. ስማ!ስማ! የዛሬ 100 ምናምን አመት በፊት ስልጣኔ ድክድክ ሲል በእምየ ምኒልክ ዘመን ቧንቧ ውስጥ የገባን ውሃ ነው ባሁኑ ዘመን ስልጣኔው ተትረፍርፎ ሳለ ቤትህ ማድረስ ያቃታቸው፡፡ መቼ ነው ግን የጥም ሚኒስቴር ካልፈረሰ ብለህ አደባባይ ‘ምትወጣው? ኤነትሬ ላይህ ላይ ይውጣብህና! እምየ ብርሃን ይሁን ሲሉ ኤሌክትሪክንም ወደ ሃገር ውስጥ ያስገቡ የመጀመሪያው መሪ ናቸው፡፡ አስተውል የዛሬ 100 አመት የገባ ኤሌክትክን ነው አሁንም በፈረቃ ‘ምትጠቀመው፡፡ የዲያቢሎስ ጭፍሮች ይፈራረቁብህና፡፡

ስማ!ስማ! አንተ አምነህ ብርህን ስታስቀምጥ እነሱ ግን አንተን አናምንም ሲሉ እስክሪቢቷቸውን የሚያስሩ ባንኮች ፌስታል ሙሉ እቃ የማይገዛ መቶ ብር የሚሰጡህ ባንኮች እንዳሁኑ ዋጋ ቢስ ሳይሆኑ በፊት የተመሰረቱት በምኒልክ ነበር፡፡ መንግስት ዋጋ ያሳጣህና!! በዚህ ዘመን ህዝቡን ሳይሆን እንቱን ለማስጠበቅ እያለ ያለምክንያት የሚቀጠቅጥህን ፖሊስም በ1896 ዓ.ም ዳግማዊ ምኒልክ ለህዝቡ ደህንነት ብለው ያቋቋሙት ነበር፡፡ አጋዚ መገጣጠሚያህ ላይ ይቁምብህና፡፡

ስማ!ስማ! ምኒልክ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ጫማን ለኢትዮጲያ ባያስተዋውቁ ኖሮ ዛሬ ላይ ሙጀሌ ያነፈረቀውን እግርህ በወረንጦ ስትዘነጥል ነበር ‘ምትውለው፡፡ ገማች ይዘንጥልሃና! ስማ! አያ ቀዳዴ… መገናኛ ሆነህ ሳለ ሳሪስ ነኝ እያልክ የምትበረነንበት ስልክ ለመልካም ነገር ታውለው ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስገቡት ምኒልክ እንደሆኑስ ታውቃለህን? ለነገሩ ስላንተማ ካንተ የተሻለ ስልክህ የሚሰልሉት እነ እንትና ነው ‘ሚያውቁት፡፡ የልጆችህ እናት ትሰልልህና!

ስማ!ስማ! ዛሬ በየሜዳ አህያ ማቋረጫው ላይ ሲያሳቅቅህ የሚኖረውን መኪና በየአሳቻው ቦታ ሲደፈልስህ የሚኖረውን አውቶሞቢልም እምየ ምኒልክ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያስገቡት ከጉዞ ድካምህ የሚሳርፍህ መስሏቸው ነበር፡፡ ኮማንድ ፖስት ሆድ እቃህ ላይ ይረፍብህና፡፡

ስማ!ስማ! እንዳሁኑ ቤትህን በጡብ ሳትገነባ በፊት ዛኒጋባህን የሰራኸው እምየ ምኒልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስገቡት ባህር ዛፍ እንደሆነስ ታውቃለህ? ቤትህን ለልማት ብለው ያፍርሱብህና!!

በነገራችን ላይ ከክፍለ ዘመን በኋላ እንደ ብርቅ የምታየውን ባቡር እኮ ጥንት እምየ ነበር ያስገቡት፡፡ ፌደራል ቤትህ ይግባና! ታውቃለህ ግን ምኒልክ ሀኪም ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ባያቋቁሙ ኖሮ ዛሬ ላይ የበሽታ ማከማቻ ነበር ‘ምትሆነው፡፡ ሙሰኛ ይከማችብህና!

ስማ!ስማ! ምኒልክ ያኔ በእጅ የሚሰራ ማተሚያ ማሽን ባያመጡልህ ኖሮ ዛሬም በሌጦ ስታትም ትገኝ ነበር፡፡ ሌጦህ ይገፈፍና፡፡ ስማ!ስማ! ዛሬ ላይ ግብሩን አሳስተው የሚጠቀሙትን እንደጉልቻ የሚቀያይሩትን ሚኒስቴር ህዝቤ ይጠቀማል ብለው ስላሰቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1900 ዓ.ም በነጋሪት አሳውጀው ያቋቋሙትም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ነበሩ፡፡ 10 ሚኒስቴሮች፡፡ ደግሞ ሳልነግርህ እናትህና እህትህ በድንጋይ እህል ከመፍጨት እፎይ ይሉ ዘንድም እኮ ወፍጮ ለሀገራችን ያስተዋወቁት ምኒልክ ናቸው፡፡ ዶዘር ይፍጭህና፡፡

ስማ!ስማ! በደህናው ጊዜ ምኒልክ በባለቤታቸው ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቋቋሙትን ሆቴል እኮ ነው አሁን ላይ ለሆዳቸው ያደሩት ምግብ እየበላህ ከጉሮሮህ ተናንቆህ እስኪ የሚጠጣ ውሃ ስትላቸው “የቧንቧ ውሃ የለችም፡፡ ስንት ሌትር የታሸገ ውሃ ይሁንልህ?” የሚሉህ፡፡ ሱቅህ ይታሸግና! ስማ!ስማ! አሁን ለምን ስትል ትጠይቀናለህ ብለው እነ እንትና የሚያዘንቡብህን ጥይት ‘ኮ ለሀገር መጠበቂያ ይሆን ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሉትም ምኒልክ ነበሩ፡፡ ብብትህ ውስጥ ፈንጅ ይትከሉብህና፡፡ መቼም እምየ የቋንቋ ተማሪ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ አቢሲኒያ ውስጥ ባይከፍቱ ኖሮ ዛሬም በዳፍንት የምትጓዝ መሀይም ትሆን ነበር፡፡ ታንክ በጀርባህ ይጓዝብህና፡፡
.
… ስማ እኔ ከላይ ከጠቀስኳቸው በላይ በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ዳግማዊ ምኒልክ ብርሃን ዘ-ኢትዮጲያ ለሀገራችን አስተዋውቀዋል፡፡ ታሪክህን አነፍንፍና ተማር አክባሪህንም አክብር፡፡
በማረጊያው ደግሞ ጉርሻ ይሆንህ ዘንድ የእንግሊዝን በሱዳን ላይ ድል በማስመልከት የመተማ ከተማ የኢትዮጵያ እንደሆነ ንግሥቲቱ እንዲወስኑ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለእንግሊዝ ንግስት ንግስት ቪክቶሪያ የድምፅ መልዕክት ልከው ነበር። ማምሻውን በሌላ ፖስት መልዕክቱን ማስደምጣችሁ ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic