>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7009

ኢትዮጲያ የማን ናት? መብቱ የዜጎች፣ ስልጣኑ የብሔሮች ነው!

ethiothinkthank.com

unity-ethiopia-satenaw-news“ኢትዮጲያ የማን ናት፡ የብሔሮች ወይስ የዜጎች?” በሚል ርዕስ ባወጣነው የመጀመሪያ ክፍል የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት ፍፁም አምባገነን እየሆነ መምጣቱን ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ውስጥ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚለው መርህ ላይ መንጠልጠሉና በዚህም ራሱ የዘረጋውን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ቀልብሶታል።
በመሰረቱ፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው ሕገ-መንግስታዊ መርህ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር ይጋጫል። ሌላው ቀርቶ ከሕገ-መንግስቱ ጋር ራሱ ይጋጫል። በአጠቃላይ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ “ፀረ-ዴሞክራሲያዊ” ነው። “በእንቅርት ላይ ጆሮ-ደግፍ” እንዲሉ መንግስታዊ ስርዓቱ ደግሞ በዚህ መርህ ላይ እንደመሆኑ ሕገ-መንግስቱ፥ ብሎም ፖለቲካዊ ስርዓት ካልተቀየረ በስተቀር ዴሞክራሲ “ላም አለኝ በሰማይ…” እንደሚሉት ሆኖ ይቀራል። በዚህ ፅሁፍ፣ “ከሕዝብ ሉዓላዊነት” መርህ አንፃር የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት እርስ-በእርሱ እንደሚጋጭ እንመለከታለን። በቀጣይ ክፍል ደግሞ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት አንፃር የተሳሳተ መሆኑን እንመለከታለን።

በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው”።ነገር ግን፣ ይህ መርህ ከሉዓላዊነት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር ይጋጫል። በዚህ ረገድ ያለውን የተሳሳተ እሳቤ በግልፅ ለመረዳት እንዲያስችለን የሕገ-መንግስቱን የቃላት አጠቃቀም እና የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያዘጋጀውን የኣማርኛ መዝገበ ቃላት መሰረት በማድረግ ፅንሰ-ሃሳቡን በዝርዝር እንመለከታለን።

በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39(5) መሰረት “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ” ማለት ሰፋ ያለ የጋራ ባህሪይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች ያሉት፣ ሊግባባበት የሚችልበት የጋራ ቋንቋ ያለው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምን፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያለውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖር “ማህብረሰብ” ነው። (የቃላት ድግግሞሽን ለማስቀረት ሲባል እንደየሁኔታው “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ” የሚለው “ብሔር” ተብሎ ሊፃፍ ይችላል።) በዚህ መሰረት፣ ብሔር በቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድና ስነልቦናዊ አመካከት፣ እንዲሁም በታሪክ፣ ኢኮኖሚና በመልክዓ ምድር የተሳሰረ ማህብረሰብ ነው። በመሆኑም፣ የብሔር መብቶች ከእነዚህ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 39 ላይ “የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብት” በሚል የተጠቀሱት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይህን ያመለክታሉ።

መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተደነገጉበት የሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል ሁለት መሰረት፣ በንዑስ አንቀፅ 39(1) “ማንኛውም ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 39(2) “ማንኛውም ብሔር በቋንቋው የመናገር፥ የመፃፍ፥ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ፥ የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 39(3) ደግሞ “ማንኛውም ብሔር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት” እንዳለው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሕገ-መንግስቱ ንዑስ አንቀፅ 40(3) መሰረት “የመሬት ባለቤትነት መብት”፣ እንዲሁም በንዑስ አንቀፅ 43(1) መሰረት ደግሞ “የልማት መብት” እንዳላቸው ይጠቅሳል።

በዋናነት በሕገ-መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብቶች ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ናቸው። ከዚህ በተረፈ፣ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል አንድ ስር የተዘረዘሩት በሙሉ የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ናቸው። በክፍል ሁለት ከተዘረዘሩት ውስጥ ከአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) በስተቀር ያሉት በሙሉ የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ግን እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ ከላይ የተጠቀሱት የብሔር መብቶች ይኖሩታል።

የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ሉኣላዊ” (Sovereign) የሚለውን ቃል “ነፃ የሆነ መሬት፣ ነፃ የሆነ፥ ምሉዕ ስልጣን ያለው ሀገር፥ መንግስት” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። “ሉዓላዊነት” (Sovereignity) ማለት ደግሞ “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት” እንደሆነ ይገልፃል። በዚህ መሰረት፣ “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” የሆነ አካል በቅድሚያ ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል።

በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሙሉ መሰረታዊ የግለሰብ መብትና ነፃነት ሊሆኑ ይችላሉ። የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብቶች ግን በአንቀፅ 39፣ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት መብቶች ብቻ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ግለሰብ ምሉዕ መብትና ነፃነት አለው። በተቃራኒው አንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ግን ምሉዕ መብትና ነፃነት የለውም።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንተሞከረው፣ “ሉኣላዊነት” (Sovereignity) ማለት “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት” ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሉዓላዊ ስልጣን እንዲኖረው በቅድሚያ ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍለ አንድና ሁለት ስር ከተዘረዘሩት 31 መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ውስጥ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብት የሆኑት በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ውጪ ያሉት በሙሉ የግለሰብ መብቶች ናቸው።

እያንዳንዱ ግለሰብ በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት የብሔር መብቶች እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ ይኖሩታል። እያንዳንዱ ብሔር ግን በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) ከተጠቀሱት ውጪ ሌላ ዴሞክራሲያዊ መብት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም፣ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እንደ ግለሰብ በራሱ ሃሳብና አመለካከት የሚንቀሳቀስ ምክንያታዊ ፍጡር ስላልሆነ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሉትም። በተመሳሳይ፣ እንደ ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ስላልሆነ “ሰብዓዊ” መብት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ፣ በሕገ-መንግስቱ ራሱ ምሉዕ መብት ያለው ግለሰብ እንጂ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አይደለም።

በአጠቃላይ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን የሚችለው እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ እንጂ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች አይደሉም። ምክንያቱም፣ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት በምዕራፍ ሦስት ስር ከዘረዘራቸው 31 መሰረታዊ መብቶች ውስጥ ሦስት መብቶች ብቻ ያሏቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች “የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” እንደሆኑ ይገልፃል። ነገር ግን፣ “ሉኣላዊነት” የምሉዕ መብትና ነፃነት ባለቤትነት እንደመሆኑ መጠን ውስን መብት ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ሊኖራቸው አይችልም። በዚህ መሰረት፣ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት እርስ-በእርሱ እንደሚጋጭ በግልፅ መረዳት ይቻላል።

በመጨረሻም፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ ምሉዕ የሆነ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አለው። በዚህ መሰረት፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን የሚችሉት ሁሉም ኢትዮጲያዊያን ወይም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ናቸው። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ ተደንግጓል። ስለዚህ፣ ሕገ-መንግስቱ እርስ-በእርስ እንዲጋጭ የተደረገበት ምክንያት ምንድነው?

በመሰረቱ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል ባለመብት ብቻ ሳይሆን ባለስልጣን ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ ሉዓላዊ ስልጣን ያለው አካል በሀገሪቱ መንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ይኖረዋል። ስለዚህ፣ የሀገሪቱ መንግስት ተጠሪነቱ ለዚህ አካል ይሆናል። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት፤ የሀገሪቱ ዜጎች መብትና ነፃነት አላቸው፣ ብሔሮች ደግሞ የሉዓላዊ ስልጣን አላቸው። ዜጎች ምሉዕ መብት አላቸው፣ ነገር ግን መብታቸውን የመጠየቅ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን የላቸውም። ብሔሮች ደግሞ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን አላቸው፣ የሚጠይቁት ምሉዕ መብት ግን የላቸውም። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት መብቱ የዜጎች ሲሆን ስልጣኑ ግን የብሔሮች ነው!

በአጠቃላይ፣ የሀገሪቱ ዜጎች የማይጠይቁት መብት ሲኖራቸው፣ የሀገሪቱ ብሔሮች ደግሞ የማይጠቀሙት ስልጣን አላቸው። የኢህአዴግ መንግስት ዘወትር ስለ ብሔር መብትና እኩልነት ይደሰኩራል። ዜጎች የመብትና እኩልነት ጥያቄ ሲያነሱ ግን እንደ ጠላት እያደነ ያስራል፥ ይገድላል፥…ወዘተ።

Filed in: Amharic