>

ከእስር ቤት የተላከ ደብዳቤ

ከእስር ቤት የተላከ ደብዳቤ  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያነበው የሚገባ

ለእናት ሀገር ሲባል፣ ማን ይፈራል….!

1. እየሩሳሌም ተስፋው (ከቃሊቲ እስር ቤት)
2. ብርሃኑ ተ/ያሬድ (ከቂሊንጦ እስር ቤት)
3. ፍቅረማርያም አስማማው (ከቂሊንጦ እስር ቤት)

by-mahilet-fantahun-zone-9በሰላማዊ ትግል ጓዶቻችን የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና፣ መልካም ህልም አላሚዎቹ የዞን 9 ጦማርያን ያለምንም ወንጀል በስርዓቱ ወደር የለሽ ፍራቻ ምክንያት ብቻ ከንጹህ ህሊናቸውና ከመልካም ስራቸው ጋር ወደ ማጎሪያ ቤት በተወረወሩ ጊዜ፣
‹‹በሉ እናንተ ሂዱ የእኛም ወደዚያው ነው፣
ድሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው›› ብለን ነበር፡፡
ይህን ብለን ሳናበቃ ግን በዚህ ሁኔታ የሀገራችን እጣ ፋንታ ምንድነው? የሚል ጥያቄ በውስጣችን ይመላለስ የነበርን የዛሬዎቹ አባሪ ተከሳሾች የሆንን ወጣቶች መደበኛ ያልሆነ ውይይት ጀመርን፡፡ በዚህ ውይይታችንም አምባገነኑን የወያኔ አገዛዝ ሊያስወግደው ቀርቶ ሊያሳምመው እንኳን በማይችል ጉንተላ መሳይ ትግል ውስጥ ሆነን ለሀገራችን የሚጠበቅብንን ያህል ዋጋ ሳንከፍል ጓዶቻችንን ተከትሎ ወደ ማጎሪያ ቤት መጓዝ ለምንወዳት ሀገራችን የሚፈይደው ነገር ምንድነው? ትግሉስ ከኛ ምን ይፈልጋል? የሚሉ የወቅቱን ወሳኝ ጥያቄዎች በማንሳት ከራሳችን ምላሾችን ለማግኘት ሞክረን ያገኘነው ምላሽም ለትግሉ ማበርከት ያለብንን አስተዋጽኦ ሳናበረክትና የአቅማችንን ሁሉ ሳንሰራ ጓዶቻችንን ተከትለን ወደ ማጎሪያ ቤቱ መጓዝ ለሀገራችን የሚጠቅማት ነገር እንደሌለና በማንኛውም መንገድ አምባገነኑን ስርዓት ሊያስወግደው በሚችል ትግል ውስጥ መሳተፍ የወቅቱ ግዴታችን መሆኑን ነበር፡፡
እናም 6 ወራት ከፈጀ ሰፊ ውይይት በኋላ ምርጫችን ሁሉን አቀፍ ትግል መርጦ ለሀገር ነጻነት በሚታገለው፣ ሀገራችንን ከፋሽስታዊው አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ሌት ተቀን ሞትን ተጋፍጠው የሚተጉ አባላትና ትግሉን ስኬታማ ለማድረግ በልበ ሙሉነት ለስልጣን ሳይሆን ለሞት የሚሽቀዳደሙ መሪዎች ወደተሰባሰቡበት፣ በአገዛዙ ፓርላማ ‹‹ሽብርተኛ›› የሚል የዳቦ ስም ወደተሰጠው ‹‹ግንቦት 7›› ወደተሰኘው ነጻ አውጪ ድርጅት አደረግን፡፡ ድንቅ ምርጫ!! መቼም የማንጸጸትበት ሁሌም በኩራት ደጋግመን የምንናገረው ምርጫ!!
ይህን ውሳኔያችንን ተከትሎ ነበር ዛሬ በእስር ላይ የምንገኘው ሦስት አባሪ ተከሳሾች የድርጅቱ ህዝባዊ ኃይል ታጋዮች ወደሚገኙበት አካባቢ ጉዞ የጀመርነው፣ (በእርግጥ በዚህ ‹‹እናት ሀገር ትቅደም›› ጉዟችን ባህር ዳር ስንደርስ ‹‹ወላጅ እናት ትቅደም›› ብሎ ተሰናብቶን የተመለሰ አንድ ‹‹ጀግና›› ወዳጃችንም አብሮን ነበር፡፡) እነዚህን ቆራጥ የኢትዮጵያ አንበሶች ከመገናኘታችን በፊት ሊቀበለን ከመጣው ደሴ ካህሳይ ጋር ሆነን በደህንነት አባላት ተብየዎቹ የስርዓቱ ወንበር ጠባቂዎች እጅ ወደቅን እንጂ፡፡
ይሁንና በስርዓቱ ጠባቂዎች እጅ መውደቃችን ውሳኔያችንን በድጋሜ እንድንመረምር አላደረገንም፤ ዛሬም በአቋማችን ጽኑ ነን፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያውያን ነጻ አውጭ ድርጅት የሆነው የግንቦት 7 አባላት ነን፡፡ ይህንንም በኩራትና በልበ ሙሉነት ለማዕከላዊ ደብዳቢዎች (መርማሪዎች?) አስረድተናቸዋል፡፡ ይህንንም ያደረግነው ምርጫችን ትክክል መሆኑን ስለምናምን እንጂ የደብዳቢዎቻችንን ጭካኔ ቀላል ይሆንልናል በማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህን መናገራችን ደብዳቢዎቻችንን አበሳጭቶ ኖሮ ሴትን ልጅ ራቁቷን አቁሞ ከሚደረግ የጭካኔ ምርመራ አንስቶ ዓይንን ታስሮ ውሃ እየደፉ እስከመደብደብ የደረሰ ግፍ በደብዳቢዎቹ መሪ ኮማንደር ተክላይ ጭምር ተፈጽሞብናል፡፡ በምርመራው መሐልም ግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ነው ብለን እንድንናገር፣ ወደ ትግሉ የገባነው አሜሪካ ባሉ የድርጅቱ አመራሮች ተታልለን ነው እንድንል ሀገር ውስጥ ፍጹም ሰላማዊ ትግል ማድረግን የመረጡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ከግንቦት 7 ጋር ይገናኛሉ እንድንል በአላዋቂዎቹ ደብዳቢዎች ይነገረን ነበር፡፡
አሰቃቂው ምርመራ የአንዳችንን ስቃይ በአንዳችን በማስፈራራት ‹‹እሱን ከምንደበድበው እሷን ራቁቷን ከማቆማት እመን/እመኝ የሚለው ማስፈራሪያ ነበር፡፡ ሆኖም ለክፉ ስራቸውና ለሀሰት ምስክር ቆጣሪነታቸው የሚተባበር አስተዳደግም ሆነ የትግል ልምድ አልነበረንምና በቃላችን ጸንተን አካላችን እንጂ መንፈሳችን ሳይጎዳ የተለመደውን የሽብርተኝነት ክስ ተጎናጽፈን ወደ ቃሊቲና ቂሊንጦ ማጎሪያ ቤቶች ተዛውረናል፡፡
በማጎሪያ ቤቶቹ ሊጠይቁን የመጡ አንዳንድ የሰላማዊ ትግል የቀድሞ ጓዶቻችንም የወሰነው ውሳኔ የተሳሳተ እንደነበር በጓዳዊነት መንፈስ ሊያስረዱን ሞክረዋል፡፡ ጥቂቶቹም ውሳኔው የወጣትነት ጀብደኝነት ነው ሲሉ ሊሞግቱን ሞክረዋል፡፡ አንዳቸውም ግን ትግሉን አስመልክቶ ላነሳንላቸው ጥያቄ ምልሽ ሊሰጡን አልሞከሩም፡፡ ሁላችንም ይህን መንገድ ከመምረጣችን በፊት በሀገር ውስጥ በሚደረገው የፓርቲ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ከፓርቲ አባልነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ድረስ በመሳተፍ የአቅማችንን ያህል አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡ ነገር ግን ዛሬም በትግሉ ውስጥ ያልተፈቱት እንቆቅልሾች ያልተመለሱት ጥያቄዎች ያስጨንቁናል፤ እና ዛሬም በአደባባይ እንጠይቃለን፡፡
ለመሆኑ በሰላማዊ ትግል ውስጥ የሚከፈለው ዋጋ እና የሚገኘው ውጤት ተመጣጣኝ የሚሆነው መቼ ነው? አራት ሰዓት የሚቆይ አንድ ሰላማዊ ሰልፍ ሲባል እስከመቼ በስርዓቱ ጨካኝ አሽከሮች ነፍሰ ጡር እናቶች ጽንሳቸውን በድብደባ ብዛት ያስወርዳሉ? እስከመቼ ወጣቶች በድብደባ ብዛት አካላቸው ይጎድላል? ህዝብ ተስፋ የሚያደርግባቸውና በታጋዮች የህይወት መስዋዕትነት ጭምር የተከፈለባቸው ፓርቲዎችስ በአንድ ሌሊት ፈርሰው ለድርጎኛ ፖለቲከኞች መሰጠታቸው መቼ ይቆማል? ህይወታቸውን ለሀገራቸው ሰጥተው ሌት ተቀን የሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ለተራ ስልጣን ሲባል በብዕር ስም እየተደበቁ ስማቸውን ማጠልሸትስ ትግሉን የት ያደርሰዋል?
‹‹በድንጎላ ኮሎኔል ማራኪ››ዎቹ ታጋዮች ጓደቻችንን በድንጋይና በዱላ ድብደባ እየገደሉ እያስረከቡን ዛሬም ምላሻችን መግለጫ ነው? (ሳሚና ተሰማ ነፍሳችሁን ይማር) በቀቢጸ ተስፋ ወደ ‹‹እናት ሀገር›› ኬንያ የሚሰደደው ታጋይስ ማቆሚያው ምንድነው? እነዚህን እንቆቅልሾች ሳንፈታ የምናደርገው የትግል ጉዞስ የት ያደርሰናል?
እናም በውሳኔያችን አልተሳሳትንም ስንል ከእነዚህ ሁኔታዎች ተነስተን ረዘም ላለ ጊዜ በመወያየት የወሰድነው አቋም እንጂ በወጣትነት ስሜትና በጀብደኝነት ያደረግነው ባለመሆኑ ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል የአጭር ጊዜ ቆይታችን ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለ19 ጊዜያት፣ ፍቅረማርያም አስማማው ለ9 ጊዜ፣ እየሩሳሌም ተስፋው ለ7 ጊዜ በአገዛዙ እስር ቤቶች በግፍ ለእስር ተዳርገናል፡፡ በአንዱም ክስ አገዛዙ ጥፋተኛ ሊያስብለን ቀርቶ ክስ ለመመስረት እንኳን የሚያበቃ ምክንያት ሳይኖረው ለሳምንታት እያጎረ በመልቀቅ ማናለብኝነቱን በሚገባ አሳይቶናል፡፡ ስለሆነም ይህን መንገድ መርጠናል፤ በሰላማዊ ትግል ብቻ የሚያምኑ ወዳጆቻችንም የሚታገሉት ለሃሳብ ነጻነት ነውና ይህን ሀሳባችንን ሊያከብሩልን ይገባል፡፡
ጓዶች ይህቺ ኢትዮጵያ ናት፣ ታላቋ ኢትዮጵያ!! ቴዎድሮስ እናታለም የሚላት፣ በላይ ዘለቀ፣ አሉላ አባነጋ፣ አቢቹ፣ አብዲሳ አጋ፣ በጽናት የተዋደቁላት ኢትዮጵያ!! የእስክንድር ነጋ፣ የአንዱዓለም አራጌ፣ የእነ ኡስታዝ አቡበክር፣ የእነ ተመስገን ደሳለኝ፣ የእነ ርዕዮት ዓለሙና የእነ እማዋይሽ፣ የእነ ንግስት ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ ፋሲል የኔዓለም፣ የእነ መሳይ መኮነን፣ የእነ ሲሳይ አጌና…የሌሎችም ጀግኖች ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ አብርሃ ደስታ፣ የእነ በፍቃዱ ኃይሉ ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ ሳሙኤል አወቀ፣ የእነ ተሰማ ወንድሙ ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ ይልቃል ጌትነት፣ ዮናታን ተስፋዬ ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ አበበ ካሴና የታላቁ ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌ ሀገር ኢትዮጵያ!! (አንዲ ሁሌም ጀግናችን ነህ!!) እኛ ደግሞ የእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ነን፡፡ በመቃብራችን ላይ ካልሆነ ኢትዮጵያ አትደፈርም፡፡ በመስዋዕትነታችንም ካልሆነ ኢትዮጵያ አትገነባም፡፡ እጃችን ቢታሰርም መንፈሳችንን ሊያስሩት አይችሉም፡፡
ዛሬም የጀግኖች አንበሶቻችን የድል ጩኸት በጆሯችን ይሰማናል፡፡ የበሰበሰውን ዛፍ ለመጣል የተዘረጋው የአንበሶች ክንድ ይታየናል፡፡ ይህ ክንድ የበሰበሰውን ዛፍ ሳይጥል አይሰበሰብም፡፡ በብስባሹ ውድቀት ውስጥም ዴሞክራሲ ያብባል፣ ፍትሃዊነት ይነግሳል፣ እኩልነት ይሰፍናል፡፡ ይህ በወኔ እስር ቤት ያሉ ወጣቶች የቀቢጸ ተስፋ ህልም አይደለም፡፡ ተደጋግሞ በታሪክ የታየ አሁንም በቅርብ የሚፈጸም እውነት እንጂ!!
ጓዶቻችን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆነን ከእናንተ ጋር ነን፡፡
ማን ይፈራል ሞት
ማን ይፈራል ሞት
ለእናት ሀገር ሲባል….!!

1. እየሩሳሌም ተስፋው (ከቃሊቲ እስር ቤት)
2. ብርሃኑ ተ/ያሬድ (ከቂሊንጦ እስር ቤት)
3. ፍቅረማርያም አስማማው (ከቂሊንጦ እስር ቤት)

ምንጭ ናትናኤል መኮንን

 

Filed in: Amharic