>

ኳስ እና የ”ቦይኮት” ፖለቲካ (ክንፉ አሰፋ)

በዘንድሮው የሰሜን አሜሪካ እና የአውሮፓ ስፖርት እና ባህል ፌስቲቫሎች ላይ የቦይኮት (እቀባ)  ዘመቻዎች ተነስተው ነበር። የዘማቻዎቹን ውጤቶችም  አይተናቸዋል። በዚች አጭር ጽሁፌ የማተኩረው በውጤቶቹ ላይ አይደለም።  በሲያትሉም ሆነ በሮም ዝግጅቶች ላይ ስለነበርኩ፣   የቦይኮት ዘመቻዎቹ ከጅምሩ ጥቅም እና ጉዳቶችን አመዛዝነው ነበር ወይ የሚለውን በጥቂቱ ለመፈተሽ እሞክራለሁ። በዚህ ርዕስ ላይ ስጽፍ  አዋራ እንደሚነሳ አምናለሁ።  በጉዳዩ ላይ እጅግ ብዙ ሰዎች ሲወያዩ ብታዘብም በፍርሃት ይሁን በሌላ ምክንያት ሃሳባቸውን በአደባባይ ለመናገር ግን ሲደፍሩ አይታይም።    ሃሳባቸውን በድፍረት የሚሰነዝሩ ወገኖችም  ቦይኮት ስለሚደረጉው ብዙዎች ዝምታን ቢመርጡ አይደንቅም።  “አህያ የለኝ ከጅበ አልጣላ” ብሎ ሃሳቡን በነጻ ለመግለጽ የሚሞክር ደግሞ ይሰደባል።    በሳይበሩ አለም፣  ወቅትን እየጠበቀች  በምትነደው እሳት ላይ ማን ቤንዚን እንደሚጨምርበት አሁን ግልጽ ሆኗል። አንዳንዶቹን የቦይኮት ዘመቻዎች ማን እንደሚጠራው እንኳን አይታወቅም። ምክንያቱም ሃላፊነቱን የሚወስድ አካል ስም እና አድራሻ የላቸውም። አንድ ሾልኮ የወጣ መረጃ  የሚጠቁመን  ገዥው ፓርቲ ሰባት ሺ የሳይበር ላይ አጥቂዎችን የወር ደሞዝ እየከፈለ አሰማርቷል። …

ምስል – ፕሮፌሰር እንድርያስ እሼቴ at Kingstowne Starbucks @kinfu

በቨርጂንያ ግዛት በምትገኝ፣ ኪንግስታውን ስታርባክስ በራፍ ላይ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሼቴ  ሲጋራውን እንደ ሲኖ-ትራክ ጭስ እያቦነነ ተቀምጧል። የወቅቱ ሙቀት በጭስና በአልኮል ደከምከም ያለ ሰውነቱ ላይ ተጨምሮበት የሉሲን አጽም አስመስሎታል። ከሁለት ባለግዜዎች ጋር ጠቀምጦ ህወሃትኛ ወጉን በነጻነት ይሰልቃል – የሞት ሞቱን።  ከዚያ አለፍ ብሎ ያለው ሞል ውስጥም ሆነ ስቶር ገባን። እዚያ  የምናገኛቸው ሸማቾች ደግሞ (በሙሉ ማለት ይቻላል) ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ናቸው።  “የባለስልጣናቱ  ዘመድ አዝማዶች ” መሆናቸው ተነገረን።

በባንክ ብድር ሳይሆን ካሽ በማውጣት ዘመናዊ ቪላ ቤቶች የመግዛት አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያውያን ሚሊየነሮች።  የአካባቢው ነዋሪ እንደነገረን ከሆነ እነዚህ  ምንጩ ያልታወቀ ሚሊየነሮች ያንን መንደር ሁለት አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ነው ገዝተው የሰፈሩበት። በአሁኑ ሰዓት በዲሲ፣ በቨርጂንያ እና በሜሪላንድ ግዛቶች የመኖርያም ሆነ የንግድ ቤት አከራዮቹ እነሱው ሆነዋል። ልብ በሉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪ በአምስት ዓመታት ግዜ ዉስጥ ብቻ  ከኢትዮጵያ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ 10 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ወደ ዉጭ እንዲወጣ ነግረውናል።… ይህን ጉዳይ ለግዜው በዚህ ልተወውና ወደ ቦይኮቱ ልሂድ።…

“ይህንን ሰው (እንድርያስን) የዲሲው ግብረሃይል አለየውም እንዴ?” ሲል አብሮኝ ከነበሩት አንዱ ጠየቀ። የስርዓቱ ቀንደኛ አማካሪ በቨርጂንያ ግዛት ውስጥ በግላጭ ተገኝቶ በዋዛ እንደማይታለፍ ሁሉም የሚያውቀው ነው። እንድርያስ እሼቴ እንዲህ በግላጭ እና በነጻነት ያለምንም ተቃውሞ ተቀምጦ በመገኘቱ እድለኛ ነው።

ግብረሃይሉ  በ”ቦይኮቱ” ጉዳይ ላይ ተጠምዷል። በእርግጥም የኳሱ “ቦይኮት” ነገር ሁሉንም ወገኖች ያግባባ አልመሰለም። ምክንያቱም ፍትሃዊነቱ፣ አድሏዊነቱ እና የፖለካ ጠቀሜታው በአግባቡ መፈተሹ አከራካሪ ስለሆነ ይመስለኛል። ይቅርታ የሚጠይቁ አርቲስቶች አሉ፣ ይቅርታ የማይጠይቁ አርቲስቶችም አሉ፣  ይቅርታ ቢጠይቁም ተቀባይነት የማይኖራቸው አሉ… ።  የዚህን ጉዳይ ቅድመ-ሁኔታ እና መስፈርቱ እንዴት እና በማን እንደሚወጣ ግልጽ አይደለም። አልያም ሁሉንም የሚያግባባ አይደለም።  ቦይኮት (ማዕቀብ) የሰላማዊ ትግል  አንደኛው መንገድ ነው። ሁሉም ተሳታፊ ሲስማማበት፣ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ሲያመዝን እና ወቅቱን የጠበቀ ሲሆን ደግሞ በተግባር ሲተረጎም ውጤታማ ይሆናል።  ማን በምን መስፈርት ቦይኮት እንደሚደረግ ሕብረተሰቡ ተስማምቶ ሲፈቅድ እንጂ አንድ ቡድን በግል ጉዳይም ይሁን በቅናት ተነሳስቶ  ሲሰራው ችግሩ እዚያ ላይ ይሆናል። በአመክንዮ እንጂ  ከጥላቻ ለመሆኑ መስፈርቱ የሁሉምም ይሁንታ ሲያገኝ ይመስለኛል። ሃመልማል አባተ ይቅርታ ብላ ትቀላቀል ዘንድ፣ ፋሲል ደሞዝ ከራዳሩ ውጭ ይሆን ዘንድ፣ የአስቴር አወቀ ጉዳይ በዝግ ችሎት ይታይ ዘንድ… ከመድረክ ጀርባ ያሉ ጀብዱዎችን ታዝበናል።

Artist Gossaye Tesfaye

ጎሳዬ ተስፋዬ በስፖርት ፌዴሬሽኑ ለስራ ተጋብዞ የመጣ ድምጻዊ ነው። ጉዞው ግን ቀላል አልነበረም። አያሌ ውጣ ውረዶችን አልፎ ስራውን ለወገኑ ሊያሳይ ብቅ ሲል እመንገዱ ላይ የኬላ ፍተሻ ገጠመው። እዚያው ላይ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠው – አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለፈጸመው በደል ይቅርታ እንዲጠይቅ። ጎሳዬ ይህችን ትንሽ የ”እለት ጸሎት” አይነት ነገር ለማድረግ ምን ገዶት።  በመጀመርያ ለ”ይቅርታው” ሙሉ ፈቃዱን ገልጾ ነበር።  ከጥቂት ግዚያት በኋላ ያማከራቸው ወገኖቹ በጉዳዩ ሳይስማሙ ቀሩ።… አርቲስቱ  ሁለት አማራጭ ነበረው። ይህን አድርጎ ከአውሬዎች ጥርስ ውስጥ መግባት፣  ወይንም ደግሞ ይህንን ሳያደርግ የሚያገኘው ጥቅም መቅረት። ምርጫው ላይ ብዙም አላንገራገረም።   በመሪር ሃዘን ሁለተኛውን አማራጭ በመውሰድ አድናቂዎቹ ጋር ላለመገናኘት ወሰነ። እርግጥ ነው።   ይህ ድምጻዊ ወያኔ አይደለም። የስርዓቱ ደጋፊም አይደለም። ሙያውን ተገን በማድረግ  የዳሽን ቢራ ማስታወቂያ በሰሩ ሰዎች ሰለባ ግን መሆኑ አይካድም። “የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ” በሚል ለሕዝብ የላከው ደብዳቤ አንጀት ይበላል።  የገዛ ወገኖቹ በዚህ ሁኔታ ስራውን እንዳይሰራ ሲያደርጉት በጭንቅላቱ ምን ሊመላለስ እንደሚችል ለመገመት አያስቸግርም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎቹስ ስሜትም ግምት ውስጥ አልገባም።  እንዲህ እያልን…የሃገር ቅርስ የምንላቸውን፣ በሚሊዮን ሕዝብ ልብ ውስጥ ያሉ ወገኖችን እየገፋን ለወያኔ ጉልበት መሆናችንን የተገነዘብነው አይመስለንም።

ቦይኮቱን የሚጠሩት ወገኖች ከሃገርፍቅር ስሜት ወይንም በአገዛዙ የበደል  ስራ ላይ ካላቸው  የተነከረ አቋም የተነሳ መሆኑ ግልጽ ነው። ሕዝቡም ቢሆን በህወሃት የግፍ አገዛዝ ላይ ብሶት አለበት። ይህንን ብሶት ያንገፈገፈውን ህዝብ በስሜት በማንሳት ለተግባር (ሞብ) መጥራት እጅግ ቀላል ይሁን እንጂ  ሁሌ ጠቃሚ አይሆንም። ሞብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝንበት ግዜ ይኖራል። ለዚህ ነው የማህባራዊ ሳይንስ ጠበብቶች  የህዝብ ስሜት ብቻውን ሲሆን አደጋ እንዳለው የሚነግሩን።  ስሜት ከአመክንዮ ጋር ሲሆን ብቻ ነው ውጠታማ የሚሆነው።

ምስል: Kingstowne Villas Owned by TPLF @kinfu

በስርዓቱ አገልጋዮች እየተጫነ የሚመጣውን የጤፍ እንጀራ፣ ከጊዮርጊስ ቢራ ጋር እየኮመኮሙ፣ ድምጻዊ ላይ የ”ቦይኮት” ዘመቻ ማድረግ ግብዝነት አይሆንም?  የገዛ ወንድሙ በዳሽን ቢራ ፋብሪካ ተቀጥሮ እየሰራ – ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ላይ የሚደረገውን ቦይኮት እደግፋለሁ ማለትም ፍጹም ፍትሃዊነት አይመስለኝም። ስርዓቱ ላይ ባላቸው የጥላቻ ስሜት ብቻ የተነዱ ለሚያደርጉት ነገር ጥቅምና ጉዳትን ማመዛዘን የተሳናቸው በርካታ እንደዚህ አይነት ወገኖች አጋጥመውኛል።  ሁሉም በእውቀቱ መጠን ያስባል። ባሰበው መጠንም ስራውን ይከውናል። ለማወቅ ደግሞ መማር ብቻ አይጠቅምም። የሰው ልጅ ከትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን  ከስህተትም ይማራል።  የሌሎችን የመስማት ክህሎት ስናዳብር ደግሞ  መረዳትን እንማራለን።  በደንብ ስንረዳ ደግሞ ማመዛዘን እንጀምራለን።

በአሁን ሰዓት የቦይኮት ግዜያችንን በሌሎች ነገሮች ላይ ብናውል ሕዝባችንን የበለጠ እንጠቅም ነበር። ይልቅስ ቦይኮት መደረግ ያለባቸው በፌርፋክስ ኪንግስታውን  የተገነቡ የባለግዜዎቹ  ቪላዎች፣ የሚከራዩ ቪላዎች ላይ ነው። ቦይኮት መደረግ ያለበት ሕዝብ እየተራበ በባለግዜዎች ወደ ዲሲ እየተጫነ የሚመጣው እንጀራና የምግብ እህል ላይ ነው።

ቦይኮቱ ( እቀባው) እርባና ኖረውም፣ አልኖረው ሂደቱ ግን የተንሸዋረረ ስለመሆኑ ዳኛና ምስክር አያሻውም። ፖለቲካ መብት ነው፣ ፖለቲካ ግደታ ነው፣ ፖለቲካ ኢኮኖሚም ነው። ይህ ብቻ አይደለም። እኔ እስከሚገባኝ ፖለቲካ ሂሳብም ነው – ቀመር። ጠላትን የመቀነስ፣ መሃል ሰፋሪን የመደመር እና ወዳጅን የማባዛት ቀመር።  ይህ ሳይሆን ሲቀር ሁሉን እየገፋን መሃሉን ዳር ከማድረግ በቀር የምንጨምረው አይኖርም።

ESCFE festival Rome- Italy, 2017 picture @kinfu

15ኛው የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ዝግጅት በሮም ላይም የቦይኮት ዘመቻ ተከፍቶ ነበር። ለዚህ ዘመቻ ሃላፊነቱን የወሰደውን አካል ለማግኘት ግን ከባድ ሆኗል።  በፌዴሬሽኑ ዙርያ ያለው ችግር በግልጽ ይታወቃል።  የሮም ለዝግጅቱ መመረጥ፣ የስፖንሰሮች አጠያያቂነት፣   ያለፈው አመት ክስረት፣ እዳ እና እዳውን ለመሸፈን የተገባው ቃል – የአመራሩ ምላሽ፣   የጀርመን ክለቦች ቅሬታ እና  የነበሩ ውይይቶች …  ወዘተ መጨረሻቸው ውጠት ባያመጣም ከፍተኛ ቅሬታ እንጅ ቦይኮት የጠራ ወገን ግን አልነበረም። ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ አካሄድ ፌዴሬሽኑን አደጋ ላይ ይጥለዋል።   ይህንን ጉዳይ ከጅምር እስከፍጻሜ ስለማውቀው እና ከሁለቱም ወገኖች ጋር የመውያየት እድሉ ስለነበረኝ ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ።  ግና ዝግጅቱ በዋያኔ ተጠልፏል የሚለው መግለጫ ከየትኛው ጫፍ ተነስቶ የት እንደደረሰ ግልጽ አይደለም። በሁሉም ወገን ያለውን ጉዳይ በጥልቅ ለምናውቀው ግን ይህ መግለጫ ፍጹም ክእውነት ያራቀ ነው። እርግጥ ነው የገዥው ፓርቲ አካላት ይህንን ኢትዮጵያዊ ተቋም ቢቻል ለመቆጣጠር  አለበለዚያም ለማፍረስ ጥረታቸውን አላቋረጡም።  አጣብቂኙ ደግሞ ለዚህ አመቺ ይመስላል።   ከዚህ በኩል በደካማ ጎን (እዳ መሸፈን)  ለመግባት ይሞክራሉ፣  ከዚያ በኩል ደግሞ በ”ቦይኮት” ተቋሙን ይገፋሉ።  ተቋሙን ሊቆጣጠሩ ወይንም ሊያፈርሱ የሚዳዱትን ማስወገድ የሚቻለው  በቦይኮት ሳይሆን በመጋፈጥና በመነጋገር ብቻ ነው። ይህንን ሊያደርጉ የሚችሉ ብርቱ ልጆች ደግሞ አሉ።  ማን እንደጠራው ያልታወቀው ቦይኮት ግን  ውጤት ባይኖረውም ፈተናው እና ግፊቱ ግን ቀላል አልነበረም። የአመራሩ አባላትም በበጎ ፈቃድ የሚያገለግሉ ሰዎች ናቸውና ይደክማቸዋል።  የተሸከሙት ሃላፊነት ግን ቀላል አይደለም።   በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አልፈው ዝግጅቱን በማካሄዳቸው መደነቅ ይገባቸዋል።  ፌደሬሽኑ ክለቦቹን ሁሉ ሰብስቦ ችግሮቹን በግልጽ ውይይት እንደሚፈታ ፕሬዝዳንቱ  ያምንበታል – ይህንንም ያደርገዋል።

በስም እና በአድራሻ የማይታወቁት አድማ ጠሪዎች  የሚናገሩት በመረጃ የተደገፈ ከሆነ ራሳቸውን መደበቅ አያስፈልጋቸውም።  ጥረታቸው መፍትሄ ለማግኘት ከሆነ ደግሞ በቅድሚያ በራስ መተማመን ይኑራቸው።  ያለበለዚያ የተያያዙት ጉዳይ  ስም ከማጥፋት የዘለለ አይሆንም። ያ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም።

የአንዳንዶቹን አካሄድ በደንብ ላጤነው የሌዊስ ካሮልን “አሊስ ኢን ዘ ወንደር ላንድ” አስተምሮት ያስታውሰኛል። አሊስ እና ድመትዋ መንገድ ላይ ተገናኙ።

“የት እየሄድሽ ነው?” አለቻት ድመት አሊስን።

አሊስ መልሳ ጠየቀች፣  “የትኛው መንገድ ይወስደኛል?”

“የምትሄጂበት መንገድ ይወስነዋል”

“የት እንደምሄድ አላውቀውም”

“የምትሄጂበትን ካላወቅሽ ሁሉም መንገድ ይወስድሻል”

እርግጥ ነው። የት እንደሚሄድ የማያውቅ ሰው መንገድ መጠየቅ የለበትም። መድረሻውን ስለማያውቅ-ሁሉም መንገድ ያስኬደዋል።  ቀይም ይሁን ቢጫ መስመር  ሳይሰመርላቸው የሚደራጁም እንዲሁ የሚጓዙበትን  መስመር አያውቁትም። በይሁንታ ይፈጠሩና  ጡንቻ ሲያወጡ በራስ እግር ቆመው መስመሩን ያልፉታል።  የናይጄሪያው ቦኮ ሃራም እና የአልቃይዳው ቢን ላደን እዚህ ላይ የሚጠቀሱ ናቸው።   በምእራብ አፍሪካ በከባድ ፍጥነት እያደገ የመጣው ቦኮ ሃራም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም ናይጀሪያ ውስጥ ነው የተፈጠረው።  አደገኛ አሸባሪ የሚባለውን ይህንን ድርጅት መሃመድ የሱፍ ሲፈጥረው መስመር አላበጀለትም ነበር። አላማው ግልጽ አልነበረም። በደፈናው የብሪቲሽን ዘመናዊ ትምህርት ለመቃወም ተብሎ ነበር የተመሰረተው።  እንደዋዛ ተለቀቀና ጡንቻውን አፈረጠመ።  አሁን አሁን የገዣ መሪውን ገድሎ የወለደች ልጅዋን እንደምትበላ ድመት ስርዓተ መንግስቱን እየበላው ነው:: ለናይጄሪያ ትልቁ ጠላቱ ራሱ ፈጥሮ እጉያው ውስጥ ያኖረው ነው።  በ17ኛው ምዕተ አመት ፈረንሳይን ለ72 አመታት የገዛው ንጉስ ሉዊስ (አስራ አራተኛ) ቀስ በቀስ እየተጓዘ ተሰሚነቱ እንደጨመረ  ‘L’etat c’est moi’ (‘I am the state’) “መንግስት እኔ ነኝ” በማለት ነበር በሃገሪቱ ፍጹም ወሳኝ ሊሆን የበቃው። በእርግጥ ይህ በአሁኑ ዘመን የሚታሰብ አይደለም።

ይቀጥላል….

Filed in: Amharic