>
5:13 pm - Sunday April 19, 4026

ከድሉ ባሻገር! (ዘውድአለም ታደሰ)

(ለሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን
ማስታወሻ ትሆን ዘንድ የተፃፈች)

poet-laureate-tsegaye-gebremedihn

አላጋጩ አይኔ፣
ከታሪክ ገፅ ላይ ስላቅ እያሰሰ
ፌዘኛው መዳፌ፣
ከትናንት ድርሳን ላይ አሽሙር እያፈሰ
ባባቱ ሲቀልድ፣
ባያቶቹ ሲያሾፍ ፣
ተጉዞ ….. ተጉዞ «አድዋ» ደረሰ!

አድዋ!

ፊደላቱ ሁሉ ስእል እየሆኑ
ያሳዩኝ ጀመረ ታሪኬን አጉልተው
“ሎሬቱ” በብእር፣
ትናንቴን አምጥቶ ፣ ዛሬ ላይ ጎለተው!

አድዋ!

ባባቶቹ ሩጫ፥
መሳቅ የለመደው ፥ ዘመንኛው ጥርሴ
በከንፈሮቼ ስር ፥ መሸሸግን ሲሻ ፥ ገረመኝ ለራሴ!
ሳቅ ይፈጥራል ያልኩት ፥ ያያቶቼ ጀብዱ
ለፌዘኛ አይሆንም፣
በደም ተቀብቷል ፣ ተጋርዷል መንገዱ!

አድዋ!

ሎሬቱ ይፅፋል ፣
ይፅፋል ፣ ይፅፋል
ያባቶቹን ወኔ ፥
በጥበብ ለማስፈር ፥ ብቻውን ይለፋል
ከፊደል ሲታገል ፥
ግዜም እንደነፋስ ፥ በፍጥነት ይከንፋል!

ሱሌኦ ያ ሱሉ ሱሌኦ

«እምቢ አለ ፥ ምኒሊክ እምቢ አለ
ብረት እያማታ፣
ብረት እያጋጨ፣ ጦሩን በሳት ሳለ!
እምቢ አለ!
ምኒሊክ አልታለል አለ
ዳኘው አባ ጎራ
የደጀን ተራራ
አፍሪካን ፣
ኢትዮጲያን ፣ እስከሰሜን ጣራ
በአለም ሊያኮራ
እምቢ አለ ምኒሊክ
ሱሌኦ ያ ሱሉ ሱሌኦ!»

ከነጭም የነጣ ፥
ብራና ጨብጦ ፥ ሎሬቱ ተቆጣ
በላዩ ደርቦ ፥ ያባቶቹን እልህ ፣ ያባቶቹን ቁጣ!

ለሳቅ አይመችም ፥ የገለጥኩት ዶሴ
እንደመሸገ ነው ፥ አልስቅ አለኝ ጥርሴ!
ያዝናናኛል ያልኩት ያያቶቼ ጀብዱ
ፌዘኛ አያስኬድም፥
በአጥንት ታጥሯል ፣ ተጋርዷል መንገዱ!

«በቃ!»
አለች ጣይቱ
አንቶሎኒን አይታ
ብርቅ አይደለም ለኛ
መውጣት ቀራኒዮ መውረድ ጎለጎታ
በቃ!
የነጩን ድንፋታ ፥ በወኔዋ ካደች
የነጩን ከፍታ ፥ በኩራቷ ናደች
እንደእሳት ነድዳ ፥ ጣይቱ ፎከረች
«እግሩን ለሹል እሾህ ፣ ደረቱንም ለጦር
ለሀገሩ ማይይሰጥ፣
አንድም ኢትዮጲያዊ ፣ እዚህ እንደማይኖር
እወቅ አንቶሎኒ
ስማችሁ ራሱ ፥ ውል የለሽ ፥ ውል አልባ
ምኒ ምኒ ምኒ!»

ለካስ እቺ ሐገር
በተረት ላይ ብቻ ፥ ፀንታ አልቆመችም
ጎበዝ ምን ይሻላል?
የአድዋ ታሪክ ፥ ለሳቅ አይመችም!
ሳቅ ይፈጥራል ፥ ያልኩት ያያቶቼ ጀብዱ
ፌዘኛ አያስኬድም፥
በአጥንት ታጥሯል ፥ ተጋርዷል መንገዱ!

አድዋ!

ያለእግር ጠፈር፣
ነጠላ አጣፍቶ ፥ ሊሞት ቤቱን ለቅቆ
የሐበሻ ሬሳ ፥ ይታያል ፈራርሶ ፥ እዚያም-እዚም ወድቆ
አዋራው ይቦንናል ፥ በደም ተቀይጦ ፥ ከደም ተደባልቆ!

ያስፈራል አድዋ!
የፈረሱ ኮቴ ፥ የብረቱ ፍጭት ፥ የቁስለኛው ዋይታ
ሐበሻ ባንድ ላይ፥
ተሰቅሏል ላገሩ ፥ ይኸው ቀራኒዮ ፥ ይኸው ጎለጎታ!
ይኸው የሾህ አክሊል ፥ እነሆ ሚስማሩ
እልፍ ጀግና ወድቋል ፥ ተሰቅሏል፣ ለክብሩ!

እየተፃፈ ነው ፥ በኢትዮጲያ ሰማይ ፥ የሐበሻ ጀብዱ
ለፌዘኛ አይሆንም ፥ በደም ተለቅልቋል ተጋርዷል መንገዱ!

እዚም-እዚያም ፥ ወድቋል የሀበሻ ገላ
ወደፊት ነው እንጂ፣
ማፈግፈግ ነውር ነው ፣ መሸሽ ወደኋላ!

ገበየሁ ወደቀ ፥ ጀግናው ክንዱ ዛለ
ደሙን ሚመልሰው፥ ያ ባልቻ የታለ?
«ባልቻ ሳፎ ኢርጋና
አባ ነፍሶ ያባ ጤና
አካና ታሲፍ ቲካ አካና
ገበየሁ ወድቋል ቶሎ ና!»

«እንዲህ ነች ሐገርህ»
ብሎ ተረከልኝ ፥ሎሬቱ በመንፈስ
ቀለም ደፍቶ አሳየኝ ፥
ሐበሻ ሲታረድ ፥ ላ’ገር ደሙን ሲያፈስ!
ለክብሩ ሲዋደቅ፥
እንደበግ ሲሸለት ፥ ለነፍሱ ሳይሳሳ
ይህ ሁሉ ለኔ ነው ፥
ይህ ሁሉ ግብ-ግብ ፥ ይህ ሁሉ አበሳ
ደልቶኝ እንድራመድ ፥ እርጥብ አፈር ሆኗል ፥ ያያቶቼ ሬሳ!

ይፅፋል ሎሬቱ ያባቶቹን ወኔ
ታሪክን ያትማል ፣ ያስቀምጣል ለኔ!
ለሳቅ አይመችም ፥ የገለጥሁት ዶሴ
እንደመሸገ ነው ፥ አልስቅ አለኝ ጥርሴ!

ወደኋላ ዞሬ ፥
አንድ ሁለት እያልኩኝ ፥ ጀግኖቹን ስቆጥር
ከሩቅ አይሃለሁ!
ፊደላትን ቀርፀህ ፥ ልቤ ላይ ለመትከል ፥ ብቻህን ስትጥር!

እልፍ ህይወት ተከፍሎ ፥
ሐበሻም ድል አርጎ ፥ ጦርነቱ አልቋል
ከድል ባሻገር ግን፥
ከፊደል ሲታገል ፥ አንድ ጀግና ወድቋል!

Filed in: Amharic