>
5:13 pm - Saturday April 19, 7862

ከእስር “ተፈተዋል” የተባሉ የቀድሞ እስረኞች የት ናቸው? [ማህሌት ፋንታውን -ዞን 9]

by-mahilet-fantahun-zone-9ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት ብቻ የፈጠራ ክስ ተመስርቶባቸው በነፃ ወይም ክሳቸው ተቋርጦ ወይም የተፈረደባቸውን ጨርሰው የሚወጡ የቀድሞ እስረኞችን (እራሴን ጨምሮ) ሳስብ የሚሰማኝን ስሜት በትክክል ለመግለፅ ቃላቶች አላገኝም። እልህ፣ ቁጭት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ አቅም ማጣት፣ሌላም ሌላም የተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ይከተኛል። “ከእስር ወጥተዋል” ቢባልም ቅሉ ህይወት ከእስር በፊት እንደነበረው ሊሆን አይችልም። ከማህበራዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና (አካላዊ እና አእምሯዊ) ችግሮች ጋር መላተም አይቀሬ ነው። ከእስር ከወጣሁ በኋላ ያለፈውን የእስር ህይወቴን የሚያስመኙኝ ክስተቶች/አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። በእርግጥ መከራ በበዛ ቁጥር በድል የምንወጣበትን መንገድ የማሰብ ችሎታችን እንደሚጨምር እና እንደምንወጣውም አምናለሁ። ይሄ ሁሉ መንደርደሪያ ከእስር “ተፈተዋል” የተባሉ የቀድሞ ጥቂት እስረኞችን ወቅታዊ ሁኔታ ለማሳየት ነው።

የዩንቨርስቲ ተማሪዎች

መገርሳ ወርቁ በ2006 ሚያዚያ ወር ከሚማርበት የሃረማያ ዩንቨርስቲ በሽብር ተጠርጥሮ ሲታሰር የ5ኛ አመት የህግ ተማሪ ነበር። ማእከላዊ ከመግባቱ በፊት ሆነ በኋላ ያልሰራውን ወንጀል እንዲያምን አሰቃቂ ድብደባ ተፈፅሞበታል። ሁለት አመት ከ4ት ወር በላይ ክሱን በእስር ሆኖ ከተከታተለ በኋላ ተመስርቶበት ከነበረው የሽብር ክስ “ነፃ“ ተብሏል። ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከእስር ተለቆ ሲወጣም በር ላይ የተቀበለው መልሶ ወደ ማእከላዊ የሚወስደው መኪና ነበር።ለሳምንት በማእከላዊ ዛቻና ማስፈራሪያ ተሰጥቶት ነው የወጣው። ከክሱ ነፃ ተብሎ ይውጣ እንጂ ከእስር ወጥቶ ከቀድሞ ህይወቱን መቀጠል አልቻለም። ትምህርቱን ለመቀጠል ቢጠይቅም አልተሳካለትም። ትምህርቱን አጠናቆ እራሱን፣ ቤተሰቡን እና ሃገሩን የሚረዳበት ጊዜ የወራት እድሜ ሲቀረው ያልጠበቀው እስር ገጥሞት ተስፋ ካደረገው ህይወት ተለያየ።
ሌንጂሳ አለማየሁ [የጅማ ዩንቨርስቲ ተማሪ የነበረ 1 አመት ከ 8ወር በላይ ታስሮ “ነፃ“ የተባለ]፣ ተሻለ በቀለ [የጅማ ዩንቨርስቲ ተማሪ የነበረ ለሁለት አመት ያክል የታሰረ ፤ የ1 አመት ከ6 ወር የተፈረደበት] እና አዱኛ ኬሶ [የአዳማ ዩንቨርስቲ ተማሪ የነበረ የ4ት አመት ከ5ወር ፍርድ ጨርሶ የወጣ]። ሁሉም ከመገርሳ ጋር በተመሳሳይ ወቅት ታስረው በአንድ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ ናቸው። ማእከላዊ ከመግባታቸው በፊት የነበሩበትን ማሰቃያ ቦታ እንደማያውቁት የሚናገሩት እነዚህ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች፤ በሃይል ያልፈፀሙትን ፈፅመናል እንዲሉ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል። ከአዳማ ዩንቨርስቲ ተይዞ የታሰረው አዱኛ ኬሶ እኛ ሲኦል ወደምንለው ማእከላዊ ሲገባ ከነበረበት ቦታ ሲያነፃፅረው ገነት የገባ እንደመሰለው ይናገራል። እንዲሁም አዳማ ላይ አብሮት ታስሮ የነበረ ጓደኛው ከነበሩበት የማሰቃያ ቦታ ወደ ማእከላዊ ሲያመጧቸው በድብደባ ብዛት በመድከሙ ሞቷል ብለው መንገድ ላይ ሲጥሉት አይቷል።
በአሁን ሰአት አራቱም ከእስር ቢወጡም ይማሩበት ወደ ነበረው ዩንቨርስቲ ተመልሰው ትምህርታቸውን ለመቀጠል ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካላቸውም። ተመልሰው የቤተሰቦቻቸው እና የጓደኞቻቸው ጥገኛ ሆነዋል።

ሠራተኞች

ከእስር ሲወጡ ወደ ቀደመ ህይወታቸው መመለስ የማይችሉ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ብቻ አይደሉም። በስራ አለም የነበሩም ተመሳሳይ ችግር ይገጥማቸዋል። የቀድሞ አሰሪ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ አለመፍቀድ (አስፈላጊውን ካሳ ከፍሎም ሆነ ሳይከፍል)፣ አዲስ ቀጣሪ አለማግኘት፣ የጤና እና ተያያዥ ተስፋ አስቆረጭ ችግሮች ይጋረጡባቸዋል።
በማእከላዊ በደረሰበት ድብደባ አንድ ጆሮው እንዳይሰማ የሆነው የዞን9ኙ ጦማሪ አቤል ዋበላ የቀረበበትን የሽብር ክስ ለአንድ አመት ከ6ወር በእስር ሆኖ ሲከታተል ቆይቶ በጥቅምት ወር 2008 “ነፃ” ተብሎ ከእስር ወጥቷል። ከፍርድ ቤት ነፃ የተባለበትን ማስረጃ ይዞ ይሰራበት ወደነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መስሪያ ቤት ሲሄድ ያልጠበቀው ነገር ገጠመው። ከስራ መባረሩን እና መመለስም እንደማይችል ይነገረዋል። 1አመት ከ6ወር ያለምክንያት ታስሮ ሲመለስ ካሳ ከፍሎ ስራውን ማስቀጠል የነበረበት መስሪያቤት እንዳባረረው በመግለፅ ስልጠና ወስዶ ግዴታውን አልተወጣምና እዳውን ይክፈል በሚልም ክስ መስርቶበታል።

ተስፋዬ ተካልኝ በ1998 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ ከተመረቀ በኋላ በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር እስከ ሚያዝያ 2003 ሲሰራ ነበር። ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ባላወቀው ምክንያት በመንግስት ደህንነት ሀይሎች ተያዞ ለ23 ወር በእስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ እየተፈፀመበት መቆየቱን፣ በእስር በቆየባቸው ጊዜያት ፍርድ ቤት አንድም ቀን ቀርቦ አለማወቁን መጋቢት 26 ቀን 2005 ከእስራት ከተለቀቀ በኋላ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ እንደሚከተለው ገልፇል።

“ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ በኤሌክትሪክ ጀርባዬ ላይ አቃጥለውኛል፣ በብልቴ ላይና በኩላሊቴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱብኝ ሽንት ችዬ አልሸናም፣ ሽንቴን መቆጣጠርም አልችልም፡፡ ኩላሊቴንም በጣም ያመኛል፡፡ ውሃ ውስጥ እየነከሩ በጣም ደብድበውኛል፡፡ አሁን ስናገር ያመኛል ብዙ አይነት የድብደባና የስቃይ መአት ደርሶብኛል፡፡

ተስፋዬ በ2005 ከእስር ከወጣ በኋላም በ2007 ለአጭር ጊዜ ታስሮ የነበረ ሲሆን፤ በ2008 በነበረው ተቃውሞ ተይዞ ከባድ ድብደባ ተፈፅሞበታል። ወደ ቀድሞ ስራው ለመመለስ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት የሚናገረው ተስፋዬ መስሪያ ቤቱ የስራ ልምድ ሊፅፍለት ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልፆለታል። በአሁኑ ሰአት ኩላሊቱን በመጠኑ የተሻለው ቢሆንም ጤናው ሙሉ ለሙሉ አልተመለሰለትም፤ ጉሮሮው ላይ የሚሰማው ህመም ምግብ መብላት እስኪያቅተው እያሰቃየው ነው።
ጥቂቶችን ለማሳያ ያክል አነሳሁ እንጂ ሁሉም የህሊና እስረኞች ከእስር ሲወጡ ዘርፈ ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል። የጤና ችግር [አካላዊ እና አእምሯዊ] ፣ ወደ ቀድሞ ስራ ወይም ትምህርት መመለስ አለመቻል፣ አዲስ ስራ አለማግኘት፣ እታሰራለሁ የሚል ስጋት፣ የደህንነት ማስፈራሪያ፣ ዛቻ እና ክትትል፣ ዳግምኛ እስር፣ የጓደኞች እና ወዳጆች መሸሽ እና መሰል ችግሮች። በርግጥ ከእስር በወጡ ግለሰቦች ዘንድ ይብሳል እንጂ ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት ብቻ ከትምህርት እና ከስራ ገበታቸው የሚፈናቀሉ፣ የደህንነት ማስፈራሪያ፣ ዛቻ እና ክትትል የማይለያቸው፣ ከተከራዩበት ቤት የሚባረሩ፣ ቤት የሚያከራይ ያጡ እንዲሁም እታሰራለሁ በሚል ስጋት ውስጥ በሃገራቸው በሰቆቃ የሚኖሩትን ቤቱ ይቁጠራቸው።

Filed in: Amharic