>
5:13 pm - Tuesday April 18, 1578

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የአፍሪካ አንድነት (ሔኖክ ያሬድ)

haile_selassie_is_speech_on_the_bible‹‹ሐምሌ ሐምሌ ሐምሌ 16 ተወለደ ጠቅል›› ከ42 ዓመታት በፊት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ልደት አስመልክቶ የሚዜም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ከብሔራዊ በዓላት አንዱ ሆኖ መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ዝግ የሚሆኑበት ንጉሠ ነገሥቱ በሐረርጌ ኤጀርሳ ጎሮ ሐምሌ 16 ቀን መወለዳቸውን በማመልከት ነበር፡፡

ለስድስት አሠርታት ግድም (ከ1909 እስከ 1967 ዓ.ም.) ከአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንንነት እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴነት ኢትዮጵያን የመሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ በአፍሪካ አንድነት መሥራችነትና አባትነትም ይታወቃሉ፡፡ ከ16 ዓመታት በፊት አፍሪካ አንድነት ድርጅትን (አአድ) የተካው የአፍሪካ ኅብረት በቅርቡ ባካሄደው 29ኛው የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ በሚገኘው የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት ሐውልታቸው እንዲቆም መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ከዓመታት በፊት የጋናው ፕሬዚዳንት ለነበሩት ክዋሜ ንኩሩማ ብቻ ሐውልት መቆሙ በተለያዩ መልክ ትችት ሲቀርብበት የነበረው ኅብረቱ ለተነሳበት ጥያቄ ዘንድሮ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት››

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) በ1955 ዓ.ም. የአአድ መሥራችና አባቱም የሆኑለት ከድርጅቱ ዋናዎቹ አንቀሳቃሾች አንዱ እንደነበሩ ምስክርነት የሰጠው የጋናው ዘጋኔያን ታይምስ በጁላይ 24፣ 1972 (ሐምሌ 17 ቀን 19614 ዓ.ም.) ዕትሙ ነበር፡፡

የናይጄሪያው ሳንዴይ ኦብዘርቨር ቀኃሥ 80ኛ ዓመታቸውን ባከበሩበት ሐምሌ 16 ቀን 1964 ዓ.ም. (ጁላይ 23፣ 1972) ባወጣው ዕትሙ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት ኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› (Haile Selassie I of Ethiopia: Father of The O.A.U.) በሚል ርዕስ ሐተታ አውጥቶ ነበር፡፡

እንደ ሰንዴይ ኦብዘርቨር አገላለጽ፣ ቀኃሥ ስለ አፍሪካ ያላቸው ውጥን እጅግ በጣም የተዋጣና የተቃና መሆኑን ጠቅሶ፣ አዲስ አበባ ‹‹የፓን አፍሪካን መዲና›› (የአፍሪካ አንድነት ከተማ) ለመባል የበቃችበትን ምክንያት አስታውሶ ነበር፡፡

‹‹የዚህ ምክንያት አስቀድሞ የአፍሪካ አገሮች በሞላ የተገኙበትና እንዲሁም ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም ውሳኔ የተላለፈበት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ በ1955 ዓ.ም. የተያዘው አዲስ አበባ ላይ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህም በላይ በይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ኢትዮጵያ የእንግሊዝኛን ወይም የፈረንሣይኛን ቋንቋ ዓይነተኛ አድርጋ አለመውሰዷ ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ውስጥ እጅግ ረዥም የሆነ የነፃነት ዘመናት ያላት አገር ናት፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት በፊት የአፍሪካ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ውስጥ ተቋቀሞ ነበር፡፡ ዳሩ ግን በራሴ አስተያየት ንጉሠ ነገሥት የመናገሻ ከተማቸው የአፍሪካ አንድነት ከተማ እንድትሆን ባይተጉበት ኖሮ እነዚህ የተዘረዘሩት ጉዳዮቸ ምንም ለውጥ ባላስከተሉም ነበር፡፡

‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም የአፍሪካ ኃይሎች ራሳቸውን ለመከላከል ይተባበሩ ዘንድ ግርማዊ ጃንሆይ ባላቸው እምነት መሠረት ፈቃዳቸውን ከግቡ ማድረሳቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ በዚህም እምነት መሠረት፣ በየትኛም የአህጉሩ ክፍል አምባጓሮ ቢነሳ ተገቢው ስምምነት እንዲፈጸም ግርማዊነታቸው ዓይነተኛ መድኅን ሆነዋል፡፡ በዚህም መሠረት የናይጄሪያ ችግር በተፈጠረበት ጊዜ የአስታራቂነት ዕርምጃ የወሰዱ ሲሆን ይህም ፍጻሜ እንዳገኘ በችግሩ ምክንያት አለመግባባት የተፈጠረባቸውን አፍሪካውያን መሪዎችን ፈጥነው ለማስማማት ችለዋል፡፡ ከዚህ በስተቀር ጃንሆይ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ድርጅት ጋር በመተባበር የወጠኑት ከባድ ሥራ 16 ዓመታት የፈጀውን የሱዳንን ችግር በማስወገድ በቅርቡ አንድ ታሪካዊ ስምምንት እንዲፈጸም አስችሏል፡፡

ግርማዊነታቸው ሴኔጋልና ጊኒ አለመግባባታቸውን ለማስወገድ በተስማሙበት ይኸውም በላይቤሪያ ዋና ከተማ በሞንሮቪያ ውስጥ በተደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ሊቀ መንበር ሆነው መርተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀደም ሲል ጀምሮ የታሪክ ሥፍራቸውን መያዛቸው ጉልህ ነው፡፡

‹‹በውጩም ዓለም ቢሆን አፍሪካ ግንባራቸው ሳይታጠፍ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከእስያ መሪዎች ጋር ለመቋቋም የሚችሉ ከፍተኛ መሪዎች ያላት መሆኑን ግርማዊ ጃንሆይ በሚገባ አስመስክረዋል፡፡ ይልቁንም የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መፈጠር፣ ቀደም ብለው እንደነበሩት እንደቸርችል፣ ኔህሩ፣ ቶማስ ጀፈረሰንና እንደሌኒንን ሁሉ የሰውን ልጅ ዕድል ለማሳደግ የረዳ መሆኑ አሁን ጃንሆይን ሊያረካ የሚችል ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ጋዜጦች በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛና ጣሊያንኛ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ ፕሬስ ክፍል ከ1957 እስከ 1966 ዓ.ም. ይታተም የነበረው መጽሔት የቀኃሥን ተግባሮች መዘከሩ ይታወቃል፡፡ አንዱ የጠቀሰው ለንደን ታይምስ (The Times London) በጁላይ 22፣ 1972 (ሐምሌ 15 ቀን 1965 ዓ.ም.) ዕትሙ፣ ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጽኑ ሥልጣን በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ታፋሪነትን አትርፎላቸዋል›› (Emperor’s firm authority earns respect among the Leaders of Africa) በሚል ርዕስ ሐተታውን አስፍሮ ነበር፡፡

‹‹ኢትዮጵያን ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰውነትና ክብር ጋር የተያያዘ በአፍሪካ ውስጥ ከሁሉም ልቆ የሚገኝ አቋም አላት፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የአፍሪካ መሪዎች ተቀዳሚ መሪ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያን ከኢጣሊያውያን ወራሪዎች ነፃ ለማውጣት ያደረጉት ተጋድሎም የዘመናዊቷን አፍሪካ ልደት የሚያበስር ነው፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ እንድትሆን ተመርጣለች፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኢትዮጵያ ስለአፍሪካ ሕዝብ የፖለቲካ ደኅንነት ላላት ተቆርቋሪነት ጉልህ ምልክት ነው፡፡ ድርጅቱ የተቃቋመውም በድንገት ከተፈጠረ ስሜት አልነበረም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በእርጋታና አንዳንድ ጊዜም በግላቸው የአፍሪካ አገሮች ገና ነፃነታቸውን ሳይጎናጸፉ የወደፊት መሪዎች ለሚሆኑት ሰዎች የትምህርትን ዕድል በመስጠት ረድተዋል፡፡ ግርማዊነታቸው በአፍሪካ አህጉር ያላቸው ተሰሚነት አገራቸው ከድንበሮቿ ውጭ ካላት ተሰሚነት የተገኘ ሳይሆን ንጉሠ ነገሥቱ ካተረፉት የመከበር ዕድል ነው፡፡

‹‹የብሔራዊና የኢንተርናስዮናል መሪ መሆን ጥቅም ሊኖረው ይችላል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበርነት በየዓመቱ የሚለወጥ ነው፤ ነገር ግን የፈረስ ኮቴ በሚመስለው የጉባዔ ጠረጴዛ አባል አገሮች ሲቀመጡ የኢትዮጵያ ሥፍራ ከጠረጴዛው ጫፍ በመጀመሪያ ላይ ሲሆን፤ ንጉሠ ነገሥቱም በጉባዔዎቹ ሁሉ በሰፊው ይሳተፋሉ፡፡ በሰሜንና ደቡብ ሱዳን ግዛቶች መካከል ለብዙ ዓመታት የቆየውን ግጭት ከፍጻሜ ለማድረስ በቅርቡ ለተደረገው የሰላም ንግግር የተመረጠችው አዲስ አበባ ነበረች፡፡

‹‹በአብዛኛው የአፍሪካ ክፍል የጎረቤት አገሮች ግንኙነቶች ውስብስብ ከሆነ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለኡጋንዳ፣ ኬንያና ታንዛኒያ የጋራ አገልግሎት የሚውለው በእንግሊዝ አስተዳደር የተጀመረው የምሥራቅ አፍሪካ ኮሚኒቲ አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ ከዚሁ የተለየ ራሱን የቻለ ነው፡፡

‹‹እንደዚሁም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፖለቲካ የተከፋፈሉ ሁለት ወገኖች ከሆኑት የእንግሊዝኛና የፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች ከቶውንም ወገን ለይታ አባል ሆና ስለማታውቅም ከሌሎቹ የምትለይበት ራሱን የቻለ አቋም አላት፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በማንኛውም አከራካሪ ጉዳይ ገለልተኛነቷን ጠብቃ መሸምገል ትችላለች፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ የሆነበትም ምክንያት የአገሪቱ ከማንኛውም ወገን ነፃ የሆነ ይዞታ ነው፡፡

‹‹ንጉሠ ነገሥቱ በአፍሪካ የፖለቲካ ንቅናቄ ግንባር ቀደም ሆነው እንዳሉ ናቸው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ባለፉት አሥር ዓመታት [ከ1955 እስከ 1965 ዓ.ም.] በሚገባ ከመርዳታቸውም በስተቀር በአፍሪካ የቀረውን የአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ርዝራዥ በተለይም የፖርቱጋልን የአፍሪካ አገሮች ቅኚ ገዥነት በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡

ከ45 ዓመት በፊት ለፊጋሮ-ፓሪስ (Le Figaro-Paris) የተሰኘ የፈረንሣይ ጋዜጣ በፈረንሣይኛ በነሐሴ 1 ቀን 1964 ዓ.ም. (8 Aout, 1972) ዕትሙ ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰማንያኛ የልደት በዓላቸውን ያከብራሉ›› (Hailé Sélassié, Vient de fêter ses 80 ans.) በሚለው ርዕሱ መንደርደርያ ያደረገው እንዲህ ነበር፡፡

‹‹ትልቁ አንበሳ ደስ ስላለው አገሳ፡፡ ጠባቂው ልዩ የተቆረጠ ሙዳ ሥጋ በአሉሚኒዬ ሣህን አመጣለት፣ ግርማዊ ጃንሆይ ከዚህ አንድ አንዱን እያነሱ ሰጡት፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀጥለው በእጆቻቸው ጎፈሩን ደባበሱት፡፡ የፊታቸው ገጽ ብሩህ ነው፡፡ አንበሳውን ተናግረውት ድምፃቸውን አሰሙት፡፡ በመጨረሻም ግርማዊነታቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው መለስ ብለው አጭር መሪ ቃል ነገሯቸው፡፡

‹‹ግርማዊ ጃንሆይ፣ እነዚህ አንበሶች በቤተ መንግሥትዎ መዝናኛ አትክልቶች ውስጥ፣ የግርማዊነትዎ በሆኑ አርማዎች ውስጥ፣ ለክብር ዘበኞች እንደ መልካም ዕድል፣ ለብሔራዊ የአየር መንገድ ኩባንያ ደግሞ ሕያው ማስታወቂያ እየሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው እንዲህ የሚታዩበት ምሳሌ ትርጉሙ ምንድር ነው?

እንደሚያስረዳውም ድል አድራጊ አንበሳ የአገራችን አምሳል የነፃነት ምስያ ነው፡፡››

ኪንና ባህል

Filed in: Amharic