>

ሦስተኛዋን ‹‹እሁድ››- በአራዳ ምድብ ችሎት June 1, 2014 በጽዮን ግርማ

tsiongir@gmail.com

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ተጠርጣሪዎቹን እሁድ ለሚሰየም ተረኛ ችሎት መቅጠሩን የተለመደ አድርጎታል፡፡ ከቀናት በፊት በሦስቱ ብሎገሮች ላይ በተሰጠው የዐሥራ አራት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ መሠረት የቀጠሮው ቀን ዛሬ ነበር፡፡ ዛሬ በዚህ ፍርድ ቤት ተገኝቼ የነበረውን ሁኔታ መከታተል ባልችልም ምንጮቼ የነገሩኝን ዝርዝር እንዲህ ጽፌዋለሁ፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች እንደተለመደው የአራዳውን ምድብ ችሎት የጓሮ በር እያለፉ ወደ አሮጌው ፍርድ ቤት ግቢ መግባት የጀመሩት ጠዋት ሦስት ሰዓት ከመሙላቱ አስቀድሞ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ከፍርድ ቤቱ ከፍ ብሎ በሚገኘው ማዕከላዊ ለሚገኙት እስረኛ ልጆቻቸው ቁርስ የማድረሻ ሰዓት ስለኾነ ዛሬም ከቁርስ መልስ ሰብሰብ ብለው ነበር ወደ ፍርድ ቤት ግቢ የገቡት፡፡

ፍርድ ቤቱ ሲደርሱ ግቢው በጸጥታ የተሞላ ነበር፡፡አንድም የተከፈተ የችሎት በር አልነበረም፣ግቢውን ከሚጠብቀው አንድ ፖሊስ በስተቀር ሌላ ሰው የለም፡፡ ጠባቂው ፖሊስ ‹‹ዋናዎቹ›› ሲመጡ አንድ ላይ መሰብሰባቸው አይቀርም ብሎ ይመስላል የሚገባውን ሰው በሙሉ አንድ ላይ እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ሰዓቱ ረፈድ እያለ ሲመጣና ጸሐዩ ሲበረታ ግን ግቢው ውስጥ የቆመው ሰው ተበታትኖም ቢሆን ጥላ ፈልጎ እንዲቀመጥ ፈቀደ፡፡ የቀጠሮው ሰዓት እስኪደርስ ድረስ ሁሉም አመጣጡ እንደገጠመለት እየተቧደነ ባገኘው ነገር ላይ ተቀምጦ ፖሊስ ሊጠይቅ ይችላል ያሉትንና ፍርደ ቤቱ ሊሰጠው ስለሚችለው ትእዛዝ ግምታዊ መላምቱን እያስቀመጠ ጭንቀቱን በተስፋ ለማራገፍ ውይይቱን ቀጥሏል፡፡

‹‹ተጨማሪ ዐስራ አራት ቀን ሊጠይቁባቸው ይችሉ ይኾን?›› አንዱ ይጠይቃል፡፡ ‹‹የሽብር ተግባሩን ጠቅሰው ሃያ ስምንት ቀን ይጠይቁባቸዋል›› ሌላኛው ሰው አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል በፍርድ ቤት ጉዳዮች በቂ ልምድ ያለው አንድ የሕግ ባለሞያ፤‹‹መዝገቡ በጊዜ ቀጠሮ ላይ የሚገኝ ቢኾንም ባለፈው ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የሽብር ተግባርና የሃያ ስምንት ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ውድቅ ስላደረገው ዛሬ መልሶ እሱን ማንሳት አይቻልም ፖሊስ ጥያቄውን እንደገና ማቅረብ ቢፈልግ እንኳን በይግባኝ እንጂ መልሶ በዚህ ችሎት የሚያቀርብበት ሥርዓት አይኖርም፡፡›› በማለት ሞያዊ አስተያየቱን ሰጠ፡፡ የሕግ ባለሞያው የተቀመጠበትን ዙሪያ ከበው የተቀመጡት ወዳጅ ቤተሰቦች አስተያየቱን ሰምተው ‹‹ቢበዛ ፖሊስ ሊጠይቅ የሚችለው ዐሥራ አራት ቀን ነው፤እሱንም ቢኾን የሽብር ተግባሩን ሳያካትት በማለት›› ተስፋን ለራሳቸው ሰነቁ፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩት ቀጠሮዎች ችሎቱ ሲሰየምበት ከነበረው ሰዓት እያለፈ ሲሄድ ሁሉም ሰው ግራ ተጋብቶ የነበረ ቢኾንም አምስት ሰዓት ሊመላ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት አንድ ዕድሜው ከሃያ አራት የማይዘለው ጎርመስ ያለ ወጣት ወደ ፍርድ ቤቱ ግቢ ገብቶ ተራኛ ኾኖ መመደቡንና ነገር ግን ችሎቱም አለመከፈቱን የጽፈት ቤት ኃላፊም አለማግኘቱን በመግለጽ የፍርድ ቤቱ ሠራተኛ የሚመስለውን አንድ ሰው ጠየቀ፡፡ ለችሎት ጸሐፊዋ ስልክ ተደወለላት፡፡ እርሷ እስክትመጣም አስቀድሞ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ሊቀርብ ከመጣው መርማሪ ፖሊስ ጋር ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡

ሠላሳ ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ እስረኞቹን ይዘው የመጡት ቁጦ (ከሌላው ጊዜ እጅግ የተለዩ) የፌደራል ፖሊሶች ወደ ግቢው ገብተው ተበታትኖ የቆመውን ቤተሰብ እንደተለመደው ሰብስበው በአንድ መስመር አቆሙት፡፡ ከፍርድ ቤቱ ግቢ ጀርባ ባለው መኪና ማቆሚያ ቦታ ለረጅም ሰዓት ተቀምጠው የቆዩትን ተጠርጣሪዎቹንም ይዘዋቸው ወደ ግቢው ገቡ፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች አቤል ዋበላና በፍቃዱ ኃይሉ እንደተለመደው በሰንሰለት ታስረው ገቡ፡፡ ማኅሌት ፋንታሁን እጆቿ በሰንሰለት ባይታሰሩም አንገቷን በሐዘን ቀብራ ነበር ወደ ግቢው የገባችው፡፡ አቤል የጠነከረ ቢመስልም የበፍቃዱ ዐይኖች መቅላት ለሊቱን በምርመራ ላይ ማደሩን ይጠቁማሉ፡፡

የእጆቻቸው ሰንሰለት ተፈቶ ችሎት ከገቡ በኋላ፤ከችሎት ውስጥ የሚወጣውን ምላሽ ለመጠበቅ ቤተሰብ ትንፋሹን ውጦ በቆመበት መጠባበቅ ጀመረ፡፡ እንደሌላው ጊዜ ቤተሰብ እንኳን እንዲገባ አልተፈቀደም ነበር፡፡ ዐሥር ደቂቃ እንኳን ሳይኾነው ለዘለፋ እና ለቁጣ የተዘጋጁ የሚመስሉ የፌደራል ፖሊሶች ወደ ተሰበሰበው ሰው ቀርበው ‹‹ግቢውን ለቃችሁ ውጡ እዚህ መቆም አይቻልም›› በማለት ማመናጨቅና መገፈታተር ጀመሩ፡፡ ‹‹ጠበቃው እስኪወጣ እንኳን እንጠብቅ የሚባለውን ከእርሱ ነው የምንሰማው›› ሲል ቤተሰብ ተማጸነ፡፡

አንዲት ሴት ፌደራል ፖሊስ እየተንደረደረች ወደ ተሰበሰበው ቀርባ ከፊት ያለውን ሰው መገፈታተር ጀመረች፡፡ ግፍተራው የደረሰባት የበፍቃዱ ኃይሉ እህት ግፍተራውን እየተከላከለች ፍርድ ቤት ግቢው ውስጥ ቆሞ የመጠበቅ መብት እንዳላት በመግለጽ ልታስረዳት ሞከረች፡፡ ፖሊሷ ተቆጣች እጅግም ተናደደች፤‹‹የምን መብት ነው ያለሽ፤ውጪ ብዬሻለሁ ውጪ፤አንተ ዱላውን አቀብለኝ›› የሥራ ባልደረባዋ ዱላውን እንዲያመጣላት ጠየቀች፡፡ ያሁሉ ሰው በተሰበሰበበት ዱላ ተቀብላ ለመማታት ተጋበዘች፡፡ የበፍቃዱ እናት ልጃቸውን ለመከላከል መሀል ገቡ ‹‹ዛሬ እናንተ ባለጊዜ ሆናችሁ ነው፤ፈጣሪ ፍርዱን ይሰጠናል›› እንባቸውን አረገፉት፡፡ ሌሎችም አገዟቸው፡፡ ቤተሰብ ተላቀሰ ፖሊሷ ግን ዱላዋን አቀባብላ ይበልጥ ተጠጋች ሰው ግቢውን ለቆ የማይወጣ ከኾነ ዱላው የማይቀርለት መኾኑን በሚገልጽ አኳኋን እያመናጨቀች አባረረች፡፡ ራሳቸውን ከፖሊሷ ዱላ መከላከል እንደማችሉ የገባቸው እናትና ልጅ እየተላቀሱ ተደጋግፈው ግቢውን ለቀው ወጡ ሌሎቹም ተከተሏቸው፡፡

10414385_810693735609308_5549846429126602484_n

ጠበቃው አቶ አመሐም ከችሎት ከወጣ በኋላ እንዳስረዱት ፖሊስ፤‹‹ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በወንጀል በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 59/2 መሰረት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቀን በምርመራ ላይ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሚስጥራዊ በኾነ መንገድ በሕቡዕ በመደራጀት በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን የያዘውን መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ከሥልጣን ለማውረድ በማሰብ፣ ይህንንም ሐሳብ በውጭ አገር ከሚገኙ አሸባሪ ድርጅቶች ጋራ በመስማማትና አገሪቱን ለማተራመስ ትእዛዝ በመቀበል፣ትእዛዙን ለማሳካት የሚያስችላቸውን ገንዘብ በመቀበል፣እንዲሁም ስልጠና በመውሰድ በአገሪቱ ላይ ብጥብጥ ለማነሳሳትና ብጥብጡንም ለመምራት በመንቀሳቀስ የሽብር ተግባር ፈፅመዋል፡፡ በመኾኑም ይህን የሽብር ተግባር ለማጣራት እንዲረዳን በፀረ ሽብር ዐዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 28 መሰረት ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠን እንጠይቃለን››የሚለውን ቀደም ሲል አቅርቦት የነበረውን ማመልከቻ መልሶ አቀረበ፡፡ እኛም ይህ ማመልከቻ ተቀባይነት ሊያገኝ የማይችልበትን ምክንያት በመጥቀስ መከራከሪያችንን አቀረብን ዳኛው ፖሊስ የጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ ብለዋል፡፡

ከዐሥራ አራት ቀናት በፊት በነበረው ቀጠሮ ችሎቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ችሎቱን ለመታደም የመጣውን ሰው ፖሊስ ከግቢው ውጪ አቁሞት ነበር፡፡ ኾኖም ተጠርጣሪዎቹ በመኪና ተጭነው ሲወጡ ከበር ላይም ቢኾን እጁን እያውለበለበ፣ስማቸውን እየጠራና እያጨበጨበ ሸኝቷቸው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ይህም አልነበረም ማንም ሰው የውጭው በር ላይ እንኳን እንዲቆም አልተፈቀደለትም፡፡

ምራቂ ወሬ

‹‹መዝገቡ በጊዜ ቀጠሮ ላይ የሚገኝ ቢኾንም ባለፈው ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የሽብር ተግባርና የሃያ ስምንት ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ውድቅ ስላደረገው ዛሬ መልሶ እሱን ማንሳት አይቻልም ፖሊስ ጥያቄውን እንደገና ማቅረብ ቢፈልግ እንኳን በይግባኝ እንጂ መልሶ በዚህ ችሎት የሚያቀርብበት ሥርዓት አይኖርም፡፡›› በማለት ሞያዊ አስተያየቱን ሰጠ፡፡ የሕግ ባለሞያው የተቀመጠበትን ዙሪያ ከበው የተቀመጡት ወዳጅ ቤተሰቦች አስተያየቱን ሰምተው ‹‹ቢበዛ ፖሊስ ሊጠይቅ የሚችለው ዐሥራ አራት ቀን ነው፤እሱንም ቢኾን የሽብር ተግባሩን ሳያካትት ነው ››በማለት ቀደም ሲል የሕግ አስተያየት ሰጥተው የነበሩት የሕግ ባለሞያ ችሎቱ ካለቀ በኋላ የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ሲሰሙ የፍርድ ቤቶቹ አሠራር ፊት ለፊት ከሕጉ ጋር እየተጣረሰ መሄድ ግራ ሲያጋባቸው ታይተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ የሕግ ባለሞያዎች ትንታኔ ዋጋ የሚያጡበት ጊዜ በጣም እየቀረበም ነው›› ብለዋል፡፡

Filed in: Amharic