>
5:13 pm - Monday April 20, 0364

ሆድ ካገር አይሰፋም (ሳምሶን አስፋው-ቋጠሮ)

By Samson Asfawድሮ! ድሮ! ያኔ – አበው ሲተርቱ፤
አበባ ወግ ቀስመው – ማር ነገር ሲያመርቱ፤
ሆድ ካገር ይሰፋል! – ይሉ ነበር አሉ፤
በትዝብተ-ህይወት – ቁምነገር ሲኩሉ፤

የታገሱት ነገር – ችለው ያሳለፉት፤
ይበጃል እንዲሉ – ለፍቅር ጤንነት፤
የነገር መጋዘን – አርገው ሲመስሉት፤
ይሉ ነበር አበው – ሆድ ካገር ይሰፋል፤
መከራም ችግርም – ከታገሱት ያልፋል!

ግና የአበው ተረት – የጥንት የጠዋቱ፤
የሆድ አቅመ-ይዘት፤ወርድና ስፋቱ፤
ከአገር እንደሚልቅ የነገሩን ነገር፤
ዛሬ በኛ ዘመን – ትርጉም ሲመነዘር፤
ሆድ ካገር በለጠ -ቀረና መስፋቱ፤
እበላ ባይ በዝቶ – መከነ ተረቱ!

እናም እኔ እላለሁ! ሆድ ካገር አይሰፋም፤
ተሃድሶ ይሻል – ይሰረዝ ተረቱም …

የሆድ አቅመ ይዘት የዙሪያ ልኬቱ …
እንኳን ከአገር ሊበልጥ ወርድና ስፋቱ..
ከቀፈት መቀነት – ከቀበቶ አይዘለልም፤
አድሮ እዳሪ እንጂ – ስንቅ አይሆን ቅርቅቡም
እናም እኔም እላለሁ ሆድ ካገር አይሰፋም!
ተሃድሶ ይሻል – ይሰረዝ ተረቱም …

Filed in: Amharic