>

ሙካቴ ኑሱ! (በዮናስ ሀጎስ)

የኬንያ አምስተኛውን ፕሬዝዳንትና ገዢ ፓርቲ ለመምረጥ የሚደረገው የዚህ ዓመት ምርጫ እኤአ ሐምሌ 8, 2017 በመላዋ ኬንያ በሚደረግ ድምፅ አሰጣጥ ስነስርዓት ይከናወናል።

kenyademonstrationsከአስር ዓመታት በፊት በ2007 በተደረገ ምርጫ በወቅቱ ለሁለተኛ ጊዜ ይወዳደሩ የነበሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ ድምፅ አጭበርብረዋል በሚል መነሻ የተነሳ ሐገራዊ ረብሻ ከአንድ ሺህ ያላነሱ ኬንያውያን ሕይወታቸውን ከገበሩበትና ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑት ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉበት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጣልቃ በመግባት ተቃዋሚውና በስልጣን ላይ የነበረው ፓርቲ ስልጣን በመጋራት አምስቱን ዓመት ሐገሪቷን እንዲያስተዳድሩ በማስማማት ደም መፋሰሱን ያስቆመ ሲሆን የወቅቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በኬንያ የመንግስት ስልጣን ተዋረድ ውስጥ የሌለው የጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣን በድንገተኛ ዐዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጎ ሲሰጣቸው ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ በፕሬዚዳንትነቱ እንዲቀጥሉ ተደርገዋል። በወቅቱ ይህን የስልጣን መጋራት ሕዝቡ «ሙካቴ ኑሱ» የሚል ተቀፅላ ስም አውጥቶለት ነበረ።

• ሙካቴ ኑሱ የስዋሂሊ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ግማሽ ዳቦ ማለት ነው። ሙሉ ዳቦው እንደ መንግስትነት ስልጣን ከታየ ያው በዚያ የብዙ ኬንያውያን ሕይወት የተመሰቃቀለበት ምርጫ የፊት መሪዎቹ ግማሽ ግማሽ ከዳቦው ለመውሰድ በመስማማታቸው ነው ሐገሪቷ ወደ መረጋጋት ልትመለስ የቻለችው።

• ከዚያ ወዲህ የዛሬ አምስት ዓመት የተካሄደው ምርጫ በአንፃራዊ ደረጃ ሰላማዊ የነበረ ሊባል ቢችልም የተቃዋሚው ፓርቲ በምርጫው መጭበርበሩን በተለያየ መልኩ በቂ ማስረጃ በማቅረብ በየፍርድ ቤቶች የምርጫውን ውጤት በተመለከተ የማስቀልበስ ሙከራ አድርጎ ከጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች ስኬት በቀር ሐገራዊ ድልን መጎናፀፍ ሳይችል ቀርቷል። ይህ ሁኔታ የፈጠረው ቁርሾ ሲብላላ ሲብላላ ቆይቶ ለዚህኛው ምርጫ በይደር እንዲተላለፍ ሆኗል። በወቅቱ በተለይ ተሰራ የተባለው የማጭበርበር ስራ የመንግስት ደጋፊዎች የሆኑ መራጮች በሌሊት ቀድመው የመምረጫ ስፍራው ላይ ቀድመው ሰልፍ ከያዙ በኋላ በምርጫ መስጫ ጣቢያው ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በመቀናጀት የድምፅ አሰጣጥ ስርዓቱ እንዲንጓተት ማድረጋቸውና ብዙ የተቃዋሚ ፓርቲ መራጮች ድምፅ ሳይሰጡ ለመመለስ መገደዳቸው ነው። ከዚያም በተጨማሪ ከዚያ በኋላ በተቃዋሚዎች የፍርድ ቤት ክስ ተጣርቶ እንደተረጋገጠው የመንግስት ደጋፊዎች የሞቱ ሰዎችን የመራጭ ካርድ ሳይቀር እንዲቆጠር ማድረጋቸው ሌላው ተቃዋሚዎች የሚያነሱት ነገር ነው።

• በዚህኛው ምርጫ ተቃዋሚዎች የመንግስትን ደጋፊዎች ቀድመው ለመገኘትና የሚደረግን ማጭበርበር ሙከራ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍለው ለማቆም ዝግጅታቸውን ድሮ ነው የጨረሱት። አሁንም የተቃዋሚው መሪ ሆነው ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ራይላ ኦዲንጋ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዚህኛው ምርጫ ላይ «ሙከቴ ኑሱ» የሚባል ነገር እንደማይሰራ ቃል በቃል ተናግረውታል። የምርጫ ቦርዱም ሙሉ ለሙሉም ባይሆን የሙት መራጮችን ጉዳይ በሚችለው አቅም ለማቆም እንደሚጥር ቃል ገብቷል። ነገሩ ግን በዚህም መሰረት የሚረጋጋ እንደማይሆን ሰሞኑን ፍንጭ ታይቷል።

• ከትላንት ወዲያ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነው ዊልያም ሩቶ ቅስቀሳ ለማድረግ ተቃዋሚዎች ጠንካራ መሰረት ወደያዙበት ኪሱሙ ግዛት አምርቶ የነበረ ቢሆንም ከፍተኛ ረብሻ በመነሳት ሕዝቡ ምክትል ፕሬዚዳንቱን አበሻቅጦ ወደመጣበት መልሶታል። የመንግስት ደጋፊዎች ይህን ውርደት ለመበቀል አፍታ ጊዜ አልወሰደባቸውም። በትላንትናው እለት የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ የመንግስት ደጋፊዎች በብዛት በሚገኙበት የኪያምቡ ግዛት የቅስቀሳ ዘመቻውን ለማካሄድ ገና ከመጀመሩ በተነሳ ረብሻ የእርሱና አጃቢዎቹ መኪና ላይ የድንጋይ እሩምታ እየወረደ ከቦታው ለመሸሽ ተገድዷል።

• ሌላው ይህን ምርጫ ሰላማዊ እንደማይሆን ከፍተኛውን ፍንጭ ያሳየው የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ኒካሳሪ ያልተጠበቀ ሕልፈት ነው። ሚንስትሩ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ሲሳተፍ ቆይቶ በሰላም ከተለያዩ በኋላ ባልተጠበቀ ሁናቴ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ እዚያ ሲደርስ ሕይወቱ አልፋለች። የተደረገው የሬሳ ምርመራ የልብ ድካም እንደገደለው ቢገልፅም ቅሉ አሟሟቱ ግን ለተቃዋሚዎች የሚዋጥ ነገር ሊሆን አልቻለም። ምክንያቱም በ2007 ምርጫ ላይም እንዲሁ ለምርጫው ቀናት ሲቀሩ ነበር የሐገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ሳይቶቲ ለምርጫ ቅስቀሳ እየተንቀሳቀሰበት የነበረው ሄሊኮፕተር ተከስክሶ በድንገተኛ አደጋ ሞተ የተባለው። ስለጣኑ ከፍተኛ እንደመሆኑና ይህ ስልጣን በምርጫው ረብሻ ጊዜ የሐገሪቷን የመከላከያ የደህንነተና የፖሊስ እዝ በስሩ የሚያስገባ እንደመሆኑ ተቃዋሚዎች ሚንስትሩ ሆን ተብሎ እንደተገደለና ቦታውን ጠንካራ የመንግስት ደጋፊ ለሆነ ሌላ ሰው ለመስጠት እንደታቀደ ይጠራጠራሉ። ጥርጣሬውን የበለጠ ከፍ ያደረገው ደግሞ የሚንስትሩ ሞት በተሰማ በሶስት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ የትምህርት ሚንስትር የሆኑት ማቲያንጊ በምትኩ እንዲሾም መደረጉ ነው። አዲሱ ሚንስትር ማቲያንጊ ካሁን በፊት ከፖሊስም ሆነ ደህንነት አሊያም መከላከያ ጋር የስራ ልምድ የሌለው መሆኑ ተቃዋሚዎችን የበለጠ የቀድሞውን ሚንስትር ሞት እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል።

• የኡሁሩ ኬንያታ መንግስትም ሁኔታው ከልክ በላይ እንዳስፈራው ጥርጥር የለውም። በምስሉ ላይ የምትመለከቷቸው የአድማና ረብሻ ጊዜ ፖሊሶች እንዲጠቀሙባቸው ተገዝተወወ የመጡ አዳዲስ መኪናዎች ሲሆን የፖሊስ፣ መከላከያና ደህንነት ክፍሉ በዚህ ሰሞን ያልተቋረጠ የሚባል ስልጠና እየተሰጣቸው ነው። ሁሉም የዓመት ፈቃድ እረፍታቸውን አስቀድመው እንዲያጠናቅቁ መመሪያ የተሰጣቸው ሲሆን ከምርጫው በኋላ እረፍት ምናምን የሚባል ነገር እንደማይኖር በግልፅ ተነግሯቸዋል።

• ምርጫውና ተከትሎት የሚመጣው ግርግር ከኬንያውያኑ በላይ ለስደተኞች በጣም አስጊ እየሆነ ነው። ቀድሞውኑም በሰላም ሐገር በጠራራ ፀሐይ የያዙት ዶኪዩመንት ፊታቸው ላይ እየተቀደደ ጉቦ እንዲከፍሉ አፍንጫቸውን ተይዘው የሚገደዱት የኔ ዓይነት ስደተኞች ከምርጫው በኋላ ከፍተኛ ረብሻ ከተነሳ ለሕይወታቸው እንኳ ዋስትና ማግኘት በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። ሐገር በቀል የስደተኛ መርጃ ድርጅቶችም ሆነ ዩኤን የስደተኛ መርጃ ድርጅት ከባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ስደተኞች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና በተቻለ መጠን ከአካባቢያቸው ሕዝብ ጋር ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጥሩ እንዲሁም አለአግባብ በፖሊስ አሊያም ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ከተያዙ እርዳታ የሚጠይቁባቸውን የስልክ ቁጥሮች በዋትስ አፕና በኤስ ኤም ኤስ እየበተነ ይገኛል። በእርግጥ በፖሊስ መያዝ ከእንግልት በቀር ሌላ አሳር ብዙም ባይኖረውም የበለጠ የሚያስፈራው ከምርጫው በኋላ ስርዓት አልበኝነት ከሰፈነና በነዚህ ስርዓት አልበኛ ኃይሎች እጅ ከተወደቀ ነው።

ፈጣሪ አምላካችን መኖርያ አድርገህ የሰጠኸንን ኬንያን ጠብቅልን! እኛን ስደተኛ ወገኖችህን በምህረት አስበን!

Filed in: Amharic