>

የሻምበል ዘውዱ ሽኝት (ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን)

በቅድሚያ ይህን ላስታውሳችሁ።

መጋቢት 30 ለሊት 8 ሰዓት። እዚሁ ፌስቡክ ላይ ዓይኔን ተክያለሁ።
በስደት ላይ ከሚገኙ የሙያ አጋሮቼ አንዱ በውስጥ መስመር
እንዲህ የሚል ጥያቄ ሰደደልኝ።
“ስማ! እናንተ ሰፈር ሻምበል ዘውዱ የሚባሉ ሰው ታውቃለህ?”
ልቤ ድንገጥ አለ።
“አዎ፣ እሳቸው ሰውዬ በህይወት ያሉ አይመስለኝም” አልኩት።
“አሉ!”
“ምን? ትቀልዳለህ እንዴ?”
“አልቀለድኩም። እዚህ እኛ ጋ ነው ያሉት!”
ማመን አልቻልኩም።እኚህ ሰው በምንም አይነት መልኩ ዩጋንዳ/ካምፓላ ይገኛሉ ብዬ አልገመትኩም። በጭራሽ! ቀድሞ ነገር በህይወት ይኖራሉ የሚል ግምት እንኳ አልነበረኝም። የት እንደደረሱ ባለቤታቸውም፣ ልጆቻቸውም ደግመው ደጋግመው ነግረውኛል። ከ1997 ምርጫ ማግስት ነው የት እንደገቡ ያልታወቀው።
*** ***
shambel Zewdu 3ያኔ (በ1997) ምርጫ ሰበብ የሆነውን ታውቃላች። የቅንጅት መሪዎችና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ዘብጥያ ተወረወሩ። በርካቶችም ሀገር ጥለው ተሰደዱ። ሻምበል ዘውዱ አያሌው በኢ/ር ኃይሉ ሻወል ስም ተከሳሽ ነበሩ _ በሌሉበት።
ሻምበል ዘውዱ የመኢአድ ከፍተኛ አመራር ነበሩ። በ97 ምርጫቅንጅትን ወክለው በሰሜን ጎንደር የፓርላማ “ተመራጭ” ነበሩ።
በሰሜን ጎንደር ገጠራማ ቀበሌዎች ወጥተው ወርደው፣ ህዝብን አደራጅተው፣ በህዝብ ድምፅ ለምርጫ ቢበቁም፣ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ። በምርጫው ውጤት ሰበብ። የቅንጅት መሪዎች ሲታደኑ እሳቸው ጠፉ። እምጥ ይግቡ ስምጥ አልታወቀም። እል••••ም!
*** ****
ከዛ በኋላ በ2000 ዓ•ም መስከረም ወር ይመስለኛል የጋሽ ዘውዱን ባለቤት ሰፈር ውስጥ መንገድ ላይ ያገኋቸው። እንዳገኙኝ እያገላበጡ ሳሙኝ። መጨመጩኝ ብል ይቀላል።
“እኔ ምለው ማዘር፣ ጋሽ ዘውዱ የት እንዳሉ ••”
አቋረጡኝ።
“ኧረ ተወኝ ልጄ፣ መከራው ለኔ ተረፈ። በሃሳብ ተብሰልስዬ አለቅኩኝ” አሉኝ ፊታቸው ጥቀርሻ እየለበሰ።
ይኼኔ “ምነው አፌን አንዳች ነገር በዘጋው” አልኩና ራሴን ረገምኩ። ብቻ ••• “አይዞዎት፣ አይዞህ” ተባብለን ተለያየን።
በሌላ ቀን ከአመታት በኋላ ያን “አይነኬ” ጥያቄ ራሳቸው አነሱብኝ።
“የኔ ልጅ ፣ የኔውን ሰውዬ ነገር አልሰማህም?”
“ኧረ ምንም አልሰማሁ። እርስዎ ያሉበትን ሰሙ እንዴ?”
“ኧረ እኔ እቴ! ጋዜጠኛ ወሬ አያጣም ብዬ ነው የጠየቅኩህ!” አሉኝ።
ዝም አልኩኝ። ዝም። “ጋዜጠኛ ማለት ሁሉን ነገር ያውቃል ማለት እንዳልሆነ” ልነግራቸው ወይም ላስረዳቸው አልፈለግኩም።
***
ከዚያ ቀን በኋላ ሀዘናቸውን፣ የልባቸውን ቁስል ላለመነካካት ሳያቸው በሩቁ መሸሽ ጀመርኩ። የዛሬ አመት ግን ፊት ለፊት ተገጣጣምን። ድንገት ታክሲ ውስጥ ስገባ እሳቸው አሉ። አንድ ወንበር ነው የተጋራነው። እናም የባለቤታቸውን ጉዳይ አነሱብኝ።
shambel-zewdu-2“•••ቢሞት ነው እንጂ፣ ሜዳ ላይ ክልትው ብሎ ቀርቶ ነው እንጂ፣በህይወት ቢኖርማ በሆነ መንገድ ድምፁን እሰማ ነበር።መንገድ”
ምን እንደምላቸው ግራ ገባኝ። ሲፈጥረኝ ማፅናናት አልችልም።
ግን የሆነ የውሸት ታሪክ መጣልኝ።
“••እንደዛ አይበሉ ማዘር። አሁን በቀደም ለት እንደጋሽ ዘውዱየገባበት የጠፋብን ዘመዴ በ15 አመቱ ከባህር ማዶ ደውሎ አለሁ አለ። (እኔኮ እንኳን ባህር ማዶ እዚህ ውጪ በር የሚባለው ጅቡቲ የሄደ ዘመድ የለኝም) እና አንድ ቀን ደምፃቸውን ሊሰሙ ይችላሉ”
“እንደአፍህ ያርገው። ድምፁን ሳልሰማው ልሞት እኮ ነው። ይኸው በሱው ሃሳብ ስብሰለሰል የበሽታ ጎተራ ሆንኩኝ። አሁንም ከሀኪም ቤት ነው ምመጣው” አሉኝ በርካታ መድሀኒቶች እያሳዩኝ።
አዘንኩ። ወደ ውስጥ።
***
መጋቢት 30 ለሊት ዩጋንዳ የሚገኘው ስደተኛው የሙያ አጋሬ (Pen Ethiopian Andinet Unionist) ሻምበል ዘውዱከኛ ጋር ናቸው አለኝ።
አላመንኩም። ፎቶአቸውን ላከልኝ። ሻምበል ዘውዱ ብቻቸውን የተነሱትን፣ ከእሱ ጋር የተነሱትን።
***** *****
በበነጋታው ጠዋት 5 ሰዓት ከቤቴ ደጃፍ አስፋልት ዳር ቆሜ አሰብኩ።
ከቆምኩበት በስተግራ አንድ ፌርማታ ብጓዝ ሻምበል ዘውዱ ቤትእደርሳለሁ። ባለቤታቸውን አገኛለሁ። በስተቀኝ ወደላይ አንድፌርማታ ብጓዝ ሴት ልጃቸውን አገኛለሁፈ። እዛ ኮስማና ሱቅ ነገር አላት። እንደህፃንነቴ ምራቄን መዳፌ ላይ አድርጌ ወዴት መሄድ
እንዳለብኝ ለመወሰን “ጨፍ” ማድረግ ነው የቀረኝ። በመጨረሻ ወደ ላይ መሄድ ወሰንኩ። ወደ ሴት ልጃቸው ሱቅ።
****
ደረስኩ። አንድ ሰው እያስተናገደች ነው። ገዢው ከሱቁ እንደወጣ ሰላም ተባባልን። ጥቂት ደቂቃ የባጥ የቆጡን ካወራን በኋላ ስለአባቷ አድራሻ አነሳሁባት። ከዚህ በፊት የማውቀውን መልስ ሰጠችኝ።
“አባትሽ ያሉበትን ብነግርሽስ?”
“አትቀልድ ባክህ! በህይወት ኖሮ ዝም አይልም!”
ከዚህ በላይ አልቻልኩም። ስደተኛው ጋዜጠኛ ፎቶ በውስጥ መስመር የላከልኝን ፎቶዎች አሳየኋት። ሁለተኛውን ፎቶ ሳሳያት ሞባይሌን ነጥቃ ወደኮመዲኖው ጀርባ ገብታ ስቅስቅ ብላ
አለቀሰች። ከአባቷ ጀርባ የገብርኤል ስእል በትልቁ ይታያል።
ፎቶው “በገብርኤል ጥበቃ ስር ነኝ” የሚል ይመስላል። በዚች ቅፅበት አንዲት የጀበና ቡና የምትሸጥ ወጣት ቡና ወደታዘዘችበት ይዛ ስትሄድ ቆም አየችኝና ቆም አለች።
“ምነው?”
“ምነው?” አልኳት እኔን። በጣቷ ዓይኔን ጠቆመችኝ። ሳላውቀው ዐይኔ እንባ አቀርዝዟል ለካ። የግል ጉዳይ መሆኑን ነግሬያት ሸኘኋትና ከሻምበል ዘውዱ ልጅ እጅ ሞባይሌን ነጠቅኳት።
“አንቺ እንዲህ የሆንሽ፣ ማዘርጋ ብሄድ ምን ሊሆኑ ነው ”
“ኧረ እንኳን አልሄድክ። ልቧን ታማ ከሆስፒታል ከወጣች ገና
ሳምንቷ ነው። ብታያት አታውቃትም። በሱ ሃሳብ የተነሳ በሽተኛሆናለች። •••በህይወት መኖሩን እንኳ ሳልሰማ መሞቴ ነው እያለች ነበር ••ወዘተ” አለችኝ።
በእፎይታ ስሜት በረዥሙ ተነፈስኩ።
እሷ በዘዴ ለእናቷ እንድትነግራቸው ተስማምተን ተለያየን። እናም ••• እየቆዘምኩ፣ በስተርጅና ስደተኛ ለመሆን የተገደዱትን ሻምበል ዘውዱን እያሰብኩ ወደቤቴ ተመለስኩ።
*****
ይህን ታሪክ መጋቢት 30/2008 ነበር የከተብኩት። ከዛ በኋላባለቤታቸው ለዓመታት በሃሳብ ሲብከነከኑ የነበሩት የሻምበል ዘውዱ ባለቤት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
••
ይህንን ዩጋንዳ ላለው ወዳጄ ነግሬው ስለ ሻምበል ዘውዱ ጠይቄው ነበር። ሻምበል ዘውዱ ጤንነታቸው ጥሩ እንዳልሆነ ነገረኝ።
ከወራት በኋላ ደግሞ ታመው ሆስፒታል ተኝተው እንዳሉ የሚያሳይ ፎቶ ላከልኝ።

ዛሬ
shambel-zewduዘሬ ሰፈር ውስጥ በርካታ ሰዎች አስከሬን አጅበው ወደ ቀብር ሲሄዱ አየሁና ጠየቅሁ።
ሻምበል ዘውዱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ሰማሁ። ከ3 ሳምንት በፊት እንደታመሙ ወደ ሀገር ቤት እንደገቡ ሰማሁ።
አዘንኩ።
ዛሬ ቀብራቸው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ተፈፀመ።
ነፍስ ይማር!!

Filed in: Amharic