>

የገለቴ ቡርቃ ነገር... (ፍስሃ ተገኝ)

gelete-burqa-by-fisha-tegegnበሰኔ ወር መጀመሪያ ሆላንድ ሄንግሎ ውስጥ በተካሄደው የኢትዮጵያ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማጣሪያ (ሚኒማ ማሟያ) ውድድር ላይ አንጋፋዋ አትሌት ገለቴ ቡርቃ የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ማጣሪያ ውድድሩን 30:40.87 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ሚኒማውን አሟልታ እና ሰንበሬ ተፈሪና በላይነሽ ኦልጂራን አስከትላ አሸነፈች።

ከዛ በኋላ የተሰማው ዜና ግን ገለቴ ቡርቃ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ ስላልተሳተፈች ለለንደኑ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዝግጅት ለማድረግ ሆቴል የገባው ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አለመካተቷ ነው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተወካዮች (ሀይሌና ዱቤን ጨምሮ) ዘንድሮ የተካሄደው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመጀመሩ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሻምፒዮናው ላይ መሳተፍ ለአትሌቶች የሚሰጠውን ጥቅም አስመልክተው ከዘረዘሯቸው መካከል በሻምፒዮናው ላይ ተሳትፈው ደረጃ ውስጥ በመግባት ውጤታማ የሚሆኑ አትሌቶች በለንደኑ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ እጩ ተመራጮች ይሆናሉ የሚለው አንደኛው ጥቅም ነበር። ይሄንን ጉዳይ ዱቤ ሲያብራራ አትሌቶቹ እጩ ተሳታፊ ለመሆን በለንደኑ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማሳተፍ የሚያስፈልገውን የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) ያጸደቀውን ሰአት ወይም ሚኒማ (የሴቶች 32:15.00) ማስመዝገብ እና ማሟላት እንዳለባቸው ጫን አርጎ ገልጾታል።

በዘንድሮው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴቶች 10 ሺህ ሜትር በተካሄደው ውድድር ደራ ዲዳ ርቀቱን 33፡58.41 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ስታሸንፍ እታገኝ ወልዱ (33፡58.95) እና ገበያነሽ አያለው (34፡00.15) እንደቅደም ተከተላቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። ሶስቱ አትሌቶች ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደባቸውን ጊዜ እንዳያችሁት ከሚፈለገው ሚኒማ (32:15.00) ውጪ ነው። በርግጥ አዲስ አበባ ከፍተኛ አልቲቲዩድ ላይ የተቀመጠች ከተማ መሆኗ እና የከተማዋ የአየሩ ሁኔታ ለአትሌቶች ፈጣን ሰአት ለማዝመዝገብ እጅግ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ሶስቱ አትሌቶች ሚኒማውን አለማሟላታቸው ምንም የሚገርም አይደለም። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌድፌሬሽን ሃገሪቷን ወክለው በአለም-አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ የትራክ አትሌቶችን ለብሄራዊ ቡድን ለመምረጥ የማጣሪያ ውድድሮች ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ሃገሮች ለረጅም ጊዜ ሲያካሂድ የቆየውና ዘንድሮም ሆላንድ ሄንግሎ ውስጥ ያካሄደው።

በሄንግሎው የማጣሪያ ውድድር ላይ በአዲስ አበባው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ “ደረጃ ውስጥ የገቡና ጥሩ ሰአት ያስመዘገቡ” አትሌቶች ይሳተፋሉ በተባለው መሰረት በኢትዮጵያው ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ከአንደኛ እስከሶስተኛ ደረጃን አግኝተው ያጠናቀቁት ደራ ዲዳ፣ እታገኝ ወልዱ እና ገበያነሽ አያሌውን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ የሀኪም ማስረጃ በማቅረብ ያልተሳተፈቸው አንጋፋዋ ገለቴ ቡርቃ፣ ሰንበሬ ተፈሪና በላይነሽ ኦልጂራን እንዲሁም ሌሎች ተሳተፉ።

የሄንግሎውን የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ማጣሪያ ውድድር ገለቴ ቡርቃ 30:40.87 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ከአስፈላጊው ሚኒማ በአስተማማኝ ሁኔታ አሟልታ ስታሸንፍ ሰንበሬ ተፈሪ 2ኛ፣ በላይነሽ ኦልጂራ ሶስተኛ ደረጃዎችን በመያዝ ለክ እንደገለቴ ሁሉ ሚኒማውን በአስተማማኝ ሁኔታ አሟልተው አጠናቀቁ። በኢትዮጵያው ሻምፒዮና ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን አግኝተው ካጠናቀቁት አትሌቶች መካከል ደራ ዲዳ ርቀቱን 30:56.48 በማጠናቀቅ ሚኒማውን በአስተማማኝ ሁኔታ አሟልታ አራተኛ ደረጃን አግኝታ ስታጠናቀቅ፣ ገበያነሽ አያሌው ርቀቱን 31:58.23 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ሚኒማውን አሟልታ 10ኛ ደረጃን አግኝታ አጠናቀቀች። እታገኝ ወልዱ በሄንግሎው የ10 ሺህ ሜትር ማጣሪያ ብትሳተፍም ውድድሩን ማጠናቀቅ አልቻለችም።

ገለቴ ቡርቃ በማጣሪያው ውድድር ላይ ፍጹም የበላይነቷን ብታሳይም በኢትዮጵያው ሻምፒዮና ላይ አለመሳተፏ እንደምክንያት ተወስዶ ራሱ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው እና እንድትወዳደር በተፈቀደላት የሄንግሎው የ10 ሺህ ሜትር ማጣሪያ ውድድር ላይ አሳምና ያሸነፈቻቸው አትሌቶች ለብሄራዊ ቡድን ተመርጠው ለዝግጅት ሆቴል ሲገቡ እሷ ግን ከቡድኑ ውጪ እንድትሆን ተደርጋለች።

ገለቴ ቡርቃ ከብሄራዊ ቡድን ምርጫ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ለረጅም ጊዜ አሳዛኝ ውሳኔዎች ተወስነውባታል። ገለቴን ለረጅም ጊዜ የምናውቃት በ1500 ሜትር ሯጭነቷ ሲሆን በዚህ ርቀት ከቁጥሬ ዱለቻ በኋላና ከገንዘቤ ዲባባ በፊት ጠንካራ ብቃት ያላት አትሌት በመሆኗ ምክንያት እሷ በተደጋጋሚ የ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ርቀቶች ሚኒማን እያሟላችና 1500 ሜትር ይልቅ በእነዚህ ሁለት ረጅም ርቀቶች ለብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ ጥያቄ ስታቀርብ ውድቅ እየተደረገባት በ1500ሜትር በተደጋጋሚ ለመካፈል የተገደደች አትሌት ነች። “1500 ሜትር ጠንካራ የፍጥነት ልምምዶች ስለሚያስፈልጉት ተገድጄ እንድሳተፍ በተደረኩበት በዚህ ርቀት የተሻለ ውጤት ለማምጣት በሚል በምሰራቸው ልምምዶች ምክንያት እግሬ እየተቀጠቀጠና በቀላሉ ለጉዳት እየተጋለጠ የወጣትነት ሩጫ ህይወቴ ተበላሽቷል” በማለት በተደጋጋሚ ቅሬታዋን ያቀረበችው ገለቴ ሰሚ ያገኘችው በቅርብ ጊዜ ነበር።

“እስከዛሬ በተደጋጋሚ በኦሊምፒክ እና በሌሎች ሻምፒዮናዎች ላይ ተሳትፋ ምን የሚረባ ውጤት አመጣች?” በሚል በገለቴ ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶችን ባነበብኩና በሰማሁ ቁጥር ይሄን ግብዳ አናቴን በብስጭት እንደነቀነኩ አለሁ። ጥያቄው የገለቴ ውጤታማ የመሆን እና ያለመሆን ጉዳይ አይደለም። ግለሰቦች እና ቡድኖች የመተዳደሪያ ህጎችን እና መስፈርቶችን ከማክበር ይልቅ እንደፈለጉ ለነሱ እንዲመቻቸው አርገው ሲቀያይሯቸው ማየት ሊያበሳጨን እና ሊያስቆጣን ይገባል። ገለቴ ለብሄራዊ ቡድን ብትመረጥ በለንደኑ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ታመጣለች ማለትም አይደለም። የመሸነፍ እና የማሸንፍ ጉዳይ ሳይሆን መርሆች፣ ህጎችና መተዳደሪያ ደንቦች ይከበሩ ነው እየተባለ ያለው።

የሚገርመው ነገር “የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከተሳተፍን የአዲስ አበባ ስታዲዬሙ የመሮጫ ትራክ የውስጥ እግራችንን ስለሚቀጠቅጠውና በቀላሉ ለተለያዩ ጉዳቶች ስለሚያጋልጠን በሻምፒዮናው ላይ አንሳተፍም” በማለት በተለያዩ ጊዜያት ከነበሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሃላፊዎች እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባሎች ጋር ጦርነት ሲገጥሙ የነበሩ አትሌቶች ዛሬ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የቴክኒክ ኩሚቴው የስልጣን ወንበሮች ላይ ቁጭ ብለው አትሌት በነበሩ ጊዜ ያቀርቡት የነበረውን ቅሬታ አሁን በአስማት መርሳታቸው ነው።

Filed in: Amharic