>

በፍጥነት ታሪክ መሆን እንዲህ ቀላል ነውና? [ኤፍሬም እሸቴ]

ቀደም ባለው ዘመን፣ ማንኛውንም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ከተማ ስም ሲጠራ፣ ነዋሪው የአንድ ብሔረሰብ አባል ተደርጎ አይቆጠርም ነበር። ልክ እንደ አዲስ አበባ። አዲስ አበቤዎች ከሁሉም ብሔረሰብ የመጡ ኢትዮጵያውያን እንጂ የአንድ የተለየ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዳልሆኑት ሁሉ ብዙዎቹ የአገራችን ዋና ዋና ከተሞች እንዲያ ነበሩ።

የትልልቆቹን ትተን፣ እኔ ያደግኹባት ትንሿ ሆለታ ገነት እንኳን የአንድ ብሔረሰብ መኖሪያና ንብረት አልነበረችም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነበረባት። እንኳን መሐል ከተማው ከተማውን ከብቦ ያለው ነዋሪ ራሱ ቅይጥ እና ውሑድ ነበር። በተለምዶ «ወላ* ሰፈር» ከሚባለው የወላይታ ብሔረሰብ ሰዎች ሰፈር ጀምሮ ጉራጌው፣ ስልጤው፣ ትግሬው (ድሮ ከተከዜ ወዲህም ከተከዜ ወዲያ ያለውንም በአንድ ነበር የምንመለከተው፤ አይ ልጅነት)፣ አማራው፣ ኦሮሞው ሁሉም ሁሉም ነበረበት።

ይህንን ለማወቅ ጥምቀት ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ከታቦቱ ፊትና ኋላ የሚከተለው ሕዝብ የሚጨፍርበት፣ የሚዘፍንበት ቋንቋ ብዛትና ዓይነት ዛሬም ትዝ ይለኛል። አብረውኝ ያደጉ፣ አብረውኝ የተማሩ ልጆች ከሁሉም እምነት እና ብሔረሰብ የተወለዱ ነበሩ። ማነህ? ምንድነህ? በማይባልበት በዚያን ዘመን ሆለታ የሁሉም አገር እንጂ አሁን እንደሚባለው ምናልባትም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪው ብቻ አልነበረችም። ከሆለታ ጋር ተመሳሳይ ጠባይ ያላቸው ከተሞች ብዙ ናቸው። ደብረ ዘይት ቢሾፍቱን፣ አዳማ ናዝሬትን፣ ጎንደርን፣ አስመራን፣ ሐረርን፣ ሐዋሳን ወዘተ ወዘተ ብንጠቅስ የሁላችንም ነበሩ፤ ሁላችንም የእነርሱ ነበርን። የሆለታ ልጅ ነኝ ስል አንድ ብሔረሰብ መጥራቴ አልነበረም። የናዝሬት ልጅ፡ የድሬ ልጅ፣ የጎንደር ልጅ ወዘተ ወዘተ ተመሳሳይ ትርጉም ነበራቸው። አማራ ነኘ ኦሮሞ ነኝ ትግሬ ነኝ ማለት አልነበሩም። በከተማዋ ተወልጄ ያደግሁ ማለት ብቻ ነበሩ።

በ፳ ዓመት ውስጥ ይህ ሁሉ ተለውጦ አንድ ልጅ ተወልዶ ያደገበትን ከተማ የእርሱ እንዳልሆነ እና ከ100 ዓመት በፊት ዘር ማንዘሮቹ የመጡበት እንዲፈልህ ሲነገረው ማየት እጅግ ይደንቃል። ድሬዳዋ ተወልዶ አድጎ ለመቀለ ጥብቅን የሚቆም ፀሐፊ ሳነብ፣ አዲስ አበባ ዘር ማንዘሩ ከኖረው አዲስ አበቤ ይልቅ ከባሌ ጫፍ ወይም ከወለጋ ያለው የበለጠ ባለቤትነት ሲሰማው ስመለከት፣ ይህም በ25 ዓመት ውስጥ ግልብጥብጡ ወጥቶ ስመለከት ልቦለድ እንጂ እውነተኛ ነገር አይመስለኝም። በዚህ 25 ዓመት ውስጥ ለተወለደ ልጅ ከጥንቱም እንዲህ እንዳልነበርን ማስረዳት ቀላል አይሆንም ጎበዝ። እንኳን እነርሱ ለእኔም ይደንቀኛል። ታሪክ መሆን እንዲህ ቀላል ነውና?

Filed in: Amharic