>
5:13 pm - Tuesday April 19, 1121

ጋሼ አሰፋን “ያገኘነውም፣ ያጣነውም አብረን ነው” እንላለን

Ato Assefa Chaboዋዜማ ሬዲዮ

ታዋቂው ጸሐፊ እና የአደባባይ ሰው(ጋሼ)አሰፋ ጫቦ አረፈ። ጋሼ አሰፋ ያረፈው ትናንት እሑድ ሚያዝያ 15 ቀን 2009 ዓም፣ በስደት በሚኖርባት አሜሪካ ዳላስ ከተማ ነው። ከ1960ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ከታዩት ትጉህ ተዋንያን አንዱ ተደርጎ የሚቆጠረው ጋሼ አሰፋ፣ በዘመነ ደርግ ለ11 ዓመታት በግፍ ታስሮ ነበር። በዘመኑ ኢጭአት የሚባለውን ፓርቲ ካደራጁትና ካዋለዱት አንዱ እርሱ ነበር። የእስሩ ምክንያትም ከዚሁ የራቀ አልነበረም። በዘመነ ኢህአዴግ መጀመሪያ ላይ የሽግግር ምክር ቤቱ አባል ሆኖ አዲሶቹ ገዢዎች ዴሞክራሲን የምር ይቀበሉ እንደሆነ የበኩሉን ለማበርከት ሞክሯል። የዚህ ተሳትፎው ውጤት ግን ለብዙ እንግልት እና እንደወጣ ለቀረበት ስደት ዳርጎታል።

ጋሼ አሰፋ በትምህርቱ የሕግ ባለሞያ ነው። ሆኖም የአደባባይ ሕይወቱን ያለጽሑፍ ማሰብም ማኖርም የሚችል አይመስልም። በ1956 ዓ ም ለሥራ ከሔደበት ባህር ዳር ከተማ “ለፖሊስና እርምጃው” ጋዜጣ በላካት ጽሑፍ የተጀመረው የጋሼ አሰፋ የጽሑፍ ጉዞ የተቋረጠው በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ነበር። የመጀመሪያው በደርግ ታስሮ በቆየባቸው ዓመታት ነበር። ሆኖም በነዚህ ዓመታት ባይጽፍም ብዙ አንብቦና ተምሮ መመለሱን ይናገራል። ሁለተኛው የጸጥታ ወቅት አሜሪካ ከገባ በኋላ ለራሱ ባወጀውና “ሱባኤ ብጤ” ባለው የጽሞና ጊዜው ነበር።

ጋሼ አሰፋ በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የኢልቦለድ አጻጻፍ ታሪክ በአጻጻፍ ስልታቸው ድንቅ ሊባሉ ከሚችሉት ጥቂቶች አንዱ ነው ማለት ማጋነን አይሆንም። በሚያነሳቸው ቁም ነገሮችም ጋሼ አሰፋ፣ አባባይና ጎንታይ፣ አሰላሳይ እና ጋባዥ ጸሐፊ ነበር። በጋዜጦችና በመጽሔቶች ያሳተማቸው በርካታ መጣጥፎች አሉ። 28 የሚሆኑ መጣጥፎች የተሰባሰቡበት “የትዝታ ፈለግ” የተሰኘው መጽሐፉ ሚያዝያ 2008፣ ልክ ከዓመት በፊት፣ ታትሟል። በተጨማሪም ጋሼ አሰፋ በሕይወት ታሪኩ ላይ የተመሠረተ ሌላ መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ እንደነበር ለወዳጆቹ ይናገር ነበር።

ቀድሞ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ተወስኖ የነበረው ጋሼ አሰፋ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በፌስቡክ ጭምር ንቁ ተሳታፊ ሆኖ ነበር። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በብሔረሰብ ተኮር (ዘውጌ) ፖለቲካ፣ በኢትዮጵያዊነት እና በሕዝቦቿ የጋራ እጣ ፋንታ ላይ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በሚሰጣቸው ትንተናዎች አዲስ የመወያያና የክርክር ገበታ ዘርግቶ ነበር። “ኢትዮጵያዊነቴና ጋሞነቴ አይጣሉብኝም” በሚለው ማዕከላዊ እምነቱ የተቃኘው የፖለቲካ ትንተናው አሰባባሳቢ ምህዳር ለመፍጠር የሞከረበት የመጨረሻው ምእራፍ ይመስላል። አንዳንድ የታሪክ ትንተናዎቹ ግን አነጋጋሪዎች ነበሩ፤ በተለይ በአክራሪ የዘውጌ ብሔረተኞች አልተወደዱለትም ነበር። ሆኖም ክርክርና ውይይትን ከመጋበዝ ተቆጥቦ አልታየም። ለኢትዮጵያ እና ለልጆቿ ያለው ፍቅር እንዳልተናወጠ በጉልህ ይታይ ነበር።

በሕይወቱ ማለዳ ወደእርሱ ዓለም የመጡት ቀኝ አዝማች ኢልታሞ ኢቻ፣ ከጋሞ ባህልና ታሪክ፣ ከሕዝብ አገልግሎት እና ከመንግሥት ቢሮክራሲ ጋራ አስተዋውቀውታል። ገና የ13 ወይም 14 ዓመት ልጅ እያለ። በዚህ ውለታው የተነሳም ይመስላል በቀብራቸው ላይ ባለመገኘቱ ከሚቆጭባቸው አጋጣሚዎች አንዱ የኢልታሞ ቀብር መሆኑን ጽፏል። “የትዝታ ፈለግ” በሚል ርእስ በታተመው መጽሐፉ ራሱን እድለ ቢስ ይለዋል። ምክንያቱ ደሞ የሚያፈቅራቸውን ሰዎች ሌላው ቢቀር በቀብራቸው ተገኝቶ እርሙን አሉማውጣቱ ነው። “የማይታደሉ አሉ። እኔ በለቅሶ ጉዳይ እንደዚያ ነኝ። እስከ ዛሬ ድረስ ዘመድ ቆሜ አስቀብሬ አላውቅም። አፈር ሲመለስ አለማየቱ በሕይወት ላይ ክፍት ቦታ የሚተው ይመስለኛል። መሞታቸው የወሬ ወሬ እንጂ አይዘነጋም። ትዝ የሚለው ሞተዋል ተብሎ የተነገረው ሳይሆን በመጨረሻ በሕይወት የተለያዩት ነው። ለኔ እንደዚያ ነው።” ብሎ ነበር።

ጋሼ አሰፋ፣ ለባለውለታው ለቀኝ አዝማች ኢልታሞ ኢቻ የጻፈው ለራሱም ሊባልለት የሚገባና የሚቻል ነው። “ኢልታሞ የሠራውን ለመሥራት የሚያስችል ብዙ አመቺ እድል አልነበረውም። የሌለውን ዕድል ወይም የተገኘችውን ውሱን ዕድል ለታላቅ ሥራ አዋለው። ይህ ከታላቅ ሰዎች መለኪያ አንደኛና ዋነኛ ነው። የቅርብ ቤተሰቡን ይህ የጋራ ኀዘናችን ነውና በመንፈስ እዚያው ከእናንተው ጋራ ነኝ እላለሁ። ኢልታሞን ያገኘነውም፣ ያጣነውም አብረን ነው እላለሁ። የማይሞት ሥራው ግን ከእኛ ጋራ ይኖራል! በሥራው ይዳኝ!!”

ጋሼ አሰፋ አገሩን አጥብቆ ይናፍቅ ነበር። “ሕልም ባየሁ ቁጥር፣ ሰመመን ባየሁ ቁጥር የኢትዮጵያ መሬት፣ የኢትዮጵያውያን ፊት ብቻ ነው የሚታየኝ” ብሎ ጽፏል። ይህም ሞቱን የመለጠ አሳዛኝ ያደርገዋል። ይህ የገፋፋቸው ወዳጆቹና ጓደኞቹ ቢያንስ ቀብሩን በኢትዮጵያ መሬት ለማድረግ በጎ ፈንድ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀምረዋል። (https://www.gofundme.com/assefa-chabo)

ዋዜማ ሬዲዮ፣ ጋሼ አሰፋን ያገኘነውም፣ ያጣነውም አብረን ነው ትላለች። በመንፈስ እዚያው ነን!

ኢትዮ ሪፈረንስ :-  ጋሼ አሰፋ ልዩ ነበር። ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያኑርልን። ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንመኛለን።

Filed in: Amharic