>
5:13 pm - Wednesday April 19, 2761

የእግዚአብሔር መልእክት በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quatero‹‹ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደአለላ ብትሆን እንደአመዳይ ትጸዳለች እንደደምም ብትቀላ እንደባዘቶ ትጠራለች፤ እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምጹም ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናገሮአልና፡፡›› ኢሳ. 1/18.
በእግዚአብሔር ለሚያምን ሰው፣ እግዚአብሔር ሁልጊዜም፣ ለዘለዓለም ሙሉና የማይወዳደሩት ኃይል እንዳለው ለሚያምን ሰው፣ ለእግዚአብሔር ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም አሁን መሆኑን ለሚያምን ሰው ‹‹ኑና እንዋቀስ›› (በእንግሊዝኛው “come now let us reason together) ማለት ለእግዚአብሔር ምን ያህል መውረድ እንደሆነ መገንዘብ የሚዳግት አይመስለኝም፤ የእንግሊዝኛው ትንሽ ሻል ያለ መስሎ ‹‹ኑና እንከራከር›› የሚል ቢሆንም ከመጨረሻው የላይኛው ዳኛ ጋር መከራከር የሚችለው ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፤ ትልቁ ነገር እሱ ፈቀደ፤ ‹‹እንዋቀስ›› አለ!
መዋቀስ ዓላማ አለው፤ ለመግባባት ነው፤ ለመስማማት ነው፤ ለፍቅር ነው፤ ለሰላም ነው፤ ለመረዳዳት ነው፤ እንደመለስ ዜናዊ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ማለት ሲቻለው፤ ኑና እንዋቀስ የሚል ኃያል አምላክ ለእኛ ምን ያስተምረናል?
የእግዚአብሔር ቃል ኑና እንማከር በማለት አልቆመም፤ እሺ ብትሉ፣ ለእኔም ብትታዘዙ፣ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምጹም ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና፡፡
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ትሕትናንና መወያየትን፣ መወቃቀስና መስማማትን ለማስተማር በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል መልእክቱን አስተላለፈ፤ ዛሬ ይህ መልእክት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ይመስለኛል፤ ዛሬ ይህ የእግዚአብሔር መልእክት ለወያኔ ይመስለኛል፤ ዛሬ ይህ መልእክት ለወያኔና ለአጋሮቻቸው ይመስለኛል፡፡
በኢሳይያስ በኩል የመጣው መልእክት ግልጽ ነው፤ ምርጫው ‹‹የምድርን በረከት መብላት›› ወይም በሰይፍ መበላት ነው፡፡
የምድር በረከትን በሙሉ ሁሉ በጄ ሁሉ በደጄ ላለ ጥጋብ ላይ ነውና ይበልጥ አይታየውም፤ በዕብሪት ላበጠም ስለሰይፍ ቢወራ አያስፈራውም፡፡
እግዚአብሔር ‹‹እንዋቀስ›› ካለ እኛ፣ ገዢዎቻችንም ለሰላም ሲሉ ለፍቅር ሲሉ፣ ለልጆቸው ሲሉ፣ ለአገር ሲሉ ‹‹እንዋቀስ›› ቢሉ ያስከብራቸዋል እንጂ አያዋርዳቸውም፤ ታሪካቸውን ያሳምርላቸዋል እንጂ አያጎድፍባቸውም፤ መንፈሳዊ ወኔ ያላቸው፣ ልበ-ሙሉ ጀግኖች ያደርጋቸዋል እንጂ ፈሪ አያደርጋቸውም፤ አርቀው የሚያስተውሉ ብልሆች ያደርጋቸዋል እንጂ ጊዜያዊ ጮሌነት አይሆንባቸውም፡፡

Filed in: Amharic