>
5:13 pm - Thursday April 19, 9184

ይደንቃል የመሰብሰብ አባዜ! [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroዕደሜ-ልኬን እሰበስባለሁ፤ የምሰበስበውን ማስቀመጫ እገዛለሁ፤እሰበስባለሁ፤ የሚደንቀው ነገር ዛሬም መሰብሰብ አላቆምሁም!

አሁን ከጥቂት ቀኖች በፊት በድንገት አንድ ጥያቄ በአእምሮዬ ውልብ አለ፤ በሃያ ሦስት ዓመት ዕድሜዬ አንደዚሁ ዓይነት ሁኔታ በዚያ በጎረምሳ ዕድሜዬ ጠይቄው የማላውቀው ጥያቄ በአእምሮዬ ውል ብሎ ሕይወቴን ለወጠው፤ አሁን በሰማን ሰባት ዓመቴ ደግሞ ሌላ ጥያቄ መጣብኝ፤ አሁን ግን ያለፈውን ለመታዘብ እንጂ የሚመጣውን ለማነጽ አይመስለኝም፡፡

ለማናቸውም ፍሬ ነገሩን ገልጬዋለሁ፤ የመሰብሰብ ጉዳይ ነው፤ ምናልባትም ሕመም ልንለው እንችል ይሆናል፤ የምሰበስብት መክንያት (ሰበብ አይደለም) ነበረኝ፤ አስተማሪ ነኝ፤ ስለኢትዮጵያ ብዙ የተለያዩ መረጃዎች፣ ስለመሬቱ፣ ስለዓየር ጠባዩ፣ ስለዕጸዋቱ፣ ስለእንስሳቱና ስለአራዊቱ፣ ስለሕዝቡና ስለኑሮው … እንዲህ በጥቅል ሲዘረዘር ትንሽ ይመስላል፤ ቤት ያስለቅቃል፤ እንዲያውም አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፤ በደጉ በደርግ ዘመን የቤት ኪራይ ረክሶ ስለነበረ አንድ ቪላ በሦስት መቶ ብር ተከራይቼ ነበር፤ ዛሬ ወደሃያ ሺህ ሳያወጣ አይቀርም፤ ነገር ግን የደርግን አዝማሚያ ሳየው እያደኸየን እንደሚሄድ ታየኝ፤ እኔ ሲገፉኝ አልወድም፤ ስለዚህ ከመገፋት በፊት ብዬ ቆጠብ ያለ ኑሮ ተመኘሁ፤

በ1967 መጨረሻ ላይ የኪራይ ቤቶች አዋጅ ሲወጣ አዲስ ቤት ለማግኘት ለመመዝገብ 130ኛ ነበርሁ፤ ከአሥር ዓመታት ያህል በኋላም ቤት ማግኘት አልቻልሁም፤ አንድ ቀን አንድ ግብዣ ላይ የቤት ነገር ተነሣና እኔ ‹‹ዛሬ ቤት የሚያገኘው የጦር መኮንን፣ ወይም ቆንጆ ሴት፣ ወይም ያናጠጠ ነጋዴ ነው፤›› አልሁ፤ እዚያ የነበሩ የደርግ አባሎች ተናደዱ፤ መዝገባችሁን እየት፤ ተራዬ ካለፈ ቆይቷል፤ ብዬ ሽንጤን ይዤ ስም እየጠቃስሁ ምሳሌ አቀረብሁ፤ ንዴታቸውን ወደተግባር ለውጠውት ኖሮ በበነጋታው ከኪራይ ቤቶች በተከታታይ እየተደወለ የሚከራዩ ቤቶችን ለማሳየት ይጠሩኝ ነበር፤ በመጨረሻም አሁን የምኖርበትን አፓርትመንት አገኘሁና ገባሁ፤ የተነሣሁበትን ትቼ በስላጭ የያዝሁትን ይዤ ብዙ ተጓዝሁ፤ ለማናቸውም አሁንም ወደዋናው ከመመለሴ በፊት አሁን ያለሁበትን አፓርትመንት አንድ የቀበሌ ሹም ለራሱ ይሁንም ለጌታው ተመኝቶት በማስፈራራት ሊያስለቅቀኝ ሞክሮ ነበር፤ እስካሁን አለሁ፡፡

አሁን ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገር፤ ሾላ የነበርሁበትን ቪላ ለቅቄ ወደአፓርትመንቱ ስገባ ቪላው ውስጥ በነበረው የእሳት መሞቂያ (ዛሬ ይህንን ለማያውቁ በመኪናዬ ሙሉ ጥሩ ደረቅ እንጨት በአሥር ብር አገዛ ነበር፤) ውስጥ ለአንድ ሳምንት ያህል ያጠራቀምኋቸውን የተለያዩ ወረቀቶች (ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ …) እየነደደኝ አነደድሁ፤ ያም ሆኖ የተረፈው አፓርትመንቱን በጣም አጠበበው፤ አሁን የማስበው ስለቤት ኪራይ አይደለም፤ አቤት የሚባልባቸው ሰዎች እንኳን በግብዣ ላይ በልቅሶ ላይም አላያቸው፤ ባያቸውም አንነጋገር! አሁን ችግሩ ያለው እኔ ዘንድ ነው፡፡

ይህንን እኔ ይረባል ብዬ የሰበሰብሁትን ዛሬ ሳየው የማይረባ ክምር በማን ቤት ልከምረው! የሚቀድመው ጥያቄ ግን እንዴትና ለምን ተሰበሰበ ነው፤ የአስተማሪነት ጣጣ ላይ ይወድቃል፤ የአስተማሪነት ጣጣ መሆን አለመሆኑን ሌሎች ይከራከሩበት፤ ለእኔ ግን ጣጣዬ ነበር፤ ይኸ የተሰበሰበው ሁሉ ወረቀት ገንዘብ ወጥቶበታል፤ በደጉ ጊዜ፣ መሬት ርካሽ በነበረ ጊዜ! ቤት ርካሽ በነበረ ጊዜ! ገንዘቤን ወረቀት ላይ ያፈሰስሁት ለሥራዬ ዋጋ ሰጥቼ ነበር፤ በኢትዮጵያ ሥራ ዋጋ እንደሌለው ያወቅሁት ቆይቼ ነው፤ እነራስ አበበ አረጋይን፣ እነራስ መስፍን ስለሺን፣ እነበላይ ዘለቀን፣ እነጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉን፣ ብዙዎች ሌሎችም እነሱ ለኢትዮጵያ የከፈሉትንና የኢትዮጵያ አገዛዞች ያስከፈሏቸውን ተገንዝቤ የኔን ቀላል አድርጌዋለሁ፤ … ወይ ጉድ! አሁንም እያዳለጠኝ ወደሌላ ነገር እየሄድሁ ነው፡፡ will continue

Filed in: Amharic