>
5:13 pm - Friday April 19, 4058

ከጋምቤላ በድጋሚ ህፃናት ታፍነው ወደ ደቡብ ሱዳን ተወሰዱ

%e1%8a%a8%e1%8c%8b%e1%88%9d%e1%89%a4%e1%88%8b-%e1%89%a0%e1%8b%b5%e1%8c%8b%e1%88%9a-%e1%88%85%e1%8d%83%e1%8a%93%e1%89%b5-%e1%89%b3%e1%8d%8d%e1%8a%90%e1%8b%8d-%e1%8b%88%e1%8b%b0-%e1%8b%b0%e1%89%a1ዋዜማ ራዲዮ– የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት በድጋሚ በጋምቤላ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ 11 ሰዎችን ገድለው ከ20 ያላነሱ ህፃናትን ጠልፈው ወስደዋል ።
የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዬች ፅ/ቤት ሀላፊ ኦኬሎ ኡማን ዴንግ ለዋዜማ ዘጋቢ እንደነገሯት ሙርሌዎቹ ከትናንት በስቲያ እሁድ እለት ባደረጉት ጥቃት 11 ሰዎችን በመግደል ህፃናትና ከብቶችን ዘርፈዋል።
በ2008 አም የሙርሌ ጎሳ አባላት ባደረሱት ጥቃት እና ዘረፋ 200 ያህል ህፃናትንና በርካታ የቀንድ ከብቶችን የዘረፉ ሲሆን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ባደረገው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ታፍነው ከተወሰዱት ህፃናት መሀከል የተወሰኑትን ማስመለስ ቢችልም 57 ያህል ህፃናት አሁንም ድረስ ያሉበት አለመታወቁን የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊው ተናግረዋል ።
በጋምቤላ በተደጋጋሚ ግጭት ከሚያነሱ ጎሳዎች መሀከል ንዌርና አኝዋክ (አኝዋ) ዋናዎቹ ሲሆኑ በ2008 አም ታፍነው ከተወሰዱ ህፃናት መሀከል የመከላከያ ሰራዊቱም ሆነ ክልሉ ያስመለሳቸው ህፃናት የንዌር ጎሳ አባላት የሆኑ ህፃናትን ብቻ መሆኑ በሁለቱ ጎሳዎች የነበረውን ቅራኔ እንዳባባሰው አቶ ኦኬሎ ተናግረዋል ።
በምን ምክንያት የመከላከያ ሰራዊቱና የክልሉ መንግስት የንዌር ጎሳ የሆኑትን ብቻ አስመለሰ የተባሉት ሀላፊው ጉዳዩን በዝርዝር ለመግለፅ አልፈለጉም ።
እሁድ እለት በዳግም ጥቃት  የሙርሌ ጎሳ አባላት የገደሏቸውና አፍነው የወሰዷቸው ሰዎች ከደቡብ ሱዳን ድንበር በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በአኝዋ ዞን ኳክ ወረዳ እኙድና ጃሌ በሚባሉ ቦታዎች በሚኖሩት የአኝዋ ብሔረሰቦች ላይ መሆኑ በርግጥም የክልሉ አስተዳደር ለአኝዋ ብሔረሰቦች ጥበቃ አለማድረጉና በሁለቱ ብሔረሰቦች መሃል ያለውን የከፋ ግጭት የሚያመለክት ጉዳይ ሆኗል።

የአኝዋ ብሔረሰቦች ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ቢያሰሙም ድንበሩ ሰፊ በመሆኑ በአካባቢው ሚሊሻ አቅም ብቻ የክልሉን ፀጥታ ማስጠበቅ ባለመቻላችን የክልሉ ፀጥታ የመከላከያ ሰራዊት እንዲጠብቅ ክልሉ ለፊደራል መንግስት ጥያቄ ባቀረበው መሰረት የመከላከያ ሰራዊት ቢገባም አሁንም ከሙርሌዎቹ ጥቃት መዳን አልቻልንም ሲሉ አቶ ኦኬሎ ገልፀዋል።
በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት አምና በጋምቤላ ክልልያደረሱትን የከብት፣የህፃናት ዘረፋና ግድያ ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት የመከላከያ ሰራዊት ባደረገው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻው የተወሰኑ ህፃናትን ካስመለሰ በኃላ ስለተቀሩት ህፃናት ጉዳይ በዘመቻው ወቅት ከተናገረው ውጭ ምን እየሰራ እንደሆነ የተሰማ ነገር የለም።
የመከላከያ ሰራዊቱ የክልሉን ፀጥታ በአስተማማኝ እንደሚጠብቅና መሰል ድርጊት ድንበር አቋርጠው በሚመጡ የውጭ ሀይሎች እንደማይደገም በወቅቱ ቢናገርም በአኝዋ ብሔረሰቦች ላይ ሙርሌዎቹ ዳግም ተመሳሳይ አደጋ ማድረስ ችለዋል።
ከደቡብ ሱዳን በመነሳት እና ድንበር አቁዋርጠው ከቀናት በፊት በጋምቤላ የአኝዋ ብሔረሰቦች ላይ የደረሰውን ዳግም አፈናና ግድያን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እስኩ አሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።

በደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚገኙት የሙርሎ ጎሳ አባላት በወረራ መልክ ወደ አጎራባች ድንበሮች በመሄድና ጥቃት በማድረስ የሚወስዷቸውን ህፃናት በጎዲፈቻ በማሳደግ ዘራቸውን የማቆየት ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።
በ2008 በጋምቤላ ያደረሱት ጥቃትና የዘረፏቸው ህፃናት ቁጥሩ በመበርከቱ ምክንያት ለአደባባይ በቃ እንጂ በተደጋጋሚ መሰል ድርጊት ሲፈፅሙ እንደኖሩ ጉዳዩን ሲያጠኑ የቆዩ አንድ ምሁር ድርጊቱ በተሰማ ጊዜ በአንድ የግል ሬዲዬ ጣቢያ ላይ ቀርበው ተናግረዋል ።

Filed in: Amharic