>

አጭር ትዝብት:- የኢሳት በዚህ ሳምንት ውይይት ከሲሳይ አጌና ጋር [እንግዳ ታደሰ]

ክፍል አንድን አየነው ፡፡ www.youtube.com/watch?v=QAyCAyrHRvI&t=223s ክፍል ሁለት ለሚቀጥለው ጊዜ እንደሚቀርብ ሲሳይ አጌና ነግሮን ጣፋጩ ውይይት እንደጣመኝ አለቀ ፡፡ ከውይይቱ ምን ተረዳሁ ? የሁለት ትውልድ ወግ ብየዋለሁ በግሌ ፡፡ ሁለቱ ወጣት ዶክተሮች ርግጠኛ ሆኘ ባልናገርም ፣ በደርግ የመጨረሻው ጊዜ የተገኙ ወጣቶች ይመስሉኛል ፡፡ በመሆናቸውም በስድሳው ፖለቲካ ጥርስ ክነቀሉት ከአቶ ፈቃደ ሸዋቀና ጋር በውይይቱ መስመሮች ውስጥ የአመለካከት ልዩነት እንዳላቸው ይታያል ፡፡ እጅግ ካላጋነንኩት ፡፡ ሲሳይ የሁለት ትውልዶችን ወግና የፖለቲካ እሳቤ እንድናይ ማድረጉ ድንቅ ጋዜጠኝነቱን ያሳያል ፡፡ በዘመኔ ካአየኋቸው ድንቅ ጋዜጠኞች ወይም አወያዮች ውስጥ  ሟቹ አቶ አሳምነው ገ/ወልድና ሲሳይ አጌና ብቻ ናቸው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም ፡፡

 ዶክተር ደረሰ ጌታቸውን በሚመለከት ፣ ውይይቱን በቀላል አማርኛ ወይም  political jargons ባልታጨቁበት ሁኔታ አፍታተው ሲያቀርቡ እንዴት ደስ ያሰኛል ፡፡ የስድሳውን ዘመን ግራ አጋቢ ፖለቲካም ከዘመኑ ወጣት እይታ ጋር አፍታተው ያስረዱበት ቋንቋ ግልጽ ነው ፡፡ በዚህ ውይይት ውስጥ የተካፈሉት ዶክተር ሰማኽኝ ጎሹም ልክ እንደ ዶክተር ደረሰ ጌታቸው የትውልድ ዘመናቸው በመቀራረቡ የተነሳ ይመስላል የዶክተር ደረሰን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ እንደሚጋሩ ውይይቱን ለተከታተለ ሰው እንደኔ ይረዳል የሚል እይታ አለኝ ፡፡

 ወደ አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ስመጣ ደግሞ ከላይ እንደጠቀሱት በስድሳው ፖለቲካ ውስጥ እንደማደጋቸው ህብረተሰባችንን የአንድነት ኃይል የሚባለው  ክፍል በዘውግ የተደራጁትን ኃይሎች አላዳምጥም የሚል አቋሙን ካላስተካከል ወደ አንድነት ልንመጣ አንችልም ብለው ይከሱና ወረድ ሲል ደግሞ የአንድነቱ ኃይል የተዝረከረከ ነው ሲሉ እንደረገሙት ውይይቱ ወደ ሚቀጥለው ጊዜ  ይተላለፋል ፡፡

 የአንድነት ኃይል የሚባለው ማነው ?

 ወያኔ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ « የአንድነት ኃይል » ተብሎ የሚጠራውን ቃል ለአማሮች ብቻ በማውረሱ ፣ ይህንን ቃል ሳያጣጥሙ የጎረሱት የዘውግ ኃይሎች ሁልጊዜ አንድነት ! አንድነት በማለት የሚጮኽውን ኃይል ሁሉ ለምን ከአማራነት ጋር ብቻ እንደሚለውሱት አይገባኝም ፡፡ በአንድነት ኃይል ውስጥ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ጉራጌዎች ፥ አፋሮች፥ ወላይታዎች ፥ ሲዳማዎች፥ ጋሞዎች ፥ ሃድያዎች ፥ ከንባታዎች  ወዘተ ሁሉ የሚካተቱበት ኃይል ነው ፡፡ አቶ ፍቃደ የስድሳው ፖለቲካ ሰው ስለሆኑ የአንድነቱን  ኃይል ልክ እንደ ወያኔና ኦነግ ከአማራነት ጋር ብቻ ሊያያይዙት ሲሞክሩ ነው ከውይይቱ ያስተዋልኩት ፡፡

እንደ መሰለኝ አቶ ፍቃደ ወደ ውይይቱ የመጡት ዘግይተው ስለሆነ ፣ ዶክተር ደረሰ ጌታቸው ያነሱትን ዋና የስድሳውን ፖለቲካ ህጸጽ ባላማዳመጣችው ይመስለኛል የአንድነቱን ጎራ ለመምታት የሄዱት ፡፡ ቢያንስ በውይይቱ  ሰአት አርፍደው በመድረሳቸው ይቅርታ እንኳ አልጠየቁም ወደ ውይይቱ ሲገቡ ፡፡ በርግጥ የትራፊክ ችግር ምናልባት ገጥሟቸው ሊሆን ይችላል ፡፡ ቢሆንም ተመልካቹን ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ ነበር ፡፡ ሳጠቃልል አንድ እንደ ማዕዘን ራስ ሁሌ የማከብረውን የአቶ አሰፋ ጫቦን ጥቅስ አንስቼ አጭር ትዝብቴን ልቋጭ ፡፡ « ጋሞነቴና ኢትዮጵያዊነቴ ተጋጭተውብኝም አያውቁ » የጋሞው ተወላጅ አቶ አሰፋ ጫቦም የአንድነቱ ኃይል ናቸው ፡፡ አማራ አይደሉም ፡፡

Filed in: Amharic