>
5:13 pm - Tuesday April 19, 6805

የ”ጥልቅ ተሃድሶ” ድራማ ተጀምሯል! [ክንፉ አሰፋ]

በቤተ ሙስና፣ የ”ጥልቅ ተሃድሶ”ው ድራማ ተጀምሯል!  የእርስ በርስ እና ራስን በራስ መተካካት ቧልት እና ፌዝ።

Adisu kabineከመጋረጃው ጀርባ ስብሃት ነጋ፣ አቦይ ጸሃይ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ደብረጽዮን እና በረከት ስምኦን የሚቆምሩትን ካርታ ሃይለማርያም ደሳለኝ እንደቬጋስ አጫዋች ፊት እያመጣ ይዘረጋዋል። በዲዮጋን ያደረጉት አብዮታዊ እና ልማታዊ “ምሁራን” ፍለጋ ውጤት ነበረው። “የዶክተር ያለህ”  ፍለጋ  ጥቂት ታማኝ አገልጋዮችና ፣ በርካታ ሮቦቶችን አስገኝቷል። “በዲሞክራሲ” በተመረጠው  “የህዝብ ምክር ቤት” የሚኒስትሮቹ ስም ይፋ በሆነ ግዜ፤ ለይስሙላ እንኳን ተቃውሞ፣ አልያም ድምጸ-ተአቅቦ ቢያደርግበት ድራማውን ያሳምረው  ነበር። በሙሉ ድምጽ ጸደቀ ተባለ።  የነዚህ ሮቦቶች ምርጫ የፍልፍሉን ቀልድ ያስታውሳል።

የድሃው ልጅ ለሃብታሙ ልጅ፣ “ምን ያንጠባርርሃል? አንተም የምትበላው አንድ እንጀራ፣ እኔም የምበላው አንድ እንጀራ…” ይለዋል።

የሃብታሙ ልጅ መለሰለት፣  “እንጀራውን ተወውና ስለ ወጡ እንነጋገር?”

ነገሩ ወዲህ ነው። ተጫዋቾች እና አጫዋቾች።  መቼም ሹመኛው ሚኒስቴር ነኝ ብሎ ደፍሮ ቢያወራም፣  ሚኒስቴር ነኝ ብሎ ግን ደፍሮ ውሳኔ አይሰጥም። ውስጡን ያውቀዋል። ሰለዚህ ስለ ተጫዋቾቹ ሳይሆን ሰለ አጫዋቾች እንነጋገር። ሰለ ሚንስትሮቹ  ሳይሆን ስለ ምክትሎቹ እናውራ።  በቀላል አማርኛ “ዶክተሩ” ከላይ ይቀመጣል። ከስር ያለው ካድሬ እንደ እንዝርት ያዞረዋል። ላለፉት 25 አመታት ከዚህ የተለየ ነገር አልነበረም። ወደፊትም ከዚህ የተለየ አይሆንም። ጨዋታው እንደነበረ ይቀጥላል።  የሳሞራ የኑስ የግል ንብረት የሆነው የመከላከያ ሚኒስቴርን ሲራጅ ፈጌሳ ይመራዋል ብሎ የሚያምን ካለ ልጅ ወይንም ጅል መሆን አለበት።  ለውጥ የሚመጣው ጌታቸው አሰፋ የደህነንቱን ስፍራ ለተቀናቃኝ አስረክቦ ቢሄድ ነበር። ወርቅነህ ገበየሁ ወ/ኪዳን የተሰጠውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነገር ወደ ኋላ ልመለስበት። ድራማውን ስንቃኘው አሁንም በጥልቅ ተሃድሶ ስም ቀልድ ነው የተያዘው።  ይህቺ ሃገር ገና ከአሁኑ የባሰ አንባገነን፣ ሙስና፣ ስቃይ እና አፈና ይጠብቃታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንስ እያሳዘኑን መጡ። በእርግጠኝነት ለመናገር ማን እንደተሾመ እንኳን ለፓርላማው ከማንበባቸው በፊት አያውቁትም። በሙስና እና በወንጀል እጃቸው የተጨማለቁ ሰዎችን ጭምር ሹመት አደባባይ ወጥተው ሲናገሩ በኩራት ሳይሆን በፍራት ነበር መሆን የነበረበት። እሳቸው ግን  ትልቅ እና ግዙፍ ለውጥ ነው ብለው ተናገሩ።  በዚህ “ጥልቅ ተሃድሶ” ሕዝባዊ አመጹ  ይቆማል ብለውም ያምናሉ።  በጥይት እና በጭስ ከ700 ሕዝብ በላይ ሲያልቅ የቶክስ ድምጽ አልነበረም ብሎ በአለም አቀፍ ሜዲያ ለሚናገር ምስኪን ጠቅላይ ሚኒስትር ማዘን እንጂ ማውገዝ አይገባም።

የሚኒስትሮቹን ምክር ቤት የእግር ኳስ ቲም አስመሰሉትኮ። የመብት ጥያቄ በመጣ ቁጥር የሚፐወዝ ቲም። ጥያቄው የስርዓት ለውጥ እንጂ የሰዎች መገለባበጥ አይደለም። ካቢኔውን ሺህ ግዜ ቢፐውዙት፤ ለሃገሪቱ ችግር መፍትሄ አይሆንም።   የእግር ኳስ ቲምም ቢሆን እኮ ሲገነባ የእያንዳንዱ ተጫዋች ብቃት እና ስነ ምግባር በባለ ሞያዎች ተገምግሞ ነው። እጃቸው በደም እና በሙስና የጠጨማለቁ ሰዎችን እያመጡ፤  የሕጻን አይነት ድብብቆሽ መጫወት ግዜ ለመግዛት ይረዳቸው ይሆን እንጂ ሕዝባዊ ቁጣውን ሊያቆመው አይችልም።  በዚያ ሰሞን በቴሌቭዥን ቀርበው መንግስታችን ጥልቅ በሆነ ሙስና ተዘፍቋል ያሉን እነሱው ናቸው። ሙስኞቹ አሁንም አሉ።  በጥልቅ ሙስና የተዘፈቁ ሰዎች የችግር እንጂ የመፍትሄ አካል እንደማይሆኑ እያወቁ በህዝብ ላይ ማፌዙ ለምን አስፈለገ? የሚደረገው ድራማ ለመግለጽ የአናንያ ሶሪን ቃል ልዋስ፣  “በዚህ ሁኔታ የሚመጣው በጥልቅ መታደስ ሳይሆን በጥልቅ መበስበስ ነው።”

“ጥልቅ ተሃድሶ” ሲሉን ቢያንስ አዲስ ምርጫ ያደርጋሉ ብለን ጠብቀን ነበር። እውነት ይቀየራሉ ብለን አምነን ተሳስተናል።እነሱ ግን ሕዝብን ሳይሆን ራሳቸውን ነው እይታለሉ ያሉት።

ከተሾሙት ሚንስትሮች ውስጥ ሁለት ፕሮፌሰሮች፣ ሁለት ኢንጅነሮች እና አስራ አራት ዶክተሮች ይገኙበታል። ያልተገነዘቡት ከለውጥ ይልቅ የዶክተር መደርደር ሾተልን ወደ ሰገባ ቁጣን ወደ ትእግስት እንደማይመልሰው ነው። የዶክትሬቱ ዲግሪም እኮ ከየት እንደመጣ ለሕዝብ የተደበቀ ነገር አይደለም።  ግን የዶክተር ያለህ እየተባለ ከየስፍራው ሲለቀም ጀነራል ባጫ ደበሌ ለምን ተረሳ? ምሁር የሚያሰኘው የዲግሪ ወረቀቱን ከሁሉም በፊት እሱ ገዝቷል። ጀነራል የሚለውን የፉገራ ማእረግም ከፕሮፋይሉ ላይ አንስቶት ነበር።  አባ ዱላ ገመዳስ ቢሆን ለአዲሱ ከቢኔ ምን ያንሰዋል? ሳይማር  ዶ/ር አባ ዱላ እየተባለ አይደል የሚጠራው?  ፕ/ር ቆስጠንጢኖስም  ከሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ  ዲግሪ ገዝቷል። እሱስ ቢሾም ምን ይለዋል?

ከሆነ አይቀር ለምን ሁሉንም ሚኒስተሮች በባለ ዶክተር ማዕረጎች አልተኩትም ነበር?  ለወረቀቱም ቢሆን ችግር የለም። የሲቪል ሰርቪስ ወፍጮ ዶክተሩን እና ፕሮፌሰሩን በገፍ እያመረተ ነው። ዘንድሮ ከአንዳንድ የርቀት ትምህርት  ቤቶች በሳምንት ግዜ ፕሮፌሰር መሆን ይቻላል።

በሸገር የሚነገር አንድ ቀልድ አለ። ወያኔ ስልጣን ሲይዝ መጀመርያ የወረረው ወታደራዊ ካምፖችን ነበር። መኮንኖችን ለመያዝ።  ወያኔ ሲወድቅ ደግሞ ተቃዋሚው  ሃይል  መጀመርያ የሚወርረው ሲቪል ሰርቪስ “ኮሌጅ”ን ነው።  እንደ ድንጋይ የሚያስቡትን እያመረተ ሕዝብን የሚፈጅ ተቋም!

መቼም ተቀለደ።  ተቀልዶ ግን አይቀርም።  መዳኛ ያልተገኘለት የህወሃት የፖለቲካ መፍትሄው የህዝብ ድምጽ ነው። የህዝብ ድምጽ ደግሞ በሶስት ቃላት ተገልጿል። ለውጥ!

“መተካካት” እያሉ ጆሮ ሲያደነቁሩ የነበረው ይኽንን ነበር እንዴ? ወርቅነህ ገበየሁ ወ/ኪዳን ከትራንስፖርት ሚኒስትር አንስቶ በወርቅነህ ገበየሁ ነገዮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መተካት?   እርግጥ ነው ፈረንጆቹ በጥቂቱም ቢሆን ተሸውደዋል። አሶሴትድ ፕሬስ ዜናውን ሲዘግብ፣ “The new ministers of foreign affairs — Workneh Gebeyehu, a former transport minister is Oromo, replacing the Tigrayans who previously held the posts.” ኦሮሞው ወርቅነህ ገበየሁ ትግሬ ይዞት የነበረውን የውጭ ጉዳይ ሚንስተር ተክቶታል ብሎናል።

ምነው እነ ደብረጽዮን በወርቅነህ ኦሮሞነት አመረሩ?  እኔ ያልገባኝ ወርቅነህ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት በሚፈቅደው ”ጉዲፈቻ” እና ”ሞጋሳ” ባህል መሰረት ወደ ኦሮሞነት ቀይረውታል እንዴ? ይህ ነገር ግልጽ ይሁን። ካልሆነ የሱን ማንነት የሚገልጸውን ዶክመንት እንልቀዋለን። ጥያቄው ሹመቱ ላይ አይደለም። ሲፈልጉ  ጠ/ሚኒስቴርም ያድርጉት። ግን በኦሮሞ ካርድ አስይዘው ማጫወታቸው ነው የሚደብረው።  የሕወሃት አባል ሆኖ ጨዋታውን በዚያው ካርድ ቢያደርገው ችግር የለውም። ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል  ይሚለውን የሂትለሩን ጎብልስ ብሂል የሙጥኝ ያሉም ይመስላል።

የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት መወገድ ያልተጠበቀ አልነበረም። ከፍተኛ የህወሃት አመራሮች የድል አጥቢያውን ታጋይ፣  ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን እንደማይወደዱት በስፋት ይነገር ነበር። ዶ/ሩ ፌስ ቡክ በብዛት ይጠቀማል። ስራውን ብርሃነ ገብረክርስቶስ ስለሚያከናውንለት ለፌስ ቡክ በቂ ግዜ ነበረው።  እታች ወርዶ ከተራው ዜጋ ጋር  በማህበራዊ ሜድያ መነጋገሩ ግን በህወሃት ዘንድ “ፖፑሊስት” የሚል ስያሜ አሰጥቶታል – ልክ እንደ አርከበ እቁባይ። በዘር መስፈርት ብቻ ከመንገድ ተወስዶ  የተቀመጠ ምኒስቴር ነበር። “ይሰረዝ !” ብለው ከፈረዱበት ቆይቷል። ከዚያ በፊት ግን ሁነኛ ሰው መፈለግ ነበረባቸው።  እነሆ አሮምኛ ተናጋሪ ትግሬ ተገኘ። የማኬያቬሊ ሊቅ!

በአሮጌ ጠርሙስ አዲስ ወይን ቢያቀርቡ አንድ ነገር ነው። በአዲስ ጠርሙስ አሮጌ ወይን ቢጨምሩ ደግሞ ሌላ የተለየ ነገር ሊመስል ይችላል። የነሱ ሙከራ ሁለቱም አይደለም።  በአሮጌ ጠርሙስ አሮጌ ወይን ይዘው የተሃድሶ ዘፈን ይዘፍናሉ። በአስተሳሰብም በመልክም አንድ የሆኑ የድሮ አሻንጉሊቶችን  እንደ እላቂ እቃ እያሽከረከሩ ያመጧዋቸውና ተሃደሶ ይሉናል።  ችግሮችን መፍታት ሲሳናቸው ስህተትን እንደመፍትሄ ይወስዱታል።  ሁለት ስህተት ደግሞ አንድ እውነት አይሆንም።  አሸዋወዱንም አላወቁበትም። ዳሩ ሕዝብ ቀድሟቸው ሄዶ እንዴትስ ያታልሉታል?

አካሄዳቸው የሚነግረን ነገር አለ። እነዚህ ሰዎች አሁንም ለለውጥ ዝግጁ አይደሉም።    ሕወሃት ፈጽሞ አይታደስም!

ህወሃት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ግድያ፣ ሙስና እና አፈና ከሃገሪቱ አይጠፋም። “አደገኛ ፎርስ ናቸው … ይጥፉ ወይንስ እንጥፋ!” ያለው ማን ነበር?

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር የምትወጣው ይህ ፋሽታዊ አገዛዝ ሲጠፋ ብቻ ነው!

Filed in: Amharic