>

ዓለምነህና ጸጋዬ አራርሶ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroዓለምነህ በአዋዜ ፐሮግራሙ ላይ ጸጋዬ አራርሳ ‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም›› ያለውን ይዞ በለዘበ ቋንቋና በለዘበ ድምጽ ደቁሶታል፤ ብዙ ሰዎች የገባቸው አልመሰለኝም፤ በጉዳዩ የተማረውና የተመራመረው ዶር. ጸጋዬ አራርሶም የገባው አይመስለኝም፤ እስቲ እኔ የገባኝን ልንገራችሁ፡፡
በመጀመሪያ በሁለቱ ሰዎች መሀከል ያለውን የትምህርት ደረጃ ልዩነት ዓለምነህ ራሱ እንዳለው እሱ ‹‹በትምህርት እጅግም አልገፋም፤›› ጸጋዬ ግን የትምህርቱን ደረጃ ጣራው ላይ አድርሶታል ተብሎ በስሙ ላይ ‹‹ዶክተር›› የሚል የትምህርት ማዕርግ እንዲጨምር አድርጓል፡፡
በትምህርት እጅግም ያልገፋው ሰው በትምህርት ጣራ ላይ በደረሰው ሰው አስተያየት ላይ የሰጠው ትችት የትምህርት ደረጃ የሚባለውንም ሆነ የሁለቱን ሰዎች እውቀትና ብስለት የሚለካ ነው፤ የዓለምነህ ትችት ስለቱ ያረፈው ጸጋዬ የሚልዮኖችን እምነት መካዱ ላይ ነው፤ ጸጋዬ እሱ ኢትዮጵያዊ ማንነት አንደሌለው ብቻ አልተናገረም፤ ማንም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ማንነት የለውም በማለትም እምነቱን ለጥጦታል፤ (ምናልባትም ኢትዮጵያዊ ማንንት ባለመኖሩ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለው የለም ብሎ ‹‹ያስብ›› ይሆናል፤ ግን የባሰ ገደል ውስጥ ያስገባዋል!) በጸጋዬ ላይ ያረፈው የዓለምነህ የሀሳብ ጉማሬ ጸጋዬ አንድ ብቻውን ሆኖ የሚልዮኖችን እምነት በመካዱ ላይ ነው፤ አንድ የተማረ ሰው (ያውም ጸጋዬ የሚል ስም ይዞ) ‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነት›› የለም ሲል እሱ የካደውን ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ከሱ ጋር በክህደት የቆሙለት ያስመስላል፤ በሌላ በኩል ስናየው አንድ የተማረ ሰው ክርስቲያን የሚባል ሃይማኖት የለም ቢል፣ አንድ የተማረ ሰው እስልምና የሚባል ሃይማኖት የለም ቢል … አለማወቅ ብቻ ነው ብለን አናልፈውም፤ ተንኮልም ያለበት መሆኑን ማጋለጥ አስፈላጊ ይሆናል፤ ዓለምነህ እዚህ አልደረሰም፤ ወይም ሊደርስ አልፈለገም፤ ዓለምነህ የሚለው የጸጋዬ ንግግር ብዙ ኢትዮጵያውያንን አቁስሎአል፤ ስለዚህም ይቅርታ መጠየቅ አለበት ነው፡፡

ጸጋዬ ለኢትዮጵያዊ ማንነት የሞቱትን ሁሉ እንደሰደበ አያውቅም ለማለት ያስቸግራል፤ ጸጋዬ የሕግ ምሁር ነው፤ በተለይም በሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ ይመስለኛል፤ እሱ እንዳደረገው የራስን ስሜት በአጠቃላይ ሕዝቡ ላይ መጫን፣ ወይም የሱን ክህደት በሕዝብ ላይ መጫን ከባድ ጥፋት ነው፤ ወደዚህ ጥፋት ያደረሰው ሌላ የተሳሳተ እምነት ነው፤ የግለሰብ መብቶች የመብቶች ሁሉ የማዕዘን ድንጋይ ነው፤ ጎሠኞች ከራሳቸው በቀር ግለሰብ አያውቁም፤ ሌላው ሁሉ ጎሣው ነው፤ የጸጋዬ አስተሳሰብ ከጎሠኛነቱ ያገኘው ነው፤ በጎሠኛነት አስተሳሰብ ጎሣ እንጂ ግለሰብ የለም፤ ጸጋዬ ይህንን አስተሳሰብ ወደጎሣ ፖሊቲካ ሲመነዝረው ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንዲክድ አደረገው፤ ዶር. ጸጋዬ አራርሳ በአንድ እጁ የኦሮሞን ሕዝብ በሙሉ ጨብጦ በሌላ እጁ ደግሞ የቀሩትን ኢትዮጵያውያን ጨብጦ በሁለቱም ላይ የራሱን የተለያዩና ተቃራኒ እምነቶች ሊጭንባቸው ይሞክራል፤ (ቅዠት እንዳይመስላችሁ!) እንኳን ከዚያ ታች (አንደሚባለው) ከአውስትራልያ ይቅርና ከአዲስ አበባም ቢሆን የእነዚህን ሰዎች አንድ ከመቶ ለማግኘት የሚችል አይመስለኝም፤ መንጠራራቱ ባልከፋ! ሲመለስ በምን ላይ ያርፋል አንጂ! ጸጋዬ የሕግ ምሁር በመሆኑ እንደሚያውቀው የግለሰቦችን መብቶች ይዞ ባልተነሣ ጥቅል እምነት ላይ ተመሥርቶ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ማንነት ላይ ፍርድ መስጠት ‹‹ይህን ያህል ያልተማረው›› ዓለምነህ እንዳለው ስሕተት ነው፤ ጥፋት ነው፡፡
እግዚአብሔር ለሁላችንም ብርሃኑን ያሳየን!

Filed in: Amharic