>
5:13 pm - Friday April 19, 6363

* ከሪዮ እሰከ ዲሲ፣ ከአማራ እሰከ ኦሮሚያ የህዝብ ሀቅ! [ነቢዩ ሲራክ]

* የህዝቡ ስሜት በየፈርጁ ይገለጻል ፣ ዛሬም  ጀግና ሙሽራ አየን   !
* ከሪዮ እሰከ ዲሲ፣ ከአማራ እሰከ እስከ ኦሮሚያ የህዝብ ሀቅ !
* እጁን ቆልፎ ” አቅመ ቢሶች ነን ፣ ታስረናል  !” ሲል ” አሸሻሪ ነህ ” አትበሉት
* ስማን ” ሰከን በል” ዘማች ፣ አዝማች ወታደሩ ፣ ሰከን   ! ! !

Meron- by Nebiy Sirakበደል ፣ ጭቆናና አድልኦና ግፍ  በከፋ ቁጥር ሀገሬው የጭቆና ቀንበር መሸከሙን አሻፈረኝ ይላል … የሰላም በሮች ሲዘጉ ፣ ለእንቢተኝነት በሮችን ይከፍታሉ  ! ሀገሬው እየተቀጠቀጠ እየተገዛም እንቢተኝነቱን በተለያዬ ፈርጄ  ብዙ መንገዶች ጉዳት ስሜቱን ሳይፈራ ደፍሮ ይገልጻል ።  ብዙዎቻችን ህመሙ እያመመን ሳንገልጸው ፣ አለያም ሆድ አደር ሆነን ስንንከላዎስ  የወገናቸውን ትክክለኛ ብሶት ፣ የህዝብ እውነት ፣ የአጋርነት ድምጽ በተለያዩ አጋጣሚዎች የገለጹ በእርግጥም የታደሉ ናቸው  ! በቅርብ ወራትበፊት በሪዮ አትሌት ፈይሳ ሌሌሳ ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ በዲሲ በአንዲት መልከ መልካም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊት ሠርግ ላይ ያየነው ነፍሳችን በሃሴት ነጥቆናል ፣ እናም ከሪዮ እስከ እሰከ ዲሲ፣ ከአማራ እሰከ እስከ ኦሮሚያ የተመለከትነው የህዝብ አጋርነት የህዝብ እውነት እውነታችን ነውና የሀገረ አሜሪካ የዲሲዋን ሙሽራ  በዛሬው የማለዳ ወግ ክብር ሰጥተን እናወሳታለን    !

” ሰከን በል  ” የሚለውን የአርቲስት ይሁኔ በላይን ወኔ ቀስቃሽ ወቅታዊ ዘፈን በሠርጓ ቀን እንዲዘፈን የመረጠችው ሀገር  ወዳድ አስገራሚና አስደናቂ ሙሽራ ቪዲዮ የደረሰኝ ከትንናት በስቲያ ነው  ፣ መረጃውን ያደረሱኝ ደግሞ እዚህ ሳውዲ የሚገኙ ቤተሰቦቿ ናቸው ። ስመለከተው በስሜት የሸነቆጠኝን የሙሽሪት ልዩ የሀገር ፍቅር መግለጫ የሆነውን የሙሽሪት የሠርግ ቀኗ ምርጫ ” ሰከን በል ” ጣዕመ ዜማ ልዩ መልዕክት የሰማሁት በመሪሩ ሀዘን ሳምንት መካከል ቢሆንም ዜማው ከፈንጠዝያና ዳንኪራ የወጣ መልዕክት አለውና ከሙሽሪት ወኔ ጋር ” ሰከን በል  ”  ሰከን በል እያልን ስለሚያገባን እናዎጋለን  …  !

የሙሽሪት ሜሮንን ቪዲዮ እንዳሰራጨው ጠየቄ በሙሽሪት ቤተሰቦች በኩል ሙሉ ፈቃድ ሰጥተውኝም ነበር ።  ቢሸፍቱ አልቅሳ ቀኑ ጥቁር የሀዘን ቀን ስለነበር ከማሰራጨት ወኔውን አጣሁት  … መረጃው ሲደርሰኝ ሠርጉ በሃገረ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እንደተከወነ የገለጸችልኝ እህቷን  የሙሽሪትን ሙሉ ስሟን ማን ይባላል ስል ጠየቅኳት  ፣ መለሰችልኝ  ” በስሟ ትገረማለህ ሜሮን መሀመድ ያሲን ትባላለች ፣ ለእኔ የእናቴ ልጅ ናት በአባቷ አፋር ናት ፣  እሷ ግን ክርስቲያን ናት ፣ መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ የቀራት ገድማት ቤተክርስቲያን የለም ፣  እንደሚመስለኝ ብቸኛዋ የአፋር ክርስቲያን እሷ ናት ! ”  አለችኝ   !  ተደመምኩ  ፣  አፋሮች ሲነሱ አባት አሊ ሚራህ ትዝ ይሉኛል ፣  ” የኢትዮጵያን ባንዴራ እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል  !” ሲሉም በቦታው ነበርኩ   !  አሳይታ  … የአፋሯ ሙሽራ ስለ ኢትዮጵያ የሆነችውን ብትሆን እሷ የጀግኖች ዘር መሆኗ ነው አክኩና አሁንም በሰማሁት ታሪክ ተደመምኩ  !

ብቸኛዋ የአፋር ክርስትያን ልትሆን የምትችለው ሙሽሪት ሜሮን ዛሬ የወገኗ ነገር አንገብግቧት  ” ሰከን በል ” እያለች በሠርጓ አዳራሽ በስሜት ስትውረገረግ ፣ እጆችዋን ወደ ላይ ከፍ አድርጋ ከነሚዜዎቿ በማንሳትና በማቆላለፍ ከህዝቡ ጋር መሆኗን በልዩው የሠርጓ ቀን በወኔ ተሞልታ ስታሳይ አለቀስኩ … በሚታየው ጥልቅ ስሜቷ ውስጤን  ነካችውና ሆዴ እንደ መባባት አለ  …

” ሰከን በል ”  የሀገር ወዳዱ የታዋቂው ዘፋኝ የይሁኔ በላይ የአዲስ አመት ልዩ ማስታወሻ ቢሆንም ሰከን ባላለው ወታደር ህዝብ እየተጨፈጨፈ ላዘነ ለተቆጨና  እንደኔ ቆሽቱ ላረረው ጥሩ ሰሜት መግለጫ ሆኖም ሰንብቷል … ዛሬ በሙሽሪት እጅ በአዳራሹ ገብቷል … ሙሽሪትን ደጋግማ ” ሰከን በል ” ስትል ስማኋት ፣ ከአርቲስት ይሁኔ ድምጽ እኩል ስታዜመው  ” ሰከን በል  ” ስትል ሰማኋት ፣ ሰከን ማለት ደግሞ ግድ ይላል  ! ወታደሩ ሰከን በል  ፣ ገዳይ አስገዳይ ጨምላቃው ፖለቲከኛም ሰከን በል  ፣ የሚሞተው  ወንድምህ ነው ፣ የሚሞተው  እህት ናት ፣ እናም ሰከን ማለት ይበጅሃል ፣ ሰከን በል  ! ስትል እስክታውን በቁጭት ስታስነካው የፈንጠዝያና ዳንኪራ ስሜት ላለመሆኑ ያሳብቅባታል  !

የሰከነ ነገር ጠፍቶ …እዚህም እዚያም ግፍ በዝቶ የማንፈልገውን እንድንደግፍ ፣  እንድንመርጥ እየተገፋን ነው …የምንወዳት ሀገራችን  ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ መጓዝን በውል ለታዘበ  ይህ እውነት የማያንገበግበው ወገኔ የለም ፣ እናም ሙሽሩት ሜሮን አንዷ ናት ፣ የሙሽሪት ሜሮን ሰከን በል ምርጫ ከእነ ሙሉ እንቅስቃሴዋ እየተመለከትኩ በሙሉ ሀገራዊ ወኔ በሀዘን ውስጥ ሆኖም በቁጭት እልህ ጥልቅ ስሜት ተዘፍቆምና በሀዘን ስሜት ውስጥ ገብቶ በእልህ ይነሸጣል  …

ይሁኔና ሙሽሪት  ” ሰከን በል ”  እያሉ ባንድ መድረክ የተጫወቱትን ያህል ሰርጾ ሊገባ የቻለው እንቅስቃሴ መሰረቱ በውስጡ ያለው እውነት ለመሆኑ አልጠራጠርም ። በሙሽሪት የደስታ ቀን በሀገር ስሜት ዋጅታ በነፍሷ አልፎ በፊቷና በመላ አካሏ የሚታየው  ቁጭት ብሎም የወገናዊነት ፣ የህዝባዊነት ስሜት እውነት ቁልጭ ብሎ በሙሽሩት ላይም ይታያል  !  ያ ብዙዎች ዘንድ በጥቂቶች ላይ ያደረው  የወገናዊነት ” ያገባኛል “ስሜት  እውነት በእርግጥም በሙሽሪት ይገለጻል  !  በሀገረ አሜሪከ በዲሲ ከተማ በታላቁ የሙሽሪት የደስታ ቀን የሠርጓ እለት አብሮበትና ከህዘብ አጋር መሆን ስለእውነት እንዲህ ወኔን ቀስቃሽ ሆኖ ጀግንነት በየፈርጁ እንድናይ ምክንያት የሆነችውን ሜሮን  ጀግና የእኛ ሙሽራ ብያታለሁ  🙂

ሙሽሪት ሜሮን ” በሰከን በል ” ልዩ ሀገራዊ ጣዕመ ዜማ ያንጸባረ ቀችው  ሀገሬ ተጎዳች በሚል ቁጭትን ” መለያየት አይጠቅምም በማለት ነበር  …
” ድር እንኳን ቀጭኑ ድር እንኳን ለስላሳው
ሲያምር ሲተባበር ይበልጣል ካንበሳው  ” ይል ዘንድ ይሁኔ በሜሮን ሰርግ  አብሮነትና የሀገር ፍቅርን በልዩ መሳጭ ስሜት ተሰብኳል   !
” ወታደሩ ሰከን በል
አፈሙዙን ሰከን ዐርገዉ
ቃታዉን እንዳተትስበዉ
ቧዶ እጁን ነው እሚጮኸው
ሠላማዊ ወንድምህ ነዉ  ”  ተበሎም ወታደሩ  “ተረጋጋ ፣  ሰከን በል ” ትበሎ ወታደሩ ምክር ሲለገሰው ” ሰከን ማለት ነው ጀግንነት ”  ተብሎ በሰርጉ አዳራሽ በህበረት ተስተጋብቷል  ፣ ያውም በልዩው የግሏ የደስታ ቀን   …   ! ጀግናዋ የኢትዮጵያ ሙሽራ  !

ህዝቤን ተውት እንዲል ደጉ አባት  … ባለቅኔው አንጎራጓሪ ” ሰከን በል ” ሲል በሰራው ነጠላ ዜማ አዛዥ ፣ ገዳይ  ፣ አስገዳይ አዛዦችም   እንዲህም ተብለዋል በይሁኔ ማራኪ ጣዕመ ዜማ
” ሰከን በሉ ህዝቤን ተዉት
ድምጹን ስሙት ፣አትግደሉት
መንግስት በአገሩ በህዝብ ላይ አይተኩስ
ዘር አጥያት ይሁን ንጉስ ከማሪዮሰ ”  የተባለው በሙሽሪት ሠርግ ላይ ደምቆ ሲሰማ ማስተዋል ፣ በተበደለ ህዝቧ የተጎዳ የሙሽሪትን ስሜት ማየት ያልቻላችሁ ካላችሁ ስሜታችሁን ፈልጉት  … እኔ ይህን የሙሽሪትን ሠርግ “ሰከን በል  !” ምርጫና ፣ የመልከ መልካሟን እህት ውስጥና ውጫዊ ስሜት ተረድቸው ረክቸበታለሁ  !

ሰሚ ቢገኝ ሀገሬው በደስታ በሀዘን ፣ በየተናጠል በህብረት ስሜት ፍላጎቱን  ፣ የዲሞክራሲ ጥማት ነጻነቱን እየጠየቀ ነው ፣ ሆዳም ካልሆነው ተትረፍርፎ ከሞላው እስካጣ የነጣው እጁን ወደ ላይ በማንሳት ” አቅመ ቢሶች ነን ፣ ታስረናል  !”  ብሎ የተቃውሞ ድምጹን ሲያሰማ ” አሸሻሪ ነህ ” አትበሉት   ! የውስጥ እውነቱ ፣ የተቃውሞ ህብረቱ መገለጫ ምልክት አድርጎታልና እየመረራችሁም ቢሆን ተቀበሉት  !

ሙሉ የሙሽሪት ሜሮንን ቪዲዮ እንዳሰራጨው ጠየቄ በሙሽሪት ቤተሰቦች በኩል   ሙሉ ፈቃድ ሰጥተውኝም ነበር ።  ቢሸፍቱ አልቅሳ ቀኑ ጥቁር የሀዘን ቀን ስለነበር ከማሰራጨት ወኔውን አጣሁት  … መረጃው ሲደርሰኝ ሠርጉ በሃገረ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እንደረከወነ የገለጸችልኝ እህት  የሙሽሪትን ስሟን ማን ይባላል ስል ጠየቅኳት  ፣ መለሰችልኝ  ” በስሟ ትገረማለህ ሜሮን መሀመድ ያሲን ትባላለች ፣ ለእኔ የእናቴ ልጅ ናት በአባቷ አፋር ናት ፣  እሷ ግን ክርስቲያን ናት ፣ መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ የቀራት ገድማት ቤተክርስቲያን የለም ፣  እንደሚመስለኝ ብቸኛዋ የአፋር ክርስቲያን እሷ ናት ! ”  አለችኝ   !  ተደመምኩ  ፣  አፋሮች ሲነሱ አባት አሊ ሚራህ ትዝ ይሉኛል ፣  ” የኢትዮጵያን ባንዴራ እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል  !” ሲሉም በቦታው ነበርኩ   !  አሳይታ  …

ብቸኛዋ የአፋር ክርስትያን ልትሆን የምትችለው ሙሽሪት ሜሮን ዛሬ የወገኗ ነገር አንገብግቧት  ” ሰከን በል ” እያለች እጆችዋን ወደ ላይ በማቆላለፍ ከህዝቡ ጋር መሆኗን በልዩው የሠርጓ ቀን በወኔ ተሞልታ አሳይታናለች ፣  እናመሰግናለን   !

እናንተም!  ሙሽሪትን ስሟት !  ” ሰከን በል  ” ትላለች ፣ ሰከን ማለት ደግሞ ግድ ይላል  ! ወታደሩ ሰከን በል  ፣ ገዳይ አስገዳይ ጨምላቃው ፖለቲከኛም ሰከን በል  ፣ የሚሞተው  ወንድምህ ነው ፣ የምትሞተቅ እህት ናት ፣ እናም ሰከን ማለት ይበጅሃል ፣ ሰከን በል  !

ለጀግናዋ ሙሽራ መልካም ጋብቻ ተመኘሁ   !

ሰናይ ቀን   !

ነቢዩ ሲራክ
መስከረም 24 ቀን 2009 ዓም

Filed in: Amharic