>

አዲሱ ዓመት በእውነት አዲስ ይሁንላችሁ! [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroለሁላችንም የነጻነት፣የሰላም፣ የፍቅር፣ የሥራና የብልጽግና ዓመት ይሁንልን
ተጠየቅ መስከረም!
ተጠየቅ መስከረም፤
ዛሬስ ዋዛ የለም!
አንተን ለመቀበል እንቁጣጣሽ እያልን፤
ከርስ እንሞላለን፤ እንሳከራለን፤ እንጨፍራለን፡፡
አልገባኝም እኔን አንተ መወደድህ፤
ስትገባ ስትወጣ ድግስ መቀበልህ፤
ዶሮው፤ በጉ፤ ሰንጋው ይታረድልሃል፤
ርጥብ ቄጠማና ደም መውደድህ ታውቋል፡፡
እንስማው ተናገር፤
የያዝከውን ነገር፡፡
ስጦታህ ምንድን ነው? ለኛ ያመጣኸው?
ክፈተው ሣጥንህን፤ እስቲ እንመልከተው፡፡
ለምለሙን ሳር እንደሁ ይጋጡት ከብቶቹ፤
ለኛ ምን ይዘሃል? ለኛ ለሰዎቹ?
ሞት ሊጠፋ ነው ወይ ባዲስ ፍልስፍና፤
መድኃኒት አመጣህ? ለሕመም.. ደሀነት ለኛ ድንቁርና?
ተጠየቅ መስከረም፤ ያመት መጀመሪያ፤
መነሻ፤ መድረሻ የሰው ልጅ የታሪክ መቁጠሪያ፡፡
ተጠየቅ መስከረም ማን አዲስ ይለብሳል? ቡቱቶውን ጥሎ፤
ፎቅ ቤት ማን ይሠራል? ጎጆውን አቃጥሎ፡፡
ተጠየቅ መስከረም፤ ያለፈው መስከረም ምን ታሪክ ነገረህ?
ምን ሰማሁ፤ ምን አየሁ፤ ምን ተሰማኝ አለህ?
መዝገቡ ምን ይላል? አንብበው፤እንስማው፤
የቱ ያመዝናል? ሥራ ነው? ምኞት ነው?
መስከረም ተጠየቅ፤
ተናገር፤ አትሳቅ!
ጎተራው ተሟጦ በዕዳ ለታሰረው፤
ለዚያ ለገበሬ ሳያርፍ ለሚሠራው፤
ሚስቱና ልጆቹ እየተላቀሱ ለሚፈጽም ተግባር፤
በጦር ግንባር ላለው ለዚያ ለወታደር፤
ካልጋ ተቆራኝቶ ታሞ ለሚያጥረው፤
ወይ አይሞት፣ ወይ አይድን ስቃይ ለታደለው፤
ለወላድዋ ድሀ ባልዋ ለሞተባት፤
የልጆችዋ ረሀብ ሰቀቀን ለበላት፤
ምን ይዘህ መጥተሃል?
ተናገር፤ እስቲ በል!
በፍርሃት፤ በስጋት፤ ስቃይ ለሚበሉት፤
ፍትሕ ይዘህ መጣህ ወይ? ሕግና እኩልነት፤
ሰላም አመጣህ ወይ? ነጻነትና ሀብት፤
ሰውን ልታድስ ነው? ወይስ ልታሻግት፤
የዘንድሮው አክሊል ትጋት ነው ስንፍና፤
ችግር ደባል ነው ወይ ዘንድሮም እንዳምና!
ተናገር… ላዳምጥህ፤
ትዝብት አይሰለችህ፤
ለኔ ያመጣኸው በሳቅህ ገብቶኛል፤
አንዲት ጥያቄ ናት ምን ሠራህ የምትል?
ይጭነቅህ ይጥበብህ ግራ ይግባህ አንተም፡፡

Filed in: Amharic