>

"የትግራይ ሕዝብ እና ሕወሓት አንድ ናቸው/አይደሉም"!? (በፈቃዱ ዘ ኃይሉ)

BefeQadu Z. Hailuጥያቄውም መልሱም ያናድደኛል። ነገር ግን ብሸሸውም አምልጬው አላውቅም። ዛሬም ከሁለቱም ወገን ሆነው ስህተትን በስህተት ለማረም እየተረባረቡ ያሉ ጓደኞች ስላሉኝ፤ ይሄ ጥረታቸውም በመሐላቸው ያለውን ልዩነት እያሰፋው እና እያከረረው ስለሆነ የበኩሌን ሳልል ማለፍ እንዳይቆጨኝ ነው መጻፌ።

የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን ይደግፋል፤ so what?

በኦሮሚያ እና በአማራ ኦሕዴድ እና ብአዴን ካላቸው ቅቡልነት ወይም ደኢሕዴን በደቡብ ካለው ተወዳጅነት ይልቅ ሕወሓት በትግራይ ያለው ቅቡልነት/ተወዳጅነት ይበልጣል። ሌላው ቀርቶ በትግራይ የሕወሓት ተቃዋሚዎች (ሁሉም ባይሆኑ እንኳ በጣም ብዙዎቹ) የሚያፀድቁለት/የሚያደንቁለት ገድል አለ። ለዚህ የሕወሓት በትግራይ ሰፊ ተወዳጅነት ማግኘት ደግሞ በቂ (?) ምክንያቶች አሉ፤ ፩ኛ) ሕወሓት እንደሌሎቹ ፎርጂድ አይደለም፤ ፪ኛ) በሌሎች ወገኖች ትግራዋዮችን ሁሉ በጥቅሉ በሕወሓት ዓይን እያዩ የመፍራት፣ የመጠርጠርና የመጥላት ገፊ ምክንያቶች አሉ፤ ፫ኛ) ሕወሓት በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ ያለውን የበላይነት ተጠቅሞ ለልኂቃኑ በረከት እያዘነበ ስለሆነ ብዙኃኑም ባይዘንብ ያካፋልኛል ብሎ የሚያስብበት ጎታች ምክንያት አለው፤ ፬ኛ) የኛው ናቸው በሚል የገዢነት ሥነ ልቦናን (entitlement) በነሱ በኩል መውረስ አለ።

በነዚህ ምክንያቶች ብዙኃኑ ትግራዋይ ሕወሓትን ይደግፋል (ብዬ አምናለሁ)። ጥያቄው ሲነሳ የትግራይ የዴሞክራሲ አራማጆች የሚሰጡት መልስ “የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን አይደግፍም” የሚል ነው። እርግጥ ያንን ማስረጃ መረጃ ይኖራቸው ይሆናል። እኔን የሚያሳምነኝ ግን እስከዛሬ አላገኘሁም። በኔ ግምት ግን መልሳቸው መሆን የነበረበት “እና ምን ይሁን?” የሚል ነበር። ከደገፈ በቃ፣ ምንም ማድረግ አይቻልም፤ የራሳችን ሕዝብ ነውና ድጋፉን መቀበል አልያም ከዚያ የተሻለ የሚደግፈው አማራጭ መስጠት ነው።

በተቃራኒው ግን ተቃዋሚው ለትግራይ ሕዝብ ምን ቃል ገባለት? ምንም። እንዲያውም ጥቂት የማይባለው የተቃዋሚው ወገን የትግራይ ልኂቃንን ከትግራይ ሕዝብ ጋር ጨፍልቆ ሲዝትባቸው መስማት አሁን–አሁን መብት መስሏል። ስለዚህ፣ የትግራይ የዴሞክራሲ አራማጆች በአሁኑ ሰዐት በተከላካይነት ቦታ ራሳቸውን ማስቀመጣቸው የሚገርም አይደለም። የሚያዋጣ ባይሆንም።

በሌላ በኩል የሕወሓት ደጋፊ አንጋሾች ደግሞ አጋጣሚዋን በመጠቀም የተፈጠረውን ካልተፈጠረው ጋር በማራገብ (ሁሉም ሠላማዊ ሰው ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ካለ ማውገዝ ሲችሉና ሲግገባቸው) የትግራይ ተወላጆች ላይ ብቻ የደረሰውን ጥቃት እየነቀሱ በማውጣት እና የግጭቱን መልክ በመቀየር ቀዳዳውን ያሰፋሉ (ላልቶ ይነበብ)። ሕወሓቶች በአጋጣሚው የትግራይ ሕዝብ ጠባቂ በመምሰል ወትሮም ያላቸውን “ከነሱ ውጪ አማራጭ የለንም” የትግራዋዮች ብሒል የሚያገኙት ከራሳቸው ከተቃሚዎቹ ስህተት እና ስህተቱን እጥፍ ድርብ አጋንነው እና ቀጣጥለው ከሚነግሯቸው የሕወሓት አንጋሾች ነው።

“ሁሉም ፍረጃዎች (stereotyping) በጥቅሉ ትክክል ናቸው”

ትግራዋዮች ሕወሓትን ይደግፋሉ የሚለው አባባል የሚያበሳጫቸው ብዙ ትግራዋዮች አሉ። በሌላ ወገን “የትግሬ አኩራፊ እንጂ ተቃዋሚ የለም” የሚል ተረት ተፈጥሯል። ለኔ፣ እነዚህ በፍረጃው የሚበሳጩት ሰዎች ጥቂቶች እንጂ ብዙኃንን አይወክሉም (they are exceptions, not the norm)። ከዚህ በፊት ኦሮሞ ሁሉ ሲፋቅ ኦነግ ነው፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ በሙሉ ሲፋቅ አማራ ወይም አማራናይዝድ ነው ተብሏል። እነዚህ አባባሎች ከባዶ ሜዳ የፈለቁ አይደሉም። የብዙኃን እውነታዎች ናቸው። በዚህ ግዜ ‘ጥቂቶቹን’ (exceptional) መሆን ፈታኝ ነው። ቢሆንም ግን የብዙኃኑን እውነታ የጥቂቶቹ ዲስኩር አይለውጠውም።

“ቤት የእግዚአብሔር ነው” የሚለው ብሒል ላይ “ኮንዶሚኒየም የገብረእግዚአብሔር” የሚል ተጨምሮበት ተረት ሆኗል። ያለ ምክንያት የሆነ ነገር አይደለም። በተለይ በአዲስ አበባ አዳዲሶቹ የኢኮኖሚ ዘውዋሪዎች እና የንብረት ባለቤቶች ትግራዋይ መሆናቸውን ሕዝብ አይቶ የደረሰበት ጥቅል ፍረጃ ነው፤ (ለሁሉም ላይሠራ እንደሚችልም መረዳት ቀላል ነው)።

የትግራይ ተወላጆች በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ ያላቸው ያልተመጣጠነ ጉልህ ድርሻ፣ በመከላከያ እና ደኅንነቱ ውስጥ ያላቸው ፍፁም የበላይነት፣ በቢዝነሱ በጥቂት ግዜ የሚከብሩ ልኂቃኖቻቸው፣ ወዘተ… ከዚያም በላይ በኢሕአዴግ ሥር ያሉ ሦስቱ ፓርቲዎች የሕወሓትን ፍልስፍና እና ኢትዮጵያን የመግዛት ዓላማ እንዲደግፉ ተደርገው እንደተፈጠሩ ይታወቃል። ይሄ ሁሉ የትግራይን አንፃራዊ እና የትግራይ ልኂቃንን ፍፁማዊ ኢፍትሓዊ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል። እነዚህን ሐቆች ንቆ “ሕወሓት የሚያስተዳድረው ትግራይን ብቻ ነው፣ የጨቆነው የትግራይን ሕዝብ ብቻ ነው፣ የሚጠየቀውም ትግራይ ውስጥ ለፈፀመው ብቻ ነው…” የሚሉ መከራከሪያዎች ልዩነታችንን ያሰፉ እንደሆን እንጂ አያጠብቡትም።

“ትግራይ ለምን አታምፅም?”

ሸገር ለምን አታምፅም? የሚደርስበት በደል እና ግፍ ተሰፍሮ የማያልቀው እና በቁጥር ከትግራይ ሕዝብ የሚበልጠው የሶማሊ ሕዝብ ለምን አያምፅም? የአኙዋ ሕዝብ፣ የቤኒን ሕዝብ፣ የአፋር ሕዝብ ለምን አያምፅም? ለነዚህ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል እንጂ እርግጡን መናገር አይቻልም። ግን ሕዝብን የሚያሳምፅ አንድ ነገር አለ፤ ተስፋ አስቆራጭ ሲደመር ተስፋ ሰጪ ሁኔታ። ሁለቱም አብረው ካልታዩት የቱም ሕዝብ አያምፅም።

ለመዝጊያ መንደርደሪያ ከሦስት ዓመት በፊት ከአብርሃ ደስታ ጋር የተጨዋወትነውን ልንገራችሁ። አብርሃን የትግራይ የበላይነት ስለሚባለው ጠየቅኩት። እንዲህ አለኝ፤ “በፊት በትግራይ በየዞኑ ያሉ ኃላፊዎች የአድዋ ተወላጆች ነበሩ። ይሄ ለምን ሆነ ብዬ መጠየቅ ጀመርኩ። ብዙ በጠየቅኩ ቁጥር በኢትዮጵያ ባሉ የመንግሥት ኃላፊነቶች ለምን ትግራዋዮች ብቻ ኖሩ ይባላል። ሳየው እነዛ በሚኒስትርነት የተቀመጡ ሰዎች እኔና ወዳጅ ዘመዶቼን አይወክሉም። በየዞኑ ኃላፊ የሆኑትም የአድዋ ልጆች የአድዋ አካባቢ ሕዝብን አይወክሉም ማለት ነው አልኩ” እንዳለኝ አስታውሳለሁ።

አዎ። ሕወሓት መጀመሪያ “ትግል ላይ” ሳለ ሲሰነጠቅ በአድዋ፣ አክሱም እና ሽረ ሰዎች በተነሳ የሥልጣን ፉክክር ነው። ኋላ ላይም እነስየ ሲባረሩ ለሻዕቢያ ሰዎች ስሱ ልብ ባላቸው እና የትግራይ ብሔርተኝነትን በሚያስበልጡ ሰዎች መካከል በተነሳ ፉክክር ነው። የትግራይ ሕዝብ እና ሕወሓት አንድ ቢሆኑ እንኳ ሕወሓቶች (የጋራ ጠላት ካላዋደዳቸው በቀር) አንድ አይሆኑም።

Filed in: Amharic