>

''ከሀብታሙ አያሌው ጋር ዛሬ በጤናው እና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ...'' (ኤሊያስ ገብሩ)

Habtamu Ayalew by Elias Gebiru 16082016“በህዝብ ትግል የህወሃት ካምፕ ይፈርሳል፤ …አንድ በሆንን ማግስት ህወሃት እንደጥዋት ጤዛ እንደሚረግፍ አልጠራጥርም”
“የአማራውን ህዝብ እንደ ቅጥል ማርገፍ የጀመሩት ዛሬ አይደለም”
“የህወሃት ሰዎች እንደደርግ ወታደር ኮፊያቸውን ዘቅዝቀው የሚቆሙበትን መሬት በኦሮሚያ ተወላጆች ደም ስላጨማለቁት መጨረሻቸው እጅግ የከፋ እንደሚሆን ይሰማኛል”
“በዚህ ወቅት የትግራይ ህዝብ ይሄንን ጨቋኝ ስርዓት ነቅሎ ለመጣል የተለየ ታሪካዊ ሃላፊነት እንዳለበት ይሰማኛል”
ሃብታሙ አያሌው

/ከሀብታሙ አያሌው ጋር ዛሬ በጤናው እና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ስንጨዋወት አጽንኦት ሰጥቶ የተናገራቸው ጠንካራ ሀሳቦችን እንዲህ አሰናድቼዋለሁ/

“በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ በተለያዩ ቦታዎች በህወሃቶች ትዕዛዝ ሳቢያ በጥይት ተመትተው በሞቱ ወገኖቼ እጅግ ሲበዛ አዝኛለሁ። እነዚህ በግፍ በህወሃት የሞቱ ሰዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ህያው ሰማዕት ሆነው ለዘላለም ይኖራሉ።
ወልቃይትን በሚመለከት፣ በእኔ እምነት ህዝቡ ማንነቱ እንዲረጋገጥለት ጥያቄ እያቀረብ መሆኑን አውቃለሁ። ይህን እንድረዳ ያደረገኝ አሁን የተደረገው አመጽ አይደለም። ህወሃት/ኢህአዴግ ጋር በነበርኩበት ጊዜ በከፍተኛ ምስጢር ይዞ ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ በታዘብኳቸው ጊዜ በድርጅቱ ላይ እምነት እንዳይኖረኝ ካደረጉ እኩይ ተግባሩ አንዱ የወልቃይት ጉዳይ ነበር።

የህወሃት የመስፋፋት ዘመቻ ወሎን፣ አፋርን፣ ወልቃይትን፤ አሁን ደግሞ ጎንደርንና ጎጃም ጋር ከሱዳን የሚዋሰኑበትን ሰፊ ድንበር እስከ ህዳሴው ድልድይ ድረስ አጠቃልሎ ታላቅ የሚሏትን ትግራይ ለመመስረት ያለመ ነበር። የአማራውን ህዝብ እንደቅጠል ማርገፍ የጀመሩት ዛሬ አይደለም። ይህንን ሴራ ከእነሱ ጋር እያለሁ ስለተረዳሁ ከዚያ የጥፋት ድርጅት ወጥቼ የቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲን በመቀላቀል በጎንደር ብቻ ሁለት ታላላቅ ሰልፎችን በመምራት እንዲህ የህዝቡ መብት እንዲከበር ብርቱ ጥረት አድርጌያለሁ። ድንበሩን/መሬቱን በተመለከተም ጥናት በማድረግ በአዲስ አበባ በፓርቲው አዳራሽ ጥናቱን ለህዝብ አቅርቤያለሁ።

የኦሮሚያ መሬት ከተማ በማስፋፋት ስም ህወሃቶች ሊቀራመቱት የያዙትን ዕቅድ የማውቅ በመሆኑ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችን በመምራት ትልቅ ተቃውሞ ሳደርግ ነበር።

ስለዚህ አሁን የሚሰማኝ፣ በዚህ ወቅት ህዝቡ ለትግል ተነሳስቶ በህወሃት በአደባባይ ሲገደል አልጋ ላይ የወደኩ ደካማ ብሆንም በቁጭት ከማልቀስ በቀር ሀዘኔን የምገልጽበት ነገር አጥቻለሁ።

አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ፣ በህዝብ ትግል የህወሃት ካምፕ ይፈራርሳል። የህወሃት ሰዎች እንደደርግ ወታደር ኮፍያቸውን ዘቅዝቀው ለመለመን የሚቆሙበት መሬትን እንኳን በኦሮሚያ ተወላጆች ደም ስላጨማለቁት መጨረሻቸው እጅግ የከፋ እንደሚሆን ይሰማኛል።

በዚህ ወቅት የትግራይ ህዝብ ይሄንን ጨቋኝ ስርዓት ነቅሎ ለመጣል የተለየ ታሪካዊ ሃላፊነት እንዳለበት ይሰማኛል።
አሁንም አላለሁ፣ እመነኝ ደርግ ወድቋል፣ ኢህአዴግም ይወድቃል። ድል የህዝብ ነው። በዚህ ታሪካዊ ወቅት አማራና ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የህወሃት አገዛዝ ለመጣል ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ሆኖ መቆም አለበት። አንድ በሆንን ማግስት ህወሃት እንደጥዋት ጤዛ እንደሚረግፍ አልጠራጥርም!

መታመሜን ተከትሎ በተለያየ መንገድ ከጎኔ ዛሬም ድረስ ለቆማችሁ በሙሉ ከልብ ዳግሜ ማመስገን እወዳለሁ። አሁን በቀን 400 ሚሊ ግራም ማደንዘዣ (ፔቲዲን) እየተወጋሁ ነው። በዚህ ሁኔታ እንዴት እንደምዘልቅ አላውቅም። ይህ ያሳስበኛል። ምን ያህል ሰውነቴን እንደሚጉዳው አላውቅም። ማደንዘዣው የጎንዮሽ ጉዳት አለው። ዛሬም ድረስ ሌላ ህክምና ስላላገኘሁ ሌላ ኢንፌክሽን ተፈጥሮ የባሰ ነገር እንዳይከሰት በመከላከል ላይ እገኛለሁ። በአብዛኛው ፀበል እና እምነት (ቅባ ቅዱስ) ነው የምጠቀመው።”

Filed in: Amharic