>

ጠቅላይ ሚንስትሮቹ የሀይማኖት አባቶች [ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ]

Bedilu Waqjira DR‹‹ . . . ሰሞኑን በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ሁከት በመታቀብ ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግና በጋራ መረባረብ እንደሚገባ የሀይማኖት አባቶች አስገነዘቡ፡፡ . . . አያይዘውም ወላጆችና ምሁራን ልጆቻቸውንና ወጣቶችን በመምከር የሰው ህይወትን ከጥፋት፣ ንብረትን ከውድመት በማዳን፣ ለእድገትና ለብልጽግና መረባረብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡ . . . ›› ይህ ዛሬ በፋና ድህረ ገጽ ላይ ያዳመጥኩት ዜና ነው፡፡ (በነገራችን ላይ፣ ብዙ አንባቢዎቼ ኢቲቪንና እንደፋና ያሉ የመንግስት ሚዲያዎችን ስጠቅስ፣ ‹‹እንዴ አንተም እነዚህን ታያለህ? ታዳምጣለህ?›› ይሉኛል፤ በመደነቅ፡፡ አዎ! እያሰለስኩ አያለሁ፣ እና የፖለቲካችንንና ያስተዳደራችንን ዝቅጣት እንደነሱ ፍንትው አድርጎ ማን ያሳየኛል!?) ለምሳሌ ከላይ ያለው ዜና በአንድ የኢህአዴግ ካድሬና በሀይማኖት አባቶቻችን መካከል ቅንጣት ልዩነት እንደሌለ ይነግረኛል፡፡
.
ሀይማኖት ከፖለቲካ ይርቃል፤ መንገዳቸው ብቻ ሳይሆን፣ ቋንቋቸውም ለየቅል ነው፡፡ አንዱ ብልጽግና ሌላው ለሰማያዊው ልእልና ይተጋሉ፡፡ ጥሩ ፖለቲከኛ ገጥሞን ባያውቅም፣ ሀገራችን የተቀደሱ የሀይማኖት አባቶች ነበርዋት፤ የፍቅርን፣ የሰላምንና የጽድቅን መንገድ የሚመሩ፡፡ በቅርብ ጊዜ እንኳን (1983 ወያኔ አዲስ አበባ ሲቃረብ) የደም መፋሰሱ እንዳይኖር፣ ጸሎት እንዲያደርጉ የሀይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን ጠርተው ነበር፡፡ ይህ ነው የሀይማኖት መንገድ! ፖለቲካው ጠመንጃ ይዞ ‹‹ግፋ በለው›› ሲል፣ ሀይማኖት በጸሎት ፈጣሪን ይለምናል፡፡
.
የጠቅላይ ሚንስትራችን ‹‹ልጆቻችሁን ምከሩ፤ ልማቱ እንዳይደናቀፍ . . ›› ያለምንም ለውጥ በሀይማኖት አባቶች ‹‹ቡራኬና ምክር›› ሆኖ መቅረቡ፣ ኢህአዴግ ህዝቡን ለመቆጣጠር ምን ያህል፣ በጭካኔ ከድንበሩ አልፎ እንደሰራ ሲያሳይ፣ የሀይማኖት አባቶችችን ደግሞ ምን ያህል ምድራዊና አለማዊ እንደሆኑ፣ ከሀይማኖቱ ከቅዱስ ቃሉ ምን ያህል እንደራቁት ያሳያል፡፡ ሀገር በህገመንግስት፣ ሀይማኖት በፈጣሪያችን ቅዱስ ቃል (በቅዱስ መጽኀፍ፣ በቅዱስ ቁርአን) ይተዳደራሉ፡፡ በነዚህ ቅዱስ መጻህፍት ውስጥ ደግሞ፣ ልማት ማለት አማኞችን በምድራዊ ህይወታቸው በጽድቅ መንገድ አመላልሶ፣ ሰማያዊውን፣ ዘላለማዊ ህይወት ማጎናጸፍ ነው፤ በሀይማኖት መንገድ ድልድይና ህንጻ ልማት አይደለም፤ እንዲያውም ፈተና ነው፡፡
.
እኔ እነሱን ለመምከር ዝቅ ያልኩ ብሆንም፣ ከዚህ ረገድ ግን መንገዳቸውን ስተዋል፡፡ በኦሮምያና በአማራ ክልል የተከሰተውን አመጽ፣ በዚህም የተከተለውን ደም መፍሰስ እንዲቆም፣ የሀይማኖት አባቶች ግሳጼና ምክር ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ እንዲያውም የመጀመሪያው ጥይት ከመተኮሱና ደም ከምፍሰሱ መቅደም ነበረበት፡፡ ሀይማኖት ሰላምና ፍቅርን መስበክ ያለበት ለምድራዊ እድገትና ልማት አይደለም፡፡ ይልቁንም ለሰዎች ኑሮ አስፈላጊና የአላህ/ የእግዚአብሄር መንገድ ስለሆነ ነው፡፡
.
ሌላው በዚህ መግለጫቸው፣ የሀይማኖት አባቶቻችንን አጋልጦ የሰጣቸው ጉዳይ መንግስትን አለመገሰጻቸው ነው፡፡ ዝርዝሩን እንተወውና በደምሳሳው የተጋጩት፣ መንግስትና የሚመራው ህዝብ ናቸው፤ በግጭቱ ከፍ ያለ ጉዳት የደረሰው በህዝቡ ላይ ነው፡፡ መንግስት ባለጠመንጃ ስለሆነ ገድሏል፤ ባለእስር ቤት ስለሆነ አስሯል፤ ባለቲቪና ሬዲዮ ስለሆነ ልሳን አለው፡፡ ሀይማኖት ጉልበት ለሌለው ጉልበት፣ ልሳን ለሌለው ድምጽ መሆን ነበረባት፡፡ ምእመኑ አጥፍቶ እንኳን ቢሆን፣ የሀይማኖት አባቶች ስለተጎዱት ፈውስና ስለሞቱት ጽድቅ ፈጣሪን፣ ስለታሰሩት መፈታትና ስለበደሉት ምህረት መንግስትን መማለድ ነበረባቸው፡፡ አንዱንም አላደረጉም!! ከጉልበተኛው ከመንግስት ጎን ቆመው፣ የመንግስትን መግልጫ ደገሙት፡፡ . . . . ያሳዝናል! ተስፋ ያስቆርጣልም፡፡ . . . እንዴት ኢትዮጵያን የሚያክል፣ ባለብዙ ሀይማኖትና ባህል ሀገር ህዝቦች በአንድ ልሙጥ ሀሳብ እንዲቀረጹ ይጠበቃል!? እንዴት ጠ/ሚንስትሩ፣ ካድሬው፣ ጋዜጠኛው፣ የሀይማኖት አባቱ ልሙጥ . . . ተመሳሳይ ይሆናሉ!? ይህ ያስፈራል፤ አደገኛም ነው፡፡ . . . መታረም አለበት፡፡

Filed in: Amharic