>

የፃድቃን ገብረተንሣይ፤ የሙታን ኑዛዜ፣ [ተክሌ የሻው]

Tekle Yeshawወያኔን አምጠው ከወለዱት አንዱ የሆነው ፃድቃን ገብረተንሣይ ሰሞኑን «የሃ[ሀ]ገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሃ[ሀ]ሳቦች» በሚል ርዕስ የሙታን ኑዛዜ ቃሉን ሰጥቷል። በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች  ኑረው፣ የሕዎታቸው ፍጻሜ ሲቃረብ፣ ወይም በድንገት ሕይዎታችን ቢያልፍ በሚሉ ምክንያቶች ውስጥ ሲሆኑ፣ ሀብት፣ንብረታቸውን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የሥልጣን ተረካቢያቸውን (ወራሻቸውን) በቃል ወይም በጽሑፍ ይናዘዛሉ። በአገራችን በኢትዮጵያም ይህ እንደ ባህል ሆኖ ሲፈጸም ኖሯል። ወደፊትም ሕግን መሠረት በማድረግ እንደሚቀጥል ይታመናል። ኅብረተሰብ በመወለድና በመሞት ሂደት ውስጥ እስካለ ድረስ ይህ ምንጊዜም የሚቀጥል ነው። ለውጥ ካለ ሊኖር የሚችለው የአወራረሱ መንገድድና ስልት ብቻ ነው የሚሆነው።

በአገራችን በኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ ኑዛዜ የሚጸፈመው፣ ተናዛዡ፣ በፀና ታሞ፣ በሕይዎት የመቆየቱ ጉዳይ አጠያያቂ ደረጃ ላይ ሲደርስ  እንደሆነ ይታወቃል። አሁን አሁን ግን ትውልዱ ከልማዳዊ አሠራር እየወጣ፣ በዕውቀትና በሕግ መመራት በመጀመሩ፣ ውርስም  በወራሾች መካከል አጨቃጫቂ እየሆነ በመምጣቱ፣አውራሾች የጤንነታቸው ሁኔታና የማገናዘብ አቅማቸው ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ፣ የማውረስ ልምድ መጀመሩ ይታወቃል። ባህላዊ አወራረሱ፣ በእያንዳንዱ ተናዛዥ የነፍስ  አባት አማካኝነት፣ የተናዛዡ ሰው የቅርብ ሰዎች የሆኑ ሽማግሌዎች በተገኙበት ፣በከፍተኛ ሚስጢር የሚደርግ እንደሆነ ይታወቃል። ኑዛዜ የሙት ቃል በመሆኑ ተከባሪነቱ ከሞራልና ከሃይማኖት አንፃር ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ግን ተፈጻሚ የሚሆነው፣ ንዝ ተቀባዮቹ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ብቃትና ደረጃ የጨበጡ፣ የጠነከረ የሃይማኖት ፍቅር ያላቸው የሆኑና የተናዛዦቹን ስም በክፉ አናስጠራም ብለው የሚያምኑ ከሆነ ብቻ ነው። ከሁሉም በላይ የተናዛዡ ሀሳብ የጸና የሚሆነው፣ በሚናዘዝበት ወቅት የነበረው የማመዛዘን ብቃት የተዛባ አለመሆን፣ የአናዛዦቹ  በንዝ ተቀባዮቹ ላይ ያላቸው ታማኒነት ከፍተኛ መሆንን ይጠይቃል። እነዚህ ሁኔታዎች አልተሟሉም ብሎ ያሰበና የገመተ የንዝ ተቀባይ፣ ኑዛዜውን አልቀበልም በማለት ኑዛዜውን ውድቅ ያደርገዋል። ይህም ክርክርና ብጥብጥ ይጋብዛል። ትውልዱን ሆድና ጀርባ ያደርጋል። አልፎ አልፎም ደም ያቃባል።  ተራውን ቤተሰባዊ ኑዛዜ ትተን፣ ታላቆቹን የሥልጣን ሽግግር ኑዛዜዎችን ስናጤን፣ የምንመለከተው ይኸንኑ ነው። ይህን በተጨባጭ ምሳሌ እንፈትሸው።

በ1880-81 ላይ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ፣ ከድርቡሾች ጋር መተማ ሲዋጉ፣ በጽኑ እንደቆሰሉና መትረፍ እንደማይችሉ ሲረዱ፣ መኳንንቶቻቸውን ሰብስበው፣ የአልጋ ወራሼ ራስ መንገሻ ነውና እርሱን ተከተሉ ብለው ተናዘዙ። ይህ ኑዛዜ ግን፣ ከ1857 እስከ 1874 ዓም ድረስ «የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥት ወአዳል ወጋ ጋላ» የሚል ማኅተም አሳትመው ሲንቀሳቀሱ ለቆዩት፣ በኋላም በ1874 ዓም ልቼ ላይ ከዐፄ ዮሐንስ ጋር ባደረጉት ስምምነት፣ ለጊዜው የሸዋ ንጉሥ እንዲሆኑ፣ ንጉሠ ነግሥትነቱ ለዮሐንስ እንዲሆን፣ ከእርሳቸው ሕልፈት በኋላ ምኒልክ እንዲነግሡ፣ ለዚህም ሲባል ተከታዮቹ ነጋሢዎች ከዮሐንስና ከምኒልክ ዘር እንዳይወጣ ልጆቻቸውን አርኣያ ዮሐንስንና ዘውዲቱ ምኒልክን ማጋባታቸው ይታወቃል። ይህን ውልና ቃል በመዘንጋት ወይም በሌላ ምክንያት ዐፄ ዮሐንስ  «ወራሼ መንገሻ ነው» ማለታቸው፣የልቼን ስምምነት ለተዋዋሉት ንጉሥ ምኒልክ የሚዋጥ አልሆነም። በሌላ በኩል፣ ምኒልክ ከቀዳማዊ ምኒልክ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው የነጋሢ ትውልድ የሚወለዱ፣ የንጉሥ ሣህለሥላሴ የልጅ ልጅ በመሆናቸው፣ የእርሳቸው ንግሥና የዘመኑ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ፍታነገሥት የሚቀበለው፣ በሕዝቡም ዘንድ ታማኒነትና ተቀባይነት ያለው ስለነበር የዮሐንስ ኑዛዜ ተፈጻሚ የሚሆንበት ሁኔታ አልነበረም። ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ፣ ምኒልክ ከ1857 ዓም ጀምሮ ለዚህ ዙፋን ኃይላቸውን ሲያደራጁና አቅማቸውን ሲፈትሹ መኖራቸው እየታወቀ፣ ንዛዜውን ወደው ይቀበሉታል ለማለት የሚቻል አይደለም። የሆነውም ይኸው ነው።

ምኒልክ ኑዛዜውን ባለመቀበል «ሕጋዊ  የዙፋኑ ወራሽ እኔ ነኝ፣ የልቼው ስምምነትም ሥልጣኑን የሚሰጠው ለኔ ነው» ብለው ተነሱ።  ይህን በኃይል የሚቃወም ካለም፣ አለሁ! ብለው ጦራቸውን ሰብቀው ትግራይ ገቡ። የዮሐንስ መኳንንቶች አቅማቸውን መዝነው ለምኒልክ አደሩ። የዐፄ ዮሐንስ ኑዛዜ አስከባሪ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኃይል ስላልነበረው ፣ተራ ኑዛዜ ሆኖ መቅረቱን ታሪካችን ይነግረናል። ኑዛዜው አደረገ የምነለው ነገር ቢኖር፣ አንደኛው ነገር፣ የመንገሻን ልብ በማሻከር  በምኒልክ አገዛዝ ላይ ለሦስት ተከታታይ ጊዜአቶች እንዲያምጹና ለእስራት እንዲዳረጉ ማድረጉ አንዱ ነው። ሁለተኛው የወያኔ ትውልድ ሥልጣናችን በምኒልክ ተነጠቅን ብሎ የትግራይን ሕዝብ በዐማራ ነገድ ላይ በጠላትነት እንዲሰለፍ ያበረከተው የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ መሆኑ ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ ፤ዐፄ ምኒልክ በ1906ዓም ሕመመቸው ጠንቶ፣ የአልጋ ቁራኛ ሲሆኑ፣ ወጣቱን የልጅ ልጃቸውን የዙፋናቸው ወራሽ እንዲሆን፣ ተናዘዙ። ንዙን ግን ፣ንዝ ተቀባዩ ከዕድሜ ለጋነት ጋር ተያይዞ፣ በተከተለው የአገዛዝ ዘይቤ ከምኒልክ ያፈነገጠ መሆን ጋር ተያይዞ፣ ከወቅቱ ሥልጣን ተሻሚዎች በተከፈተበት ፕሮፓጋንዳ፣ የምኒልክን ኑዛዜ የተቀበሉት የቤተክህነት አባቶችና የምኒልክ መሣፍንቶችና መኳንቶች፣ የኑዛዜውን ቃል ሽረው፣ ልጃቸውን ዘውዲቱን ንግሥተ ነገሥታት ብለው በዙፋኑ በማስቀመጥ፣ የወቅቱን ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ንጉሥ ብለው ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ በማድረግ ለሥልጣን እንዳበቁ ይታወቃል።

የሁለቱ ንጉሦች ኑዛዜዎች በሕይዎታቸው መጨረሻ ላይ ፣ንዝ ተቀባዩ ባላደራም ሆነ፣ የንዝ ተቀባዩን ፍላጎትና ዓላማ ተሸካሚ የሆነውን የሕዝብ ፍላጎት ያላገናዘቡ፣ ንዞቹ ሲደረጉ ከተለያየ አቅጣጫ ያልታዩ፣ ሊከተሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ግንዛቤ ያላስገቡ፣ በሞራልና በሃይማኖት ላይ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው፣ የሙታኖቹ ቃሎች/ኑዛዜዎች በሥራ ሳይውሉ መቅረታቸውን እንገነዘባለን። ንዞቹ በተናዛዦቹ ሕይዎት ፍፃሜ ላይ የተሰጡ፣ ሞራልና ሃይማኖት እንጂ፣ ሌላ አስገዳጅ ኃይል ያልነበራቸው በመሆኑ፣ በባለኃይሎች ሳይፈጸሙ ቀርተዋል። ተናዛዦቹ ግን፣ የተመኙትን ለታሪክም ቢሆን፣ የፈለጉትንና የተመኙትን ተናግረው አልፈዋል።

ስለንዝ ይህን ሁሉ ለማለት የወደደኩት፣ ሰሞኑን ፃድቃን ገብረተንሣይ የተባለው የወያኔ ባለሥልጣን፣ከላይ በመግቢያው በተጠቀሰው ርዕስ የጻፈው ከኑዛዜ ቃል አልፎ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ችግር የማይፈታ፣ ግን ወያኔ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ የዐማራውን ነድንና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን ፈጽሞ ለማጥፋት የጀመረውን የጥፋት ጉዞ አጠናክሮ እንዲቀጥል «ጊዜ እንስጠው» የሚል መልዕክት የያዘ ሰሚና አስፈጻሚ የሌለው የኑዛዜ ቃል በማንበቤ ነው።

ከዚህ ላይ አንባቢ እንዴት ሰሚና አስፈፃሚ የለውም? ብሎ ሊጠይቅ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ሰሚ የለውም የተባለበት ምክንያት፣ ወያኔ፣ከደደቢት በረሃ እስከ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ድረስ ባደረገው ጉዞ፣ ችግሮች በገጠሙት ቁጥር ቆዳውን እየቀያየር፣ ብይ ተጫዋቾች፣ «ሰይብል፣ ብከረባበስ» እንደሚሉት እየተንከረባበሰ ከዚህ የደረሰ በመሆኑ፣ የሕዝቡን አመኔታ ፈጽሞ ባጣበትና ፀረ-ወያኔ እንቅስቃሴው በመላ አገሪቱ እንደሰደድ እሳት በተቀጣጠለበት ወቅት የተደረገ ኑዛዜ በመሆኑ ነው። ሕዝባዊ ቁጣው ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከመሀል እስከ ጠረፍ ገንፍሎ፣ ሕዝቡ ብሶቱን፣ በአደባባይ እያሰማ ነው። የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ያስከተለው ሕዝባዊ ቁጣ በጎንደር አደባባይ ከወያኔ ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ እንደ ሐምሌ ጎርፍ ገንፍሎ ወጥቶ ፍላጎቱን ገልጿል። በአዲስ አበባ የመስፋፋት ጥያቄ የአዲስ አበባና የአካባቢው ነዋሪ ወጣት፣ አቋሙንና ፍላጎቱን በግልጽ  አሳይቷል።  የወለጋ፣ የሐረር፣ የከፋ፣ የሸዋ፣ የወሎ፣ የጎንደር፣ የጎጃም፣  የሲዳሞ፣ የባሌ፣ የኢሉባቡር እና የጋሞጎፋ ነዋሪ ሕዝብ አቋሙን በተለያዩ ጊዜ በግልጽ አሳይቷል። ሕዝቡ እንድትናንቱ በወያኔ ተረግጦ ለመገዛት ፍላጎት የሌለው መሆኑን በአደባባይ አሳይቷል። በመሆኑም የወያኔን አገዛዝ ለማራዘም የሚደረግን የኑዛዜ ቃል፣ ሕዝቡ መስሚያ ጆሮ የለውም።

ወያኔ ፍላጎቱን ሲያስፈጽም የኖረው፣ በገነባው የስለላ መዋቅር፣ በዘር ላይ በመሠረተው የጦር ሠራዊት፤ ፍርድ ቤት፣ አቃቢ ሕግ፣ የአስፈጻሚ አካላት፣ በቋንቋ ላይ ለያያቶ ባደራጃቸው የዘር ድርጅቶች እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ ክፍሎች በአሁኑ ወቅት፣ ግማሾቹ አካላቸው በሥጋ፣ ኅሊናቸው በገንዘብ ታስሮ እንደድሮው ተራውጠው የወያኔን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚችሉበት ወኔውም ሆነ፣ ጉልበቱ የላቸውም። ቱባ ባለሥልጣኖቹ  የሕዝቡን ቁጣ ፈርተው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ከአገር አስወጥተዋል። የቆሙት ባንድ እግራቸው ነው። ይህም በመሆኑ በሙሉ ልባቸው መስዋዕትነት ለሚጠይቀው ትግል ፈጽሞ ፈቃደኞች አይደሉም። ይህ የጎንደር እና «በኦሮሚያ ክልል» በተካሄደው ሕዝባዊ አመጽ አስፈጻሚ አካሎቹ እንደድሮው ገድለው፣ አስረውና አስፈራርተው አመጹን ማስቆም አለመቻላቸው፣ ባንፃሩ ከሕዝቡ ጎን መቆማቸው በግልጽ ተስተውሏል። ባንድ ቃል፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ የትግሬ ወያኔዎች እንደጥንቱ መግዛት፣ መንዳትና መግድል የማይችሉበት፣ ተገዥዎች ደግሞ፣ እንደጥንቱ ተጨቁነውና ተረግጠው ለመገዛት ፈቃደኛ ያልሆኑበት አብዮታዊ ወቅት ላይ ያለች በመሆኑ፣ የፃድቃንን የሙታን ኑዛዜ የሚሰማ ጆሮም ሆነ፣ ኑዛዜውን የሚያስፈጽም ኃይል የለም። ይህን በተመለከተ ማለትም የወያኔ መንግሥት ተብየ የማፈኛና የመቆጣጠሪያ መዋቅር ሽባ መሆኑን ፃድቃን እንዲህ ሲል ውስጥ አዋቂነቱን ገልጿል።

«አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ የህዝብ አመኔታ በመንግስት ላይ በጣም ዝቅተኛ የሆነበት፣ በህዝቦች መካከል ያለው መቀራረብና መዋደድ የቀነሰበት፣ጥላቻ እየበረታና በግልጽ እየተነገረ፣ የህዝቦች የእርስ በርስ መናቆር እንዳይመጣ የሚፈራበት ስለሆነም ውስጣዊ አንድነታችን በጣም የላላበት፣ የመንግስት መዋቅር የመፈጸም አቅሙ ደካማ የሆነበት፣ከዚህ የተነሳም ህዝቡ ተስፋ የቆረጠበት፣በየአካባቢው ፖለቲካዊ ችግሮች ሲነሱ በታጠቀ ሃይል (ፖሊስና መከላከያ) የሚፈታበት፣ህዝቡ አሁን የሚታየው ችግር ይፈታል፣ አይፈታም፣ እንዴት ይፈታል እያለ ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ  የገባበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው።» በማለት የወያኔ አገዛዝ የመጨቆኛ ተቋሞች ሽባ መሆናቸውንና ሕዝቡ ለለውጥ መነሳሳቱን ሳይደብቅ፣ ግን ወያኔና ግብረ አበሮቹ በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን በፍርሃት ተውጦ ነግሮናል። ይህ ከፍተኛ ፍርሃት የወለደው የፃድቃን ኑዛዜም ግብ፣ ወያኔና ግብረ አበሮቹ ከሕዝብ የዘረፉትን ሀብትና ንብረት ተጠብቆ የሚዘልቁበት፣ በአገርና በሕዝብ ላይ ክህደት የፈጸሙ ወንጀለኞች ለፍርድ አደባባይ እንዳይቀርቡ፣ ለዚሁ መድህን ይሆናል ያለውን፣ ራሱ ጽፎ፣ሕዝብ አጸደቀው ያለውን  ሕገመንግሥት በሥራ ላይ ማዋል ያልቻለውን አገር አፍራና የችግሮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን ሕገመንግሥት ተብየ እንጠብቀው ይለናል።

ፃድቃን ገብረተንሣይ በዚህ የሙታን የኑዛዜ ቃሉ ሊያስተላልፍ የፈለጋቸው መልዕክቶች የሚከተሉት ናቸው።

(1) ወያኔ በትጥቅ ትግሉ ዘመን አብዮታዊና ዴሞክራት እንደነበር፣ በሂደት ይህ አቋሙ መሸርሸሩን፤

(2) የወያኔ የትጥቅ ትግል መቋጫው«በሕዝብ የፀደቀው ሕገመንግሥት» መሆኑና፣ ይህ ሕገመንግሥትም ዲሞክራሲን፣ ዕኩልነትን፣ ነፃነት፣ አንድነትን የሚያረጋግጥ ፍቱን መሣሪያ እንደሆነ አምኖ፣ ግን በሂደት በመመሪያዎችና በፖሊሲዎች እየተሻረ፣ አገሪቱና ሕዝቡ አሁን ለሚገኙበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መግባታቸውን፤

(3) አገሪቱና ሕዝቡን ከገቡበት ችግር መውጫው ብቸኛ መንገድ ሁሉም በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎች ተሰባስበው ሕገመንግሥቱና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት ችግሮቹን መፍታት እንደሚቻል እምነቱና ፍላጎቱ መሆኑን፤

(4) የትግራይ ሕዝብ ለወያኔ ሥልጣን መጨበጥ ባበረከተው ይህ ቀረሽ ያልተባለ ድጋፍና ለዚህ ውለታም ወያኔ ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ የአገር ሀብት ዘርፈው እንዲበለጽጉ ያደረገው ድርጊት፣ በሌሎች ነገዶች ላይ ቅሬታና ምሬት ያስከተለና ይህን የትግራይ ሕዝብ የጥላቻና የመገለል ሰለባ እንደሆነ አምኖ፣ ሕዝባዊ አመፁ በዚህ ከቀጠለ በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚከተለው ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በመገመት፣ ይህ ጥፋት እንዳይከተል ተቃዋሚዎችን ለማለዘብ፣ የትግራይንም ሕዝብ ለማንቃት የተላለፈ  መልዕክት ነው። የመልዕክቶቹ ግብም፣ ወያኔ የዘረጋው የዘር ፖለቲካና በቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌደራሊዝም በወያኔ የበላይነት እንዲቀጥል፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አፍራሽ የሆነውን ሕገመንግሥት  ተጠብቆ እንዲዘልቅ፣ ለዚህም ወያኔና የወያኔ ትውልድ የዚህ ባለውለታ ሆኖ እንዲቆጠር የሚፈልግ ነው። አገሪቱ ለገጠማት ችግር ብቸኛው መፍትሔ  ሕገ-መንግሥቱን በሥራ ላይ ማዋል  እንደሆነ ፣የአገሪቱን ብሔራዊ  ጥቅም፣ የሕዝቡን አንድነትና ተንቀሳቅሶ የመሥራት ነፃነት የገፈፈውን፣ አጥፊ ሕገመንግሥት መጠበቅ እንዳለበት እምነቱና ፍላጎቱ መሆኑን ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ ነግሮናል። በዚህም የተነሳ በ20 ገጽ ጽሑፉ ውስጥ 60 ጊዜ ሕገ-መንግሥት የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። እንዲህም ሲል የሕገ-መንግሥቱን ፍቱን መሣሪያነት ሊነግረን ሞክሯል። እንዲህም ይለናል፦

አንደኛ፦ «የትጥቅ ትግሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ያኔ ሁኔታው በፈቀደው መሰረት በህዝብ ተሳትፎ ሕገ መንግስት አፅድቀን በዚህ ሕገመንግስት እየተመራን መጓዝ ከጀምርን ሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥረናል።» (ስርዝ የተጨመረበት)

ማንም እንደሚያውቀው፣ ሂደቱም እንዳረጋገጠው ፃድቃን «በህዝብ ተሳትፎ ፀደቀ» ያለው ሕገመንግሥት፣ ሕዝብ የተቃወመው እንጂ፣ የተሳተፈበት አይደለም። ቢሳተፍበትማ ኖሮ፣ ይህ ሁሉ ተቃውሞ ከወያኔ ልደት እስከ ምንኩስና ዘመኑ ባልቀጠለ ነበር። በግልጽ እንደሚታወቀው፣ ለሽግግር ጊዜው ቻርተርና በኋላም ለሕገመንግሥት ተብየው መነሻ መሠረት የሆነው ሰነድ፣ ሻዕቢያ፣ ወያኔ እና ኦነግ ተሰኔ ላይ ተሰብስበው፣ የማዕከላዊ መንግሥት (ደርግን) ጥለው እንዴት ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍለው እንደሚያስተዳድሩ፣ ኤርትራ በምን ሁኔታ መገንጠል እንደምትችልና ዕውቅና እንደሚሰጣት የተስማሙበት፣«የተሰኔ ማንፌስቶ» በመባል የሚታውቀው ሰነድ ነው። የዚህ ሰነድ አዘጋጅ ደግሞ የኦነጉ ሌንጮ ለታ እንደሆነ ራሱ በብዙኃን መገናኛ መሣሪያዎች ነግሮናል። ዕውነቱም ይኸው ነው። በዚህ ሰነድ ሕዝብ ያለመሳተፉን ያልህል፣ የሽግግር መንግሥቱም ቻርተር ሲጸድቅ፣በሻዕቢያ፣ በወያኔና በኦነግ ዕውቅናና ፈቃድ የተጣቸው የነገድ ነፃ አውጭነን ያሉ፣ ግለሰቦች የሰነዱን ጥቅምና ጉዳት፣ ወደፊት ሊያስከትል የሚችለውን ሳይመዝኑና ለሕዝብም ሳይቀርብ በሦስት ቀን ስብሰባ ጸደቀ የተባለ መሆኑ ይታወቃል። ይህ በሕዝብ ተሳትፎ ፀደቀ የሚያስብለው አንዳችም መሠረት የለውም። ከሁሉም በላይ ይህ የሽግግር ቻርተር ፀደቀ ሲባል፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከ35% በላይ የሚሆነው የዐማራ ነገድ፣ በድርጅትም ሆነ በግለሰብ  በውሳኔው ላይ ለውጥ ማምጣት ባይችልም ለስም እንኳን ተወካይ አልነበረውም። በመሆኑም ቻርተሩ በዐማራው ነገድ ላይ ተገዶ የተጫነበት እንጂ፣ የፈቀደውና የተስማማበት አይደለም። ይህን ፃድቃን የኢትዮጵያን የሦስት ሺ ዘመን ታሪክ በመካድ በመቶ ዓመት እንደገደቡት፣ ካልካደ በቀር፣ ዐማራው ተወክሏል ሊል የሚችልበት ማስረጃ የለውም።

የሽግግር ጊዜ ተብየው ተጠናቆ፣ ሕገመንግሥት ተብየው ሲዘጋጅም ሆነ ሲፀድቅ ፣ የሕዝብ ተሳትፎ አልነበረም። የተደረገው፣ የወያኔ ፍላጎት የሆነው ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ የዐማራ ነገድንና ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ሃይማኖት ለማጥፋት ፍላጎት ያላቸው የነገድ ድርጅት አባሎች የመለስና የቡድኑ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ተሰብስበው፣በኋላይ እንደታየው፣ ፃድቃንም እንዳመነው፣ በሥራ ላይ የማይውሉ፣ ግን ለወያኔ የምዕራባውያንን ድጋፍ ሊያስገኙ ይችላሉ የተባሉ፣ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የተቀበለቻቸውን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶችን የሕገመንግሥቱ አካል እንዲሆኑ በማድረግ፣ፀረ-ኢትዮጵያ አንድነት የሆኑ ግለሰቦች የተስማሙበት እንጂ፣ ሕገመንግሥቱ ለሕዝብ ቀርቦ ውይይትና ክርክር የተደረገበት አለመሆኑን ፃድቃን ይስተዋል አይባልም። ሕዝብማ ቢያጸድቀውና ቢስማማበት ኖሮ፣ ዛሬ ወያኔን ያራደው ሕዝባዊ አመጽ ሊቀሰቀስ ቀርቶ የሚታሰብ አልነበረም።

ሁለተኛ፦«— ይህ አሁን የምንገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን ከፍተኛ ጉዳት ከመድረሱ በፊት እንፍታው። ችግሩን ለመፍታት ደግሞ በኢህደአዴግና (በኢሕአዴግ ለማለት ይመስላል)  ድርጅቱ በሚመራቸው የመንግስት ይሁን የፖርቲ (የፓርቲ ለማለት ይመስላል) መዋቅሮች ታጥረን በምናደርገው እንቅስቃሴ ብቻ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም። ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው መዋቅር በተጨማሪም ከየፖርቲና (ከየፓርቲና ለማለት ይመስላል) የመንግስት መዋቅር ውጭ ያሉ ፖለቲካዊ ሃይሎችና ምዕላተ ህዝቡ በስፋትና በንቃት ሲሳተፍበት ነው በእርግጠኝነት ችግሩን መፍታት የሚቻለው ከሚል መነሻ ሃሳብ የሚነሳ ነው። ይህ ደግሞ በከፍተኛ የህዝቦች  መስዋዕትነትና ተሳትፎ የፀደቀውን ህገመንግስታችንን መሠረት አድርገን በህገመንግስቱ የተቀመጡትን ሰብአዊና(ስርዝ የተጨመረበት) ፖለቲካዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግና በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ፖለቲካዊ ሃይሎችም ያለምንም ተፅዕኖ ያልተገደበ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አድርገው በመጨረሻም በገለልተኛ በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ነፃ ዲሞክራሲያዊና ያለምንም ተፅዕኖ የተከናወነ ምርጫ መሆኑ ተረጋግጦ የተካሄደ ምርጫ የሚሰጠንን ውጤት ተቀብለን ለመጓዝ ቆርጠን ስንነሳ ነው በሚል አስተሳሰብ ላይ ያጠነጥናል።»

ይህን ዓይነት ጥሪ የተቃዋሚው ጎራ በተከታታይ ሲያቀርበው የነበረ ነው። «የአማራጭ ኃይሎች»፣ «ፓሪስ አንድና ሁለት»፣ «ቅንጅት»፣ «ኅብረት»፣ «መድረክ»፣ ወዘተ የተሰኙ ስብስቦች ላለፉት 25 ዓመታት ሳይታክቱ ሲያቀርቡት የነበረ ጥሪ ነው። ለነዚህ ጥሪዎች ፃድቃንን ጨምሮ የወያኔው ቡድን የሰጠው አዎንታዊ መልስ የለም። መልሱ «እኛ ትክክል ነን! ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከእኛ የተሻለ፣ሀሳብም ዕውቀትም ያለው የለም» የሚል እንደነበር እናስታውሳለን። ፃድቃንም ዛሬ እርሱ እንደ አዲስ ላቀረባቸው ጥሪዎች፣  በግሉም ሆነ በቡድ  እንደዛሬው በግልጽ ሀሳቡን ሲሰጥ አልተደመጠም፤ አልታየም። ሆኖም« የናቁት ያስቀራል ራቁት» ነውና የሕዝቡ ትዕግሥት ተሟጦ፣ ግፉ ገደቡን ጥሶ ሲፈስ፣ ማዕበሉ ማንን ሊጠራርግ እንደሚችል፣ ከመሸም ቢሆን፣ የባነነው ፃድቃን፣ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ ቋያ ላይ ውኃ ለማፍሰስ፣ ነባሩን የሕዝብ ጥያቄ፣ በማር ለውሶ፣ «ሕዝብ የተሳተፈበት» የሚለውን ሕገ አራዊት ሕገመንግሥት ነፍስ ዘርቶ፣ የወያኔን አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም የትብብር ጥሪ አቅርቧል። ጥሪው አዲስም ባይሆን፣ የወያኔው ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ያውም «ጦር ሠሪ» ከሚባሉት አንዱ የሆነው ፃድቃን የችግሩን መኖር ማመኑ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በዚህ ረገድ ለጻድቃን የሚቀርብለት ጥያቄ፣ ለችግሩ መፍቻ መሣሪያ እንዲሆን ያቀረበው «በሕዝብ ተሳትፎ የጸደቀ» የሚለው ሕገመንግሥት፣ ሕዝቡ የማያውቀው፣ የኛ ነው የሚሉትም ያላከበሩትና የማይገዙበት ስለሆነ፣ አሁን አገሪቱ ለገጠማት ችግር ዋናው የችግሯ ቋጠሮ ይኸው ሕገመንግሥት ተብየ የዘረጋው በነገድ ላይ የተመሠረተ ፌዴሬሽንና የሚመራበት የዘር ፖለቲካ ስለሆነ፣ የችግራችን መፍቻ አይሆንም የሚል ነው። የችግሮች አካል የሆነ፣ የመፍትሔ አካል ሊሆን አይችልምና የወያኔው ሕገመንግሥት አገሪቱ ለገጠሟት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍቻ መሣሪያ አይሆንም የሚለው፣ በአንፃሩ የፈራቸው ችግሮች እውን እንዳይሆኑ ከፈለገና ካመነ፣ ብሔራዊ ዕርቅ የሚያወርድ፣ መሠረቱ ለሠፋና በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ለሚጸድቅ ሕገመንግሥት ዝግጅትና ይህኑ ለሚያስፈጽም ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች ያሳተፈ የሽግግር መንግሥት የሚመሠረትበትን መንገድ ማመቻቸት እንዲቻል፣ የበኩሉን አዎንታዊ ተጽዕኖ በወያኔው አባሎች ላይ ለማሳደር የምትችለውን አድርግ ነው መባል ያለበት።

ሦስተኛ፦በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ከፍተኛ ችግር መፍታት የሚቻለው«–ሃገር ወዳድ የሆኑ ፖለቲካዊ ሃይሎች በሚያማማቸው (በሚያስማማቸው ለማለት ይመስላል) ፖለቲካዊ መድረሻ ተገናኝተው በመጀመሪያ የሀገራችንን የራሳችንን ችግሮች ስናስወግድ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህንን ደግሞ ህገመንግስቱን መነሻ (ስርዝ የተጨመረበት) በማድረግ ሊጀመር ይችላል ብየ አስባለሁ።»

የአገሪቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በሚያስማሙዋቸው መዳረሻዎች ላይ ተወያይተው የጋራ ውሣኔ ላይ ለመድረስ በቅድሚ መጫዎቻ ሜዳውን የተቆጣጠረው ወያኔ በሀሰት ከሶ ያሰራቸውን የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦችን በከፍተኛ ይቅርታ በነፃ መፍታት አለበት። ፃድቃን ያመናቸውን ሕገመንግሥቱን ሻሪ የሆኑ መመሪያዎችንና ፖሊሲዎችን በይፋ መሻር አለበት። የጠረሽብር ሕጉ፣ ሰዎችን በነፃ የመንወሳቀስና የመኖር ነፃነት የሚገፉ ደንቦችን ማንሳት አለበት። አገር እንዳይገቡና በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ ያገዳቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች ሕጋዊ ዋስትና ሰጥቶ ወደ አገር እንዲገቡ በግልጽ ማወጅ አለበት። ይህ በሌለበት ሁኔታ በጋራ ለመወያየትና የጋራ መፍትሔ ላይ መድረስ ስለማይቻል። ፃድቃን ይህን የቤት ሥራ ሠርቶ መድረኩ ለውይይት ሲመቻች፣ የሀሳብ የበላይነት ያለውና የሕዝቡን ዕውነተኛ ድጋፍ ያገኘ ድርጅት አገሪቱን ሊመራበት የሚችለው ሕጋዊ ሥርዓት ዘርግቶ ወደፊት መራመድ ይቻላል። ከዚህ ባለፈ የወያኔ ጊዜ መግዣና አፍኝ ሥርዓት መቀጠያ የሆነው ሀሳብ፣ ገዥ ሊሆን አይችልም።

አራተኛ፦ ፃድቃን በአገራችን የተከሰተው ዘርፈ ብዙ ችግር ለማለፍ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ግድ እንደሚል ጠቅሶ፣ ችግሩን ለመፍታት ተጨባጭ ሁኔታውን አውቆ ፣ከዚሁ ሁኔታ ጋር «የተጣጣመ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ዋና መነሻ ሕገ መንግስት ነው ብየ አምናለሁ።» ይህን ሀሳቡን ሲያጠናክር ፃድቃን እንዲህ ይላል። « —የሃገራችንን ሁኔታ ያገናዘበ በማንኛውም ደረጃ በጣም ጥሩ ሊባል የሚችል ህገ መንግስት አለን። ይህ ሕገመንግስት ህዝቦች ፈቅደው እንዲመሩበት ያወጡት የሃገሪቱ የመጨረሻ ህግ ነው።» (ስርዝ የተጨመረበት) ይላል።

ይህ  አባባል ከክህደት ያለፈ ፍሬ ነገር የለውም። እንኳን ተቃዋሚው ወገን፣ ተራው ዜጋ ሊቀበለው የማይችል ተራ ቅጥፈት ነውየሀሳቡን አቀራረብና መዳረሻው ምን እንደሆነ በግልጽ ስለሚታይ፣ የሕዝቡን ቁጣ ከማባባስ ውጭ፣ አባባሉን የሚገዛው ቀርቶ፣ሊሰማው የሚፈልግ የለም። ግቡ ኢትዮጵያን ከገጠማት ችግር ለማውጣት ሳይሆን፣ ወያኔና ደጋፊዎቹን ከሚጠብቃቸው የሕዝብ ቁጣ ማውጫ፣ ከሕዝባዊ ማዕበል ማፈትለኪያ ስልት ስለሆነ፣ ሰሚ ጆሮ የለውም። ምክንያቱም በአገር አንድነትና ሉዐላዊነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ዳር ድንበር ላይ ክሕደት የፈጸሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ለፍርድ ሳይቀርቡ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የገደሉ፤ ያፈናቀሉ፣ ያሰሩና ያሰቃዩ ወንጀለኞች ሳይጠየቁ፣ በዳይ ሳይክስ፣ ተበዳይ ሳይካስ፣ ከሁሉም በላይ የነዚህ ወንጀሎች ሁሉ መሣሪያ ሆኖ ያገለገለው ሕመንግሥት ይቀጥል ማለት የሕዝባዊ ተቃውሞውን ዓላማና ግብ ካለመረዳት ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ ለወንጀለኞች መከታ ለመሆን የታሰበ በመሆኑ ሰሚ የለውም።

አምስተኛ፦ «ሕገመንግስቱ በህዝባዊ የትጥቅ ትግሉ ውስጥ አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መንፈስ የተላበሰ ኢህአዴግ በሚመራው መንግስት እንዲኖር የሚፈለገውን የመንግስት አሰራርና ባህርይ መለኪያ (Standard) ይሆናል ብለን ያስቀመጥነው የትጥቅ ትግሉ ድሎች መቋጫ ነበር እላለሁ።»

ወያኔ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ አካል መሆኑ ይታወቃል። ማንም  እንደሚገነዘበው የ1960ቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ግራዘመም ሶሻሊስታዊ እንጂ፣ ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑ ግልጽ ነው። በመሠረቱ አብዮት የነበረን ማጥፋት፣ ማንነትን ማስለወጥና ማስካድ፣ የራስን ወርቅ መለያና መታወቂያ ጥሎ ፣ የሌሎችን መዳብ ማንነት መላበስ በመሆኑ፣ ከዲሞክራሲ ጋር የሚጣጣም አይደለም። ምክንያቱም ዲሞክራሲ በሂደት ፣ባለውና በነበረው መልካም ዕሴቶች ላይ ቀስ በቀስና ደረጃ በደረጃ እየተጨመረ በሕዝቡ ፍላጎትና ነፃ ውሣኔ የሚዳብር እንጂ፣ የተወሰኑ  እናውቅልሃለን በሚሉ ቡድኖች ከላይ የሚጫን አይደለም። የዲሞክራሲ ዋልታዎችም፣ የብዙኃን ውሳኔ ገዥነት፣ የጥቂቶች መብት ተከባሪነት፣ የሰብአዊና ዲሞክራዊያ መብቶች ደረጃ በደረጃ ተከባሪነት፣ መሪዎችን የመምረጥና የመመረጥ ነፃነት መረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት መስፈን፣ ሥልጣን የሕዝብ መሆንና ባለሥልጣኖች ለሕዝብ ተጠሪዎች መሆን፣ ወዘተ መሆን ናቸው። በዲሞክራሲ የሰዎች የማምለክ ነፃነት የተረጋገጠና የሃይማኖቶች ዕኩልነት ዕውን የሚሆንበት እንደሆነ ይታመናል። የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካና የሰዎች የሀሳብ ነፃነት የተከበረበት ነው። በአጠቃላይ ሰብአዊነት ከፍተኛ ቦታ የተሰጠው አመለካከት ነው። እነዚህ መብቶች እንኳን በዘረኛው የወያኔ ድርጅት ቀርቶ በየትኞቹም የፖለቲካ ድርጅቶች ተግባራዊ ሆነው አያውቁም። የነበረው ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባለው፣ ጠቅላላ አባላቶቹ መብትና ነፃነታቸውን «ማዕከላዊ ኮሚቴ» ለሚሉት የሚሰጡበት፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚባለው ደግሞ፣ ከአባላቱ ተሰጠኝ ያለውን መብትና ነፃነቶቹን «ለሥራ አስፈጻሚ »ለሚባሉት ከ7 እስከ 11 ለሚሆኑ ሰዎች የሚሰጡበት፣ ሥራ አስፈፃሚው በበኩሉ፣ ከማዕከላዊ ምክር ቤት ተሰጠኝ ያለውን መብትና ነፃነቱን ላንድ «ጸሐፊ ወይም ሊቀመንበር ወይም ሰብሳቢ» ለሚሉት የሰጡበት በመሆኑ፣ ምንጊዜም ቢሆን፣ በሕዝብ ስም የሚወሰኑ ውሣኔዎች የጠቅላላ አባላቱን አብዛኛውን ፍላጎት የሚወክሉ ሳይሆኑ፣ የሊቀመንበሩን ብቸኛ ፍላጎት የሚገልጽባቸው እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ወያኔ አብዮታዊ እንጂ፣ ዲሞክራት አልነበረም። ዲሞክራት ሆኖም አያውቅ። ሊሆንም ፍላጎት የለውም።

ከሁሉም በላይ ወያኔ ዘረኛ ከመሆኑም አልፎ ፀረ-ሃይማኖት እንደነበር፣በርሃ ሳሉም ሆነ በሥልጣን ላይ ሆነው፣ በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖት ተካታዮችና ተቋሞች ላይ የሚፈጽሙት ግፍ በግልጽ እየታየ ነው። በባዶ ስድስት እስር ቤቶቻቸው ሰዎችን በቁመናቸው በመቅበር ያጠፉትን ሕዝብ ቁጥር የግፉ ተቃባይ ቤተሰቦችና የተቀበሩባቸው ቦታዎች ብቻ ናቸው የሚውቁት። ወያኔ ጠባብና ዘረኛ፣ ፀረዲሞክራሲና ፀረ-ብዙኃን አስተሳሰብ መሆኑን ከሚያመላክቱን ማስረጃዎች መካከል ኢሕአፓን ከአሲንባ ያስለቀቀበትና የትግራይ ነፃ አውጭ ድርጅት አባሎችን በስምምነት ስም በግፍ ያረደበት ሁኔታ አፍ አውጥተው የሚናገሩ ዘመን ተሻጋሪ ነቃሾች ናቸው።

ፃድቃን በሕዝብ ተሳትፎ ጸደቀ የሚለን ሕገመንግሥት፣ ቋሚ መሠረቱና ዋልታው ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን፣ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው። ይህም በመሆኑ፣ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-አገር ነው። ከሁሉም በላይ የአልባኒያው ኤንቨር ሆጃ (Enver Hoxha) ተከታይና አምላኪ የነበረው ወያኔ፣ ዲሞክራት ነበር ማለት ከማሳቅ አልፎ ያሳፍራል። የወያኔን ሕገመንግሥትም ሕዝቡ የሚጠላው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።

አንደኛ፦ ሕገመንግሥቱ ሕዝቡ የመከረበትና የተስማማበት አይደለም። በመሣሪያ ኃይል የተጫነበት ነው።

ሁለተኛ፦ አገሪቱን በነገድ ከፋፍሎ ለዘመናት በሥጋ ልደት፣ በደም ውሕደት፣ አንድ የሆነውን ሕዝብ በቋንቋ ከፋፍሎ ሆድና ጀርባ ከማድረግ አልፎ፣ ፃድቃን እንዳለው በሕዝቡ መካከል መራራቅና መነጣጠል የፈጠረ መሆኑ ነው።

ሦስተኛ፦ ሕገመንግሥቱ የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የውሣኔ አሰጣጥ በሕዝቡ ላይ የጫነ ኮሚኒስታዊ አሠራር በመሆኑ ነው። ስለሆነም በወያኔ የተዘጋጀው ሕገመንግሥት የምዕላተ ሕዝቡን ይሁንታና ፈቃድ ያላገኘ ብቻ ሳይሆን፣ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ማለትም የግለሰቦችንና ያንድ ድርጅትን የበላይነት ያሰፈነ በመሆኑ መለወጥ ያለበት ነው። ዲሞክራሲያዊ ሕገመንግሥት በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ በግልጽ ውይይትና ክርክር መዘጋጀት አለበት። ይህ ካልሆን፣ ፃድቃን የፈራው የአንድ ነገድ ከምልዓተ ሕዝቡ መገለል የማይቀር መሆኑን መናገር ነቢይነትም ሆነ ክፉ አሳቢነት አይሆንም።

ስድስተኛ፦ ፃድቃን በትግሬ ወያኔ አገዛዝ ባለፉት 25 ዓመታት ለወያኔ ትውልድና ዘር በዘረፋና በንጥቂያ የተገኘውን ጥቅም  ምዕላተ ሕዝቡ የተጠቀመ ያስመሰሉትን የመንገዶችና የከተሞችን ዕድገት በማሳያነት በመጥቀስ፣ በእርሱ እይታ ችግር የሚለውን እንዲህ ይገልጸዋል። « በአጭር አነጋገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲሰፋ ይፈላጋል። ቢያንስ በሕገመንግስቱ ዕውቅና የተሰጣቸው መብቶች ሳይሸራረፉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ መንግስት እነዚህን በሕገ መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው መብቶች የሚገድቡ አሰራሮችና መመሪያዎች በማውጣት ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ እያጠበበው ይገኛል። ይህ ሁኔታ በሃገራችን ውስጥ ላለው ፖለቲካዊ ቀውስ አንድ ትልቅ ምክንያት ነው።» (ስርዝ የተጨመረበት)

ከዚህ ላይ ፃድቃን ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ከመሸ ቢሆንም፣ የወያኔ አገዛዝ፣ ፀረ-ሕዝብ ነው የምንለው፣ ራሱ ላጸደቀው ሕገ መንግሥት ተገዥ አለመሆኑ አንዱ የሆነውን ማመኑ ነው። እንዳለውም ወያኔ በራሱ ሕገ መንግሥት አለመገዛቱ የችግሩ አንዱ አካል ቢሆንም፣ የችግሮቹ ዋነኛ ምንጭ ግን ሕገመንግሥቱና በርሱ ላይ የተመሠረተው የአገዛዝ ሥርዓት ወይም ዘይቤ ነው። የዚህ ችግር መፍትሔውም የችግሩን ምንጭ ማድረቅና ሥርዓቱን ከነአገዛዙ ማስወገድ ነው። ፃድቃን ለወያኔ አገዛዝ መቀጠል ባለው ከፍተኛ ፍላጎት፣ ወያኔ ሆን ብሎና አስቦ ክርችም አድርጎ የዘጋውን የዲሞክራሲ ምኅዳር፣ «እያጠበበው ይገኛል» በሚል ይገልጸዋል። መጀመሪያውኑ  ወያኔ ዴሞክራት አልነበረም። የዲሞክራሲም ምኅዳር አልከፈተም። ያልተከፈተና ያልነበረ እንዴት እየጠበበ መጣ ይባላል? ዞሮ ዞሮ የፃድቃን ጥሪ ልንጠፋ ነውና ከመጥፋታችን በፊት መውጫ ቀዳዳ እንፈልግ፣ መውጫውም የሞትንለት፣ የታገልንለት፣ በትግላችን ያገኘነው ሕገመንግሥት በሥራ ላይ ይዋል የሚል፣ ተሂዶበት ውጤት ባላስገኘ መንገድ፣ ደጋግመን ለ25 ዓመታት እንድንላቅጥበት የቀረበ ፣እናንተ ሙቱ፣ ተራቡ፣ ተሰደዱ፣ ተሰቃዩ፤ እኛ እንኑር፣ እንብላ፣ እንበልጽግ፣ ጠያቂም አይኑረን፣ እንዳሻን ኢትዮጵያና ሀብቷን እንጠቀምባት የሚል «የጅል ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ» አይነት ጥሪ ነው።

ሰባተኛ ፦ ፃድቃን ወያኔ የምዕራባውያንን ለጋሺና አበዳሪ መንግሥታት ልብ ለማማለል ፣ ከሁሉም በላይ የነፃ ገብያና የዲሞክራሲ ፊታውራሪ ነኝ የሚለውን የምዕራቡን ዓለም ሠፊና ያልተቋረጥ ድጋፍ ለማግኘት ሲል፣ በሕገመንግሥቱ የሸነቆራቸውን አንቀፆች ተግባራዊ አለማድረጉን ጠቅሶ፣ ለዚህም  ምክንያቱ እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ ምክንያቶች እንዳሉና እነዚህም «የፖለቲካ ስርዓቱ እና መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ወሳኝ ድርሻ» እንደሆኑ ገልጿል።

በፃድቃን እምነት የፖለቲካ ስርዓቱ ዋነኛ ችግር በገዥው ፓርቲና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት ፈጽሞ ጠፍቶ፣ ገዥው ፓርቲና መንግሥት አንድ ከመሆናቸው የሚመነጭ እንደሆነ ይነግረናል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ታሪካዊ አስተዳደጉ የዜጎች በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም የሌለው መንግሥት፣ በአጠቃላይ የሥራ አስፈጻሚው ክፍል ደግሞ በተለይ የፈለገውንና ያመነበትን ለማድረግ የሚከለክለው የሌለበት ሁኔታ እንዳለ ያምናል። ይህንም እምነቱን ሲያጠናክር እንዲህ ይላል፤ «የስራ አስፈጻሚው አካል የፈለገውን ነገር ከማድረግ የሚያግደው ተቆጣጣሪ አካል የለም።» በማለት ወያኔ ያሻውን ያደረገ እና እያደረገም እንደሆነ ነግሮናል። ይህ ደረቅ ሐቅ ነው።

የየአካባቢው ሕዝባዊ አመፆች መነሻና መዳረሻም ይኸው ወያኔ ያላንዳች ተቆጣጣሪና ሀግ ባይ አገርና ሕዝብ የማጥፋት ድርጊቱ ከገደብ አልፎ በመፍሰሱ ምክንያት ነው። ፃድቃን ያልተገነዘበውና ሊገነዘበውም የማይፈልገው ጉዳይ፣ በእርሱ አገላለጽ «የፖለቲካ ስርዓቱና መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ወሳኝ ድርሻ» የመያዝ ጉዳይ በድንገት ወይም በሂደት የተፈጠረ አለመሆኑን ነው። ይህ በተከታታይ ድርቅና ድርቁ ባስከተለው ረሃብና መሰደድ ተማረው መሣሪያ መልጠው ዱር ቤቴ ያለው የወያኔ ትውልድ፣ የዘመናት ምኞቱን ዕውን ለማድረግ፣ ይህ ወያኔ መራሹ መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ የበላይነቱን መያዝ የማይታለፍ እንደሆነ አምኖ በዕቅድ የተንቀሳቀሰ ነው። ዛሬ መቀሌ ውስጥ ሕዝቡ «አፓርታይድ» ብሎ የሰየማቸውን ሰማይ ጠቀስ ፎቆችና የተንጣለሉ ቪላዎች የገነቡ፣ ሰባራ ጫጩት ከቤተሰብ ሳይወርሱ ቢሊየነሮችና ሚሊየኖሮች የሆኑ፣ አዲስ አበባ ቦሌ ክፈለ ከተማ «ሕዝቡ መቀሌ» ብሎ በሰየመው አካባቢ በተገነቡ ፎቆችና ቪላዎች፣ የሚሽሞነሞኑ ሰዎች፣ ካለዚህ ቁርኝት ሊታሰቡ የሚችሉ አይሆኑም።  በሽግግር ወቅት ተብየው «በጦርነት ለተጎዱ ክልሎች ቅድሚያ ልማት ይሰጥ» የሚል ሕግ አውጥቶ ትግራይ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ሀብት ለ8 ተከታታይ ዓመታት እንድትገነባና ኢኮኖሚዋ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገር የተደረገው በዚሁ በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ መንግሥት ተብየው  በኢኮኖሚው ውስጥ የበላይነቱን እንዲይዝ በመደረጉ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ ታስቦና ታቅዶ የተሠራ ነው። ዛሬ የወያኔ ጄራሎች ፃድቃንን ጨምሮ ለገነቧቸው ፋብሪካዎች፣ ሕንፃዎች፣ ለያዙት ሠፋፊ የእርሻ መሬቶችና የከተማ ቦታዎች ምንጩ ይኸው ወያኔ መራሹ መንግሥት ተብየ በኢኮኖሚው ውስጥ በያዘው የበላይነት  ከሕዝብ ተነጥቆ የወሰዱት መሆኑን ፃድቃን አይገነዘብ ለማለት ያስቸግራል።

ዛሬ ፃድቃን በድንገት ሳይሆን፣ ከመሰሎቹ ጋር አውጥቶ አውርዶ፣ ይህን ሊለን የፈለገው፣ለሕዝብና ለአገር ተቆርቋሪ ሆኖ፣ ወይም ለዲሞክራሲዊ ሥርዓት ግንባታ አስቦ ሳይሆን፣ በወያኔ አገዛዝ እርሱና መሰሎቹ ከአገርና ከሕዝብ ዘርፈው ያከማቹትን ሀብት በብቸንነት የሚጠቀሙበት ሁኔታ የማይኖር መሆኑን ሕዝቡ በየአቅጣጫው የሚያስተጋባቸው መፈክሮችና እየወሳዳቸው ያሉት እርምጃዎች ሰላም ስለነሳቸው ነው። በመሆኑም ፃድቃን፣የጥፋቱ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ወያኔና እርሱ  ያራመደውን  የዘር ፖለቲካና የተከለውን አገር አፍራሽ ሕገመንግሥት ተብየ፣ ከማውገዝ ተቆጥቦ፣ ግዑዙን ኢሕአዴግንና አስፈጻሚ አካሉን የጥፋቱ ተጠያቂ ለማድረግ ሞክሯል። ይህ ደግሞ «ዶሮን ሲያታልሏት፣ በመጫኛ ጣሏት» ከሚባለው አባባል ተለይቶ የሚታይ አይደለም። የአገራችን የችግር ቋጠሮው ወያኔ የተከተለው የዘር ፖለቲካና የተከለብን በዘር ላይ የተመሠረተ «ሕገመንግሥት» ነው። መፍትሔውም  በተጋጋለው ሕዝባዊ አመጽ  ወያኔንና ሥርዓቱን ማስወገድ ነው።

ስምንተኛ፦ ፃድቃን ገብረተንሣይ አገሪቱና ሕዝቧ አሁን ወዳሉበት የውድቀት ጉዞ እንዴት ሊደርሱ እንደቻሉ ምክንያቶቹን እንዲህ ሲል ይደረድራቸዋል። «የትጥቅ ትግል እና ከዚያም በኋላ በነበሩ ጥቂት ዓመታት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አስተሳሰቦችና ተግባሮች አልነበሩም ባልልም መሰረታዊ ባህሪው ግን ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ነበር የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ መቋጫ በህዝብ ተሳትፎ የፀደቀው ህገመንግስት ነው እላለሁ።» ካለ በኋላ፣ወያኔ የመንግሥት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ፣«የኢህአዴግን ዴሞክራሲያዊነት እሚፈታተኑ ሶስት ትልልቅ ክንዋኔዎች ተጽመዋል። እነዚህም ክንዋኔዎች የተፈቱበት መንገድ የኢህአዴግን ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ያጎሉ ከዛም በላይ ተቋማዊ (Institutionalize) እንዲሆን ያስቻሉ ናቸው ብየ አምናለሁ።» በማለት የወያኔ አገዛዝ አሁን እየደረሰበት ላለው ቀውስና ሕዝባዊ አመጽ ያበቁት ችግሮች፣ « አንደኛ፦ ከኦነግ ጋር  ቅራኔ አፈታት፣ ሁለተኛ፦ በህወሃት ውስጥ የተፈረውን የውስጠ ፓርቲ ቀውስ አፈታት፣ ሶስተኛ፦ የ1997 ዓም ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ የተፈታበት አግባብ ናቸው።» በማለት የችግሩን መገለጫ ክስተቶች ወያኔ/ኢሕአዴግ ለገባበት ቀውስና አገሪቱ ለገጠማት ዙሪያ ገብ ችግሮች መሠረታዊ ምክንያቶች እንደሆኑ ለማስረዳት ሞክሯል። እነዚህ ፃድቃን ችግሮች ናቸው ብሎ የደረደራቸው፣ አገሪቱ አሁን ለምተገኝበት ደረጃ ያደረሳት መሠረታዊ ችግሮች ሳይሆኑ፣ መሠረታዊ ችግሩ ከተከሰተባቸው አያሌ ክስተቶች ጥቂቶቹ ናቸው። ከፍ ሲል ማሳየት እንደተሞከረው፣ የአገሪቱና የሕዝቡ መሠረታዊ ችግር፣ ወያኔ የተከተለው የዘር ፖለቲካና በዚህ ላይ የመሠረተው የጎሣ ፌደራሊዝምና የዚሁ ማስፈጸሚያ የሆነው ሕገመንግሥት ተብየው ናቸው።

ችግሩን በቅጡ ሳያውቁ፣ መፍትሔ ላይ መድረስ አይቻልም። የኢነግና የወያኔ ቅራኔ መሠረቱ የሥልጣን ክፍፍል ነው። ኦነግ በሰው ብዛት፣ በተሰጠኝ ክልል ባለኝ የተፈጥሮ ሀብት እኔ ወያኔ የኔ ከሚለው የበለጠ ስለሆነ፣ የወሳኝነቱ ቦታ ለእኔ ይገባኛል የሚል ጥያቄና አቋምr ነው ያለው። ወያኔ ደግሞ፣የለም እኛ ታግለን ባገኘነው ድል የሰጠንህንና የፈቀድልንህን ይዘህ ተቀመጥ የሚል ነው። ይህ የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር አይደለም። የወያኔ ከሁለት መከፈልም የወያኔ የውስጥ ጉዳይ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ አይደለም። ወያኔ በዚህ መልክ ሲከፋፈል ይህ የመጀመሪያው አይደለም። የመጨረሻውም አይሆንም። በመሆኑም የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር አይደለም። በተመሳሳይ ሁኔታ የ1997ቱ ምርጫ ውጤት መቀበልና አለመቀበል፣ ያገሪቱ መሠረታዊ ችግር ሳይሆን፣ ወያኔ ላፀደቀው ሕገመንግሥት ተገዥ አለመሆን በመሆኑ፣ መሠረታዊ ችግር ሊሆን አይችልም። ይህም በመሆኑ ፣ፃድቃን መሠረታዊ ችግርን ከስበቦችና ከክስተቶች የመለየት አቅም ያንሰዋል ወይም ዕውቀት የለውም ለማለት አይቻልም። ማለት የሚቻለው የችግሮቹ  ምንጮች ከመሠረታቸው ከታወቁ፣ ወደ ግማሽ መፍትሔአቸው ስለሚያመራ፣ ያ እንዲሆን ባለመፈለጉ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ በሕዝብ ተሳትፎ የፀደቀው ሕገመንግሥት የሚለው ከተሻረ ለዘመናት እርሱና ቡድኑ ሲቋምጡለት የነበረው በዘረፋ ሀብታም የመሆን ጉዳይ፣ ተጠያቂነትን አስከትሎ ወደ ድህነት የሚያመራ መሆኑን ጠንቅቆ በማወቁ ነው።

ዘጠንኛ፦ ፃድቃን የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ እንደሆነና ኢትዮጵያዊ ሆኖ እንደሚኖርም ሊሰብክ ሞክሯል። አዎ! የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። ይህን ከወያኔ በቀር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ የለም። ወያኔ ግን ኢትዮጵያዊ አይደለህም ብሎ፣ በቋንቋ አጥር አስገብቶ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ በሥልጣን  የመቆየት አጋጣሚ ካጣ ሊገነጥለው እንደሚችል መንገዶችን እያመቻቸ እንዳለ በግልጽ ይታያል። ይህን ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ አይሆን ሲል አይደመጥም። ይህን የልጆቹን ጉዞ ካልገታ፣ ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባው ወያኔ እንጂ፣ ሌላ ኃይል አለመሆኑን ፃድቃን ይስተዋል አይባልም።

ከዚሁ ጋር አያይዞ፣ ፃድቃን «በመሃል አገር ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥላቻ ይንጸባረቃል። የትግራይ ሕዝብ በስርዓቱ እላፊ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ይታያል። ተጨባጭ ሁኔታው ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው።» በማለት የአደባባዩን  በጆሮ ሊነግረን ሞክሯል። ልብ በሉ፣ ይህ አባባል «የገብርኤልን ግብር የበላ ለፍልፍ ለፍልፍ ይለዋል» ይባላል። ይህ ጥላቻ በትግራይ ተወላጆች ላይ እንዲፈጠር ማን የጠቡን ዘር ዘራ? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ ወያኔ/ሕወሓት የሚል ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በ1968 ዓም ወያኔ ባወጣው ፕሮግራሙ፣የትግራይ ሕዝብ አውራ ጠላት ዐማራው ነው ብሎ የትግሬ ነገድ በነቂስ ዐማራን እንዲያጠፋ ቀስቅሷል፤ አደራጅቷል። ዐማራውን ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ፣ ገዥ፣ ወዘተ የሚሉ ስሞች ለጥፎ፣ በመላ አገሪቱ በሚኖሩ ነገዶች በጠላትነት ተፈርጆ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እንዲፈጸምበት ሠራዊቱን አዝምቷል። በዚህም ባለፉት 25 ዓመታት 5 ሚሊዮን ዐማሮች ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ አድርጓል። ወያኔ ራሱ ሤራ አድርቶ በቁጥጥሩ ሥራ ያዋላቸውን ዐማሮች ፣ በነፍሰ ገዳይ ጀሌዎቹ የነገዳቸውን እየጠራ «ሽንታም ዐማራ» «ፈሪ ዐማራ» «ልሀጫም ዐማራ፣ ልጋጋም ዐማራ» የሚሉ ስድቦች በምላተ ነገዱ ላይ የሚያወርደው ወያኔ፣ ሌላው ቢቀር ጥላቻውን መግለጹ ለፃድቃን ምኑ ታምር ሊሆንበት እንደቻለ የሚያስገርም ነው። ሰዎች የዘሩትን ያጭዳሉ። የትግሬ ተወላጆችም ወያኔ የዘራላቸውን ማጨዳቸው የማይቀር ነው። «ጥንት ነበር እንጂ፣ መጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ» የሚባለው አባባል ለዚህ ለፃድቃን የተጠላን እሮሮ ተገቢ ቦታው ሳይሆን አይቀርም።

በሥርዓቱ ትግሬ አልተጠቀመም ለሚለው አጭሩ መልስ « ግመል ሰርቆ አጎንብሶ» የሚለው የአባቶቻችን አባባል ከበቂ በላይ ምላሽ ይሆናል ብየ እገምታለሁ። ባይጠቀምማ፣ ትናንት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ ሁኔታ በደል ሳይፈጸምበት ተበደልን ብለው በርሃ የገቡት ልጆቹ ወደ በርሃ ለመግባት የሚቀድማቸው ባልነበር!

ፃድቃን በማጠቃላያ ሐሳቡ እንዲህ ይላል።« —-አሁን የሚታየው ፖለቲካዊ ችግር ከፖለቲካዊ ስርዓቱ አወቃቀርና የኢኮኖሚ ሁኔታው የሚነሳ ስለሆነ፣ስርዓታዊ (Systematic) ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለሆነም ነው ኢህአዴግ ችግሩን እያየ እያወቀ እየተነጋገረበት እያለም ለመፍታት ያስቸገረው ብየ አምናለሁ። ለወደፊቱም በገዥው ፓርቲ መዋቅርና ገዥው ፓርቲ በቀየሰው የህዝብ እንቅስቃሴ ብቻ አይፈታም የምለው።» በማለት የችግሩ አካል እና ፈጣሪ የሆነው ወያኔ ለችግሩ ብቻውን መፍትሔ ማስገኘት እንደማይችል እምነቱ መሆኑን አስረድቷል። ፃድቃን በዚህ የማጠቃለያ ሀሳቡ፣እስካሁን እየገነባ የመጣውን ማለትም፣ በሕዝብ ተሳትፎ የፀደቀው ሕገመንግሥት ለችግሮቹ ሁሉ መፍቻ ይሆናል ያለውን ሐሳቡን የሻረው እንደሆነ እንገነዘባለን። ወያኔ/ኢሕአዴግ ከሕዝባዊና ከዲሞክራሲያዊ እምነቱ እያፈነገጠ የሄደባቸውና ለዚህም ማሳያ ብሎ የጠቀሳቸው የኦነግ ቅራኔ አፈታት፣ የ1997 ምርጫ ውጤት ያስከተለው ችግር፣  እንዲሁም በወያኔ መካከል ለተፈጠረው ችግር ፣ችግሮቹን ለመፍታት የተጠቀሙበት ስልት፣ የችግሮቹ ሁሉ መሠረት ነው ሲል የቋጨውን ሀሳብ ከዚህ ላይ የቀደመ አቋሙን ሽሮ፣ የችግሩ ምንጭ ሥርዓታዊ እንደሆነ አረጋግጧል። ይህም ችግሩ  ዕውነተኛው  ቋጠሮ ሥራዓታዊ መሆኑንና የሥርዓቱ  መሠረት ደግሞ በሕገመንግሥቱ እንደሆነ መጠራጠር አይቻልም። መፍትሔውም ሥርዓቱን ከመሠረቱ መቀየር ነው። ይህም ሕዝቡን በቋንቋ የከፋፈለውን ሕገመንግሥት ተሽሮ፣ አገራችን፣ የግለሰቦች ነፃነትና የግል ሀብት የተከበረባት፣ ነፃ ገበያ እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት፣ ሥልጣን የሕዝብ ሆኖ፣ ባለሥልጣኖች ለሕዝብ ተጠያቂ የሚሆኑበት፣ ወዘተ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መዘርጋት ስንችል ነው።

Filed in: Amharic