>

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባበሩ፤ የታሪክ ግዴታችሁን ተወጡ እያለን ነው! [ሸንጎ]

ኢትዮጵያውያን ከባላባታዊ አገዛዝ ተላቀው የነፃነት አየር ለመተንፈስ ሲዘጋጁ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣኑን ከሕዝብ ቀምቶ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ለ17 ዓመታት እያሸበረ ረግጦ ሲገዛ ኖረ። አለመታደል ሆኖ ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ ሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሕዝባችን ሥልጣኑን ተቀምቶ ላለፉት 25 ዓመታት በጠባብ ብሄረተኛውና በዘረኛው በህወሓት አስከፊ የጭቆና አገዛዝ እየተረገጠ ይገኛል። ይህ ጠባብ ብሄርተኛ ቡድን የብሄር ጥላቻን መርዝ እየረጨና እንደ ፖለቲካ መቆያ ስልት እየተጠቀመ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ከፋፍሎና አዳክሞ ለአደጋ አጋልጧቸዋል። ዛሬ በአገዛዙ ያልተማረረ ኢትዮጵያዊ ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም። በሸንጎ እምነት የሀገራችን ሁኔታ ከመጥበሻው ወደ እሳቱ እንዲሉ፣ በየጊዜው ሁኔታዎች እየተባባሱና አስከፊ እየሆኑ መጥተዋል።
ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብታም ሆና ሳለ ብልሹ አስተዳደሮች በዓለም ደረጃ በድህነትና በረሃብ እንድትታወቅ አድርገዋታል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ ላሉት ችግሮች ሁሉ አልፋና ኦሜጋው አምባገነናዊ፣ ጠባብ ብሄርተኛውና በሙስና የተዘፈቀው የህወሓት ብልሹ አገዛዝ ነው። ይህ ኪራይ ሰብሳቢ ቡድን አባላቱን ሃብታም እያደረገ  አብዛኛውን  የኢትዮጵያን ሕዝብ በድህነትና በረሃብ አለንጋ ይገርፈዋል። ሕዝብ ለመብቱ ሲነሳ ህወሓት የሚስጠው መልስ ልዩ ኃይል ልኮ ሕዝቡን ማጥቃት ነው። የዚህ አገርአቀፍ የሆነ አስቃቂ የሥርዓት ግፍ መፍትሄው የህወሓትን አምባገነናዊ አገዛዝ ለአንዴና ለሁል ጊዜ በሕዝባዊ ትግል ከሥልጣን ማስወገድና አግላይ ያልሆነ የሀገሪቷን ዜጎች ሁሉ በእኩልነት የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ብቻ ነው። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያ አንድነትና የተቃዋሚ ኃይሎች በመተባበር በአንድነት፣ በአንድ ቋንቋ፣ በጋራ መታገል ይኖርባቸዋል። በእኛ እምነት መላው ዓለም ተቃዋሚውን ሊያክብረውና  ሊቀበለው የሚችለው በጋራ በሚያገናኘን መለስተኛ  ፕሮግራም ዙርያ በመሰባሰብ  ለአንድ ብሄራዊ ዓላማ ተፈላልጎ፤ ተፈቃቅዶና ተባብሮ ሲነሳ ነው።
ህወሓት፤ በኢህአዴግ  ሽፋን  ሕዝብን  እየረገጠ  የሚገዛው፤  ባለፉት  25  ዓመታት በወገኖቻችን ላይ የፈጸመው ግፍ በሀገራችን አራቱም  ማዕዘናት  የተካሄደ  ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብም ጠንቅቆ የሚያውቀው ሃቅ ነው። ህወሓት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ይጠቅሙኛል ያላቸውን እርምጃዎች ሁሉ ወስዷል። ሰብዓዊና  ዴሞክራሲያዊ  መብቶችን  ረግጧል፣  የነፃውን  ፕሬስ  አፍኗል፣  የሕዝብን  ድምፅ ሰርቋል፣ ኅብረ-ብሄር የሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶችን አፍርሷል፤ በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ድምፃቸውን  ያሰሙ  ወገኖቻችንን  አስሯል፣  ገድሏል፣  ከሀገር  እንዲሰደዱ  አድርጓል፣ እህቶቻችን በዐረብ አገሮች ስብዕናቸው እንዲደፈር አድርጓል፣ ወጣቶች ተሰደው በባህር እንዲሰምጡ፣  በበረሃ  እንዲሰየፉ  አስተዋጽዖ  አድርጓል፣  ሕዝብ  በሕዝብ  ላይ  እንዲነሳሳ መሠሪ የጠብ አጫሪነት ሚና ተጫውቷል፣ ኢትዮጵያዊነትን በመሸርሸር የጎሣ ፓለቲካን አስፍኗል፣ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ለማጋጨት ጥሯል፣ ኤርትራን አስገንጥሎ ሀገራችንን ያለ  ወደብ  አስቀርቷል፣  የሀገራችንን  መሬት  ቆርሶ  ለሱዳን  ለመስጠት ተስማምቷል፣ ነዋሪዎችን ከቀዬአቸው እያፈናቀለ  ለምና  ድንግል  መሬታችንን ለ”ኢንቬስተሮች” ቸብችቧል፤ በጎንደርና በወሎ መሬቶችን እየነጠቀ ወደ ትግራይ ክልል አጠቃሏል፤ ነዋሪውን ሕዝብ ሳያማክር በብሄርና  በቋንቋ  በማደራጀት  ስም  መሬት  ካንዱ ወደ ሌላው በማካለል ተዋድዶና ተቃቅፎ አብሮ የኖረን  ሕዝብ  ደም  በማቃባት  ሥፍር ቁጥር የሌለው ወገናችን እንዲገደል በማድረግ በኅብረተሰባችን ውስጥ የነበረውን መልካም ግንኙነት እንዲበጣጠስ አድርጓል፣ የአማራውን ሕዝብ እየከፋፈለና እያሳደደ መቆሚያና መኖሪያ አሳጥቶታል..ወ.ዘ.ተ፣ ወ.ዘ.ተ። በአጠቃላይ ህወሓት ለሀገር አንድነት፣ ለልማትና ዕድገት የቆመ አገዛዝ ሳይሆን ዜጎቿን  እየበደለና  እየረገጥ  አፍኖ  በመግዛት  ሀገርን ለማጥፋት ሌት ተቀን ቆርጦ እየሠራ ያለ አምባገነንና  አሸባሪ  አገዛዝ  ነው።  የሀገራችን ችግሮች እምብርትም ችግሮችን በመቀፍቀፍ የሚታወቀውና የዜጎችን መብቶች የሚረግጠው ይኽው አምባገነኑ ህወሓት ነው።

በሃያ አምስቱ የህወሓት አገዛዝ ዘመን በሀገራችን ውስጥ ሰላም ሰፍኖ አያውቅም። በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ በአርሲ፣ በጎንደር አደባባይ ኢየሱስ፣ በሲዳማ፣ በአኝዋክ፣ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች…ወ.ዘ.ተ ላይ የፈጸማቸው ጭፍጨፋዎች ለአብነት ከሚጠቀሱት ጥቂቱ ናቸው። በቅርቡ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሳቢያ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በጎንደር  እየተካሄድ  ያለው  ግፍ  የሀገራችንን  ሕልውና  አሳሳቢ  ደረጃ   ላይ   አድርሶታል። አገዛዙ ሁኔታዎችን በጥሞና መርምሮ ትክክለኛ መፍትሄ መስጠት ባህሪው አይደለምና ለሕዝብ ጥያቄ እየሰጠ ያለው ምላሽ አሁንም ኃይልን በመጠቀም ፀጥ  ለጥ  አድርጎ ለመግዛት መሞከርን ነው። የሚዘገንነው ደግሞ ማንም የውጭ ኃይል  ጣልቃ  ሳይገባበት በጎንደር ሕዝብ ቆራጥነትና ደፋርነት የሚካሄደው ሕዝባዊ አመጽ “የሽብርተኞች አድማ፤ የኤርትራ መንግሥት እጅ የገባበት፤ የግንቦት ሰባት/አርበኞች  ቅስቀሳ”  እና  ሌላም  ሌላም እያለ የፈጠራ ወሬ ያስተጋባል። የጎንደር ሕዝብ ምንም ያላሰበውንና  ያላደረገውን  ራሱ ፈጥሮ  ሕዝባዊ  አመጹ  “በትግራይ  ተወላጆች  ላይ”  እልቂት  ለማምጣት  ነው  ይላል። የጎንደር ሕዝብ እንደሌላው  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  ሁሉ፣  ህወሓት  ወንድሞቹና  እህቶቹ የሆኑትን የትግራይ ተወላጆች የማይወክል መሆኑን ጠንቅቆ የሚያውቅ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን፤ በጨዋነትና በትዕግስት የሚታገል ሕዝብ ነው።  ባጭሩ፤  የተመጽዋችነት ከረጢቱን ለመሙላት የሚጠቀምበትን  ካርድ ብቅ በማድረግ ችግር ፈጣሪዎቹ  አሸባሪዎችና የሻዕቢያ ተላላኪዎች ናቸው በማለት የአብዬን ወደ እምዬ እንዲሉ በሌሎች ላይ ለማላከክ እየሞከር ይገኛል። ይህ ጊዜ ያለፈበት  ብልጣብልጥነት  በኦሮሞያም፤  በኦጋዴንም፤ በጋምቤላም ወዘተ ታይቷል።   ሀቁ ግን ችግር ፈጣሪው እራሱ የህወሓት አገዛዝ ነው።

ወልቃይቴዎች ሕገ-መንግሥት ተብዬው በሰጣቸው  መብት  መሠረት  በተለያዩ  ጊዜያት በተለያዩ እርከኖች  ላይ  ለሚገኙት  የአገዛዙ  አካሎች  በሕጋዊ  መንገድ  የማንነት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ይህም ጥያቄያቸው፤ “እኛ አማራ እንጂ ትግሬ አይደለንም፤ የጎንደር አካል እንጂ የትግራይ አካል ለመሆን  አንፈልግም”  የሚል  ነው።  ሆኖም፤ በተጨባጭ ያገኙት ምላሽ ወልቃይቴ ነን ያሉትን ንብረታቸውን መዝረፍ፣ ማሰር፣ ሴቶችን መድፈር፣ መሬታቸውን መቀማት፣ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉትን  አፍኖ  ደብዛቸውን ማጥፋት፣ በሥራ መስክ አድልዖ ማድረግ…ወ.ዘ.ተ፣ ወ.ዘ.ተ ናቸው። ይባስ ብሎ አቤቱታቸውን ለአገዛዙ እንዲያሰሙ ሕዝብ የመረጣቸውን ወኪሎች አስሯል። በሰላም በመወያያት ችግሮችን ለመፍታት የሚጥሩ ወገኖችን ማሰርና ማሰቃየት ለህወሓት አዲስ አለመሆኑን ገና ከጠዋቱ የ1983 ዓ. ም የሰላምና ዕርቅ  ኮንፈረንስ  ላይ  ለመሳተፍ የተወከሉትን የተቃዋሚ ኃይሎች ማሰሩን ልብ ይሏል። ግፍ ሞልቶ ሲትረፈረፍ ሕዝብ መብቱን ለማስከበር ማናቸውንም እርምጃዎች  ይወስዳልና በጎንደርም  እየሆነ  ያለውም ይኼው ነው። በመሆኑም ሥፍር  ቁጥር  የሌለው  ሕዝብ  አልገዛም  ባይነቱን  በግልጽና በአደባባይ እየገለጸ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የጎንደር ወጣት፤ ሽማግሌ፤  መንፈሳዊ  አባት፤ እናት፤ ሴት፤ ወንድ፤ ሃብታምና ድሃ ሳይለይ  መላው  ሕዝብ  በሕዝባዊ  አመጹ  እየተሳተፈ ነው። በህወሓት ልዩ ቡድን የተገደሉትን የግል ባለ ኃብት ጎንደሬ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ለማክበር የወጣው ሕዝብ “የሦስት ጥምቀቶች” በዓልን ሕዝብ ቁጥር ያካትታል። ይህ ብቻ ሕዝቡ  ቆርጦ  የተነሳ  መሆኑን  ያሳያል።

አሁን ያለው መፍትሄ አንድና አንድ ነው። ኢትዮጵያ፣ የዓለምአቀፉን የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርን ፈራሚ ስለሆነች ይህንኑ ስምምነቷን አገዛዙ በተግባር  መተርጎም  ያለበት  ጊዜ ነው። ሀገራችን ወደ አስከፊ የሕዝብ  መተላለቅና  የንብረት  መውደም  ውስጥ  ከመግባቷ በፊት ለአገዛዙም የወንድ መውጫ በር እንዲሉ የሚበጀው አሁን ያለው  ፍጥጫ  ውጤቱ መጥፎ እንዳይሆን የሕዝብን ጥያቄ አዳምጦ በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ መሞከር ነው። ከሕዝቡ ጥያቄ አንዱና  ዋናው  የታሰሩትት  የኮሚቴ  አባላት  ያለምንም  ቅደመ  ሁኔታ መፍታት ነው። ሁለተኛው ሕዝቡን ለማስፈራራት ወደ ጎንደር  የተላከው  የህወሓት  የጦር ኃይል ወደ ካምፑ እንዲመለስ ማድረግ ነው።

አገዛዙ ይህንን ዕድል ተጠቅሞ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ሳይፈታ ቢቀር ለሚደርሰው የሕዝብ እልቂትና የንብረት መውደም ተጠያቂው ሙሉ በሙሉ ህወሓትና ህወሓት ብቻ መሆኑን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን። በአርቆ አሳቢው ሕዝባችን በኩል ደግሞ አገዛዙ ለሚያሰራጨው የጥላቻና የከፋፋይ ደባ ሰለባ ሳይሆን የሀገርና የወገንን ንብረት በመንከባከብ እስካሁን እንደሚያደርገው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን  በተላበሰ  መልክ  አንድነቱን  አጠንክሮ እጅ ለእጅ ተያይዞ የአገዛዙን ፀረ-አንድነትና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ቅስቀሳ በማምከን በወንድማማችና በእህትማማችነት መንፈስ በአንድነት በመታገል የአገዛዙና የሆድ-አደሮችን ቅስም በመስበር ትግሉን በማጧጧፍ ወደማይቀረው ሕዝባዊ ድል በሚያመራው ጎዳና ላይ እንዲጓዝ   እናሳስባለን።  በማንኛውም   ሕዝባዊ   እንቅስቃሴ   ውስጥ   አንዳንድ   ጋጠወጦች  የሚፈጥሩት አላስፈላጊ ጥፋት ሊኖር እንደሚችል በዓለም ላይ በተደጋጋሚ የታይ ቢሆንም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሠሩ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች መወገዝ ይኖርባቸዋል። በጎንደር ውስጥ ቤቶችና ንብረቶች ሲወድሙ አንድም ግለሰብ የሰውን ንብረት እንዳይነካ መደረጉ የሕዝቡን ጨዋነት ያስመሰክራል። ይህ ደግሞ ለመላው የዓለም ሕዝብ ከፍተኛ ትምህርት  ነው  እንላለን።
የሀገር ዳር ድንበርን ለመጠበቅና ሕዝብን ለማገልገል የተሰለፋችሁ የመከላከያ ሠራዊትና የፀጥታ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጣችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ግዳጃችሁ ሀገርንና ሕዝብን ማገልገል ነው። ከሕዝቡ ጎን ቁሙ እንላለን። ውሎ አድሮ እንደማንኛውም አምባገነን ትቢያ ለሚሆነውን አገዛዝ መጠቀሚያ በመሆን ታሪክና ትውልድ እንዳይጠይቃችሁ ወደ ሕዝብ ጎራ እንድትቀላቀሉ ከአሁኑ እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) በተደጋጋሚ እንዳቀረበው አሁንም የተቃዋሚ የአንድነት ኃይሎች፣ ድርጅቶችና መሪዎች፣ ሀገራችን መዳረሻው ወደማይታወቅበት አዘቅት ውስጥ  እያመራች  መሆኗን  በመረዳት  አዘቅቱ  ውስጥ  ከመግባቷ   በፊት   እንድንታደጋት በጋራ መታገል እንደሚገባን  አሁንም  በድጋሚ  ጥሪያችንን  እናቀርባለን።  ተቃዋሚዎች በሕዝብ የተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መመሥረት የሚችሉት የፖለቲካ ውድድር በማድረግ ስለሆነ ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ሀገር ስትኖር ነውና ተባብረን ሀገራችንን  ከህወሓት  መንጋጋ  እናላቅቃት  እንላለን።  ይህን  ማድረግ  ሳንችል  ብንቀር ታሪክና ትውልድ እንደሚጠይቀን በመረዳት ለዚህ  ሀገር  አድን  ጥሪ  አወንታዊ  ምላሽ በመስጠት  አሁንም በጋራ እንድንታገል ሸንጎ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
በመጨረሻም ሸንጎ ከጎንደር ሕዝብ ጎን መቆሙን እያረጋገጠ፤ የሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት እንዲከበር፣ ዜጎች በሕግ ፊት በእኩልነት እንዲታዩ፣ የዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ዜጎች በማኅበራዊና  በፖለቲካው  ዘርፍ  እኩልነታቸው  እንዲረጋገጥና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትመሠረት የሚታገል  ድርጅት  ነውና  የጎንደር  ሕዝብ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ትግል  ሙሉ  በሙሉ  ይደግፋል፣  ተጠናክሮ እንዲቀጥልም  የድርሻውን  ያበረክታል።  በአንፃሩ  ደግሞ  አገዛዙ  በጎንደርና   በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚያካሂደውን ጭፍጨፋ እስራትና ግድያ ሸንጞ በከፍተኛና በማያሻማ ቋንቋ ያወግዛል።
የተባበረ ትግል የድል ዋስትና ነው!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

 

Filed in: Amharic