>
9:29 am - Tuesday September 25, 2018

አቶ አሰፋ ጫቦና የትዝታ ፈለግ መጽሃፍ [እንግዳ ታደሰ]

Assefa_chabo_yetizeta_feleg_largeባለፈው ቅዳሜ ዕለት የሰንበት ቡና ፉት ከምንልባት አንድ ካፌ ቤት ውስጥ ሰብሰብ እንዳልን ፣ አቶ አሰፋ ጫቦ በተደጋጋሚ ስሙን የሚጠቅሱት እንደሳቸው አጠራር – አፋሩ/ ዩሱፍ ያሲን በአንዲት ከረጢት የአቶ አሰፋ ጫቦን የትዝታ ፈለግ መጽሃፍ ሸክፎ ብቅ አለ ፡፡ « የአሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት መጽሃፍ ደራሲ » የሆነው የቀድሞው ዲፕሎማት ጋሽ ዩሱፍ ፣ አገር ቤት ስትታተም በምትታወቀው ጦቢያ መጽሄት ላይ ፣ ሀሰን ዑመር አብደላ በሚል የብዕር ስምም ይታወቃል ፡፡

ገና በትኩሱ ኦስሎ ውስጥ እንደ አቶ አስፋ ጫቦ መጽሃፍ የደረሰንን መጽሃፍ አላስታውስም ፡፡ ወዲያው ከጋሽ ዩሱፍ እጅ ላይ ገንዘብ እጅ በእጅ ወዳጅ እንዲደረጅ በማለት መጽሃፉን ተረከብነው ፡፡ ጋሽ ዩሱፍ ራሱ የጻፈውን መጽሃፍ ለሰዎች ሁሉ ያለገንዘብ ሲሰጥ ፣ ስለማውቀው በአቶ አሰፋ ጫቦ መጽሃፍ ላይም « ጥቂት ተመጣጣኝ እርምጃ እንዳይወስድ » ሰግቼ ነበር ፡፡ ግን ያን ዕለት አልሆነም ፡፡

ጋሽ ዩሱፍ መጽሃፉን በየጃችን ሲያቀብለን ዘወትር ካፌ ቤት ተደዋውለንና ተጠራርተን የሚሞግተኝና ፥ የምሞግተው አንድ ወዳጄ የኦነግ አባልም አብሮን ነበር ፡፡ ጋሽ ዩሱፍ አንድ መጽሃፍ አውጥቶ ለኦነጉ ወዳጄ ሰጠው ፡፡ በመሃል ገባሁና ፣ጋሽ ዩሱፍ ተሳስተሃል እርሱ እኮ ፊደል የቆጠረው በቁቤ ስለሆነ አማርኛ አያነብም ደግሞም አቶ አሰፋ ጫቦ ነፍጠኛ ማነው ብለው በከተቡት መጣጥፍ ውስጥ ኦነግን ስለሚጎሽሙ መጽሃፉን የሚወደው አይመስለኝም ብየ የዕለቱን ጨዋታ ከፈትኩ ፡፡

አዎ ! ወዳጄ የኦነጉ አባል እንዳልኩት አሰፋ ኦነግን አይወድም ብሎ በማሳሳቅ ጨዋታውን ሊዘል ሞከረ ፡፡ ለማንኛውም ይህን መጽሃፍ እዚሁ አጠገባችን ላሉት የቀድሞው የኦነግ መሪ አቶ ሌንጮ ለታ መጽሃፉን ካላገኙት ባያውቁኝም እኔ ራሴ ገዝቸ እንዲያነቡት ላበረክትላቸው እፈልጋለሁ ፡፡ ኧረ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል እንዲሉ በነካ እጄ አቶ ሌንጮን ለታ ካነሳሁ አንድ የቀድሞ ጨዋታን ላንሳ ፡፡ አንድ ቀን አሁንም የአቶ አሰፋ ጫቦን አባባል ልዋስና ፣ ከአፋሩ/ አቶ ዩሱፍ ያሲን ጋር ጥቁር ቡና ይዘን ስንጫወት ፣ አቶ ሌንጮ ለታ ባጠገባችን ሲያልፉ ቆም አሉና ፣ ጋሽ ዩሱፍን በንግሊዘኛ አናግረው እርሳቸው ዘወትር ወደሚያዞትሩበት መዝናኛ ቤታቸው ገቡ ፡፡

ነገሩ ግርም ብሎኝ ፣ ጋሽ ዩሱፍን ዘወትር ስትገናኙ በንግሊዘኛ ነው እንዴ የምትወያዩት በማለት ስጠይቀው ፣ ልክ እንደ አቶ አሰፋ ጫቦ ጋሽ ዩሱፍም እያዋዛ ይጫወታል ፣ የለም ! አንተ የሸዋ ነፍጠኛ መሆንህን ተረድቶ ይሆናል በአማርኛ ስናወራ ስለሰማ እንደዛ ቆጥሮህ መሆን አለበት ብሎ አሳቀኝ ፡፡ ዉነቴን ነው ምናልባት ጋሽ ዩሱፍ ለአቶ ሌንጮ ይህን መጽሃፍ ካልሰጣቸው በኔ ይሁንብኝ እኔ ነኝ ገዝቼ የምሰጣቸው ፡፡

የአቶ አሰፋ ጫቦን መጽሃፍ አንዴ ከጀመሩት አቁሙት አቁሙት አያሰኝም ፡፡ ሚስት ያለው ከሚስቱ ጋር ጊዜ ስለሚያሳጣ እንዳያነታርክ ፣ ቢያንስ ሚስትን ከጥሩ ጥሩ ፊልሞች ጋር ቴሌቪዥን ላይ እንድትውል ማድረጉ አይከፋም ፡፡ የአቶ አሰፋ የጽሁፍ ስታይል አፈሳሰስ እጅግ ያስደምማል ፡፡ በአንድ« ቢያጆ » የጽሁፍ ርዕስ አዙረው ፥ አዙረው የተነሱበትን ርዕስ ሳቱት ብላችሁ ስታስቡ የተነሱበት ርዕስ ላይ በሚገርም ሁኔታ መጥተው ይቋጩታል ፡፡ የቱን አንስቼ የቱን እንደምል ቢቸግረኝም ፣ በተለይ « በማተቤ ልዳኝ » የምትለዋ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎችና ፣ በአጠቃላይ ፖለቲካችንን ሲዘውሩት የነበሩትን ሰዎች ማንነት አቶ አሰፋ ጫቦ ቁልጭ አድርገው ሲያሷያችሁ … እውነትም ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን አገር ስለሆነች እንጂ ! እንዲህ ሃዲዷን ስታ ስትንገራገጭ 25 ዓመታትን አይደለም አንድ ወርም ያህል አትከርምም ነበር ፡፡ ካልተሳሳትኩ ከሶስት ቀን በፊት ነው ኢትዮጵያA350 ኤየር ባስ የተባለውን አውሮፕላን የተረከበችው? ይገርማል !! እነ አቶ ዳዊት ቦሌን ከነአውሮፕላኑ ሊያፈርሱት እንደነበር ስንቶቻችሁ ሰምታችኋል ? የጦር መርከቦችን እንደሸጧቸው ፥ ኢትዮጵያ አየር ኃይል አያስፈልጋትም ፣ የአየር ኃይል ሚልሽያ እንጂ እንዳሉት ይህችን እንኳ አቶ አሰፋ አላሉም ፣ ብቻ ምን አለፋችሁ የአቶ አሰፋ ጫቦን መጽሃፍ አንብቡት ፡፡

መጽሃፉ እጄ የገባበት ቀን እጅግ የከረረ ጸሃይ ስለነበር ቀዝቀዝ የሚያደርግ ቢራ ለመጎንጨት ከካፌዋ ቤት ለቀን ወደ አንድ ቢራ ቤት ጎራ እንዳልን ፣ ቢራችንን አዘን ስንጨዋዋት…እዚህ ቦታ ግን አቶ ዩሱፍ የለም…ታላቁ የሞስሊሞች አቢይ ጾም ረመዳን መሆኑንን ሳንዘነጋ ፣ ሰረቅ እያደረግሁ ከመጽሃፉ አንዳንድ ርዕስ እየመርጥኩ ሳነብ ፣ አብረውኝ ያሉት በሙሉ የድሬዳዋና ፥ የሃረር ሰዎች ስለነበሩ…አቦ ! አትደብረና… ወይ ተጫወት ከኛ ጋር ወይ ላይብረሪ ሂድ እያሉ ሲጎሽሙኝ …አበሻና ኮንስፓረሲ ??

ባጠቃላይ የአቶ አሰፋ ጫቦ መጽሃፍን ከፍቶ..ከወዳጅ ጋር መጨዋወት ያቀያይማልና ቤቴ ይሻላል ብየ ወደ ቤት መሄዱን መረጥኩ ፡፡ ይኽው አሁንም ከሥራ መልስ በሚገኘው ጊዜ ከአቶ አሰፋ መጽሃፍ ጋር እዛናናለሁ ፡፡

Filed in: Amharic