>

የኢትዮጵያ-ኤርትራ የጦርነት ጨዋታዎች፣ [ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም - ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ]

ይህን አስቂ ኝ (አስለቃሽ) ትአይንት  (ትያትር)  ፊልም ከዚህ ቀደም አላየነውምን?Wargames Amharicእ.ኤ.አ ሚያዝያ 2011 ዘ-ህወሀት የሕዝብን ስሜት ለማስቀየስ (ለማወናበድ ) ስለሚያካሂደው የጦርነት ጨዋታ  ትችት በጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡

ዘ-ህወሀት ማለት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘው የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች የመረጃ ቋት ስም ዝርዝር ውስጥ ስሙ ተመዝግቦ የሚገኝ አሸባሪ ድርጅት ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 አሁን በህይወት የሌለው የዘ-ህወሀት መሪ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ለመለኮስ እና ከግብጽ ጋር ደግሞ የውኃ ጦርነት ለማካሄድ የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም ስለጦርነት አይቀሬነት ድምጹን ከፍ አድርጎ በማጉላት የወሬ ክኩን ይሰልቅ ነበር፡፡

በዚህም መሰረት ይኸው በአሁኑ ጊዜ እ.ኤ.አ ሰኔ 2016 ወደለመድነው የጦርነት አረንቋ ተመልሰን ለመዘፈቅ አሀዱ/አንድ በማለት ጀምረናል፡፡

ባለፉት ጥቂት ቀናት እንደገና በድጋሜ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ስለ”ጦርነት” ሰበካ፣ ስለጦርነት ሟርት እና ስለጦርነት ከበሮ ድለቃ ሌት ከቀን እየተለፈፈልን ሳንወድ በግድ እንድናዳምጥ በመደረግ ላይ እንገኛለን፡፡

እናም ይህንን የሕዝብ ስሜት/ቀልብ ማስቀየሻ ጦርነት እንደገና መመልከት ይኖርብናልን?

የዘ-ህወሀት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ጌታቸው “አፈ ጮሌው” ረዳ እንዲህ በሏል፣ “በሁለቱም ወገኖች በኩል ከፍተኛ የሆነ እልቂት ተፈጽሟል፣ በይበልጥ ደግሞ በኤርትራ በኩል ያለው ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እርምጃዎችን ስንወስድ ቆይተናል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ እስከ አሁን ድረስ ስንወስዳቸው ከቆዩት እርምጃዎች በዓይነቱ እና በመጠኑ ከፍ ያለ እርምጃ መውሰድ በጣም ጠቃሚ ነገር ስለሆነ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ወስደናል፡፡“

ኤርትራ በበኩሏ 200 የኢትዮጵያ ወታደሮችን በመግደል ከ300 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ቁስለኛ አድርጊያለሁ የሚል መግለጫ ይፋ አድርጋለች፡፡

የካሊፎርኒያ ግዛት የዩኤስ አሜሪካ ታዋቂ የምክር ቤት አባል/ሴናተር የሆኑት ሂራም ጆሀንሰን ከብዙ ጊዜ በፊት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ጦርነት በሚመጣበት ጊዜ የመጀመሪያው የጥቃት ሰለባ የሚሆነው “እውነት” ነው፡፡“

ሁለት የጦርነት ተፋላሚ ቡድኖች በአንድ ዓይነት “እውነት” ላይ የጋራ ስምምነት ሲያደርጉ የምመለከት ከሆነ “እውነት” የመጀመሪያ እና ብቸኛ የጥቃት ሰለባ ሆኖ ስለመቆየቱ መገረም የምጀምር ይሆናል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የጠነባን ዓይጥ ማሽተት እጀምራለሁ፡፡ የጠነባን ዓይጥ ገና ከ10 ሺ ሜትሮች ርቀት ላይ ማሽተት እችላለሁ፡፡ ያ ሽታም  በኢትዮጵያ-ኤርትራን ጦርነት በሚባለው ላይ ተንሳፎ ይገኛል! (እፍ እፍ እፍ!!!)

በእርግጥ የጆሀንሰን ቁም ነገር የጦርነት ሰለባ መርህ አነጋገር  በጦርነት ተጫዋቾች ላይ አይሰራም፡፡

ለበርካታ ዓመታት ሳስተውለው እንደቆየሁት የዘ-ህወሀት አመራሮች ከሕዝብ ጋር መጥፎ የሆነ የግንኙነት አባዜ ላይ እንደወደቁ አድርገው እራሳቸውን በሚቆጥሩበት ጊዜ ለዚያ ማስቀየሻ ዘዴ ጦርነትን ያውጃሉ፡፡

ዘ-ህወሀት በህዝብ ላይ የሚፈጽመውን ሰብአዊ ወንጀል፣ ሙስና፣ ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም እና ሰላማዊ ዜጎችን መጨቆንን ለመደበቅ ሲያስብ የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ስሜት ለማስቀየስ የሚያጋልጡትን መጥፎ ዜናዎችን ማፈን እና የሕዝብን ስሜት የማስቀየስ መንገድ እንደሚጠቀም እገምታለሁ፡፡

ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ለዘ-ህወሀት መጥፎ ዜናዎች እንደነበሩ ምንም ዓይነት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡

ባለፈው ሳምንት የዩኤስ አሜሪካ የቦንድ እና የአክሲዮን ልውውጥ ኮሚሽን ዘ-ህወሀት ህገወጥ ወንጀለኛ በሆነ መልኩ ከደጋፊዎቹ እና ጥቅም አገኛለሁ ብለው ለቦንድ ግዥ ክፍያ ሲፈጽሙ ከቆዩት ኢትዮ-አሜሪካውያን 6.5 ሚሊዮን ዶላር በህገወጥ መልክ ዘርፎ በመገኘቱ ያወናበደዉን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲመልስ ቅጣት ጥሎበታል፡፡ ዘ-ህወሀቶች ኮሚሽኑ ለሚያቋቁመው አስተዳዳሪ እ.ኤ.አ ሀምሌ 8/2016 ከማለፉ በፊት መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

ይህ ድርጊት ለዘ-ህወሀት ትልቅ ውርደት እና የኢትዮጵያውያንን እና የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ኪስ በማራቆት በአፍሪካ ታላቅ ግድብ እሰራለሁ በማለት መቋጫ የሌለው ዲስኩሩን ሲያሰማ በነበረው እና አሁን በህይወት በሌለው በወሮበላ ዘራፊው መሪ በአምባገነኑ መላስ ትውስታ ላይ ታላቅ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ነገር ነው፡፡

ባልተመዘገበ እና ህገወጥ በሆነ የቦንድ ሽያጭ በማጭበርበር ግዙፍ የሆነ ግድብ በአፍሪካ እገነባለሁ ማለትን እስቲ አስቡት ጎበዝ! ቦንድ የማጭበርበር እኩይ ምግባሩን መከላከያ ዘዴ መሆኗ ነውን?

በዩኤስ አሜሪካ ሕግ መሰረት ያልተመዘገበ ቦንድ መሸጥ ሕገ ወጥ ነው በማለት ከሶስት ዓመታት ገደማ በፊት የተናገርኩ ሲሆን ከተናገርኩ ከሶስት ዓመታት በኋላ የዘ-ህወሀት መሪዎች የማጭበርበር አባዜ የተጠናወታቸው በመሆኑ ከማሰሮው ውስጥ እጃቸውን እንዳስገቡ እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ ማሰብ እችላለሁ፡፡

የሚሰማ ጆሮ እና የሚያስተውል አእምሮ የላቸውም እንጅ እ.ኤ.አ ግንቦት 8/2013 ፊት ለፊት እና በቀጥታ ነግሪያቸው ነበር፡፡ ይህንን ነገር አታድርጉ! ያልተመዘገበ ቦንድ አትሽጡ! በዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል እና የአካባቢ መንግስታት ሕግ መሰረት ወንጀል ነው ብዬ ነግሪያቸው ነበር፡፡ ወንጀልን አትስሩ፣ ከጊዜ በኋላ አደጋው የሚያንዣብብ እና የሚያስጠይቃችሁ ይሆናል በማለት በግልጽ ተናግሬ ነበር፡፡

እንደተናገርኩት ከሶስት ዓመታት በኋላ ያልተመዘገበ ቦንድ ሽያጭ (ወንጀል ነው፣ የ1933 የቦንድ ድንጋጌ ክፍል 20 (b)ን ይመልከቱ) ወንጀል ስለሆነ ማጅራታችዉን ተያዙ፡፡

ሆኖም ግን የዘ-ህወሀት ያልተመዘገበ ቦንድ ዋና ሻጮች የወንጀል ቅጣቱን በማጭበርበር አንደተለመደው ሊያልፉት አልቻሉም፡፡

በእርግጥ አላለፉትምን?

የዘ-ህወሀት መሪዎች ለበርካታ ዓመታት ያህል ሰብአዊ መብቶችን እየደፈጠጡ ምንም ዓይነት ተጠያቂ ሳይሆኑ ደረታቸውን ነፍተው ተቀምጠው እንደሚገኙት ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በአሜሪካ ሕጎች ላይም አፍንጫቸውን በመንፋት ከወንጀል ተጠያቂነት የሚያመልጡ መስሎ ታይቷቸዋል፡፡

በምንም ዓይነት መልኩ ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡

ጉዳዩ በኮሚሽኑ (SEC) ግልጽ እና ይፋ ከሆነ በኋላ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂዩማን ራይትስ ዎች (ሂራዎ)/Human Rights Watch (HRW) “ጭካኔ የተመላበት እርምጃ፡ ለኢትዮጵያ ኦሮሞዎች ተቃውሞ የተሰጠ የግድያ እና እስራት ምላሽ“ በሚል ርዕስ ትልቅ ዘገባ አቅርቧል፡፡

ያ ዘገባ “ከመጠን ያለፈ እና አላስፈላጊ የሆነ የጥላቻ ኃይል መጠቀም እና ዜጎችን በጅምላ በቁጥጥር ስር የማዋል፣ መጥፎ የእስር ቤት አያያዝ፣ የሰላማዊ አመጽ እንቅስቃሴውን ለማኮላሸት የመረጃ ምንጮችን መቆጣጠር“ በማለት ዝርዝሩን አቅርቧል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት የሂራዎ/HRW የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክር የሆኑት ሌዝሊ ሌፍኮው እንዲህ ብለው ነበር፣ “የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች የሰው ልጆችን ህይወት ከቁብ ሳይቆጥሩ የጭካኔ ተኩስ በመክፈት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን፣ አርሶ አደሮችን እና ሌሎችን ሰላማዊ ዜጎችን ገድለዋል፡፡“

ለሰው ልጆች ህይወት ምንም ዓይነት ቁብ ሳይሰጡ በሰላማዊ ተቃዋሚ ስብስብ ላይ የጭካኔ ተኩስ መክፈት በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ሰብአዊ ወንጀል ነው፡፡ ይህንን የምለው ለታሪክ ምዝገባ ብዬ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2015 የዘ-ህወሀት ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በአመጹ ላይ የተገደሉት ሕዝቦች “ሁከት እና ብጥብጥን ዓላማ ያደረገ የተደራጀ እና የታጠቀ አሸባሪ ኃይል በመፍጠር ሞዴል አርሰ አደሮችን፣ የህዝብ መሪዎችን እና ሌሎች በክልሉ የሚኖሩትን የጎሳ ቡድኖች መግደል በመጀመራቸው ነበር” ብሏል፡፡

የሚገርም ነገር እኮ ነው ጎበዝ! በመንገድ ላይ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ የሁለተኛ ደረጃ እምቦቃቅላ ተማሪዎች እና የኮሌጅ ተማሪዎች በምን መስፈርት እና መለኪያ ነው “የተደራጀ እና የታጠቀ አሸባሪ ኃይል” ሊባሉ የሚችሉት? ወያኔ በእራሱ የፍርሀት ምዕናብ እየፈጠረ በህዝብ ላይ የሚነዛው ሽብር ካልሆነ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

ውሸት እና ቅጥፈት በሚነገርባት ምድር ፑፍ የተባለው ድራጎን (ዘንዶ)፣ ሳንዲ እየተባለች የምትጠራውን ተንቀሳቃሽ ሲኒማ ልጃገረድ ውሸት እና ቅጥፈት ወደሚነገርባት ምድር የወሰደበትን ታሪክ  አስታወሰኝ፡፡ ሳንዲ እዚያ ከደረሰች በኋላ በሬ ወለደ እያለ የሚናገረውን ፕናክዮንን አገኘችው፡፡

ውሸት እና ቅጥፈት በሚነገርባት ምድር ፑፍ እና ሳንዲ ማንም አይቷቸው የማያውቅ ቀይ እና ሰማያዊ ላም እንዲሁም ቀይ እና ነጭ ዝሆንም አዩ፡፡

13 ወራት ሙሉ ውሸት እና ቅጥፈት በሚነገርባት በዘ-ህወሀት ቁጥጥር ስር ባለችው ኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ልጆች እና የኮሌጅ ተማሪዎች ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር እንደተዘጋጀ ቡድን ተቆጥረው “የተደራጀ እና የታጠቀ አሸባሪ ኃይል” ሆነው ይታያሉ፡፡

ኢትዮጵያ 13 ወራት ሙሉ የፀሐይ ብርሀን የሚፈነጥቅባት ሀገር መሆኗን ነበር እኔ የማስታውሰው፡፡

በነገራችን ላይ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ሌሎች እ.ኤ.አ በ2007 በኬንያ ተደርጎ በነበረው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ተከስቶ በነበረው ውዝግብ ወደ 2000 ገደማ በሚሆኑ ሰላማዊ ኬንያውያን ዜጎች እልቂት ላይ እጃቸው አለበት በሚል የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እ.ኤአ. በ2012 ክስ መስርቶባቸው ነበር፡፡

ሂራዎ/HRW በኦሮሞ ሰላማዊ አመጸኛ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው እልቂት እንዲጣራ ነጻ የሆነ አጣሪ አካል እንዲቋቋም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሆኖም ግን ዘ-ህወሀት እንደተለመደው የዝሆን ጆሮ (የጅብ ሆድስ አለኝ) ይስጠኝ በማለት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል፡፡

ዘ-ህወሀት ወደ 20 ሚሊዮን ገደማ የሚሆነውን ህዝብ እያሰቃየ ያለውን የረሀብ ሁኔታ አያያዝ በሚመለከት እያደረገ ስላለው ፍጹም የሆነ ብቃትየለሽነት እና ይኸ አውዳሚ የሆነ ረሀብ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ሰቆቃ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እይታ ደብቆ ለማቆየት እያደረገ ባለው አሳፋሪ ጥረት የህዝብ ግንኙነት ስራው በመጥፎ ሁኔታ ተበላሽቶበታል፡፡

ከዩኤስኤአይዲ/USAID እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋች አቃጣሪዎች መጥፎ ሸፍጥ ጋር በመተባበር ዘ-ህወሀት ድርቁ ካጠቃቸው አካባቢዎች ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይወጣ በማድረጉ እና ጋዜጠኞች ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ እውነታውን ለእራሳቸው እና ለህዝቡ ፈልፍለው እንዳያወጡ በመከልከሉ ደባ ተሳክቶላቸዋል፡፡

እስከ አሁን ድረስ ዘ-ህወሀት ስለረሀቡ ሁኔታ ስለጠቅላላ ተጠያቂነቱ እና ግዴለሽነቱ፣ ለብቃትየለሽነቱ እና ወንጀለኛነቱ ምንም ነገር ባለመሆኑ ስኬታማ ሆኗል፡፡ (ለዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ ለጋይሌ ኢ. ስሚዝ የጻፍኩትን ደብዳቤ ይመልከቱ፡፡)

ዘ-ህወሀት ሁሉንም መጥፎ ዜናዎች ሁሉ ፍጹም በሆነ መልኩ ለምን እንደሚያፍን ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡

ዘ-ህወሀት የህዝብን ስሜት ለማስቀየስ መጥፎ ዜናዎችን በማፈን የጦርነት ወሬዎችን ከማምረት እና የጦርነት ነጋሪት ከመጎሰም የተሻለ ምን የተሻለ ስልት ሊኖረው ይችላል?

በዘ-ህወሀት እና በስተሰሜን በኩል ባሉት ጠላቶቹ መካከል የሚካሄደው ጦርነት በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ይደረግ እንደነበረው የጽጌረዳ ጦርነት ዓይነት ነው፡፡ የተለያዩ አባላት በሆኑት በአንድ ቤተሰብ መካከል የሚደረግ ጦርነት የውስጥ ጦርነት ነው፡፡

ዘ-ህወሀት እና ጠላቶቼ ናቸው እያለ የሚወነጅላቸው ኃይሎች በወንድማማችነት በአንድ ላይ ሆነው ለበርካታ ዓመታት በመዋጋት ወታደራዊውን አገዛዝ በማስወገድ ስልጣንን ተቆጣጠሩ፡፡ በወታደራዊ ኦፕሬሽን እና በህዝብ ግንኙት ስራ በአንድ ላይ ሆነው በመረዳዳት በወታደራዊ ጓደኝነት ሲታገሉ ቆይተው ነበር፡፡

በርካታ የዘ-ህወሀት አመራሮች ከጠላቶቻቸው ጋር የቤተሰብ እና የስጋ ዝምድና ትስስር እንዳላቸው ከበቂ በላይ ማስረጃ ሊቀርብበት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡

ዘ-ህወሀት እ.ኤ.አ በ1991 ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ አሁን እየከሰሷቸው ካሉት ጋር አስቂኝ በሆነ የመድረክ ላይ ተውኔት በደስታ ስልጣንን ተካፍለው እንደ አበደ ውሻ ጭራቸውን በመቆለፍ ቆዩ፡፡ ያ ሁኑታ ግን እ.ኤ.አ በ1993-94 ላይ ተቋረጠ፡፡

እ.ኤ.አ ከ1998-2000 ባለው ጊዜ ውስጥ ሁለቱ የጦር ጓደኛሞች በድንበር ጦርነት ተጠመዱ፡፡ ኤርትራውያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በመጣስ የኢትዮጵያን ግዛት ተቆጣጠሩ፡፡ ሆኖም ግን በግጭቱ ከ70 እስከ 120 ሺ የሚገመት የወታደሮች እና የሲቪል ዜጎች ህይወት ከተገበረ በኋላ ተቆጣጥረውት ከነበረው ግዛት በኃይል ተባረሩ፡፡

አሁን በህይወት የሌለው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስቡ አለቃ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ወዲያውኑ የድል ዜናን አወጀ፣ እናም በዓለም አቀፍ የሽምግልና እርቅ ሰበብ በተሰላ የፖለቲካ የሸፍጥ ስሌት እና በሀገር ክዳት ወረውት የነበረውን የሀገሪቱን አንጡራ ግዛት ተመልሶ ኤርትራውያኖች እንዲወስዱት በመፍቀድ የተንበርካኪነቱን የመድረክ ላይ ተውኔት አከናወነ፡፡

አምባገነኑ መለስ ጠንካራ የሕግ መከላከል ጥረትን ማድረግ ሲችል የሽምግልና የዕርቅ ስምምነቱ የተጻፈበትን ወረቀት ዋጋ አያወጣም በማለት የሀገርን ጉዳይ እንደተራ ነገር በመቁጠር ጉዳዩን አጣጣለው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የቀድሞ የጦር ጓደኛሞች በጦርነት ላይ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ የሌባ ጣቶቻቸውን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ በመቀሰር የተለመደ ተራ ቅጥፈታቸውን በማራመድ ላይ ናቸው፡፡

ሆኖም ግን እነዚህ ውሸት እንጅ እውነት በአፋቸው የማይገባ ኃይሎች በእርግጠኝነት ጦርነት ያካሂዳሉ ወይስ ደግሞ የጦርነት ጨዋታ በመጫወት ላይ ነው የሚገኙት?

ሆኖም ግን ለምን እርስ በእርሳቸው እንደሚዋጉ ትክክለኛውን ነገር አይናገሩም፡፡

አንድ የኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣን እንዳቀረበው ውንጀላ ከሆነ የኤርትራ መሪዎች በሰው ልጆች ላይ የመብት ረገጣ ማለትም ማሰቃየትን፣ ግድያ እና በባርነት መያዝን ጨምሮ የሰብአዊ መብትን ይደፈጥጣሉ የሚል ዘገባ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የምታቀርበው ኢትዮጵያ ናት የሚለው የመድረክ ላይ ትወና የተተወነው በኢትዮጵያ ነው በማለት በኢትዮጵያ ከምስክሮች የሚሰበሰበው መረጃ እንዳትረጋጋ ለማደረግ ጥረት ለምታደርገው ሀገር ለኤርትራ ጥሩ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ እንድታገኝ አስችሏታል፡፡

የተመድ ዘገባ ለጦርነቱ መንስኤ መሆን ችሏልን?

“ሀገሮች ለምን እንደሚዋጉ“ በሚል ርዕስ ሪቻርድ ኔድ ሌቦው በ2010 በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ አራት ታሪካዊ ዓላማዎች፡ ፍርሀት፣ ፍላጎት፣ ዝና እና በቀል በሚል መንግስታት ጦርነትን እንዲቀሰቅሱ ይመሯቸዋል በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል፡፡ አብዛኞቹ ጦርነቶች ለዝና እና ቀደም ሲል አንዱ መንግስት በጠላቱ ላይ ድልን በመቀዳጀት ግዛቱን ያስለቀቀው ከሆነ ያንን ለመበቀል ሲባል የሚደረጉ ናቸው በማለት ይሞግታሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ዝና፣ በቀል እና ግዛትን ለመያዝ ሲባል በሁለቱ መንግስታት መካከል ለጦርነት መንስኤ ሊሆን ይችላልን?

እኔ የማደርጋቸው የአምባገነንነት እና ጦርነት ጥናቶች በእነዚህ ነገሮች የሚቀሰቀስ ሌላ የተለዋጭ ገለጸ ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡

“የጦርነትን ካርድ” ማውጣት በአምባገነኖች የእጅ መጽሐፍ ውስጥ ያለ አሮጌው የማጭበርበር ዘዴ ነው፡፡

የእጅ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፣ “የህዝብ ጥላቻ ሲመጣ ጦርነትን አውጅ፡፡ እውነተኛ ወይም ደግሞ የውሸት የማስመሰያ ጦርነት አውጅ፡፡ ምንም ዓይነት ችግር የለውም፡፡ ስለጦርነት አውራ፡፡ የጦርነት ቅስቀሳን ሆን ብለህ አሰራጭ፡፡ የጦርነት ከበሮ ምታ፡፡ የጦርነት ጨዋታዎችን ተጫወት፡፡“

ግን ለምን ጦርነት?

ምክንያቱም ጦርነት የተረጋገጠ እና በተግባር የተፈተነ የህዝብ ስሜት ማስቀዬሻ ፍቱን ዘዴ ነው!

ከሮማ ነገስታት ጀምሮ እስከ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የጦርነት ጌቶች እና ትናንሽ አምላኮች የጦርነት ካርድን ተጫውተዋል፣ እናም በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመቆየት የግዛት ዘመናቸውን ለማስቀጠል ሲሉ በህዝቡ ልብ ውስጥ የአርበኝነት ትኩሳትን ይቀሰቅሳሉ፡፡

በምዕተ ዓመታት የጦርነት ቴክኖሎጂው ሊቀየር ይችላል ሆኖም ግን የማታለል ማሽኑ፣ ማጭበርበሩ፣ ሸፍጡ እና የጦርነት ናፋቂዎች የከበሮ ድለቃ ዜማ እና አፈጻጸም እስከ አሁንም ድረስ ያው ነው፡፡

አምባገነኖች ሁልጊዜ በጦርነት ቃላት ይጀምራሉ፣ እናም ህዝቦቻቸውን በጦርነት ውሸት ፕሮፓጋንዳዎች፣ ፍብረካዎች እና ስለጦርነት ዝርዝር መረጃዎች የሌለው እና አሳሳች መረጃዎችን በማቅረብ በፕሮፓጋንዳ ጎርፍ እንዲጥለቀለቅ ድርጋሉ፡፡

አምባገነኖች በጦርነት መጀመሪያ አካባቢ ሊተነበይ የሚችል የአካሄድ ስርዓትን ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ ስለጦርነቱ አስፈላጊነት ግዙፍ የሆነ መግለጫ ለህዝብ ያቀርባሉ፣ እንደዚሁም ሁሉ በሀገር ውስጥ ታላቅ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ተስፋን በመሰነቅ በጠላታቸው ላይ ግዙፍ የሆነ ጥላሸት የመቀባት ዕኩይ ምግባርን ያራምዳሉ፡፡

ታምራዊ በሆነ መልኩ የእናት ሀገር ፍቅርን ከመቅጽበት ይለብሳሉ፣ በሰንደቅ ዓላማዎቻቸው ውስጥ ይጠቀለላሉ እናም ኃያል አርበኞች ይሆናሉ፡፡ አርበኝነትን ለማነሳሳት በመሞከር የተወሰዱ ግዛቶችንም እናስመልሳለን በማለት ቃል ይገባሉ፡፡

አምባገነኖች የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ዓይን ባወጣ መልኩ በሀገር ወዳድ ብሄራዊነት እና የትምክህት እንቅስቃሴዎችን ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ ስለማይቀረው የጦርነት ጥቃት፣ ስለማይታዩ ጠላቶች፣ ሳይታሰብ ስለሚመጡ አሸባሪዎች፣ ስለሀገር ሉዓላዊነት መደፈር እና ስለሌሎች ነገሮችም ሁሉ ገደብ የሌለው ፕሮፓጋንዳ እና ቅስቀሳ በማካሄድ በህዝቡ ዘንድ ፍርሀት እንዲነግስ ያደርጋሉ፡፡

በሚያገኙት በማንኛውም አጋጣሚ ሁሉ ህዝቡ ስሜታዊ ሆኖ በጠላቶቻቸው ላይ በቁጣ እንዲነሳ በመቀስቀስ የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት አሳፋሪ እና የሌለ ታሪክ በመፍጠር እነርሱ አገር ወዳድ አርበኛ የእነርሱ ተቃዋሚዎች እና ጠላቶች ደግሞ ምንም ዓይነት የሀገር ወዳድነት አርበኛነት የሌላቸው አድርገው ይፈርጃሉ፡፡

ሁሉም ነገር ሲከሽፍ እና ሲወድቅ አምባገነኖች በህዝቡ ላይ ፍርሀት እና ስሜታዊነት እንዲነግሱ በማድረግ የህዝብን ስሜት በማስቀየስ እነርሱ ከተዘፈቁበት ሰብአዊ ወንጀል እና አምባገነናዊ አገዛዝ ለማምለጥ ጥረት ያደርጋሉ፡፡

አብዛኛውን ጊዜ የጦርነት ቃላት ስለአርበኝነት እና ስሜታዊነት በመቀስቀስ ከመክሰስ እና ጥላሸት ከመቀባት የበለጠ ኃይል የላቸውም፡፡ ወደ ሌላ ወደየትም ፈቀቅ ሳይሉ ስም በማጥፋት እና ጥላሸት በመቀባት ላይ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ፡፡

ሆኖም ግን አምባገነኖች አብዛኛውን ጊዜ በጦር ሜዳ አውድ ውስጥ የጥይት ጭሆት ካቆመም በህዋላ ስለጦርነት ማውራት እና የጦርነት ነጋሪት መጎሰምን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

ሆኖም ግን ጦርነት ለአምባገነኖች የማታለያ ሀሳብ ነው፡፡

የአምባገነኖች የመኖር ህልውና በጀመሩት ጦርነት የማሸነፍ ዝንባሌ የሚወሰን ይሆናል፡፡

በጦርነት የአምባገነኖች መሸነፍ ማለት የህልውናቸው ፍጻሜ ማለት ነው፡፡

የተሸነፉ አምባገነኖች አብዛኛውን ጊዜ በመፈንቅለ መንግስት ወይም ደግሞ በሌሎች ህዝባዊ አመጾች ሊወገዱ ይችላሉ፡፡ አምባገነኖች በሚሸነፉበት በእያንዳንዱ ጦርነት የመሰደድ፣ የመታሰር እና የመሞት ዕድላቸው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

ጥቂት የአፍሪካ አምባገነኖች ዓይን ባወጣ መልኩ ያለምንም ተጨባጭነት ሁኔታ በለኮሱት ጦርነት ቢሸነፉም ቅሉ ለበርካታ ጊዚያት በስልጣን ላይ ተጣብቀው ቆይተዋል፡፡ በእርግጥ ሽንፈታቸውን ለምክንያት እና ለይቅርታ በመጠቀም ህዝቦቻቸውን ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ ለመግዛት ይጠቀሙበታል፡፡ ጠላቶቻቸውን እንደ ጭራቅ በመቁጠር በእራሳቸው ህዝቦች ላይ እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ህዝቡ ለጥ ገጥ ብሎ እንዲገዛላቸው ይጠቀሙበታል ፡፡

አምባገነኖች ስለሚጭሩት የጦርነት እሳት እውነታነት የሂትለር ቀኝ እጅ ከነበረው ከኸርማን ጎሪንግ የበለጠ እውነታውን ያረጋገጠ በዚህ ዓለም ላይ የለም፡፡ ኸርማን እ.ኤ.አ በ1945 ኑረምበርግ በተሰየመው የዓለም አቀፍ ችሎት ላይ ቆሞ ሲጠየቅ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፡

“በተፈጥሮ ተራው ህዝብ ጦርነትን አይፈልግም፡፡ ይኸ ነገር ግንዛቤ የተወሰደበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከሁሉም በላይ የሀገሪቱ መሪዎች ናቸው ፖሊሲውን የሚወስኑት እናም በዚያ አቅጣጫ ህዝቡን የሚስቡት… ድምጽ ወይስ ድምጽ አልባ [ዴሞክራሲያዊ ወይስ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ መንግስት] ህዝቡ ምንጊዜም ቢሆን መሪዎች በሚያስቡት ነገር ላይ ሊመጣ ይችላል፡፡ ያ ቀላል ነገር ነው፡፡ ሁላችሁም ልትሰሩት የምትችሉት ነገር ቢኖር ጥቃት እየደረሰባቸው መሆናቸውን ንገሯቸው፣ እናም የአርበኝነት ጉዳይን ቸል በማለት ሀገሪቱን ለከፍተኛ አደጋ በሚጥሉት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ውግዘት አካሂዱ፡፡ ይህ ጉዳይ በእያንዳንዱ ሀገር ሙሉ በሙሉ ይሰራል፡፡“

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2011 አሁን በህይወት የሌለው የወሮበላ ዘራፊው ሀዋሃት መሪ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የጎሪንግን አባባል እንዳለ በመውሰድ እንዲህ በማለት የገደል ማሚቶውን አሰምቶ ነበር፡

“አሁን በቅርቡ ኤርትራ አልሸባብን እና በሀገር ውስጥ የበቀሉትን አውዳሚ ኃይሎች በማሰልጠን በሀገራችን ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ ሆኖም ግን ግብጽ ለዚህ የሽብር ድርጊት በዋናነት ከጀርባ ቆማለች፡፡ እስከ አሁን ድረስ የነበረን ስልት ልማታችንን በማፋጠን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ማስከበር ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ዝም ብለን በቸልታ ቆመን ምንም ዓይነት መከላከል ሳናደርግ የምናይበት ሁኔታ የለም፡፡ ዝም ብሎ መከላከል የሌለው ድርጊትን እያራመድን መቆየትን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርገን ለመቀጠል አንችልም፡፡ ስለዚህ የኤርትራ ህዝብ አምባገነኑን አገዛዝ ለማስወገድ የሚያደርገው ትግል እንዲፋጠን መንገድ መቀየስ አለብን፡፡ ይህንን ስንል እንዲሁ ዘው ብለን በሀገራቸው ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንገባለን ማለት አይደለም፣ ሆኖም ግን ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነውን እጃችንን ረዘም አድርገን ወደዚያ መላክ ይኖርብናል፡፡ የኤርትራ መንግስት በእኛ ላይ ጥቃት ለማድረስ የሚሞክር ከሆነ እኛም ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ እንሰጣለን“ ነበር ያለው አፈር ይቅለለውና፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2006 የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረትን ከሶማሊያ ለማስወጣት እና አልሻባብን ለማጥፋት 843 ቀናት ያህል ጦሩን እዚያ ካቆየ በኋላ ስኬታማ ሳይሆን ሀፍረቱን ተከናንቦ ሰራዊቱን ከሶማሊያ በሚያስወጣበት ወቅት በተመሳሳይ መልኩ እንዲህ በማለት ነበር የጦርነት አመክንዮውን የገለጸው፡

“አካላዊ ጉዳትን በሚመለከት ወይም ደግሞ የወረራው አካላዊ ሁኔታን በሚመለከት ካለፈው የክረምት ወቅት ጀምሮ ምን እንደተደረገ ለመግለጽ የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የታጠቁ ኃይሎችን በማሰልጠን፣ በማስታጠቅ እና ሰርገው እንዲገቡ በማድረግ ላይ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩት እነዚህ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው በመግባት ከደህንነት ኃይሎች ጋር ግብግብ በመግጠም ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት እነዚህን ሰርጎ ገብ ኃይሎች  አሰልጥኗል፣ አስታጥቋል፣ እስከ ድንበሩ ድረስ ለሰርጎ ገቦቹ የመጠለያ እና የትራንስፖርት አገልግሎትም አቅርቧል፡፡ በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ላይ የጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ድርጊት ካለፈው የክረምት ወቅት ጀምሮ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡“ 

እ.ኤ.አ በ2009 ጭራውን በእግሮቹ መካከል በመወተፍ ከሶማሊያ ሲወጣ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የፈላስፋ ሸፍጡን በመያዝ እንዲህ በማለት ጉራውን ቸረቸረ፣ “ለኢትዮጵያ አዎንታዊ አመላካከት የሌለው የሶማሊያ ህዝብ መንግስት ቢኖርም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ የተሻለ ነው፡፡ በሶማሊያ ውስጥ የተረጋጋ መንግስት እንዲኖር ማድረግ ብሄራዊ ፍላጎታችን ነው፡፡“        

ይኸው አምባገነን ሰው እ.ኤ.አ ታህሳስ 2006 አሸባሪዎችን ከሶማሊያ ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል በማድረግ አባርረን እንመለሳለን ብሎ ነበር፡፡

አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የሰራው ነገር ቢኖር በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ሶማሊያውያን ሞትና እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ የጅምላ ተፈናቃይ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡

በሶማሊያ ውስጥ ሄደው የሞቱ የመለስ ዜናዊ የጦር ወታደሮች ብዛት ስንት ነው?

እ.ኤ.አ በ2009 አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከይስሙላው ፓርላማ ፊት በመቅረብ እንዲህ በማለት ተናገረ፣ “በሶማሊያ ውስጥ ስንት ወታደሮች እንደሞቱ ፓርላማው ማወቅ አስፈላጊው አይደለም፡፡“

አምባገነኖች ህዝቦቻቸውን የጦርነት እራት እንዲሆኑ በማድረግ በጦርነቱ ምን ያህል ወታደሮች እንደሞቱ ማወቅ የእናንተ ስራ አይደለም በማለት መናገር ይችላሉ፡፡

እንደዚሁም ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ዘ-ሀወሀት እና ኤርትራ የጦርነት ከበሮ በመደለቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በጦርነት ከበሮው የድምጽ ቅላጼ በመደነስ ላይ ይገኛሉ፡፡

በእርግጥ አስገዳጁ የጦርነት ማስጠንቀቂያ ሁልጊዜ ከሚጠበቁት ሲመጣ የቆየ ነው፡፡

የዩኤስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ጥላቻው በአስቸኳይ እንዲቆም” እና “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሁለቱም መረጋጋትን ለማስፈን እንዲተባበሩ እና በቀጣናው ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲመጣ” በማለት የተለመደ የተዕማጽኖ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ባንኪሙን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “ከሰባት ዓመታት በፊት የድንበር ውዝግባቸውን በሰላም እንዲፈቱ የቋጨውን ሕግ በማክበር ከማንኛውም ጠብ አጫሪነትን ከሚቀሰቅሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል“ የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዋና ጥያቄ ሆኖ መነሳት ያለበት ጉዳይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ጦርነት ነው ወይስ ደግሞ የጦርነት ጨዋታዎች ናቸው የሚለው ነው፡፡

እኔ የማውቀው ነገር የለኝም!

ለእኔ የጦርነት ጨዋታዎችን እያካሄዱ ይመስለኛል፡፡

ሁለቱም ወገኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ገደልን አቆሰልን እያሉ በመለፍለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ለእኔ ሁሉም ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡

እኔ በእርግጠኝነት የማውቀው ነገር ቢኖር ይህንን የሰርከስ ተውኔት ቀደም ሲል የተመለከትኩት መሆኑን ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 ዘ-ህወሀት ሲፈጽም የነበረውን የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ፣ ሙስና፣ ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀምን እና ሌሎችንም ዕኩይ ድርጊቶች መፈጸሙን በማስመልከት ለመደበቅ እና የኢትዮጵያን ህዝብ እና የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ስሜት በማስቀየስ ላይ ዒላማ ያደረገ ባለሶስት ዙር የፖለቲካ ጦርነቶችን የፕሮፓጋንዳ ሰርከስ ተመልክቻለሁ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ስለጦርነቱ እየተደረገ ያለው ንግግር እና የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ዘ-ህወሀትን ጥልቅ በሆነ መንገድ ሊያስወግድ የሚችል ድብቅ የህልውና ጦርነት ነውን?

በእኔ አስተያየት ግብታዊ በሆነ ህዝባዊ አመጽ ምክንያት ዘ-ህወሀት አእምሮው በማይቀረው ስልጣኑን እና ቁጥጥሩን የማጣት አባዜ ውስጥ ተዘፍቆ ስለሚገኝ የማስመሰያ የፍርሀት ጋጋታ ጨዋታ ነው፡፡ ሁሉም የጦርነት ዲስኩሮች በድብቅ አእምሮ ውስጥ ተሸብቦ ለሚገኘው አገዛዝ ጥልቅ ፍርሀት እና መሰረታዊ የሆነ የፖለቲካ ብስጭትን የሚገልጹ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ኬኔዲ በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገው ነበር፣ “ቀደም ሲል  በቂልነት በነብር ጀርባ ላይ ሆነው መጋለብን ይፈልጉ የነበሩ ሰዎች መጨረሻቸው በነብሩ ሆድ ውስጥ ሆነው መገኘት ነው፡፡“

ወደፊት በተቆጣ እና በተራበ የነብር ሆድ ውስጥ ሆኖ የመገኘት ዕድል የዘ-ህወሀትን አመራሮች እና ደጋፊዎች ሌት ቀን እንቅልፍ ነስቶ ሁሉንም ቀናት የጦርነት ነጋሪትን በመጎሰም እንዲቆዩ አስገድዷቸዋል፡፡

ዘ-ህወሀት ስለጦርነት በጥልቅ በማሰብ ላይ ይገኛል፣ ሆኖም ግን ከኤርትራ ጋር ስለሚያካሂደው ጦርነት አይደለም፡፡

እያሳሰበው እና ሌት ቀን ረፍት ነስቶ እያሰጨነቀው ያለው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ስለሚያደርገው ጦርነት ነው፡፡

እኔ ስለዘ-ህወሀት እውነቱን በመናገር ላይ ነው ያለሁት ምክንያቱም የዘ-ህወሀት አባላት እያንዳንዳቸው ሁልጊዜ እየተነጋገሩ ያሉበት ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ ቢያድርግ ምን…? በማለት ብርክ ይዟቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2016 የጦርነት ማቆሚያ ስለመሆኑ ወይም ደግሞ ቀደም ሲል ጀምሮ የሚተዋወቁት ወንድማማች ቡድኖች የህዝብን ስሜት ለማስቀየስ ሲሉ የጦርነት ጨዋታዎችን ሲያካሂዱ ለማየት ስለመቻሌ በእርግጠኝነት የማውቀው ነገር የለም፡፡

በአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ላይ ያሉ ባሉ ቡድኖች መካከል ጦርነት ሊካሄድ ይችላልን? በማህጸን ውስጥ ያሉ አንድ ዓይነት መንትዮች በህይወት ለመቆየት የአንዱ መኖር ለሌላው ህልውና አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን በተመሳሳይ መልኩ ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት እያንዳንዳቸው እርስ በእርስ ይፈላለጋሉ፡፡ ያላንዱ ህልውና የሌላው ህልውና ሊቆይ እንደማይችል ያውቃሉና፡፡

በአሁኑ ጊዜ ጦርነት ማናቸውም ቢሆኑ የማይፈልጉት ነገር ነው፣ እናም ይህንን በሚገባ ያውቁታል፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2015 የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ተግባራዊ እንዲሆን አጽድቋል፡፡ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የተጣለበት ሀገር ጦርነትን አካሂዶ ስለማሸነፉ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው፡፡

ጨካኝ እና አረመኔ የነበረው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔቪል ቻምበርላይን በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በጦርነት ጊዜ የትኛውም ወገን እራሱን አሸናፊ ነኝ በማለት ሊጠራ ይችላል፡፡ ማንም ቢሆን አሸናፊ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ሁለቱም ወገኖች ተሸናፊዎች ናቸው፡፡“

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማን ነው ተሸናፊ ሊሆን የሚችለው?

ስለጦርነት ሁለት ዝሆኖች በሚገጥሙ ጊዜ የሚጎዳው ሳሩ ነው የሚል የተለመደ አባባል አለ፡፡

በዝሆኖች መካከል በሚደረገው ጦርነት ሳሩ አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ የማይችለው ለምንድን ነው?

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2011 እንዲህ በማለት ጽፌ ነበር፣ “ከኤርትራ ጋር ጦርነት ወይም ደግሞ ጣልቃገብነት ለማድረግ ስለመሞከሩ እና ከግብጽ ጋር የውኃ ጦርነት ስለመደረጉ ወደፊት ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል… ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በዚያ ዕጣ ፈንታ ላይ ማንም ቢሆን ዓይኑን ለአንድ አፍታም ቢሆን አይነቅልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሊደረግ የሚችለው ብቸኛው የዜናዊ ጦርነት የህዝብን ስሜት የማስቀየስ ጦርነት ብቻ ነው“ ብዬ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝ 2011 “የኤርትራ ህዝብ አምባገነኑን አገዛዝ ለማስወገድ ፈጣን መንገድ መከተል አለበት“ በማለት ዜናዊ አስፈራርቶ ነበር፡፡

ያለፉት አምስት ዓመታት እውነታ ለእራሳቸው ይናገራሉ፡፡

ምንም የማታውቅ ሞኝ ነህ ብላችሁ ጥሩኝ፡፡ ከዚህም በላይ ስለጅኦ ፖለቲካ ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌለኝ ትላንት እንደተወለድኩ አድርጎ መናገር ይቻላል፡፡

ምንም የማላውቅ እና ትላንት እንደተወለድኩ አድርጎ ማየቱ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ትላንት ማታ አልተወለድኩም!

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2011 የተናገርኩትን እንደገና እ.ኤ.አ ሰኔ 2016ም እደግመዋለሁ፡፡ “የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የህዝብን ስሜት ለማስቀየስ የተደረገ የጦርነት ጨዋታ ነው፡፡”

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

ሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም

 

Filed in: Amharic