>

ያስራ ሦስት ወር ወሬ ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ [በዕውቀቱ ስዩም]

Bewiketu Siyumፈረንጆች ያልተገደበ የንግግር ነጻነት አላቸው፡፡ ምን ዋጋ አለው ታድያ፤ በፈረንጅ አገር ሰው ርስበርሱ አይነጋገርም፡፡ ኒዮርክ ወይም ሎንዶን ውስጥ ባቡር ተሣፈር፡፡ ምድረ ፈረንጅ ምላሱን ቤቱ ጥሎት የመጣ ይመስል እንደተለጎመ ተሳፍሮ እንደተለጎመ ይወርዳል፡፡ ልታወራው ስታቆበቁብ ፊቱን እንደ ቪኖ ጠርሙስ በጋዜጣ ውስጥ ይሸፍናል፡፡ ለፈረንጅ ጋዜጣ ማለት ከጎረቤት የሚከልል ግድግዳ ማለት ነው፡፡ አበሻ አሜሪካ ውስጥ ብዙ ዘመን በስብሶ እንግሊዘኛውን ባያሻሽል አይግረምህ፡፡ ከማን ጋር ተነጋግሮ ያሻሽለው?

(በቀደም ለታ ፤ ካንዱ ከተማ ወደ አንዱ ከተማ በባቡር ስመጣ ፤ አንዲት ዐርባ ዙር የሥጋ መቀነት በወገቧ የጠመጠመች ፤ ትልቅ የሥጋ ጉንፍ ከብብቷ በታች ያንጠለለች ወፍራም ኣሮጊት ካጠገቤ ቁጭ ብላ ነበር ፡፡ ሲያቀብጠኝ ወግ መጀመር አምሮኝ hi I’m from Ethiopia “ብላት ዐይኗን ካይፖዷ ላይ ሳትነቅል “ What do I care ?” (እና ምን ይጠበስ) ብላኝ ብላ ገገመች፡፡ በዘጠኝ ወር የአሜሪካ ቆይታየ ከፈረንጅ ጋር የተለዋወጥሁት ረጅም ንግግር ይህ ነው እንግዲህ 🙂

(ከጥቂት ዓመታት በኋላ ንግግር የሚባለው ነገር በራሱ ጨርሶ እንደማይቀር ምን ዋስትና አለን? በመጀመርያ ጥንታዊ ሰው በስሜትና በምልክት ይግባባ ነበር፡፡ ቀጥሎ ንግግርን ከባዶ ላይ ፈለሰፈ፡ለሺህ ዘመናት ያክል ሲናገር ሲናገር ኖሮ ደከመው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንግግር እንደ እንጥል መቁረጥ ሊወገድ ይችላል፡፡ የሰው ታሪክ ዑደት ነው፤ ዞሮ ወደ መነሻው ይመለሳል፡፡

በተቃራኒው፤ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው እንደ ጉድ ይነጋገራል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት እኔና ምዑዝ ከአራት ኪሎ ምኒባስ ተሳፍረን ወደ ውሀ ልማት እየመጣን የኮርኔስ የፎቁን እንቀባጥራለን ፡፡ (የባጥ የቆጡን ብሎ ማን ካዲሳባ አንባቢ ጋር ይደናቆራል)፡፡ አድዋ ድልድይ ስንደርስ አንድ ተሳፋሪ ገባና- ገና ሙሉ በሙሉ ሰውነቱ ምኒባሱ ውስጥ ገብቶ ሳያልቅ “ አሁን በተናገራችሁት ላይ ለመጨመር “ ብሎ ባልተናገርነው ላይ መጨመር ጀመረ፡፡

ድሮ በደጉ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኛትን ተካፍሎ ይበላ ነበር፡፡አሁን ደግሞ ያገኛትን ተካፍሎ ያወራል፡፡ ለምሳሌ ያዲሳባ የታክሲ ወያላ ከተሳፋሪው ጋር ያወራል፡፡ ከሹፌሩ ጋር ይከራከራል ፡፡ ተሳፋሪውና ሹፌሩ ስልክ ይዘው ጆሮ ከነፈጉት በመስኮት አንገቱን አውጥቶ ከጎረቤት ታክሲ ወያላ ጋር ይፎጋገራል ፡፡ በስነልቦና ሳይንስ ማውራትና መደመጥ ከህክምና ይቆጠራል፡፡ ወሬኛ ማህበረሰብ ጤነኛ ማህበረሰብ ነው ፡፡

ተቀበል !
ኢትዮጵያ አገሬ
ያስራ ሦስት ወር ወሬ
ስንት ገባ ይሆን የውጭ ምንዛሬ ?

የፕሬስ ነጻነት ባለበት አገር ውስጥ ሕዝብ ብሶቱን በይፋ ይገልጻል፡፡ መንግሥት አቤቱታውን ሰምቶ ያስተዳደር ማሻሻያ ያደርጋል፡፡ የፕሬስ ነጻነት ይህ ነው ትርጉሙ፡፡ እኛ አገር ግን ምንድ ነበር የሚደረገው ? ሕዝ ብ በጦቢያ ጋዜጣ ላይ መንግሥትን “ በደልከኝ” ብሎ ይወቅሳል፡፡ መንግሥትም ባዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ“ ደግ አደረግሁ!” ብሎ ይመልሳል፡፡ አሁንማ እሱም ቅንጦት ሆኖ ቀረ፡፡

ምኒባሱ ውስጥ ከምዑዝ ጋር የምናወራው ወሬ ምን ነበር?፤ የኔና የምዑዝ ሦስት የጋራ ጭብጦች የታወቁ ናቸው፤ እጦት ሽፍደትና የህይወት ዐላፊ ጠፊነት፡፡
ከእለታት አንድ ቀን በባልደራስ ኮንደሚኒየም ጥግ ሳልፍ ራዳሯን የሣተች ትንኝ ካይኔ መስታወት ጋር ተላተመች፡፡ በጭንቄ መሀል ሆኘ በደህናው ዐይኔ ባጠገቤ የምታልፍ ልጅ ዐየሁና “እሙ ካይኔ ላይ ትንኝ አውጭልኝ ” ብየ ተማጸንኳት ፡፡ ግልምጥምጥ አድርጋኝ አለፈች፡፡ አዝለሽ ሆስፒታል ውሰጅኝ ያልኳት ነው ያስመሰለችው፡፡
ምኡዝ አዳምጦኝ ሲያበቃ
“ልጂቷ ቆንጆ ነበረች?”
“ በዛ ጭንቅ ላይ ሆኘ ይሄን እንዴት ላውቅ እችላለሁ፡፡ ጾታዋን የለየሁትም እኔ ሆኘ ነው ”

“ ግዴለህም ቆንጆ ናት ” አለ ምኡዝ ” ቆንጆ ሴቶች ሁሉ ነገር ለከፋ ይመስላቸዋል፡፡ ገና ጡት ሲያጎጠጉጡ ጀምሮ ኑራቸው በለከፋና በጅንጀና ስለሚጠመድ ፤ የሆነ ጊዜ ላይ ከጅንጀና ውጭ ያለውን ዓለም ይረሱታል፡፡ ይገርምሀል፤ ባለፈው ሥጋ ቤት አንድ ኪሎ አስመዝኘ እቆርጣለሁ፡፡ መቸም የዘንድሮ የሀረር ሰንጋ የጫት ገረባ እየበላ ስለሚደልብ ስጋው ኮብል ስቶን ማለት ነው፡፡ የመጀመርያውን ኮብል ሙዳ ባዋዜ ወልውየ እንምንም ዋጥሁት፡፡ ሁለተኛው ጉርሻ ግን እየተንፏቀቀ ወርዶ ደረቴ ላይ በተጠንቀቅ ቆመ፡፡አበሻ ብቻውን የማይበላበት ምክንያት የገባኝ ያኔ ነው፡፡ ዐየህ! አበሻ ብቻውን የማይበላው ጉርሻ ደረቱ ላይ ሲቆም ጓደኛው ፈርስት ኤድ እንዲሰጠው ነው፡፡ እና ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ እየተናነቅሁ ዞር ስል የሆነች ቺክ ተመለከትኩ ፡፡ ቺኳ ሲፈጥራት ማቄጥ አብዝቶ የታደላት ናት፡፡ ምን የመሰለ ስቴፓ አስከትላለች፡፡ ምን የመሰለ የወተት ቅል አስቀድማለች፡፡
(ወይ ምኡዝ በጣእረ ሞት ተይዞ እንኳ ባይኑ ቂጥና ጡት የሚመዝን ጉድ!)
እናልህ ! በእጄ ወደ ጀርባየ እየጠቆምኩ ሥጋ አንቆኝ ነው ጀርባየን ምችልኝ የሚል ምልክት አሳየኋት፡፡ እየተሽኮረመመች ወደ ትሪዋ አቀረቀረች፡፡ ፓ ቢሃይንድሽ የሰጠ ነው“ ምናምን ያልኳት ነው የመሰላት፡፡ ዝነኛ ወንዶችና ቆንጆ ሴቶች የመጨረሻ self –centered ናቸው፡፡ ምድር ዛቢያዋን ትታ በእነሱ ገጽታ ዙርያ የምትሽከረከር ነው የሚመስላቸው፡፡ እኔ በዛ ሰአት መተንፈስ አቅቶኛል፡፡ምድር እንደ ዲሽ ተገልብጦ ይታየኛል፡፡ ከሞቴ በላይ አሟሟቴ ዝግንን አለኝ ፡፡ሰው በራብ በሚሞትበት አገር ውስጥ እግዜር እንዴት በመብል እንድሞት ይፈርድብኛል ?አምላኬ አሪፍ አኗኗር ብትነሣ ኝ አሪፍ አሟሟት እንዴት ትነፍገኛለህ ?ምናምን እያልሁ ወቀስኩት፡፡

“አሪፍ አሟሟት እንዴት ነው?” አልኩት ምዑዝን፡፡
“ምናባህ አቅልሃለሁ፡፡ ቢቸግረኝ እንጂ የሞት ምን እርፍና አለው ብለህ ነው? አንድ ሰው በተቻለው መጠን ላለመሞት ነው መጠንቀቅ ያለበት፡፡ የግድ መሞት ካለበት ደግሞ በደንብ ተዘጋጅቶ፤ ፒኤችዲውን ሠርቶ ፤ዝዋይ የሚገኘውን ያበባ ርሻ ለታላቋ ልጄ፤ ዱባይ የሚገኘውን የነዳጅ ኩሬ ለታናሽ ልጄ ብሎ ተናዞ ፤ንስሀ አባቱን ቢራ ጋብዞ ቢሞት አሪፍ ነው፡፡ ሲሞትም አረፋ ደፍቆ ረፈራግጦ ሳይሆን ዝንጥ ብሎ የመንኮራኩር ሞተር የተገጠመለት አልጋው ላይ ጉብ ብሎ ቀበቶውን ካጠበቀ በኋላ ” see you in heaven kids “ብሎ በምኝታቤቱ መስኮት ወጥቶ እልልም !ልክ የኤልያስ ሠረገላ አይነት መሺን ወደ አእምሮህ አልመጣም?
“ታሪኩን ቀጥል”
“ከዛ መተንፈስ እያቃተኝም መጣ፡፡ የሆነ ሽሜ ሰውየ ስሟሟት ሾፎኝ ኖሮ ሊጎርስ ያድቦለቦለውን ሙዳ ወደ ትሪው መልሶ ወደ እኔ ሲያዘግም ተመለከትኩት፡፡ እግሩን እንደቡል ዶዘር ጎማ በዝግታ እየሳበ እንደምንም ከደረሰልኝ በኋላ ከኋላየ ዞሮ ያለ የሌለ ጉልበቱን አጠራቅሞ ጀርባየን ሲጠልዘው ከወንበሬ ነጥሬ ወለሉ ላይ ተዘረርኩ፡፡ከሙዳው ስጋ ጋር ሳንባየን አብሬ ሳልተፋው አልቀረሁም፡፡ ፈርስት ኤድ ሳይሆን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ደንበኛ ድብድብ ነው፡፡ ሼባው ሊያድነኝ ሲሞክር በእጁ ጠፍቼበት ነበር፡፡ ያንን ጉልበት ኬት አመጣው? በኋላ ሳጣራ ሽማግሌው የንግሥት ዘውዲቱ ነጋሪት መቺ የነበረ ሰው ነው“
”አሁን በተናገራችሁት ላይ ለመጨመር፤ ትናንት በነጋሪት መጽሄት ላይ የታተመውን የኮምፒውተር አዋጅ አንብባችሁታል?“ አለ አንድ ተሳፋሪ ገና ገብቶ አጠገባችን ቁጭ እያለ ፤ ምኒባሱም ቀጠለ፡፡

Filed in: Amharic