>

በሁለት ሰዓት አስር ዘፈን

ዮና ቢር

ዘመኑ የቀይ ሽብር ጊዜ ነበር። አዲስ አበባ በወረቀትና በደም የምትጥለቀለቅበት ጊዜ። ወጣት ከሆንክ በማንኛውም ደቂቃ ልትመታ ትችላለህ። መንግስት ባይመታህ ጓደኛህ ይመታሃል።

Artist Msfen Abebe- hqdefault.jpg RIPበዚህ ንዳድ ዘመን አንድ ወጣት በጀርባው ጊታር አንግቦ መርካቶ አነዋር መስጊድ ከሚገኘው ታንጎ ሙዚቃ ቤት (የአሊ አብደላ ሙዚቃ ቤት) ለመድረስ ይጣደፋል። የወጣቱ አመጣጥ ሙዚቃ ለማስቀረጽ ሲሆን ከሚያስተምርበት ሲዳሞ ክፍለሃገር ፈቃድ ወስዶ አዲስ አበባ ገና መግባቱ ነበር።

በዚያ እለት ተኩስ በመበራከቱ ቀውጢዋ መርካቶ አለወትሮዋ ጭር ብላለች። በዚህ መሃል አገር አማን ብሎ ከነጊታሩ የሚያጣደፈውን ጎፈሬ ወጣት በድንገት <ቁም!> የሚል ድምጽ አስደነበረው።
<እጅ ወደላይ!> አለው ያው ድምጽ ወጣቱ አላወላወለም እጁን አነሳ። በዛች ቅጽበት የተሸከመውን ጊታር ለመንካት ቢሞክር ኖሮ “ያዥልኝ ቀጠሮ” የሚለውን ዘፈን ላናውቀው እንችል ነበር።

የዛን ጊዜው ወጣት ሌላ ሳይሆን ተወዳጁ ድምጻዊ መስፍን አበበ ነበር።

መስፍን ታሪኩን ሲቀጥል የዛን ቀን አሊ ታንጎ ሱቅ ገብቶ መቀረጽ ጀመረ። አስር ዘፈኖችን አንድም ጊዜ ሳይደግምና ሳያቋርጥ በቀጥታ ተቀርጾ ወደ ሲዳሞ ተመለሰ።

ከዚያ በኋላ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከተኩስ ድምጽ አረፍ ሲል የሚሰማው መስፍንን ሆነ። መስፍን ገበያውን ተቆጣጠረው። ሆኖም መስፍን ዘፈኖቹ እንደተወደዱ አላወቀም ነበር። አንድ ቀን ከአዲስ አበባ የመጣ የሚያውቀው ሰው <አዲስ አበባ ላይ ታዋቂ ሆነህ አንተ አሁንም እዚህ ገጠር ውስጥ ታስተምራለህ?> ሲለው ነበር ዘፈኑ እንደተወደደ የሰማው።

መስፍን ኮርድ ሳይዝ በቀጥታ ሜሎዲውን በጊታር መጫወቱ ስለተወደደለት በርካታ ወጣቶች ላይ ተጽእኖ አምጥቷል። መስፍን በተለይ ያዥልኝ ቀጠሮ፣ አይሽ አይሽና፣ ቦረና ገነቴ፤ ደሴ ላይ ነው ቤቷና መልካም ልደት የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ካሴቶችን አስቀርጿል።

በተፈጥሮ ጨዋታ አዋቂ የነበረው መስፍን ትዳር እስኪመሰርት ድረስ አንድ ካሴት ባወጣ ቁጥር አዳዲስ ሴቶች ይተዋወቁት እንደነበር በቀልድ ይገልጽ ነበር።

አይሽ አይሽና ይመጣል እንባዬ
አንቺም ወይ እድልሽ እኔም ወይ እጣዬ
የቸገረ ነገር የጠፋለት መላ
እንዴት ይለያያል ሰው ሳይጠላላ?

እያለ ያዜመው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።

መስፍን ሆይ

በዘፈንህ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስታስደስት ኖረሃልና ባለህበት ቦታ ነፍስህን ደስ ይበላት!!!

Filed in: Amharic