>

ትዝታ ዘጎጃም፤ የዱር ላሞችን፣ የጠፋ ሕዝብና ቀዬን ፍለጋ [ሙሉቀን ተስፋው]

Muluken Tesfaw ke fuwfuwtew gar(ይህን ማስታዎሻ የጻፍኩትና ወደ ቦታው የተጓዝኩት በነሐሴ 2007 ዓ.ም. ነበር፤ ጉዞዬ ከሞጣና ከጉንደ ወይን በኩል እንደ ሆነ አንባቢ አስቀድሞ ይረዳ)

የጫካ ከብቶችንና የጠፋ ቀዬን ፍለጋ ነው ወደ ጎጃም የሔድኩት፡፡ የምን የዱር ከበት? የምን የጠፋ ሕዝብና ቀዬ ነዉ? እንደምትሉ ማወቅ ባልችልም እገምታለሁ፡፡ አዎ- ለሰሚዉ ግራ፣ ለሚያነበዉም ‹አጃኢብ› ነዉ፤ ግን የጠፋ ቀዬና ሕዝብ አለ፤ ከአራዊት ጋር ሕብረታቸውን ያደረጉ ከብቶችም አሉ፡፡

ሐረር ያደገ ሰዉ ስለ ቁንደዶ ፈረሶች ሊሰማ ስለሚችል ላይደንቀው ይችላል፡፡ ደሴም የኖረ ሰዉ ወደ ማታ ብቅ ሰለሚሉት የጦሳ ነጫጭ ፍየሎች ስለሚያውቅ ግርምት ላይፈጥርበት ይችላል፡፡ በደሴ የጫካ ፍየሎች አሉ፤ በሐረር የጫካ ፈረሶች አሉ፡፡ ሁሉንም እድሜና ጤና ከሰጠን አብረን እንጎበኛቸዋለን፡፡ ጎጃም የምወስዳችሁ ግን ስለ ጫካ ከብቶች ልነግራችሁ፤ እንዲሁም ስለ ጠፋዉ ሕዝብና ቀዬ ላወጋችሁ ነዉ፡፡ ያ ሕዝብ የሠራዉ ጥፋት ባይኖርም እንደ ሰዶምና ገሞራ ሕዝብ ‹‹ነበሩ›› ተብሏል፡፡ ዙዓር ተራራ በአካባቢዉ ባይኖርም እንደሎጥ ቤተሰቦች ታሪክ ነጋሪ ሰዎች ተርፈዉልናል፡፡

ከግንደ ወይን ደብረ ወርቅ አልፈን ወደ ብቸና እየተቃረብን ነዉ፡፡ ከጎኔ የተቀመጠዉ ሰዉ ‹‹የነ ጉዱ ካሣ እርስት ዲማ ጊዎርጊስ በዚህ በኩል ነዉ የሚኬደዉ›› አለኝ፡፡ የተሳፈርኩበትን መኪና ‹ወራጅ› ልለዉ ካሰብኩ በኋላ የእግር መንገድ እንዳለብኝ ሳስብ ተዉኩት፡፡ ትናንት ስጓዝባቸዉ የነበሩ እግሮቹ የድካም ስሜት አላቸዉ፡፡ የጠፋዉን ቀዬና የጫካዎቹን ከብቶች ፍለጋ ስለምሄድ የበዛብህን የቀለም ትምህርት ቤት፣ የፊታዉራሪ መርሻን ደብር፣ የነ ቄስ ሞገሴን አድባር ሌላ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቼዉ አለፍኩ፡፡ ‹የዲማዉ ጊዎርጊስ እንድሳለምህ ፈቃድህ ይሁን› ከማለት ዉጭ ምርጫ አልነበረኝም፡፡ በሐሳብ ስናዉዝ ብቸናን አልፈን ወደ ደጀን ተመዘገዘግን፡፡

የጎጃምና የጎንደር ሲራራ ነጋዴዎች በአባይ በርሃ ሽፍቶች በተደጋጋሚ መዘረፋቸዉ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖትን (የንጉስ ተ/ኃይማኖት ልጅ) በእጅጉ አሳሰባቸዉ፡፡ ነጋዴዎቹ ጎሐ ጽዮን እስኪደርሱ ድረስ 40 ኪሎ ሜትር ያክል ርዝመት ያለዉን ገደል፣ ጫካና በርሃ ከሽፍታ ጋር መጋፈጥ ግዴታቸዉ ነበር፡፡ ከአባይ በርሃ ሽፍቶች ጋር ተያይዞ ብዙ ገጠመኞች ይነገራሉ፡፡

አንድ ጊዜ በዘመናዊ ቀልድ ፈጣሪነታቸዉ የምናውቃቸዉ አባ ገብረ ሐና ከእምየ ምኒልክ ሸዋ ከርመዉ ሲመለሱ የበረሓውን ሽፍቶች ማለፍ የሚችሉበትን ዘዴ ቀየሱ፡፡ ጎሓ ጽዮን ላይ ሲደርሱ አንድ ገበታ፣ ልብሰ ተክህኖ፣ ጥላና ጸናጽል በመያዝ በርሓዉን ይወርዳሉ፡፡ ሌቦች አባን አዩዋቸዉ፡፡ ‹‹የማን ታቦት ነዉ?›› ብለዉ ይጠይቃሉ፡፡ አባም ‹‹ተልባ ማሻ ጊዎርጊስ ይባላል፤ ኃጢያትን ሁሉ ያስተሰርያል›› በማለት ለሌቦቹ ይነግሯቸዋል፡፡ ያዉ ሌቦቹም ከሀይማተኛዉ የጎጃምና የሸዋ ሕዝብ የወጡ በመሆናቸዉ እንኳንስ ሊቀሟቸዉ ‹ብጽዓት› /ስለት እየሰጡ ሸኟቸዉ፡፡ ፍቅር እስከ መቃብርን ያነበበ ሰዉ የአባይ በርሓን ማቋረጥ የሲና በርሓን አሊያም የመከራ በርን (ባብኤል መንደብ) አቋርጦ ምድረ ከንዓን ከመግባት አያንስም፡፡ በዘመኑ የነበሩ ሽፍቶች ከሰማሌ የባህር ላይ ወንበዴዎች አያንሱም ለማለት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ አባይ በርሐን ማቋረጥ ከሞት ጋር መጋፈጥ ነበር፡፡

ራስ ኃይሉ ነጋዴዎቹን ከነዚህ ሽፍቶች ለመጠበቅ ጎሐ ጽዮን ማዶ ወታደሮችን አሰፈሩ፡፡ የወታደሮች መኖሪያ ከሳር የተሰሩ ጎጆዎች አሻግሮ ሲመለከቷቸዉ የውሻ ክራንቻ (ጥርስ) ይመስሉ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከተማዋ ‹የውሻ ጥርስ› የሚለዉን ስያሜ አገኘች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከተራራዉ አናት ላይ የሰፈሩት ወታደሮች ለነጋዴዎቹ ደህንነት መከታ ለመሆን ስለሆነ ‹ደጀን› የሚል ስያሜም መጣ፡፡ ይህችን አነስተኛ የወታደሮች ካምፕ ጣሊያኖች ‹ፎርቲው› በማለትም ይጠሯት ነበር፤ ስትራቴጂክ ቦታ ማለት ነዉ፡፡ ይህች ከተማ አሁን ድረስ ደጀን የሚለዉን ስያሜ መርጣለች፡፡

የደጀን ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ካለ ባለሙያ (ደጉ ጊዜ ይባላል፤ በጣም ካስገረሙኝ ስሞች መካከል የደጉ ጊዜ አንዱ ነው) ጋር ፈቃድ ለመጠየቅ ከወረዳዉ ቤተ ክህነት ሄድን፡፡ ፈቃድ እንዳገኘን ጉዞ ጀመርን፡፡ ከደጀን 10 ኪሎ ሜትር ወደ ማርቆስ በሚወስደዉ መንገድ ‹የትኖራ› የምትባል ከተማ አለች፡፡ የትኖራ የተቆረቆረችዉ በደርግ ዘመን ሲሆን ገበያዋ የጦፈ በመሆኑ ጎጃሜ ‹እስካሁን የት ነበርሽ?› አላት፡፡ የይትኖራ ገበያ በሰሜን የሀገራችን ክፍሎች ካሉት የከብት ገበያዎች ሁሉ ትልቁ ገበያ ነዉ፡፡ ሁልጊዜ ማክሰኞ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፣ ከጎንደር እስከ ሐረር ድረስ እየመጡ ሰንጋ ይመሸምቱበታል፡፡ እንደ አጋጣሚ የትኖራ የሄድኩት ማክሰኞ በመሆኑ ይህን ታላቅ ገበያ የማየት እድል ገጥሞኛል፡፡ አማርኛዉ፣ ትግርኛዉ፣ ኦሮምኛዉ፣ ጉራጊኛዉ… ሁሉ ይነገራል ማክሰኞ በየትኖራ፡፡

ከየትኖራ ከተማ በስተ ደቡብ ምስራቅ በኩል የአባይን ሸለቆ በርቀት እያየን በጭቃማዉ መሬት ጉዞ ጀመርን፡፡ ሱሪዬን ካሊሲዉ ውስጥ ሸግሽጌ በጭቃ እየዳከርኩ ወደ ገደሉ ገሰገስኩ፡፡ የደጀንና የአዋበል ምድር ጉም የሚተፋ ይመስል አገሩ ሁሉ ጭጋግ ዉጦታል፡፡ ለ45 ደቂቃ ያክል እንደተጓዝን የዉሃ ፏፏቴ ድምጽ ተሰማኝ፡፡ ጢስ አባይ በየት መጣ? ብዬ ስጠይቅ ሌላ የአባይ ገባር ወንዝ መሆኑን ነገረኝ- ደጉ ጊዜ፡፡ የመጨት ወንዝ ፏፏቴ በጉሙ ውስጥ ድምጹን ሰማሁት፤ አየሁትም፡፡

ከገደሉ አፋፍ ላይ ሆነን የጫካ ከብቶቹን አየናቸዉ፡፡ የሚያድጥ ጭቃማ አደገኛ ቁልቁለት ስንወርድ እጄንም እንደ እግሬ ልጠቀምበት ተገደድኩ፡፡ ወዳጄ ‹‹ጫማችን ብናወልቅ ይሻላል›› የሚል ሐሳብ አቀረበ፡፡ ቁልቁለቱን በዳዴ ወረድነዉ፡፡ የ‹እግር ጥናን ጫካ› የዱር ላሞቹ ብቻቸዉን ነግሰዉበታል፡፡

የጫካ ከብቶችየጫካ ከብቶቹ ታሪክ ወዲህ ነዉ፡፡ ገደሉ የአቡነ ተክለ ኃይማኖት ገዳም ነዉ፡፡ ቦታዉ የ‹እግር ጥና› ይባላል፡፡ የተሰየመበት ምክንያት ጸበሉ የተለያየ ደዌ ይፈውሳል፡፡ በተለይ አካላቸዉ አልታዘዛቸዉ ላሉ ሰዎች አይነተኛ መፍትሄ እንደሆነ በጸበሉ ያገኘናቸዉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ አንድ ግለሰብ በእንጨት ወሰካ ዘመዶቹ ተሸክመዉ አመጡት፡፡ ተጠምቆ ሲድን በእግሩ ገደሉን ለመውጣት ሲሞክር አካሉ ተንቀጠቀጠበት፡፡ ‹‹እግር ጥና እግር ጥና›› እያለ ራሱን በማበረታታቱ የእግር ጥና ተ/ኃይማኖት ተባለ፡፡ በርካታ ሰዎች ከዚሁ ጸበል አግኝተናል፡፡

ከዛሬ ሁለት መቶ አመታት በፊት በጸበሉ የተፈወሰ ሰዉ አንዲት ክበድ ጊደር በስለት ያስገባል፡፡ ጊደሪቱ ማንም ሳይነከባከባት በጫካዉ ከጥጃዋ ጋር መኖር ጀመረች፡፡ ማታ ማታ ከገደሉ ስር እያደሩ ቀን ቀን ደግሞ ጫካዉን ብቻቸዉን ነገሱበት፡፡ የመጨትን ወንዝ ያለምንም ተቀናቃኝ ይጠጡታል፡፡ ትውልዳቸዉ እየረባ ሄደ፡፡ በ1970ዎቹ አካባቢ ቁጥራቸዉ 23 ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በደርግ የህብረት ስራ ማህበራት በተበራከቱበት ዘመን ‹የአምራቾች ማህበር› የጫካ ከብቶቹን ከገደሉ አስወጥተዉ ወደ ወል ሀብትነት ቀየሯቸዉ፡፡ ሆኖም ከብቶቹ ወደ አዉሬነት ተቀይረዉ ስለነበር መልመድ አልቻሉም፡፡ ከእረኞች አምልጠዉ ለመሄድ ሲሞክሩ ብዙዎቹ ገደል ገብተዉ ሞቱ፡፡ የተቀሩትም መልመድ ባለመቻላቸዉ እንደገና ወደ ተፈጥሮ ጫካቸዉ መለሷቸዉ፡፡ ከብቶቹ ቁጥር በሁለት አበይት ምክንያቶች ሊጨምር አልቻለም፡፡ አንደኛዉ ብዙ ጊዜ ገደል ይገባሉ፤ ሌላኛዉ በየአመቱ የነሐሴ ተ/ኃይማኖት አንድ አንድ በሬ ይታረዳል፡፡ የከብቶቹ ቀለም ከግንባራቸዉ ላይ የነጭ ቦቃና ድፍን ቀይ ሲሆኑ ኮርማቸዉ ግን ጫጎ ቀለም ነዉ፡፡ የላሞቹ አቋም ከሌሎች ላሞች የተለየ ነዉ፡፡ ቁመታቸዉ ትላልቅና እንደበሬም ሻኛ አላቸዉ፡፡

አሁን አሁን ግን የጫካ ከብቶቹ በማወቅም ባለማወቅም ተፈጥሯዊ የሆነ ባህሪያቸዉን እንዲያጡ እየተደረገ ነዉ፡፡ ከአንድ አመት በፊት የደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ የከብቶቹን ዝርያ ለማጥናት በሚል ጥበቃ ቀጠረላቸዉ፡፡ ጥበቃው ደግሞ እያሰረም ለማለማመድ ሞከረ፡፡ ምንም እንኳ ዩንቨርሲቲው ከጫካዉ ጥናቱን ጨርሶ ቢወጣም ጥበቃው ግን ሊወጣ አልፈለገም፡፡ ከስድስት ወር ወዲህ ደግሞ ከጫካዉ ውስጥ ቤት ሰርተውላቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ የከብቶቹን ተፈጥሯዊነት እያጠፋዉ በመሆኑ የወረዳዉ ቤተ ክህነትና የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት መላ ቢፈልግለት ለማለት እወዳለሁ፡፡ በግልጽ አማርኛ አንዳንድ የቤተ ክህነት ሰዎች ከጥበቃው ጋር ሆነው የላሞቹን ወተት እያለቡ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ላሞቹም ሰው በግድም በውድም ለምደዋል፤ በዕውነቱ ይህ የሚያሳዝን ነው፡፡

የጠፋው ቀየ፡ ሰዎች እንደገና ሰፍረውበታል።ከዚህ ገደል የሁለት ሠዓት ተጨማሪ የእግር ጉዞ በኋላ የጠፋዉ ቀበሌ ‹‹ገንቦጭ›› ይገኛል፡፡ መስከረም 13 ቀን 1952 ዓ.ም. በጎጃም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያም ‹እግዚኦ› ያስባለ ክስተት ተከሰተ፡፡ የገንቦጭ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደሁልጊዜው ሁሉ ስራቸዉን እያከናወኑ ነዉ፡፡ እረኞች ከብቶቻቸዉን እየጠበቁ ነዉ፡፡ ጉብሎች ‹እንካስላንትያና እንቆቅልሽ› ይጫወታሉ፡፡ ቀሳዉስት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያ ውስጥ ቃለ እግዚአብሄር ይቀኛሉ፡፡ ከአጎራባች ቀበሌም ለስራ የመጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ ግን ይህ ተፈጥሯዊ የሰዉ ልጆች ኡደት መስከረም 13 ቀንን ማለፍ ሳይሆን እኩለ ቀን ድረስ እንኳ አልቀጠለም፡፡

የገንቦጭ ገደል ከሁለት ተቆረሰ፡፡ የአንድ መቶ ሰዎችን መኖሪያ በላይ ወደቀበት፡፡ የገንቦጭ መንደር የት እንደገባ ጠፋ፡፡ በላዩ ላይ ጫካ ሆነ፡፡ ነዋሪዎች ከነቤታቸዉ መሬት ውስጥ ተዳፈኑ፡፡ አማሬት የሚባል አጎራባች ቀበሌ የመጡ ሁለት ሰዎች መጨት ወንዝን ተሸግረዉ አጎራባች ወረዳ በህይወት ተገኙ፡፡ ከደጀን ወረዳ ተስፈንጥረዉ ማዶ ካለዉ አዋበል (ሉማሜ) ጅት ቀበሌ ላይ አረፉ፡፡ አደጋው የቀየውን ሰዎች ለይቶ የሚያጠቃ ሆነ፡፡ እንግዶችን አባረረ፡፡ ተራፊዎቹ ስለሁኔታዉ ሲገልጹ አስቀድሞ አዉሎ ንፋስ ተነሳ፤ ከከፍተኛ አቧራ ጋር መሬቱ ተሰነጠቀ፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነዉን አናዉቀዉም ይላሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የሎጥ ቤተሰብን ይመስላሉ፡፡ ጅት ቀበሌም እንደ ዙዓር ተራራ አገለገለች፡፡ ገምቦጭ ግን እንደሰዶም ጠፋች፡፡ ኦ ገምቦች ምን ይሆን ሀጢያትሽ!
በሠዓቱ በሕይወት ከተረፉት ሰዎች መካከል አንደኛዉ አሁንም በሕይወት አሉ፡፡ አማሬት ቀበሌ ይገኛሉ፡፡ ግለሰቡን ለማገኘት ሌላ ተጨማሪ ሦስት ሠዓታትን መጓዝ ይጠይቃል፡፡ በጉዞ ለሰነበተ ሰዉ አስቸጋሪ በመሆኑ አልሞከርኩትም፡፡ የበረታ ሂዶ ሙሉ ታሪኩን ሊረዳ ይቻለዋል- ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ያውጋ የነበረ ነዉና፡

ታሪኩን የተሟላ ለማድረግ ፍላጎቱ ያለው ወጣት ከሞት የተረፉት ሽማግሌ ከማጣታችን በፊት ቃለ መጠይቅ አድርጎ ቢያስቀር ወሮታ እንደዋለልን እቆጥራለሁ፡፡ ሐሳቤን ሳላሳካ ለስደት በመዳረጌ ሐዘኔ የበረታ ነው፡፡

Filed in: Amharic