>

በውቀቱ ስዩም

—በክራር ባታሞ ዜማ ተከበሻል
የልቤ ትርታ እንዴት ይሰማሻል
Bewketu Siyum 21052016ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዜማ ደራሲው ካቤ ጋር እየተቀጣጠርኩ የከሸፈ የዘፈን ግጥም ሳበረክት አድር ነበር፡፡ ዘፋኞች ፤አቀናባሪዎችና ገጣሚዎች ተሰብስበው ቡና ተፈልቶ፤ እጸ -ሰመመን (ጫት) እየተበላ ጨዋታ ይደራል ፡፡ ከእለታት አንድቀን ቸኮል የተባለ ጎረምሳ “ ጥበብ አጣድፋ ጠርታኛለች ” ብሎ፤ የገጠር መምርነት ሥራውን ጥሎ ተቀላቀለን፡፡ ቸኮል ዜማ እንደ ነሥር የሚመጣበት ሰው ነበር :: ጥሩ ወግ አዋቂ ነው፤ ግን ወግ ይጀምርና ድንገት”ዜማ መጣልኝ! ዜማ መጣልኝ! ሳያመልጠኝ ቀድቸው ልምጣ”ብሎ በመጮህ ወደ ምኝታ ቤቱ ይሮጣል፡፡ ከተመደበለት ምኝታ ቤት ውስጥ የተጠመደች ቴፕሪከርደር ትጠብቀዋለች፡፡
ከዚያ ይመለስና “ አንድ ድሃ ባላገር ቆንጆ አፍቅሮ አባቷን ደጅ ጠና ” ብሎ ወግ ይጀምራል፡፡ በጀ! ስንለው “ ኧረረ ፡! አሁን ለማርታ አሻጋሪ የሚሆን ዜማ መጣብኝ “ይልና የቡና እቃውን እያተራመሰ ፤ ቄጤማውን እየጣሰ ይሮጣል፡፡

ነገሩ ከሥስት’ዜ በላይ ሲደጋገም አቤ ትእግሥቱ አለቀና እንዲህ አለው ” እኔ ምልህ ቸኮል! እንዲህ የሚያሯሩጥህ አሜባ ነው ዜማ?”

(ለማንኛውም ቸኮል የጀመረውን ወግ እኔ ልጨርሰው
አንድ ድሃ ባላገር አንዲት አፍቅሮ አባቷን ደጅ ጠና ፡፡
ኩሩው አባት “ ልጄን ለማግባት መፈለግህ ጥሩ ነው፡፡ ለመሆኑ መሬት አለህ?”
“የለኝም!”
“ከብት አለህ?”
“የለኝም!”
ሙያ አለህ?
” የለኝም“
“ታድያ ብድራት ይሆናል ብለህ ነው?
ለምክር አፍቃሪ ፤ አንባቢያን ብድ-እራት ስለማይሆን ጠንክራችሁ ሥሩ ለማለት ነው )

2 አንድ ታዋቂ ዘፋኝ ዲሲ ውስጥ ታፍሮና ተከብሮ ይኖር ነበር ፡፡ ባንድ ጎደሎ ቀን መንግሥትን በይፋ ደግፎ በመናገሩ የዲሲ ሰው ጠምዶ ያዘው፡፡ የሚያውቃቸው ሰዎች ከሩቅ ሲያዩት ማርሽ ቀይረው ሲመርሹ ታዘበ፡፡ በተስቦ እንደታማ ሰው፤ ሁሉም ከሩቅ ሲሸሸው ተመለከተ፡፡ስሙን የሚያድስበት አጋጣሚ ሲጠብቅ ሲጠብቅ ኖረ ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አንድ የኢትዮጵያ መንገደኛ አውሮፕላን ሚዲተራኒያን ውቅያኖስ ውስጥ መግባቱን የሚገልጽ ዜና ሰማ ፡፡ ዘፋኙ ያደጋው ሰለባዎችን የሚዘክር ዘፈን ዘፍኖ ከህዝብ ጋር ለመታረቅ ፈለገ፡ ፡ ዜማውን ራሱ ደረሰ፤ ግጥሙን ጓደኛ ፊደል ተባበረው፤
አረንጓዴ ብጫ ቀይ ነው ሰንደቁ
አምላክ ይቅር በለን ወገኖች አለቁ
የሚል የሀገር ፍቅርን ፈሪሀ እግዜርን ያስተባበረ ግጥም ጽፎ ሰጠው:-)

ግጥሙንና ዜማውን ይዞ ወደ አቀናባሪ ሄደ፡፡የዲሲ አቀናባሪዎች ነገ ከነገ ወድያ እያሉ በደጅ ጥናት ቀጡት ፡፡ ካንዱ አቀናባሪ ወደ ሌላው ሲንከራተት ወራት ነጎዱ፤
ባደጋው ልጆቻቸውን ያጡ ፤አርግዘው ወለዱ፤
ባደጋው ሚስቶቻቸውን ያጡ፤ ሌላ ሴት ወደዱ፤

አንድ ቀን ጓደኛየ ፊደል ዘፋኙን እንዲህ አለው“ ስማ ! ያውሮፕላኑ አደጋ ስለተረሣ ለምን ዘፈኑን አትተወውም?”
ዘፋኙ ግን በእልህ መለሰ “ ኖ ኖ ኖ !የፈጅውን ጊዜ ይፍጅ እንጂ ዘፈኑን ሠርቸ ለሸገር ሬድዮ እልክላቸዋለሁ፡፡ ቢፈልጉ ቀጣዩ አውሮፕላን ሲከሰከስ ይልቀቁት”

ይቺን የምጽፈው ኢቫን ጋዲ የተባለው ያበሾች ክለብ ውስጥ ቁጭ ብየ ነው፡፡ ራሱን “ትንሹ ኤፍሪም” ብሎ የሚጠራ ግን ኤፍሬምን ወልዶ ማድረስ የሚችል ቅርስ ሰውየ “ጎዳናው” የሚለውን ዘፈን ለመዝፈን እልህ አስጨራሽ ጥረት እያደረገ ነው ፡፡ ከተስተናጋጆች አንዱ ጮክ ብሎ እንዲህ አለው፤
“አሁን ለማስመሰል የሞከርከው ድምጽ የኤፍሬም ታምሩ ነው ወይስ የኤፍሬም ማዴቦ?”
ዘፋኙ አንዱን ዘፈን ጨርሶ ወደ ሌላ ከመቀጠሉ በፊት እኔን አይቶኝ፤
“አሁን በመካከላችን ታዋቂው ገጣሚ በእውነቱ ስዩም በመካከላችን ይገኛል” ብሎ አስተዋወቀ፡፡ ተስተናጋጆች ወደኔ አቅጣጫ እያዩ አጨበጨቡ፡፡ ደረቴ በኩራት ስለተነፋ ሸሚዜ ጠበበኝ፡፡ ወድያው ግን “ እና ምናባቱ እናርገው?”የሚል ያንድ ሰካራም ድምጽ ከጭብጨባው በላይ ጠብድሎ ተሰማኝ፡፡ ደረቴ ወደነበረበት ተመለሰ፡፡

ከብላቴናነቴ ጀምሮ ሙሉቀን መለሰን ስወደው ኑርያለሁ፡፡ አስቴር ዐወቀ፤ ኤፍሪም፤ ሙሉቀን እና አበበ ተካ በዜማ ባያጣፍጡት ኖሮ የጉብዝና ወራቴ ምንኛ እጅ እጅ ይል ነበር! ስለምትመኘው ነገር ተጠንቀቅ አንድ ቀን ልታገኘው ትችላለህና!ይላል ጠቢብ፡፡ አንድ ቀን ራሴን ሙሉቀን መለሰ ቤት አገኘሁት ፡፡ በርግጥ ያገኘሁት በልጅነቴ የማልመውን ሙሉቀንን አልነበረም፡፡ ሙሉቀን የወጣትነት ሥራውን ሲኮንን ደረስኩበት ፡፡ የዘፈን ምንጭ ሰይጣን ነው ይላል፡፡ (ነገሩ እንዲህ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ባህል ሚኒስትር ሰይጣን ላገራችን ኪነጥበብ ያደረገውን አስተዋጽኦ አስታውሶ ቢሸልመው ደስ ይለኛል፡፡)

ሙሌ የተራኪነት ተሰጥኦ አለው፡፡ ስለአማርኛ ዘፈን ታሪክ ሲነሣ ጠንከር ያለ ትንታኔ ያቀርባል፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ዘፈን የሰይጣን መሆኑን ይረሳና በግሉ ስላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይተርካል ፡፡ በርግጥ የታዋቂ ዘፋኞችን ችሎታ ያጣጥላል፡፡ አንዱን ስሙን የማልጠቀሰውን ዘፋኝ ሣነሳበት “ እሱ እንዲያውም መዝፈን አይደለም ዘፈን እንዲያዳምጥ እንኳ ሊፈቀድለት አይገባም ” አለኝ ፡፡ በተለይ ጥላሁንን ገሠሠን ተችቶ አያባራም፡፡”እሱ እኮ የጉልበት ዘፋኝ ነው”ይለዋል፡፡ ነገሩን ማስ ማስ ሳደርገው ከጥላሁን ገሠሠ ጋር ያለው ግኑኝነት የፉክክር ብጤ ይመስላል ፡፡ አልፈርድበትም!“ ሁለት አንበሶች ባንድ ዋሻ ውስጥ አይኖሩም ” ይላል ጎርኪ፡፡
በቅርቡ ሙሌ፤ “ናፍቆት ኢትዮጵያ” ከተባለ መጽሄት ጋር ዘለግ ያለ ቃለ-መጠይቅ አድርጓል፡፡ ከምልልሱ ውስጥ ይቺን በፈገግታ ቀንጭቤ ልሰናበት፡፡

ናፍቆት- ለመሆኑ እስከ ስንተኛ ክፍል ተምረሃል?
ሙሉቀን፡- ረሳሁት እስከ ሦስተኛ ክፍል የተማርኩ ይመስለኛል።
ናፍቆት ፡- ድምፃዊው ጥላሁን ገሠሠ በሁለት ክፍል ይበልጥሃላ!
ሙሉቀን፡- እሱ እዚያ ደርሷል እንዴ?
ናፍቆት – አዎ የምናውቀው እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ መማሩን ነው ….
ሙሉቀን፡- እንዲያውም አሁን ትዝ አለኝ አምስተኛ ክፍል ድረስ ነው የተማርኩት።

Filed in: Amharic