>

እንደ ሰሜን ዋልታ የራቀው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት! [ሙሉቀን ተስፋው]

Journalist Muleken Tesfaw on DWየትንሳኤ በዓልን እንኳ ሳላከበር ነበር ወደ ሰሜን ዋልታ የተጓጓኩት፡፡ ሰማይ ዳር የአገር ሁሉ መጨረሻ ለማለት ነበር ያኔ ልጅ እያለን የምንጠቀምበት፤ የትንሳኤ በዓል ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሊከበር እኔ አስቀድሜ ቅዳሜ ለእሁድ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ተነሳሁ፤ ጠያራው የሜዲትራኒያንን ባሕር አቋርጦ ፍራንክፈርት ጀርመን እሁድለት አረፈ፡፡

የዓለም አቀፉን የፕሬስ ነጻነት ቀን ለማክበር ከጀርመን ወደ ፊንላንድ ለተጨማሪ አራት ሰዓት መጓዝ፤ ወደ ሰሜን ዋልታም መቅረብ ይጠበቅብኝ ነበር፡፡ የመገናኛ ብዙሃን በእኛ አገር የፊንላንድን ያክል ርቆናል፤ ነጻ ያልሆነችን አገር ወክዬ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ቀንን ለማክበር ነበር የሔድኩት፡፡

የፍራንክፈርት ከተማን ስላላየሁት የማወራችሁ የለም፤ አውሮፕላን ማረፊያው ግን እንዲህ ነው አይባልም፡፡ ለሰርግ የተሠራን ዳስ መጠን ለመግለጽ ‹ፈረስ ያስጋልባል› ይባላል፤ እንዲህ ዓይነቱን ሁዳድ ግን ምን ብሎ መግለጽ ይቻላል? ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ይልቅ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ማወዳደር የተሻለ ይሆናል፡፡ የሚያርፉና የሚነሱ ጠያራዎች ብዛት ጉንዳን ናቸው፡፡ በየአምስት ደቂቃው እስከ አምስት ጠያራ አርፎ አምስት ደግሞ መሬትን ይሰናበታል፡፡

የትንሳኤለት ከሰዓት 8፡00 ላይ የፊንላንድ ዋና ከተማ ሔልስንኪ ገባን፡፡ ሔልስንኪ ትንሽ ግን ደግሞ የገንት አምሳያ ሽሙንሚነት ከተማ ናት፡፡ የበጋው ወቀት እየመጣ ስለሆነ በፊንላንድ የማታቃጥል ፀሐይ አለች፡፡ በመጀመሪያ ቀን ገርሞኝ ነበር፤ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ የቆየች ፀሐይ አላስችላት ብሎ ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት ተመልሳ መጣች፡፡ ብርሃን አይቶ ቆጥ ላይ የሚወጣው የእኛ አገር ዶሮ ፊንላንድ ቢሔድ ምን ይውጠው ነበር? የፊንላንድ አገርና የፀሐይ ፍቅር ምን ያክል ቢዋደዱ ነው ተለያይተው ለስድስት ሰዓት እንኳ መቆየት ያቃታቸው፡፡ ሙሉ በጋ በሆነ ጊዜ ፀሐይ ፈጽሞ አትሔድም፡፡ በቃ አትሔድም፡፡ ግን የሰሜን ዋልታ መሬትና የጮራ ፍቅር ከሦስት ወር በላይ መቆየት አያውቅም፡፡ እንደ አዲስ ፍቅረኛ ተጨባብጠው እፍ እንዳላሉ ሁሉ ወዲያው ይኳረፋሉ፡፡ ያኔ የሰሜን ዋልታና ጮራ ይቆራረጣሉ፡፡ አልይሽ አልይህ ተባብለው ይፋታሉ፡፡ የሰሜን ዋልታም ፀሐይን አባሮ ወዳጅነቱን ከጨለማ ጋር ያደርጋል፤ ከድርገት ጋር ያብራል፡፡ ሰሜን ዋልታማ ምን ተድኼው? ድርገቱ ውበቷን ለሚያጠፋው ይብላኝላት ለሔልስንኪ እንጅ! በማይነጋ ሌሊት ለተዋጡት ዝምተኛ ዜጎቿ እንጅ፡፡ ደግነቱ ጮራና ሰሜን ዋልታ ያለ ሽማግሌ እንደገና መልሰው ይጋባሉ፡፡ እንደ እኛ አገር መንግሥትና የመገናኛ ብዙሃን ተቆራርጠው ዓመት መድፈን አያውቁበትም፡፡

ወይ ግሩም! ከተማ ግን ያን ሊመስል ይችላል በአያሌው? ምኑን ከምን ቢያገናኙት ነው ገነትን በመሬት ላይ መፍጠር የቻሉት? ብዙ ሰው የማይበዛባት ውበት ላይ ውበት የደፋባት፣ ዘመናዊን ከባህላዊ የሥነ ሕንፃ ኪነ ጥበብ ጋር አካታ የያዘች፡፡ ባቡርና መኪና እየተጋፉ ተመሳሳይ መንገድ ይጋራሉ፡፡ ባቡር በቀይ መብራት ከቤት መኪና ጋር የሚቆምባት ከተማ፤ ሔልስንኪ፡፡ ዜጎቹ ግን በገነት እየኖሩ ዝምተኛዎች ናቸው፡፡ የንጽሕናዋ ነገር ይገርማል፡፡ መላ ከተማዋ በምን ኦሞ ብትታጠብ ይሆን እንዲህ ጸኣዳ የሆነችው? አዲስ አበባ ቦሌ ልገባ ስል ጫማዬን አሳጥቤው ነበር፤ ለቀናት በሔልስንኪ ስቀመጥ ግን እንኳን መልሶ ሊቆሽሽ ከአዲስ አበባ ያመጣሁት ጭቃ ራሱ የት እንደሔደ አላውቅም፡፡ በከተማዋ በየትኛውም መንገድ ላይ ነጭ ልብስ ልብሶ ቢንከባለል አንዳች ቆሻሻ ይዞ አይነሳም፡፡ እንደ አዲስ አበባ በየቦታው የቆሻሻ ገንዳ እየሸተተ አያስቸግርም፡፡ አንድ መንገድ አልፎ ሰፊ ፓርክ አለ፤ ሌሌላኛውን አልፎ ሌላ ፓርክ አለ፤ ሌላኛውን አልፎ ሌላ ፎንቴን አለ፡፡ ግን ሁሉም ልዩ ልዩና የሚያምር፤ የማይሰለች፡፡

ማክሰኞ የዓለም የፕረስ (ሚዲያ) ነጻነት ቀንን ለማክበር ወደ ፊንላንዲያ አዳራሽ አመራን፡፡ ፊንላንዲያ አዳራሽ ስብሰባው እስኪጀመር ዓይኔ መግቢያ አካባቢ ወደለው የስእል ማሳያ ቦታ ነጸረ፡፡ ሕሊና በዛብህ እና ማኅደር ኃይለ ሥላሴ በተባሉ ሁለት አንስት ኢትዮጵያውያን ፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች የተነሱ ፎቶዎችን አየሁ፡፡ አንደኛው የፎቶ ኤክዚቪሽን ታሪክ ‹‹መጪው ጊዜ ከኢሕአዴግ ጋር ብሩሕ ነው!›› የሚል ቢል ቦርድ ጀርባቸው ላይ አድርገው በሰቆቃ የሚያለቅሱ እናቶችና ወጣቶች ናቸው፡፡ ለቅሶና ብሩህነት ከወዴት ይገናኛል? ሐዘን እንዴት ፍስሃ ሊሆን ይችላል? ደግነቱ ፈረንጅ አማርኛ ስለማያውቅ ምን እንደተባለ አያውቅም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ በሊስትሮነት የተሠማራች እናትን ይዳስሳል፡፡ ሊስትሮዋ እናት ጫማ እየጠረገች ካጠገቧ ልጇን አስተኝታለች፡፡ ፎቶ ግራፈሮቹ በሚገርም ሁኔታ የአገራችን ምስቅልቅል ሁኔታ ገልጸውታል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭትም በአንዲት ፈረንሳያዊት የፎቶ ባለሙያ ተለጥፎ ነበር፡፡

በሁለት ቀናት የተጠናቀቀው የፕረስ ነጻነት ቀን ብዙ ጉዳዮችን ዳሷል፡፡ እያንዳንዳቸውን በቀጣይ ጊዜያት እመለስባቸው ይሆናል፤ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፤ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ እንዲያውም በሁለተኛው ቀን በአየርላንድ የሚኖር ዶክተር ተድላ የተባለ ኢትዮጵያዊ በአገራችን ያለውን የሚዲያ አፈና ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡

በፊንላንድ በተለይም በሒልስንኪ ብዙ ተቋማትን ጨምሮ የማየት እድል ገጥሞኛል፡፡ የፊንላንድ ባለሥልጣናት ለጋዜጠኞች ቅርብ ናቸው፡፡ የንግድ ሚንስትሯ፣ ጠቅላይ ሚንስትራቸው ብሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንትን በቅርብ አይቻቸዋለሁ፤ በአገሬ የክፍለ ከተማን ከንቲቫ ለማግኘት ምን ያክል አድጋሚ እንደሆነ አውቃለሁና በዚህ ተገርሜያለሁ፡፡ የሚዲያ ተቋማቶቻቸው አሠራር ገራሚ ነው፡፡ ከ5 ሚሊዮን ብዙ የማይበልጥ ሕዝብ ባላት አገር ሔልስንኪ ስናውት የተባለው ጋዜጣ በየቀኑ ከ300 ሺህ ኮፒ በላይ ያትማል፡፡ የእኛ አገር ሕዝብ መቶ ሚሊዮን ደርሷል፤ ዐሥር ሺህ ጋዜጣ ግን ማስነበብ አልቻልንም፡፡

የፊንላንድ ትምህርት ቤቶች ዝንባሌን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ወደፊት ጋዜጠኛ ለመሆን የሚሹ ልጆች የሚማሩበት የተለየ ትምህርት ቤት አለ፤ ለሁሉም እንደሚፈልጉት ልጆች ይማራሉ፡፡ ትምህርት ቤት ምግብ ነጻ አለ፡፡ ማንም እንግዳ ቢሆን ገብቶ ይበላል፡፡ ቤተ መጽሐፍቶቻቸው አንባቢያን እንዲመጡ ብቻ አይደለም የሚጋብዙት፤ ቤተ መጽሐፍቱ በራሱ ወደ ሚያነቡት ሰዎች ቤት ይሔዳል እንጅ፡፡ ትልልቅ አውቶቡሶች በየቀኑ ገጠር ድረስ እየዘለቁ ንባብ ለሚፈልጉ ሰዎች በነጻ አገልግሎት ይሠጣሉ፡፡ ቪሶሪያ ጋዜጠኛ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ሃያ አፍሪካውያንና እስያውያን ገባን፡፡

በፊንላንድ እንግዳ ሆኖ ሲገባ በር ላይ የሚጠየቀው ኮት ማስቀመጥ ይፈልግ መሆኑን ነው፡፡ አካባቢው ብርዳማ በመሆኑ ሰዎች ውጭ ሲወጡ ተንቀሳቃሽ ቁም ሳጥን ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን ቤቶች በሙሉ የተሠሩት በሙቀትም ሆነ በብርድ አማካይ የሙቀት መጠን እንዲኖራቸው ሆነው በመሆኑ የሰሜን ዋልታ አካባቢ ነዋሪዎች ኮታቸውን አውልቀው ቤት ውስጥ ይዘንጣሉ፡፡ የኮት መስቀያ የሌለበት መኖሪያ አሊያም መስሪያ ቤት አላየሁም፡፡ ኮቶቻችን አውልቀን እየዘነጥን አንደኛው ክፍል ስንገባ የታሪክ መምህሩ የቀዝቃዛው ጦርነትን በተመለከተ በአገሮች መካከል የነበረውን ሽኩቻ በምስልና በድምጽ ያሳያቸዋል፡፡ ሶቬቶች ከምዕራባውያን የሚዘነዘርባቸውን ጥቃት ለመከላከል ያደርጉት የነበረው ልምምድ ጥይት ሲተኮስ፣ ቦንብ ቢወረወር፣ በመሬትም ሆነ በሰማይ ከሚመጣ ጥቃት ራሳቸውን እየወደቁ አሊያም ወይም እየሮጡ ጥግ ፍለጋ ሲሔዱ የሚያሳየውን ልምምድ ስመለከት የክፍሉን ሁኔታ ከማየት ይልቅ ፊልሙ ላይ አፈጠጥኩ፡፡

በሐሳቤ የመጣው ግን በአገሬ ያለውን ጨቋኝ ሥርዓት ለማስወገድ ምን ዓይነት ልምምድ ነው የሚያስፈልገው? አልኩ፡፡ በሐሳቤ አወጣሁ፤ አወረድሁ፡፡ ከአምባ ገነን ሥርዓት አፈና፣ እንግልትና ስቃይ ለማምለጥ የሚቻልበትን መንገድ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ አሰብኩ፡፡ መምህሩን አመስግነን ስንወጣም ሐሳቤ እዚያው ላይ ነበር፡፡ ወደ ሰማይ ቀና ስል ሰማያዊ መላጣ ሰማይ ነው፡፡ ይህን ያክል ርቀት እንኳ መጥቼ የሰማይን ዳር አሊያም ምሰሶ አላገኘሁትም፡፡ ሰማዩ ነፋስና ፀሐይ እንጅ መልስ የለውም፡፡ ከአፈና ሥርዓት መላቀቅ!

ከትምህርት ቤት ወደ አንድ ትልቅ ቤተ መጽሐፍት ሔድን፡፡ የሚያነቡም የተኙም ሰዎች አገኘን፡፡ የምታስጎበኘን አንስት ‹‹ሰውየው ተኝቷል እኮ!›› አልኳት፡፡ ‹‹እኛ ፊኒሾች በጣም ነጻዎች ነን›› አለችኝ፡፡ ሰው ገብቶ ላይብራሪ መጽሐፉ ላይ ቢተኛ ማንም ግድ አይሰጠውም፡፡ ያላንቀላፋው ያነባል፤ አሊያም ትቶት ይወጣል፡፡ ሰውየውን አለማየት ቢፈለግም ብቻውን መሆን የሚችልበት ቦታ ብዙ አለው፡፡ የእኔን ጥቆማ ሳስበው የአገሬ አምባገነንት ባሕሪ እዚህም ድረስ ተከትሎኝ እንዲታስወጣው ፈልጌ ይሆን እንዴ? ውስጤን ጠየቅኩ፡፡ እኔ እንጃ!

ከላይብራሪ ወጥተን ወይንና ሕብስት ወዳለበት ቤት ጎራ አልን፡፡ ወይን በዓይነት በዓይነቱ ቢከማችም ጃምቦ ሲቀዳ በማየቴ አዲስ አበባ ያለው መሠለኝ ለጊዜው፡፡ የሚበለውና የሚጠጣው ደምቆ እኛ አፍሪካውያንና ኤዥያውያን ድምጻችን ጮክ ብለን እናወራለን፡፡ ዘወር ዘወር እያልኩ ፊኒሾችን አየዋቸው፤ ስለእኛ ግድ የላቸውም፡፡ ድምጻቸው አይሠማም፡፡ ወይ ጉድ! ፍጹም ጸጥ ብለው የሚበሉትን ይበላሉ፤ የሚጠጡትን ይጠጣሉ፤ ሞባይል ይጎረጉራሉ፡፡

የአገሬን የባሕል ልብስ ለብሼ በተገኘሁባቸው ስብሰባዎች ደግሞ ብዙዎች እንደ ድንቅ እያዩ ፎቶ ግራፍ አብረንህ እንነሳ ይሉኛል፡፡ ሦስት ሽማግሌ አንስቶች ከአይስላንድ እንደሆኑ ገልጸው የት አገር ነህ? አሉኝ፡፡ ገምቱ እስኪ አልኳቸው፡፡ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣… ቀበጣጥረው አገሬን ባለማወቃቸው ተናደድኩ፡፡ እመቤቴን በጣም ተሰማኝ፡፡ የሚገርመው እኮ ደግሞ አንደኛዋ የታሪክ መምህር ናት፡፡ ለማንኛውም ወደ አገሬ ኢትዮጵያ ከመጣችሁ ለእያንዳንዳችሁ አንዳንድ ቀሚስ አሠርቼ እሰጣችኋለሁ አልኳቸው፡፡ ኢትዮጵያ የት ናት? እያሉ ሲጠይቁኝ ትግስቴ እያለቀም ቢሆን ጎጉል ማፕ ከፍቼ ንሱ አልኳቸው፡፡

ስለነጻ ሚዲያ ነጻነት ሲያወሩኝ በሚዲያ ነጻነት ቀን የቀረበውን ማጠቃለያ ሐሳብ የእኛን አገር የመሠለውን እንዲያቡት አሳየዋቸው፡፡ ይህችው የታሪክ መምህር የሆነችው ‹‹ታዲያ እናንተ አገር ጋዜጠኝነት ነጻ ካልሆነ ስንመጣ ታስረህ ወይም ጠፍተህ ብናገኝ ማን ቀሚሱን ይሠጠናል?›› አለችኝ እየሳቀች፡፡ አነጋገሯ ቀልድ ይመስል ነበር፤ እኔን ግን ውስጤን መታኝ፤ ምን እላታለሁ? የአፍሪካ አገር ውስጥ እኮ ጋዜጠኛ ሲኮን ለሦስት ነገሮች መዘጋጀት ግድ ነው፤ አንደኛው ለመታሰርና ወርቃማውን እድሜ በእስር ለማሳለፍ፣ ሁለተኛው ለመገደል አሊያም የአካል ጉዳተኛ ለመሆን የመጨረሻው ግን ለመሰደድ፡፡ ለእነዚህ አንስቶች ስለዚህ ብነግራቸው አይገባቸውም፤ ከአንድ ሳምንት በፊት ተመስገን ደሳለኝንና ውብሸት ታዬን አይቻቸው ነበር፡፡ ስለ ተሜ፣ ውብሸት አሊያም እስክንድር ብነግራቸው ምን ይገባቸዋል? ፊላንድ አገር ውሻ በቀን ሦስት ጊዜ አልተናፈሰም ተብሎ ባለቤቱ ይከሰሳል፡፡ ዓሳማዎቹ ሲታረዱ በቂ ማደንዘዣ አልተሰጣቸውም ተብሎ ሰው ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል፡፡ በእንዲህ ያለ ማኅበረሰብ ውስጥ ለሚኖር ሰው ስለጻፈ ታሠረ፤ ታስሮም ተደበደበ ብሎ ማስረዳት ድካም ነው፡፡

ሐሙስ ዕለት ስዊዲን ስቶኮልም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግብዣ አድርገውልኝ ነበር፡፡ ስለሆነም ረቡዕ ሞንሟኒት ሔልስንኪን ለቅቄ ወደ ባልካን ባሕር አመራሁ፡፡ ከሔልስንኪ እስከ ስቶኮልም 500 ኪሎ ሜትሮች ያክል ይርቃል፡፡ የተነጠፉ ሰጋጃዎች የሚመስሉ የከተማዋን ናፋቂ ፓርኮች ትቻቸው ወጣሁ፡፡ በቪኪንግ ላይን መርከብ ወንበርና አልጋ ተይዞልኛል፡፡

ወደ መርከቧ ስገባ ነጮች እንደ ደብረ ብርሃን በጎች ረጃጅም ጸጉር ያላቸውን ውሾች በገመድ እየጎተቱ አሊያም ታቅፈው ይገባሉ፡፡ መርከቧ ወደ 12 የሚሆኑ ፎቆች አሏት፡፡ አምስተኛ ፎቅ ላይ ሻወርም ሽንት ቤትም እንዲሁም ስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ያለው በካርድ የሚከፈት ክፍል ይዣለሁ፡፡ እቃዎቼን ክፍሌ ውስጥ ቆልፌ የሀዲስ ዓለማሁን ‹‹ትዝታ›› የሚል መጽሐፍ ብቻ ይዤ ስምንተኛ ፎቅ ወዳለው መዝናኛ በሊፍት ወጣሁ፡፡ ምሽት ሦስት ሰዓት ሆኗል፤ ግን ጸሐይ እንደቆመች ነው፡፡ ድራፍቴን ከማን አንሼ በሚል የሐበሻ ወኔ ይዤ ትዝታን እያነበብኩ በትዝታ ነጎድኩ፡፡ ነገ የአርበኞች ቀን ነው፡፡ በአርበኞች ቀን ደግሞ የአርበኛ መጽሐፍ ማንበብ መታደል ነው፤ ያውም ደግሞ በባልካን ባሕር ከነፋስና ከውበት ጋር እየተላጉ፡፡

ትንባሆውን ሲምግ የቆየ ነጭ ቀርቦ ሲያየው አማርኛው ስዕል ይሁን የልጆች ጨዋታ የትኛው እንደመሰለው እርሱ ያውቃል ‹‹ምንድን ነው?›› ሲለኝ በአጪሩ መጽሐፍ አልኩት፡፡ በጥያቄው መሠረት የአማርኛ ቋንቋ እንደሆነ አስረዳሁት፡፡ መቸም ለመገረም ነጪን የሚያክል የለም፡፡ ስለመጽሐፉ ይዘት ቢጠይቀኝ ብየ ብመኝም ዝም አለኝ፡፡ ጠይቆኝ ቢሆን ኖሮ ስለአርበኞች አባቶቻችን፣ የነጮችን የበላይነት እንዴት አድርገው እንደሰበሩት ልግተው ነበር፡፡ ግን እንደኛ አገር ሰው በግድ ላውራህ ማለትም ከበደኝ፤ እርሱም ዝም ብሎ የውስጤን እንኳ እንዳልተነፍስ ኩም አደረገኝ፡፡

ፀሐይ ደበዘዘች፡፡ ብርዱንና ንፋሱን ለመከለል (መ ጠብቆ ይነበብ) ጥግ ለጥግ ብሔድ ሁሉ የምችለው አልሆነም፡፡ የባልካን ባሕርን ከጨለማ ጋር አጋፍጨ ወደ አንሳንሰሩ ገባሁ፤ ክፍሌ ውስጥ ገባሁና ላፕ ቶፔ ላይ ቻላቸው ዋኘውን ‹‹አሸበል ገዳየ›› እስከ መጨረሻው ድረስ ከፈትኩት፡፡

‹‹ጎሃ ጽዮን ማዶ ደጀን ላይ ስደርስ፣
የሠራ አካላቴ ይለዋል ደስ ደስ!
የማርቆስ ኮበሌ የደጀን ሹርባ
ትምጣ የብቸና የሸበሏ ሎጋ…

ማምየው ….
ሉማሜና ደጀን ሞጣና ብቸና
ከደጀን አልፌ ደብረ ወርቅ ሳቀና
አዴት እንገናኝ ህመሜ ሳይጠና….
ሁልጊዜ ፋሲካ ሁልጊዜ ድግስ
አገሬን ላሳይሽ እንሒድ ማርቆስ…››

የሴኪዩሪቲ ካሜራ የሚያየው ሰው መቼም አብዷል ሳይለኝ አይቀርም፡፡ ወደ ሐሳቤ ስመለስ ለካ ጎጃም አይደለም፤ ፊንላንድም ለቅቂያለሁ፤ ስዊድንም አልደረስኩም፡፡ ጠቁሮ ኅብረቱን ከጨለማ ጋር ካደረገው የባልካን ባሕር ላይ ነኝ፡፡ እንኳንስ በእስክስታ የሚያግዘኝ እዚያ ሁሉ እልፍ ሰው አንድም እንኳ ጥቁር ሰው አላየሁም፤ ቢኖርስ እኔ በሬን ጠርቅሜ ዘግቼም አይደል? ትዝታዎቼ እዚህና እዚያ ረገጡ፤ አንዴ ጎጃም፣ አንዴ አዲስ አበባ፣ አንዴ ፊንላንድ፣ አንዴ ደግሞ ገና ካላየኋት ስቶኮልም፡፡ ከ16 ሰዓት የባሕር ላይ ጉዞ በኋላ እነ ስዩም (ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ልጅ) እና ወ/ሮ ዘውዲቱ ስቶኮልም ይጠብቁኛል፡፡

ሰላም!

ቪኪን ላይን መርከብ፤ የባልካን ባሕር

Filed in: Amharic