>

ከጃን ሸላሚነት ወደጃንሆይነት [በዕውቀቱ ስዩም]

bewketu Siyum 3እንኳን ለሠራተኞች ቀን በሰላም አደራሳችሁ፡፡ ያው በኔና በብጤዎቼ አቆጣጠር እያንዳንዱ ቀን ያለም ሠራተኞች ቀን ነው፡፡
ባገራችን ሁለት አይነት መደቦች ነበሩ፡፡ ለፍቶ አዳሪና ቀማኛ፡፡ ከንግሥተ ሳባ እስከ ዛሬ ያለው ያገራችን ታሪክ ባመዛኙ መንግሥታዊ ሌብነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሥልጣንን ተገን እስካደረገ ድረስ ዝርፍያ ነውር አይደለም፡፡ ዘራፊዎችን ታሪክ በደማቅ ይዘክራቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮንን ሠርቆ ካመጣው ቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የህዝብ ባንክ እስከተዘረፈበት ” አክሱም ኦፕሬሽን“ ድረስ ስርቆት የጀብድ ምልክት ሆኗል፡፡
ገበሬዎችና ለፍቶ አዳሪዎች መታሰቢያ የላቸውም፡፡ የገበሬ ሃውልት አይተህ ታውቃለህ ወዳጄ? “ ደማችንን አፍሰስን ” የሚል እንጅ “ላባችንን አፍስሰን” ብሎ የሚኮራ ዘመናይ ገጥሞህ ያውቃል? ኧረ ለመሆኑ፤ አዝማሪ የሚዘፍንለት የታወቀ አንጥረኛ ሰምተሽ ታውቂያለሽ?

“ከፈረሰኞች የምናውቃቸው
በሻህ አቦየ ኃይሌ አንዳርጋቸው ”

ተብሎ ይዘፈን ነበር፡፡ ለፈረሰኞች ኮርቻ ግላስና ልጓም የሚሠሩ ሰዎች ግን እንደበሻህ አቦየና እንደ ኃይሌ አንዳርጋቸው አይታወቁም፡
ለፍቶ አዳሪ ስም የለውም፤ታሪክ የለውም፡፡
እንዲያ ነው !!

አንዳንዴ ለፍቶ አዳሪዎች ንቀትና ድህነት ሲያንገፈግፋቸው ይሸፍቱ ነበር ፡፡ ባፍሪካችን ብቸኛ የክብርና የጥቅም ምንጭ የሆነውን የመንግሥት ስልጣን ለመቆጣጠር ሞክረዋል ፡፡ ከነዚህ ሞካሪዎች አንዱ በኢያሱ ቀዳማዊ ዘመን ተነሥቶ ወድቋል፡፡
የኢያሱ ታሪክ ጸሐፊ ይህንን ሽፍታ በጣም ስለናቀው ስሙን እንኳ መዝግቦ ሌያስተላልፍልን አልፈቀደም ፡፡ ሁሉም ሽፍቶች በሚጠሩበት የወል ስም “ ወረኛ ” ብሎት አልፏል ፡፡ እኔ በሙያ ስሙ አክብሬ፤ “ጃን ሸላሚ” እለዋለሁ፡፡ ጃን ሸላሚ ማለት ንጉሥ የሚጠቀምባቸውን ጌጦችና ቁሳቁስ የሚሠራ ማለት ነው፡፡ ያለ ጃን ሸላሚ ንጉሥ መናኛ፤ ቀትረቀላል ሰው ነው፡፡

ያ ጃን ሸላሚ ከተወለደበት አገር ወጥቶ፤ ወደማያቁት አገር ከተሻገረ በኋላ ራሱን የንጉሥ ልጅነኝ ብሎ አስተዋወቀ፡፡ የተወሰነ ተከታይ አፍርቶም ነጋሪት እያስመታ አንድ ሐሙስ ከነገሠ በኋላ በጦርነት ተማረከ ፡፡ አደባባይ ላይ ለፍርድ ቀርቦም በመኳንንት ተመረመረ፡፡
መርማሪ- ነገድህ ከየት ነው?

ጃንሸላሚ: -ከባለጌ ነገድ ነኝ፡፡ ( የዛሬውን አያርገውና ባለጌ ማለት ባላገር ማለት ነበር፡፡ ባአለ=ባለቤት፤ ጌ=አገር) ለብዙ ዘመን ደብረወርቅ ነበርኩ፡፡ ከዝያ ወደ ሸዋ ሄድኩ፡፡ ከዝያም አሥረው ወደዚህ አመጡኝ፡፡
መርማሪ- በእግዚአብሄር ስም ፤ከምን ትውልድ እንደሆንክ እውነቱን ንገረን
ጃንሸላሚ- ከነገደ ዣን ሸላሚ ነኝ…የወርቅ የብርና የብረት ሥራ በተቻለኝ መጠን እሠራ ነበር፡፡ እንዲህ ስኖር ለምግብና ለልብስ የሚሆን ገንዘብ አጥቸ ተቸገርሁ። ድህነት ሲጠናብኝ ቅድም እንደነገርኳችሁ ምግቤን የማገኝበት ሥራ ፍለጋ ወደ ሸዋ ሄድኩ“

ጃንሸላሚ ይህንን ከተናዘዘ በኋላ ሳይገባው ለመንገሥ በመቃጣቱ ተወንጅሎ በስቅላት ተገደለ፡፡ ብርቅ ያንጣሪነት ችሎታውም አብሮት ዛፍ ላይ ተንጠለጠለ፡፡

እስከዛሬ ድረስ ጥቂት የማይባል ያገሬ ሰው ለፍቶ ፤ በላቡ እንጀራ በልቶ ቤት ሠርቶ “ አንቱ” ተብሎ መኖር እንደማይችል ያውቃል፡፡ ስለዚህ ከተቻለ ጠቅላይ ምኒስተርነትን ፤ካልተቻለ የቀበሌ ሊቀመንበርነትን በትረ ስልጣን ለመጨበጥ ይዋደቃል፡፡ጃንሸላሚነት ካላዋጣ ወደጃንሆይነት ለመሻገር መሞከር ያባት ነው፡፡

አንሸወድ! ለፍቶ አዳሪውን ከጥቅምና ከመታሰቢያ ማግለል ያገራችን ብቻ ሳይሆን የሠይፍ አምላኪዋ ዓለማችን ዓመል ነው፡፡ ብሬሽት የተባለው ጀርመኔ ከጻፈው ዝነኛ ግጥም የትርጉም ትርጉም ጠቅሼ ላጥ ልበል!!
Young Alexander conquered India.
He alone?
Caesar beat the Gauls.
Was there not even a cook in his army?

አፍለኛው እስክንድር ህንድን አስገበረ
ብቻውን ነበረ?
ቄሳርም ጎሎችን ድባቅ ሲመታቸው
ወጥ ቤቷ ተረሣች
ለዘማቾች ራት የሠራችላቸው

Filed in: Amharic