>
5:13 pm - Monday April 20, 5626

ይድረስ ለአኙዋ ወዳጄ፤ ይነ ፑዋ! ኦሎ ቦንጎ! [በናትናኤል ፈለቀ]

Natnael-Feleke.ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ ከቤት የሸከፍኩትን ጋቢ እና ቅያሪ ልብስ እንደያዝኩ ማዕከላዊ በተለምዶ ሳይቤሪያ በመባል የሚታወቀው የእስረኞች ማጎሪያ ሕንፃ 7 ቁጥር ገባሁ፡፡ ውስጥ 7 ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ 8ኛ ሆኜ ነው የተቀላቀልኳቸው፡፡ ምንም ሳልናገር ቆሜ ክፍሉን አየሁት፡፡ ሰዎቹን አየኋቸው፡፡

አንድም ቃል ሳንለዋወጥ አንደኛው “ኢትዮጵያ” ብሎ በሀዘኔታ ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡
ኦቻን ኦፕዮ የአኝዋክ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በ1996 በጋምቤላ የተቀሰቀሰውን ግጭት ሸሽተው ወደአሁኗ ደቡብ ሱዳን ከተሰደዱት ኢትዮጵያውያን መካከል ነበር፡፡ በወቅቱ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይፈፅም የነበረውን ግድያ በመሸሽ ለቀናት ጫካ ውስጥ ተደብቆ ከቆየ በኋላ ነበር ቀናትን የፈጀ የእግር ጉዞ አድርጎ ደቡብ ሱዳን የገባው፡፡ ከጁባ አቅራቢያ የአለ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ ከ8 ዓመት በላይ የቆየው ኦቻን ቤተሰብ መሥርቶ፣ ሁለት ልጆችን ወልዶ በጁባ የተረጋጋ ሕይወት መኖር ጀምሮ ነበር፡፡
የ1996ቱ የጋምቤላ ቀውስ በተቀሰቀሰበት ወቅት ክልሉን በርዕሰ ብሔርነት ይመሩ የነበሩት አቶ ኦኬሎ ኦኳይ በደቡብ ሱዳን መንግሥት ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው ሲሰጡ ከጁባ አብረዋቸው የታሰሩት የአኝዋክ ተወላጆች መካከል ኦቻን ኦፕዮ ነበር፡፡
ወደደቡብ ሱዳን ሲሸሽ ጫካ ውስጥ እሾሃማ የዛፍ ቅርንጫፍ የቀኝ ዓይኑን መቶት የማየት ችሎታውን ቢጋርድበትም የቀረችውን የማየት ችሎታውን በአኝዋክኛ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ የእስር ግዜውን ያሳልፋል፡፡ (በነገራችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደአኝዋ የተረጎሙት ኡመድ አግዋ በአሁኑ ወቅት በሽብር ወንጀል ተከሰው ቂሊንጦ ይገኛሉ፡፡)

ኦቻን ሲበዛ ሠላማዊ ሰው ነው፡፡ የሁለት ልጆቹ ነገር አብዝቶ ያሳሰበው ቀን ግን ከሰው ጋር መነጋገር አይፈልግም፡፡ አንድ ቀን ድንገት ብቻውን ስቅስቅ ብሎ ያለቅስ ጀመር፡፡ ሰባት ቁጥር በግዜው የቀረነው እሱ፣ እኔና ዘግየት ብሎ የተቀላቀለን ቢልሱማ የሚባል የሐሮማያ ዩንቨርስቲ ተማሪ ነበርን፡፡ ሁለታችን በጣም ተደናግጠን ምን እንደሆነ ጠይቀነው ሊነግረን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ቆይቶ ሲረጋጋ ልጆቹ እንደናፈቁት እና ምን አጥፍቶ እንዲህ ያለ ፈተና እንደገጠመው እንዳልገባው እያማረረ አጫወተኝ፡፡

በነኦኬሎ ኦኳይ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ ሆኖ ቀድሞ ቂሊንጦ የወረደው ኦቻን ነበር፡፡ ከጥቂት ግዜያት በኋላ እኔም በነሶልያና ሽመልስ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ ሆኜ ቂሊንጦ ስወርድ ኦቻንን ዞን3 አገኘሁት፡፡ እንደመጀመሪያው ሁሉ ተንከባክቦ ግቢውን አላመደኝ፡፡
ኦቻን የአኝዋ አስተማሪዬም ነበር፡፡ ለቤት የመጀመሪያ ልጅ መሆኔን ስለሚያውቅ በአኝዋ ባሕል እንደሚደረገው ኡመድ እያለ ነው የሚጠራኝ፡፡ ትንሽ የማይባሉ የአኝዋ ቃላትንም አስተምሮኛል፡፡

የአኙዋኩ ጓደኛዬ የተከፈተበት የሽብር ክስ የአገር ግዛት አንድነትን ለማፍረስ ሞክሯል በሚል ተቀይሮለት ጥፋተኛ ተብሎ ቂሊንጦ ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ እስር ስገባ ያስተዋልኩት በሐዘን ተሞልቶ “ኢትዮጵያ!” ሲል ያማረረው ፊቱ እስከ ሕይወቴ ፍፃሜ አብሮኝ ይዘልቃል፡፡ ይህችን አጭር ጦማር ያለህበት ድረስ መንፈስ ይዞት ይመጣ እንደሆን ይነ ፑዋ! ኦሎ ቦንጎ! ብዬሃለሁ፣ ኦቻን ኦፒዮ፡፡

Filed in: Amharic